የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሜዳዎች በስፖርታዊ ጥበብና ክህሎት፣ በታክቲክና ቴክኒክ ብቃታቸው የሚያስደምሙ፣ የእግር ኳስ ጠቢባን የሚታዩባቸው፣ ሕዝቡ በኳስ ፍቅር የሚጎርፍባቸው ከመሆን ይልቅ፣ የደጋፊዎች እርግጫና ጡጫ አስቀያሚ ቃላት መሰናዘሪያ አለፍ ሲልም ብሔር ቀመስ መሻኮቻዎች ከሆኑ ውለው አድረዋል፡፡
የሜዳ ጦርነቱ ወደ ሠፈርም ተጋብቷል፡፡ የአንዱ ክለብ ደጋፊነቱ የታወቀውን ግለሰብ በደቦ የሚደበድቡ አጉራ ዘለሎች በከተማው የተንሰራፉበት፣ የንግድ መደብሮችን የሚያወድሙ ቡድኖች በክለብ ደጋፊ ስም የተሰባሰቡበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች አካሄድ ከስፖርታዊነት ይልቅ በደብዳቢና አስደብዳቢነት፣ ተሳዳቢና አሰዳቢነት ላይ ሥራዬ ብለው ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ከሰሞኑ በተለያዩ የክልል ከተሞች በተከናወኑ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ባደረጓቸው ጨዋታዎች ተከስቶ የታየውን መመልከቱ ይበቃል፡፡
ይህንን ድርጊት አደብ የሚያስገዛ አካል የሌለ እስኪመስል ድረስ ከጨዋነት የራቀው የሜዳ ላይ ስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል በሜዳ የተጀመረውና ልቅ የወጣው ይህ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ በየመንደሩ ወደሚገኙ ኪዮስኮችና መዝናኛ ቤቶች መዛመት ጀምሯል፡፡
ሊጉን በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለዚህ ራሱን የቻለ የዲሲፕሊን መመርያና ደንብ ቢኖረውም መሬት ማውረድ የሚችል ሙያውን በውል የሚረዳና የሚያውቅ አመራር ባለመኖሩ ሕጉ ከወረቀት ማለፍ አልቻለም፡፡ የስፖርታዊ ጨዋነቱ ጉዳይ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያየረ በዜጎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖና ሥጋት እያሳደረ ይገኛል፡፡
ክፍተቱን እንደ መልካም አጋጣሚ የሚወስዱ የስፖርቱ አጉራ ዘለሎች፣ ሜዳ ውስጥ በተለይም ከዳኝነት ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ ስህተቶች መድረኩን የጦርነት አውድማ ለማስመሰል ሲዳዳቸው መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ከሰሞኑ በ19ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የጨዋታ መርሐ ግብር በአንዳንድ የክልል ከተሞች ማለትም ወልዲያ ላይ በወልዲያ ከተማና በፋሲል ከተማ መካከል በነበረው ጨዋታ ላይ በተፈጠረው ረብሻ የመሀል ዳኛውና ረዳቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ እንግዳ ቡድን ባለሜዳው ላይ ጎል ማስቆጠር በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ፣ ሜዳ ውስጥ በሚፈጠር ግርግር የጨዋታ ዳኞች ከፍተኛ ድብደባና ውክቢያ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ተደባድበዋል፡፡ ንብረት ሲወድም በአደባባይ ታይቷል፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን አሁንም ሊጉን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የብሔራዊ ፌዴሬሽን አመራሮች፣ ውሳኔን በውሳኔ ከመሻር ያለፈ ለቀጣይ አስተማሪ የሚሆን፣ በክለብ አመራሮች፣ በተጨዋቾች፣ በአሠልጣኞችና በዳኞች ላይ የጨዋታ ዳኞችና ሌሎች በተለይም ከዲሲፕሊን ጋር ተያይዞ የተቋቋሙ አካላት ውሳኔ ሲያሳልፉ፣ ውሳኔው ነገ ስለሚሻር ትዝብት አታትርፍ እየተባሉ፣ አለፍ ሲልም ማስፈራሪያና ዛቻ ሲያስተናግዱ ይስተዋላል፡፡
ነገር ግን ሁሉም ስለጨዋታ ፍትሐዊነት ሲናገሩ ይደመጣል፣ ከወሬም ሲያልፍ የጨዋታ ፍትሐዊነት ትርጉም ማለትም ለሁሉም ክብር፣ ያለምንም አድሎ ፍትሕ መስጠት፣ ሕግና ደንብ ለሁሉም ያለ ምንም አድሎ ተግባራዊ ማድረግ፣ በሕጉና በደንቡ መሠረት መጫወት፣ በሕጉና በደንቡ መሠረት መዳኘት፣ በሕጉና በደንቡ መሠረት ያለምንም አድሎ ማስተዳደር፣ በአቅምና በችሎታ ተጨዋቾችን፣ አሠልጣኞችን፣ ተመልካቾችን፣ የጨዋታ ዳኞችንና አመራሮችን ማክበርና መምረጥ፣ የሴቶችን መብት በሕጉና በደንቡ መሠረት ማክበር፣ የወጣቶችን ህልም ተግባራዊ እንዲሆን ያለምንም የዘር፣ የሃይማኖትና የፆታ አድሎ በሕግና በደንቡ መሠረት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሳይሰብኩ ያለፉበት ጊዜ የለም፡፡
አተገባበሩም ከላይ ወደ ታች የሚወርድ ሆኖ ከምንም ነገር የፀዳ፣ ቀና አመለካከት ያለው፣ ዓላማውም በትክክለኛው መንገድ፣ በሕግና በደንብ ሥራ ላይ መዋል እንዳለበት የሚያምኑም በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ ፍትሐዊ የጨዋታ ሥነ ምግባሮች ከዚህም በላይ የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ምርጫ ሳይቀር በምን መልኩ መተግበር እንዳለበት የሚያሳስቡ ስለመሆናቸው ጭምር ሲነገር ይደመጣል፡፡
ፍትሐዊ የስፖርታዊ ጨዋነት መርሕ እነዚህ ከሆኑ፣ በኢትዮጵያ በተለይም ከቅርብ ወራት ወዲህ በእግር ኳስ ሜዳዎችና ከሜዳ ውጪ የሚስተዋሉ ድርጊቶች ለምን ይከሰታሉ? የሚሉ ወገኖች አይጠፉም፡፡ ጥያቄውን ከሚያነሱት አንዳንዶቹ ‹‹ሜዳ ላይ የሚስተዋለው ግጭትና አምባጓሮ ወትሮም የነበረና ያለ ነው፡፡ የዘንድሮው ግን ከመቼውም ጊዜ የሚነፃፀር አይደለም፡፡ አሠልጣኞች፣ ተጨዋቾችና የቡድን ደጋፊዎች ውጤት ሲያጡ ምክንያቱን ወደ ውስጥ ከመመልከት ይልቅ ውጫዊ ሲያደርጉት ይስተዋላል፡፡ ጨዋታው ለሚወስደው ጊዜ የተቀመጠው ሕገ ደንብ፣ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች እስኪቀሩት ጥፋት ቢፈጸም፣ በተለይ የጨዋታ ዳኞች ለጥፋቱ ተመጣጣኝ የሕግ ውሳኔ ከወሰኑ እንደ ወንጀለኛ ይቆጠራሉ፡፡ ከዚህ ሲያልፍም ሕይወታቸውን ጭምር ሊያሳጣ የሚችል ድብደባና ውክቢያ ይፈጸምባቸዋል፡፡ ከሰሞኑ እየታየ ያለውም ይኼው ጥሬ ሀቅ ነው፤›› በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት ያጎሉታል፡፡
ስለዚሁ ጉዳይ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ አመራር ሲናገሩ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግም ሆነ በሌሎች ዲቪዢዮኖች ለችግሮቹ በዋናነት ተጠያቂው ከእሳቸው ጭምር አመራሩ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለው አመራር ሁሉም እንደሚያውቀው የአገልግሎት ጊዜውን ያጠናቀቀ ነው፡፡ ከአመራሩ አብዛኛዎቹ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ለሁለተኛ ጊዜ ለመምራት ዕጩ ሆነው ለምርጫ የቀረቡ ናቸው፡፡ ምርጫውን በብቃት ለማለፍ ደግሞ የእያንዳንዱ ክልልና ክለብ ድምፅ ወሳኝ ነው፡፡ ስለሆነም ማንኛውም ክልልም ሆነ ክለብ ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ የሆነ የዲሲፕሊን ጥፋት ቢፈጽም፣ አስተማሪና ተመጣጣኝ የሆነ ዕርምጃ ለመውሰድ ሞራሉም ሆነ አቅሙ አይኖረውም፡፡ ዕርምጃውን እወስዳለሁ የሚል ክሆነ ደግሞ የምርጫውን ውጤት ምንም ሆነ ምን ለመቀበል ዝግጁነቱ ያለው ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው የንዑሳን ኮሚቴዎች ውሳኔ በማግሥቱ ሲሻር የምንመለከተው፤›› በማለት ያለውን ተግዳሮት ያስረዳሉ፡፡