- ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሠራሩን የሬጅስትራር በቴክኖሎጂ የተደገፈ አደረገ
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አሠራራቸውን ዘመናዊ ለማድረግ፣ ዘመናዊ ሕንፃ ለመገንባትና ደረጃውን የጠበቀ ደመወዝ ለመክፈል የበጀት እጥረትና የግዥ ችግር እንዳለባቸው፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ተናገሩ፡፡
ፕሬዚዳንቱ አቶ ዳኜ መላኩ ሚያዝያ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፣ እሳቸው ወደ አመራር ከመጡ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ የፍርድ ቤቶች የሥራ አፈጻጸም እየተሻሻለ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታዩ ያሉ የክስ መዝገቦች በ2009 ዓ.ም. እና በ2010 ዓ.ም. የተከፈቱ ናቸው ብለዋል፡፡ ቀደም ብሎ በነበረው አሠራር ከአምስት እስከ ስድስት ዓመታት ይፈጁ የነበሩ የክስ መዝገቦች፣ በአሁኑ ጊዜ ተጠናቀው ውሳኔ ማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡ ከ2009 ዓ.ም. ወዲህ ከ700 የማይበልጡ መዝገቦች መኖራቸውንና በ2011 ዓ.ም. ሁሉም ነገር በተቀላጠፈ ሁኔታ ተጠናቆ፣ ቀጠሮዎች በሙሉ በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቁና ኅብረተሰቡ የተፋጠነ ፍትሕ እንደሚያገኝ ተናግረዋል፡፡
አዲስ የደመወዝ ስኬል በማጥናት ማስተካከያ በማድረጋቸው፣ የፍርድ ቤት ሠራተኞችና ዳኞች ደስተኛ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ዳኜ፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፋይል ለመክፈት ሙሉ ቀን ይወስድ የነበረውን የሬጅስትራር አሠራር ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ፣ በአንድ መስኮት ይሰጥ የነበረውን በ17 መስኮቶች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስረድተዋል፡፡ ይኼም በመሆኑ አንድ ተገልጋይ በግማሽ ሰዓት ጉዳዩን እንደሚጨርስም አክለዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ካለበት የችሎት እጥረት የተነሳ ዳኞች የሚያስችሉት በወረፋ በመሆኑ ቀጠሮዎች እንደሚራዘሙ ገልጸዋል፡፡ አሁንም ችግሩ ባይፈታም ተጨማሪ አምስት ችሎት ማስቻያና ሁለት ትልልቅ አዳራሾች (ሰበር ችሎት ማስቻያ) መሠራቱን ተናግረዋል፡፡
ይኼም ቢሆን በቂ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ዳኜ፣ የበጀት እጥረት እንዳለባቸውና ለመንግሥት ንብረት ማስወገድና ግዥ ኤጀንሲ ግዥ እንዲፈጸምላቸው ሲጠይቁ፣ ቶሎ እንደማይፈጸምላቸውና እንደ ልባቸው ለመሥራት ችግር ውስጥ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ ሁሉንም ነገር የሚይዝላቸው ዘመናዊ ሕንፃ ለመገንባት የከተማ አስተዳደሩ ቦታ እንደሰጠ ገልጸው፣ በ2011 በጀት ዓመት ግንባታ ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በጠቅላይ ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነቡት የሬጅስተራር ጽሕፈት ቤቶች፣ በርካታ አገልግሎቶች እንደሚሰጡና በቴክኖሎጂ የተደገፉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ አንድ ፋይል ተከፍቶ ወደ ዳታ ከገባ በኋላ ለችሎት ጸሐፊ እንዲሰጥ፣ ችሎት ጸሐፊው ፋይሉ የትኛው ችሎት እንደሚታይ ከመራበት በኃላ ወደ ስካነር ማሽን ውስጥ ገብቶ እንደሚቀረፅ፣ ከዚያም በሰርቨር ውስጥ እንዲቀመጥ እንደሚደረግና መዝገቡ ወደ ተቀጠረበት ችሎት እንደሚላክ አስረድተዋል፡፡
መዝገቡ ቢጠፋ ወይም ቢቀደድ በስም፣ በመዝገብ ቁጥር ወይም ከሁለት በአንዱ በመፈለግ በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ልዑል ሐጎስ አስረድተዋል፡፡ ባለቀለም መዝገቦችም ዘመናዊ መደርደሪያ ተዘጋጅቶላቸው በቁጥር ቅደም ተከተላቸው መቀመጣቸውን በማስጎብኘትም አሳይተዋል፡፡