Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየትውልድ ቅብብሎሽና የሴቶች ንቅናቄ

የትውልድ ቅብብሎሽና የሴቶች ንቅናቄ

ቀን:

ዓይን አፋር ሆና አንገቷን ያልደፋች፣ ከጓዳ ወጥታ አደባባይ የዋለች፣ ያልተገረዘች ሴት ዓይን አውጣና ማኅበራዊ እሴቶችን የምትጋፋ ተደርጋ የምትቆጠርበት መጠቋቆሚያ ትሆን የነበረበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ ለነገሩ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትልልቅ ከተሞች መጠነኛ መሻሻል ያሳይ እንጂ አሁንም ድረስ መብቴን የምትል፣ ራሷን ችላ ለመኖር የምትጣጣር እንደ አፈንጋጭ መታየቷ አልቀረም፡፡ ከትምህርቷ ቀርታ ለአንዱ የምትዳርበት ሁኔታም የተለመደ ማኅበረሰቡ ባህል አካል ነው፡፡

     ራሳችንን ማሻሻል እንፈልጋለን ብለው ቅድሚያ ለትምህርትና ለሥራቸው የሚሰጡ ሴቶችን ደግሞ በሆነው ባልሆነው ያልተገባ አስተያየት የሚሰነዝሩባቸው አሽሟጠው ሊያሳቅቋቸው የሚሞክሩ አይጠፉም፡፡ በተቃራኒው የሴት ስኬት ተዓምር የሚሆንባቸውና ‹‹እንዴት ቻለች›› በሚል ድምፀት የሚያንቆለጳጵሷቸውም ያጋጥማሉ፡፡

     ሴትነት ፈተና በሆነባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ሴትነት የሚታይበት መነጽር በሰውነት ልክ ሳይሆን፣ ውሉ ባልታወቀ ማኅበረሰባዊ ተፅዕኖ ነው፡፡ ስለ አለባባሷ፣ አነጋገሯ፣ መልኳ፣ ሥራዋ፣ አዋዋሏና ሌሎችም ግላዊ ነገሮቿ  ሁሉም ከፍ ዝቅ አድርጎ ሊናገራት፣ እንዲሁም ሊተቻት ሕጋዊ ፈቃድ ያለው እስኪመስል የተሰማውን ሊልላት ይችላል፡፡ ያለፍላጎቷ እጇን በኃይል ይዘው ካላወራሁሽ የሚሏት በለከፋ አላስወጣ አላስገባ የሚሏት መብቷን እንደተጋፉ፣ ክብሯን እንደነኩ ሳይሆን ሴትነቷን የወደዱላት ባለውለታዎቿ ተደርገው የሚታዩበት ሁኔታ እንዳለም ከማንም ኢትዮጵያዊ የተደበቀ አይደለም፡፡

- Advertisement -

     በሥጋት የተከበበው የእለት ከእለት እንቅስቃሴዋ ለእሷ የተለመደ ሰላማዊ ሕይወቷ ነው፡፡ እንኳንስ ክብሯን ለሚጋፋው ጎረምሳ ካለችበት የተለየ ኑሮ ለማታውቀው ተበዳዩዋ ሴትም ሁሉ ሰላም ነው፡፡ ለከፈኝ ብላ መቆጣቷ ከጥጋብ ሊቆጠርባትም ይችላል፡፡ ጆሮ የምታገኘው፣ ጥቃቷ የሚታይላት ማስጠንቀቂያው ካለፈ አንዱ አሲድ ደፍቶባት ሕይወቷን እንዳልነበር አድርጎ ካገለባበጠው፣ ማንነቷን ከቀየረው፣ አፍኖ ከደፈራት፣ አንገቷን ካስደፋት፣ በራስ መተማመኗን ከነጠቃት፣ አሊያም እንደ ወራሪ ጠላት በጥይት ከደበደባት አሊያም እንዳይሆኑ አድርጎ በስለት ወጋግቶ ከገድላት ነው፡፡

     ለዚህም ለሰባት ተፈራርቀው ደፍረዋት ለሞት የተዳረገችውን ታዳጊ የሀና ላላንጎን ጉዳይ ማንሳት ይቻላል፡፡ በወንድ ጓደኛቸው አሲድ ተደፍቶባቸው የሕክምና ወጪያቸውን ለመሸፈን ተቸግረው ዕርዳታ የሚጠየቅላቸውን ሴቶችም ዓይነተኛ ማሳያ ይሆናሉ፡፡ ከወራት በፊት በማኅበራዊ ሚዲያ ተለቆ የነበረው ሁለት ወንዶች አንዲትን ሴት አስረው ብልቷን በእሳት ሲያቃጥሉ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምሥልም አስደንጋጭና ሴትነትን ከሰውነት በታች አድርገው የሚያዩ ብዙ እንዳሉ የሚያስረዳ ነበር፡፡ ባህር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ወንዶች ሚስቶቻቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ የመግደላቸው ዜና በተደጋጋሚ ጊዜ መሰማቱም አገሪቱ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያስጠራ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ ይህ የአብዛኛዎቹ ሴት ኢትዮጵያውያን ኑሮ በሥጋት የተተከበበ እንዲሆን እያደረገው የሚገኝ አሳዛኝ እውነታ ነው፡፡

     ዓለም ስለ ሴቶች እኩልነት፣ የአመራር ተሳትፎ ላይ ትኩረቱን አድርጎ በሚሠራበት በዚህ ዘመን በግፍ ስለሚገደሉ ሴቶች፣ ስለሚደበደቡ፣ ስለሚደፈሩና ሌሎችም ፆታዊ ጥቃቶችን ስለሚያስተናግዱ ሴቶች ማውራት ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት እምብዛም መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ ማለት ግን በኢትዮጵያ የሴቶች መብት ማስከበር ላይ ትኩረት ያደረጉ ንቅናቄዎች የተጀመሩት ገና አሁን ነው ማለት አይደለም፡፡ 

     በአንዳንድ ብሔረሰቦች የሴቶች የመብት ጥያቄና ከባህላዊ እሴቶች ጋር ተያይዞ የሚታይ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ‹‹በጉራጌ ባህል ብንመለከት የቃቄውርዶት አለች፡፡ በኦሮሞ ባህል ደግሞ የሲቄ ባህል አለ፡፡ በሲቄ ባህል ሴት ልጅ በቤት ውስጥ የሚደርስባትን ጭቆና ከጓደኞቿ ጋር በመሆን አደባባይ ወጥታ ድምፅዋን ታሰማለች፤›› ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥርዓተ ፆታ ዳይሬክተሯ ወይዘሮ አልማዝ ታፈሰ ናቸው፡፡

     አውሮፓውያን የሴቶችን እኩልነት ጥያቄ ከማንሳታቸው መቶ ዓመት በፊት ነበር ውርዶት ስለ ነፃነትና የሴቶች እኩልነት መታገል የጀመረችው፡፡ ገና በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ሳለች ለአንድ ግለሰብ ሦስተኛ ሚስቱ ሆና እንደተዳረች ነበር፡፡ የሴቶችን የጋብቻ እኩልነት፣ ስለ ንብረት መብትና ነፃነት አንስታ ትሞግት የገባችው፡፡ የነፃነት ታጋዩዋ ውርዶት ለሴቶች በመታገሏ ለአራት ዓመታት ያህል ታስራ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

     ለሴቶች የተለየ ክብር የምታጎናፅፈው የሲቄ ብትርም በኢትዮጵያ የሴቶችን እኩልነትና የመብት ጥያቄ ምልክት ሆና ዛሬ ድረስ ትወሳለች፡፡ የኦሮሞ ሴቶች በደል ሲደርስባቸው መብታቸውን ለማስከበር የሚጠቀሟት ተምሳሌታዊ ብትር ነች፡፡ በደል የደረሰባት ሴት ብሯን ይዛ መብቷን ታስከብራለች፡፡ ብትሯን ይዛ ድምፅዋን ታሰማለች፡፡ የሲቄ ጥሪ የሁሉም ሴቶች ድምፅ፣ የሴትነት ክብር ደጀን ነው፡፡ በሁለት ወገን መካከል የሚፈጠር ግጭት ሲቄን በያዘች ሴት ይበርዳል፡፡

     ይህ ዓይነቱ ሥርዓት በሌሎች ብሔረሰቦች የታሪክ ክፍል ውስጥ ስለመኖር አለመኖሩ መረጃ የለም፡፡ ነገር ግን በሁለቱ ብሔረሰቦች ውስጥ ያለው ሥርዓት የሴትን መብት በማስጠበቅ ረገድ ወርቃማ ልማድ ተብሎ ሊታይ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ስለነበሩ የሴቶች መብት ንቅናቄ ታሪክ ሲወሳም እነዚህ ሁለቱ ንቅናቄዎች እንደ መሠረት ሆነው ይነሳሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የሴቶች ንቅናቄ ጉዳይ ሲነሳ በየአገዛዝ ዘመኑ የነበሩን ከማንሳት በቀር ጎልተው የሚወጡ እምብዛም ናቸው፡፡

     ‹‹ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ የሴቶችን መብት የማስከበር ንቅናቄዎች ይደረጉ ነበር፡፡ በእነዚህ ንቅናቄዎች ወንዶችም ጭምር የንቅናቄው አካል ሆነው ይታገሉ ነበር፡፡ በደርግ ዘመንም እንዲሁ ሴቶች ተደራጅተው ትግል እንዲያደርጉ ተደርጎ ነበር፡፡ ምንም እንኳ አደረጃጀቱ የሴቶችን ጥያቄ መሠረት ሳያደርግ በመንግሥት የተቋቋመ ቢሆንም መድረኩ ግን ነበር፤›› ይላሉ ዳይሬክተሯ በየዘመኑ የነበሩ የሴቶችን ንቅናቄዎች ሲያስታውሱ፡፡

      በአሁኑ ወቅት ያለውን የሴቶች ንቅናቄዎች አጠቃላይ ሁኔታ ከቀደሙት ጋር ሲያስተያዩ ብዙ ነገሮች ነጥረው የወጡበት አንዳንድ ሲንከባለሉ የመጡ ወሳኝ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በአሁኑ ጊዜ በኢሕአዲግ አገዛዝ የሴቶች ጉዳይ የተለያዩ ገጽታዎች ኖረውት ነው የሚተገበረው፡፡ አንደኛው ገጽታ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ገብቶ በሚኒስቴር ደረጃ እንዲቋቋም መደረጉ ነው፤›› በማለት ጉዳዩ የተሻለ ትኩረት ያገኘበት አጋጣሚ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህም እንደ መሠረታዊ ለውጥ የሚታይ እንደሆነ፣ በግልና በቡድን ሲደረጉ የነበሩ ትግሎችን በአንድ ማምጣት ያስቻለና ወሳኝ የሆኑ የሴቶች የመብት ጥያቄዎች ምላሽ ያስገኘ እንደሆነ አክለዋል፡፡

     በስኬት ከሚያነሷቸው ዋናዋና ነገሮችም የሴቶች የመብት ጉዳይ የሕገ መንግሥቱ አካል እንዲሆን መደረጉ፣ በዚህ ውስጥም እንደ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ያሉ ጠንካራ ማኅበራት እንዲፈጠሩና በሴቶች መብት አጠባበቅ ላይ ትልቅ እንቅፋት የነበረውን የቤተሰብ ሕጉ እንዲለወጥ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን እንደ ወሳኝ ነጥብ ያስቀምጣሉ፡፡

     ኢትዮጵያ ለሴት ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚችሉ፣ እንዲሁም በነበሩ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች የተከሰቱ የእኩልነት ጉዳዮችንና ጥቃትን መከላከል ላይ ያተኮሩ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ተቀብላ ፈርማለች፡፡ ከእነዚህ ሕጎቸ መካከል እ.ኤ.አ. በ1948 የወጣውን UN Charter እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ1949 የወጣውን Universal Declaration Of Human Right ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሁለቱም ስምምነቶች ሴቶች በፆታቸው ምክንያት ማንኛውም ዓይነት መድልዎ እንዳይደረግባቸው ይከለክላሉ፡፡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም ማንኛውም ዓይነት በሴቶች ላይ የሚደርስ መድልዎን ለማስቀረት እ.ኤ.አ. በ1981 የወጣውን Convention On Elimination Of All Forms Of Discrimination Against Women (CEDAW)ም እንዲሁ ኢትዮጵያ ፈራሚ አገር ነች፡፡

     መሰል ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንደተፈረሙ የፈራሚ አገሮቹ የሕግ አካል ሆነው ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ የሕግ አካል ቢሆኑም በተለያዩ ምክንያቶች ተፈጻሚ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ‹‹የፖሊሲዎች መኖር የመንግሥትን ፈቃደኝነት ከማሳየት ባለፈ ምንም ተፅዕኖ መፍጠር አልቻሉም፡፡ ተፈጻሚነት የላቸውም፡፡ እነዚህ ፖሊሲዎች ባለመፈጸማቸው ተጠያቂውስ ማነው፤›› ሲሉ የሚጠይቁት የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን ናቸው፡፡

     እነዚህ ፖሊሲዎች ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው ማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የቤት ሥራ ቢሆንም ‹‹በጠየቅን ቁጥር ነው ምላሽ የምናገኘው፡፡ ፖሊሲ ስለወጣ ብቻ ተደስተን መተው የለብንም፤›› በማለት የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ በሙሉ ያለዕረፍት ግፊት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ በሴቶች ዙሪያ የሚሠሩ አዳዲስና ነባር ማኅበራት ተናበው መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

     እስካሁን በተደረጉ ንቅናቄዎች የሴቶች ጉዳይ የአገር ጉዳይ ሆኖ ለአንድ አገር ዕድገትና ሥልጣኔ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ታምኖበት በብሔራዊ ደረጃ መዋቅር ተዘጋጅቶለት፣ ስትራቴጂና አቅጣጫ ተበጅቶለት፣ ብሔራዊ ግብ ተነድፎለት የሚሠራበት አገራዊ ጉዳይ ለመሆን በቅቷል፡፡ አሁን ያለበት ደረጃ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ግን የጅማሮውን ያህል መሄድ አለመቻሉን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

     ‹‹ከጅማሮው አንፃር ገና ነው፡፡ በፊት የነበረው የተበታተነ ትግል በአንድ ሆኖ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት ቢቻልም አንዱ የጀመረውን አንዱ የማያስቀጥልበት ሁኔታ መኖሩ ለውጡ የጅማሮውን ያህል እንዳይሆን አድርጎታል፤›› በማለት በትውልድ መካከል ያለው ቅብብሎሽ ደካማ መሆን የጅማሮውን ያህል ብዙ ለውጥ እንዳያመጣ እንቅፋት መሆኑን ይናገራሉ ወይዘሮ አልማዝ፡፡ ለምሳሌ በቃቄ ውርዶት ተጀምሮ የነበረው የጋብቻ መብት ጥያቄ ከጅምሩ ቀጥሎ ቢሆን እስካሁን ብዙ ለውጦችን ማምጣት ይቻል ነበር፡፡ በሲቄ የነበረው የሴቶች ድምፅ እስካሁን ቀጥሎ ቢሆን ሌላው ቢቀር እስካሁን ቤት ውስጥ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይቆም ነበር፡፡ በአጠቃላይ እንደ አጀማመሩ አይደለም የሚሉት ወይዘሮ አልማዝ በትውልድ መካከል ጠንካራ ቅብብሎሽ ቢኖር ከዚህ በላይ መሥራት እንደሚቻል ያምናሉ፡፡

     የሴቶች ጥያቄ ለዘመናት ሲንከባለል እዚህ የደረሰ ከማኅበረሰብና ከባል ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በቀላሉ የሚመለስ አይደለም፡፡ ነገር ግን እስካሁን በተሠሩ ሥራዎች ለውጦችን ማየት ተችሏል፡፡ ከቤተሰብ ሕጉ መሻሻል ባሻገር የሴቶች የመሬት ይዞታ መብት እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ ሴቶች አመራር ላይ እንዲወጡ ከማድረግ አንፃር ግን አሁንም ብዙ ይቀራል፡፡

    ከዚህ ባሻገርም በአሁኑ ወቅት በሴቶች ዙሪያ እየሠሩ ያሉ ነባርና አዳዲስ ማኅበራት እርስ በርስ ተረዳድተው፣ ተናበው መሥራታቸውም ከዚህ በኋላ ለሚኖረው የተጠናከረ ትግል ወሳኝ እንደሆነ ይስማማሉ፡፡ ‹‹እንቅስቃስዎች ሁሉ በየጊዜው አዲስ የሚጀመሩ ሳይሆን ቀጣይነት እንዲኖራቸውና የተነጠሉም እንዳይሆኑ ዕውቅና ሰጥቶ አብሮ መሥራት ያስፈልጋል፤›› የሚሉት ወይዘሮ ሳባ አብሮ ተቀራርቦ መሥራቱ ከሩቅ የሚሰማ ድምፅ እንደሚፈጥር ይናገራሉ፡፡

    እ.ኤ.አ. በ2009 የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት በሴቶችና ሕፃናት ላይ ብቻ የሚሠሩ 42 አባል ማኅበራት ነበሩት፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን የሚገዛው ሕግ ከወጣ በኋላ ግን ለሁለት ተከፈለ፡፡ አንዱ የኢትዮጵያ ሴቶች በጎ አድራጎት ማኅበራት ኅብረት ሲሆን፣ 70 አባላትና ተጨማሪ 10 በመብት ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች ያሉት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ዩኒየን ኦፍ ኢትዮጵያን ቻሪቲ ኤንድ አሶሴሽን የሚባለው 60 አባል ማኅበራት ያሉት ነው፡፡ ‹‹የተሻለ ውጤት ማምጣት የሚቻለው አብረን ብንሠራ አብረን ብንታገል ነው፤›› የሚሉት ወይዘሮ ሳባ ሁሉም ተባብሮ እንዲሠራ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...