የኢትዮጵያ ግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ የሚፈልጋቸው የተለያዩ ማዳበሪያዎች ላለፉት 50 ዓመታት ያለምንም የላቦራቶሪ ፍተሻ ወደ አገር ሲገቡ ቆይቶ በመጨረሻ ይህ አሠራር ጎጂነቱ እየታወቀ በመምጣቱ መንግሥት ስድስት ዓይነት አስገዳጅ የማዳበሪያ ደረጃዎች አዘጋጀ፡፡
ሰኞ ሚያዝያ 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚመለከታቸው አካላት ውይይት ከተደረገ በኋላ የማዳበሪያዎቹ ደረጃዎች የሚፀድቁ ሲሆን፣ ለሚቀጥለው የግብርና ምርት ዘመን ወደ አገር የሚገቡ ማዳበሪያዎች በዚሁ አሠራር ውስጥ ያልፋሉ ተብሏል፡፡
ደረጃ ከወጣላቸው የማዳበሪያ ዓይነቶች በጥቅሉ ወደ አገር የሚገቡት ምጥን (ብሌንድ)፣ ውህድ (ኮምፓውንድ)፣ ፈሳሽ፣ የተፈጥሮና ባዮ ማዳበሪያዎች ይገኙበታል፡፡
ላለፉት 50 ዓመታት ወደ አገር ሲገቡ የቆዩት ማዳበሪያዎች፣ በተለይም ዳፕና ዩሪያ ፍተሻ ተደርጎላቸው የያዙት ንጥረ ነገር የተሟላ መሆኑ ሳይረጋገጥ ይገቡ ነበር ተብሏል፡፡
የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የአፈር ለምነት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ሰለሞን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የማዳበሪያዎች ደረጃ ባለመውጣቱ አገር ውስጥ የሚገቡ ማዳበሪያዎች አስፈላጊውን ንጥረ ነገር መያዝ አለመያዛቸው አይታወቅም ነበር፡፡
‹‹ይህ ሁኔታ ችግር በማስከተሉና የአገሪቱ የማዳበሪያ ፍላጎት በመጠንም በዓይነትም በመጨመሩ ደረጃ ማውጣት አስፈልጓል፤›› ሲሉ አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የማዳበሪያዎቹ ደረጃና የላብራቶሪ ምርመራ የሚካሄድበት ማንዋልም ተዘጋጅቷል፡፡ አቶ ተፈራ ጨምረው እንደገለጹት፣ ሚያዝያ 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የመጨረሻ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ደረጃዎቹ ይፀድቃሉ፡፡
ከማዳበሪያ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ የግብርና አፈር ለምነት ካርታ በማውጣት ሒደት ላይ ትገኛለች፡፡ የአፈር ለምነት ካርታ ዝግጅቱ ከማዳበርያ ደረጃዎች መውጣት ጋር ተደምሮ፣ ለአገሪቱ ግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አቶ ተፈራ ጠቁመዋል፡፡