Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየተዘጉ በሮች ይከፈቱ!

የተዘጉ በሮች ይከፈቱ!

ቀን:

ብዙዎቻችን ከእኛ ውጪ ስላሉ አካላት ሲነገረን ማዳመጥ የምንፈልገው የሆነውና እውነታውን ሳይሆን፣ እኛ እንዲሆኑልን የምንፈልገውን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም የምንተቻቸው አካላት የሚተቹበትን እንጂ እውነታውን መስማት የኮሶ ያህል የሚመር ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡ ፖለቲከኞች፣ የአገር መሪዎችና ሌሎችም ከዚህ ክፉ ወጥመድ ሊያመልጡ አልቻሉም፡፡ የፖለቲካ ልዩነት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ እንኳ አንዱ ስለሌላው የሚናገረውና መስማት የሚፈልገው አሁን ላይ አስፈሪነት እየታየበት ነው፡፡

ችግሩ የሐሳብ፣ የአመለካከት፣ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት መኖሩ አይደለም፡፡ አንዱ የሌላውን ሐሳብ ተረድቶ ተጠየቂያ በሆነ መንገድ የሐሳብ ክርክር መኖሩም ችግር አይሆንም፡፡ ሐሳብን በለጋነቱ መግደል፣ ከመደመጡ በፊት ማምከን ግን ተገቢነት የለውም፡፡ እንዲሁም ጤናማ በሆነ አመለካከትና በበቂ መረጃዎች ላይ በተመሠረተ ትንተና ከሆነ ልዩነቱን አንጥሮ ለማወቅ ብቻም ሳይሆን፣ በሐሳብ ለመቀራረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ግን መቼ ይሆን ነገሮችን በዚህ መንገድ ወደ ተግባር ምዕራፍ ተሸጋግረው የምናያቸው? ይህን ለማየት እናፍቃለሁ፡፡ ታላቁ ዳኛ ህሊናዬ ማዘኑ እስከ መቼ? እያለ ይጠይቀኛል፡፡

በፖለቲካም ቢሆን አንዱ ሌላውን ከመሳብ ይልቅ ያሉትን መሠረታዊ ችግሮች እንዲስተካከሉ፣ ስህተትን ማሳየት ከጤነኛ አዕምሮና ከተማረ ዜጋ የሚጠበቅ ጤናማ ጠባይ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ መንፈስና በጎሪጥ ከማየት አልፎ ለሚሠራው ሥራ የሚሰጠው ትንታኔ አንድን ወገን ብቻ መሠረት ያደረገ ሲሆን ይታያል፡፡ በዚህ ምክንያት መንገዱ ሁሉ የዳጥና የመሰናክል ይሆናል፡፡ ከአገራችን ዋና ዋና ችግሮች መካከል ዘረኝነት ትልቁ በሽታ ነው፡፡ በዘረኝነት መንፈስ የሚናጡ ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር እየተበራከተ ነው፡፡ ከተላላኪ እስከ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች በዚህ ክፉ በሽታ ተለክፈው ማየት የተለመደ ነው፡፡ ሸዋ፣ ወሎ፣ ትግራይ፣ ኦሮሞ፣ ወላይታ፣ ወዘተ ተብሎ በስምና በአካባቢ ያልተፈረጀውን ሰው ማየት ይከብዳል፡፡ ዘረኝነትን የሚያራግቡ መንደርተኞች ጥቂቶች አይደሉም፡፡  

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

 መንፈሳዊ ተቋማት የዘረኝነት በሽታው ፀንቶባቸዋል፡፡ ከክልል ከተሞች ደግሞ በአዲስ አበባ አገረ ስብከት ውስጥ የሚታየው ዘረኝነት የከፋ ነው፡፡ የአገራችንን እውነተኛ መልክ ያጠፉ፣ ዘመን አመጣሽ ብልሹ አሠራሮች እስካልተወገዱ፣ ብቃትና ክህሎት ያላቸው፣ የሕዝቡን አስተሳሰብ በተሻለ ሁኔታ ሊለወጡና ሊቀርፁ የሚችሉ መሪዎች ካልተሾሙ በቀር የጠቅላይ ሚኒስትር መቀየር ብቻውን ለውጥ አያመጣም፡፡

ነገሩ ሁሉ ‹አንድ ሰው አስቦ አንድ በሬ ስቦ› ይሆናል፡፡ ዛፍ ያለ ቅርንጫፍ እንዴት ያምራል? ግንድ ብቻውን ‹‹እኔ አቶ ግንድ እያለ ቢፎክር፣ ግንድ ሁኖ ከመቅረት በቀር ምን ያምርበታል? ጠቅላይ ሚኒስትሩና አብረዋቸው የሚሠሩት ሚኒስትሮች በቅንነት አስበው ካልተደጋገፉ ምኑን ለውጥ ይመጣል ትላላችሁ፡፡ በመናገር አገር አትለማም፡፡ በማውራትና በሚዲያ በመጮህም አገር አትታነፅም፡፡ በጩኸትስ ቤት የሚታነፅ ቢሆን አህያ በቀን መቶ ጊዜ በሚያናፈው ጩኸቱ መቶ ቤት በሠራ ነበር፡፡ መደማመጥ የጠፋበት ችግሩ አንድና አንድ ነው፡፡ በየሰው ልቦና ውስጥ የተዘጉ በሮች ስላሉ ነው፡፡ እነዚህ መከፈት ይኖርባቸዋል፡፡

አለዚያ ልፋቱ ከንቱ፣ ጉልቻ መለዋወጥ፣ ደረቅ ጩኸትና ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ ስለዚህ መፍትሔው የልቦናችንን በር መክፈት ነው፡፡ በዘረኝነት፣ በጎጠኝነት፣ በጎሰኝነት፣ በጥላቻና በመሳሰሉት የተዘጉት ሁሉ መከፈት አለባቸው፡፡ ይምረረንም፣ ይጣፍጠንም የልቦናችንን በር ከፍተን አዕምሮአችንን ከፍርኃትና ከጥርጣሬ ንህ አድርገን ሕዝቡ የሚለውን ለማዳመጥ እንሞክር፡፡ በቅንነትና በበጎ ሕሊና የሕዝቡን የልብ ትርታ ካዳመጥን ሌሎች እንኳን ተሳስተው ከሆነ ቢያንስ ስህተታቸውን በትክክል ለመረዳት ያስችለናል፡፡ የልቦናችንና የቢሮአችን በር ዝግ አድርገን ስለአገር መልካም የሚናገሩትን፣ በአገር ላይ ለውጥ ይምጣ የሚሉትን ጦማርያንን በማረሚያ ቤት መዝጋት ግን ተገቢነት የለውም፡፡ ለአገርም አይጠቅምም፡፡ መከፈት ባለበት ሰዓት ያልተከፈተ (የተዘጋ) ደጅ ደግሞ በኋላ ቢከፈት እንኳን እውነቱን ለመረዳት ያስቸግራል፡፡ ‹እግሬን ታጥቤያለሁ እንዴት እቆሽሻለሁ?›፣ ‹ልብሴን አውልቄዋለሁ እንዴት እለብሰዋለሁ?› እያልን የማይጠቅሙ ምክንያቶችን በመደርደር የመሥሪያ ቤታችንና የልቦናችን በር በቅንነት ካልከፈትን፣ ከወሬ ያለፈ ተግባር ማየት ሞኝነት ይሆንብናል፡፡

‹‹የዘር ጥላቻ የሚያሠራጭ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነ ከሰው ተራ የወረደ ያልሠለጠነ ኋላቀር ክፉ አውሬ ነው፡፡›› (የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ሐረግ ምንጭ ገጽ፣ 125) የሚለው አነጋገር ጥሩ ነጥብ ያለው ነው፡፡ ፌንጣ በኃይል እፈናጠራለሁ ስትል ክንፏዋን በነፋስ ታስገነጥላለች ይባላል፡፡ ለዚች አገር ኢሕአዴግ ብቻ ነው መፍትሔ ማለት ግፍም ክፋትም የሚያመጣ ሊሆን ይችላልና መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ስለ ሕዝብ ሳይታሰብ ሲቀር፣ የጥፋት ሰው ስለሚያመጣ ከዚህ ያለው አስተሳሰብ መንጻት ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ዓለም እንቅፋት የሌለበት ሜዳ አይገኝም፡፡ ያልታረሰ መሬት እህል ቢዘሩበት አያበቅልም፡፡ በፖለቲካ ያልታሸ መሪም፣ ያልለፋ ቁርበት ይሆንና አመሉ ለሕዝቡ አይመችም፡፡ በብዙዎች ዘንድ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ (ዶ/ር) መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ያደረጉት ንግግር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ ነገር ግን ቢከፍቱት ተልባ ሆኖ እንዳይቀር የሚል ሥጋት ያሳድራል፡፡ በንግግርና በቃላት ጥርቅም ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚሉ ሰዎች እየተበራከቱ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን ከቁም ነገር ሥፍራ ሊያውሉት ይገባል፡፡ ሕዝቡ ሥራ ተሠርቶ ማየት ይፈልጋል፡፡ ከሰማይ ዝናብ ዘንቦ ምድሩን ካላራሰውና የተዘራውንም እህል እንዲበቅል ካላደረገው፣ ጉርምርምታና ነጎድጓድ ብቻውን በምድር ላይ አንዳች ጥቅም ሊያስገኝ አይችልም፡፡ ከንግግርም በላይ፣ የተግባር ምዕራፉ ከቃል የበለጠ ያስተምራል፡፡ ‹‹አርኀው ኆኀተ መኳንንት››፣ መኳንንት ደጆቻችንን ክፈቱ!

(ተመስገን ዘገየ (ዲ/ን)፤ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...