Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየአዲሱ መሪ ሐሳብና ያልተነካው ሙስና

የአዲሱ መሪ ሐሳብና ያልተነካው ሙስና

ቀን:

በልዑል ዘሩ  

የኢትዮጵያ መንግሥት ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሲያስመርጥ አይደለም የራሱ የገዥው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎችን ይቅርና  ሕዝቡንም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን (ተቃዋሚ ከማለት ይህ ስያሜ የተሻለ ያቀራራርባል፣  እንጠቀምበት ብለው የጠየቁትም እሳቸው ናቸው)፣ ተስፋ እንዲያሳድሩ  ያደረጋቸው ንግግርና የቀጣዩ ጊዜ አቅጣጫን ለምክር ቤቱና ለመላው ሕዝብ አቅርበዋል፡፡ በርካታ ነጥቦች ከተነሱበት ንግግራቸው መሀል ታዲያ ስለአስመራሪው ሙስናና መጠናከር ስላለበት ሕዝባዊ ትግሉ ከማሳሰብ አለመቆጠባቸው አንዱ ነበር፡፡ 

በዚህ ጸሐፊ ዕይታ ይህ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ተግባራት አንዱ ነውና ዛሬ ሙስና ላይ ያነሱትን መመልከት ተፈልጓል፡፡ በቀጣይም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር መሀል ፈጣን ትግበራ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ነቅሼ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ነበር ያሉት፡፡ ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕዝባችንን ብሶት ካጋጋሉት ዋና ዋና ምክንያቶች መካካል ሙስና አንዱ ነው፡፡ ሙስናን ፀረ ሙስና መሥሪያ ቤት በማቋቋም ብቻ መከላከል እንደማይቻል ተረድተን፣ ኢትዮጵያችን አንዱ ሠርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር  እንዳትሆን ለመጠበቅ ሁላችንም የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ እጠይቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ሙስና በመላው ዓለም አገሮች ውስጥ አለ፡፡ ዋነኛ የሥርዓቶች ብልሽት ማሳያ፣ ወይም ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም የጥቂቶችን አጋባሽነት የሚያረጋጋጥ በሽታ ቢሆንም፣ የአስከፊነቱ ደረጃ ይለያያል እንጂ ሙስና የሌለበት አገርም የለም፡፡ በዓለም ላይ በዴሞክራሲ ረገድ በጣም የተሻለ መንግሥትና ሥርዓት እንዳላቸው የሚነገርላቸው እንደ ዴንማርክ፣ ኒውዚላንድ፣ ፊንላንድ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ስዊዘርላንድ፣ ሲንጋፖር፣ ኔዘርላንድ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያና የመሳሰሉ አገሮች በሙስና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተብለው የተፈረጁ መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ‹‹ሙስና የለባቸውም›› ግን አልተባለም፡፡ ‹‹ሙስና አለባቸው ግን የሙስናው ደረጃው ዝቅተኛ ነው፤›› ማለት ነው፡፡

እንደ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሬቲንግና ዴሞክራሲ ኢንዴክስ የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ የሙስናና የዴሞክራሲ ደረጃ አውጭ ድርጅቶች፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ዘገባ ይፋ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ በእነዚህ አካላት ዕይታ እ.ኤ.አ. በ2017 መጨረሻ ላይ የወጣ አንድ መረጃም አለ፡፡ የ150 አገሮች ጥናትን መሠረት አድርጎ በቀረበው መረጃ በሙሰኝነት ለአፍሪካ አገሮች ከተሰጣቸው ደረጃ ናሚቢያና ሩዋንዳ 41ኛና 40ኛ ደረጃ ሲያገኙ፣ ደቡብ አፍሪካ 52ኛ፣ ሴኔጋል 54ኛ አግኝተዋል፡፡

በዚህ ጥናት መሠረት ከ150 አገሮች መካከል ኢትዮጵያ 86ኛ ደረጃ ተሰጥቷል፡፡ ምናልባት ይህ ደረጃ ኢሕአዴግ በተሃድሶ መድረኩ የደረሰበትንም ሆነ፣ ሕዝቡ ክፉኛ እያዘነበት ያለውንና አሁንም መንግሥት ጉሮሮውን ሲያንቀው ዕርምጃ መውሰድ እየጀመረበት ያለውን የሙስና መረጃ እንዳላካተተ ግልጽ ነው፡፡ በተለይ በከተሞች ካለው የበላይነት አንፃር ሙስናው ዋነኛ የኢፍትሐዊነት ገዥ መሬት መሆኑም ገሃድ እየወጣ መጥቷል፡፡

በእርግጥም ተደጋግሞ እንደሚባለው ኢትዮጵያውያን በሙስና እየተማረሩ ናቸው፡፡ ያውም ቀስ በቀስ እያቆጠቆጠ ከመጣ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት፣ ከመልካም አተዳዳር ዕጦት ከሚመነጭና ብዙኃኑን ሕዝብ ክፉኛ ከሚያማርር ሙስና አንፃር ሕዝቡ ወገቡ መቆረጥ ጀምሯል፡፡ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ‹‹የእኛ ሙስና ይሻላል›› የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም፣ ራሱ ገዥው ፓርቲ በተሃድሶ እንዳረጋገጠው ሙስናው የሕዝቡንም ሆነ የፖለቲከኛውን የሥልጣን አተያይ እስከ መቀየር የደረሰ ወራዳ ተግባር ሆኗል፡፡ በተለይ በከተሞቸ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባበሰ የመጣ፣ በዋናነት በፖለቲካ ሥልጣን ላይ ተመሥርቶ የሚፈጸምና ክፉኛ አገራዊ አብሮነትን የሚሸረሽር (ኢፍትሐዊነትን በማንገሥ) በመሆኑ፣ ከአቅማችን በላይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡  ፈጣን ዕርምት ካላገኘም ወደ ገደል የሚወስድ አደገኛ መንገድ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በከተሞች፡፡

ከፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ትንታኔ አንፃር ከተሞች ከገጠር በተሸለ ለፈጣን ልማትና ዕድገትም ሆነ ለውድቀትና ብልሹነት እጅግ ቅርብ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የተለያዩ  የዓለም ከተሞች  በሚያስገርም ደረጃ በአንድ ጊዜ ለብዙዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩት፡፡ እንዲሁም ከፍ ያለ የገቢ ምንጭ የሚሆኑት፡፡ በዚያው ልክ በመልካም አስተዳዳር ዕጦትና የሥራ ዕድልን መፍጠር ባለመቻል ለከፋ ችግርና ሕዝባዊ ማዕበል የሚጋለጡትም ትንሽ አይደሉም፡፡ በዚያውም ለአገር ክስረትም መንስዔ ሲሆኑ ታይተዋል፡፡ ትሪፖሊን፣ ካይሮን፣ ደማስቆን፣ ባግዳድን…. ልብ ይሏል፡፡

በሙስና ደረጃም ስንመለከት ከተሞች ከገጠር በበለጠ ለሙስና የታጋለጡ ናቸው፡፡ በሥርዓትና ሕግ ካልተመራ የከተሞች መሬት እንደ ማዕድን ነው፡፡ በተለይ ቀስ በቀስ ተጠቅልሎ በጥቂቶች ዕጅ የመግባት ዕድሉ በጣም ሰፊ ከመሆኑ ባሻገር፣ ቢሮክራሲው እንደ ሕዝብ ሀብት በጥንቃቄ ካልጠበቀው የጥገኝነት መፈልፈያ  መሆኑም የታወቀ ነው፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የኦሮሚያ ከተሞች ባለፉት ዓመታት የተፈጸመው ግፍ፣ እንደ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ ሌላው ይቅርና እነ ደብረ ብርኃንና ሆሳዕና እንኳን… የታየባቸው ሕገወጥ የመሬት ንጥቂያ ዕውን የመንግሥት መኖርን ያመለክት ነበርን? የሕዝቡንስ የመሬት ባላቤትነት ያረጋግጥ ነበር ብሎ ለመጠየቅ የሚያስገድድ ነው፡፡ በራሱ በመንግሥት ስግብግብ የመሬት ጨረታ አንድ ካሬ መሬት ግማሽ ሚሊዮን ብር ሊሸጥ ምን ቀረው? ታዲይ ይህ ጣሪያ የነካ ዋጋ እንደ ምንም ብሎ ‹‹መሬት መዝረፍና መቀራመት ወይም ሞት››ን ለአመራሩ  አያስተምር ይሆን?

በከተማ አስተዳዳሮች ብዙዎቹ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለአድሎአዊ አሠራርና ዜጋ ለማማረር በጣም ቅርብ ናቸው ለማለት ያስደፍራል፡፡ በአንድ በኩል በአንድ ላይ ታጭቆ የሰፈረ ሕዝብ ፍላጎት፣ በሌላ በኩል ከተሞች ከገጠር የሚፈልስ ሕዝብ የመሳብ ኃይል ስላላቸው ተገልጋይ መብዛቱ አይቀሬ ነው፡፡ ስለሆነም ከመንግሥታዊ አገልግሎት አንፃር የአስተዳዳር፣ የፍትሕና የፀጥታ አገልግሎትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሕዝቡን  እየተሳተፉ፣ በግልጽነትና የተጠያቂነት ቅኝት በሥነ ምግባር መምራት ካልተቻለ ዋነኛ የብልሽት ምንጮች መሆናቸውን መጠራጠር አዳጋች ነው፡፡ እዚህ ላይ በተለይ በዋና መዲናችን ቢሮክራሲውን ለማስተካካል ስንት እየተደከመ ተግባሩ ሽንፍላ የማጠብ ያህል ከብዶ ያለው ለምንድነው ማለት ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

እዚህ ላይ ባለፉት ዓመታት በሕገወጥ ግንባታ ስም ምን ያህል ዜጋ ቤት አልባ ሆኖ እርቃኑን ቀረ? በመልሶ ማልማት ስምስ (ልማቱ ቢያስደስትም) ያለበቂ ካሳና ምትክ ቦታ ስንቱ የኖረውን ተስፋ አሟጦ እጁን ለድህነት ሰጠ? እነዚህን ተግባራት በመፈጸም በኩልስ እንዴት ያለ አስተዳዳርን በመተግበርና ግልጽነትን በማረጋጋጥ ለማከናወን ተሞከረ? ከሁሉ በላይ በተሃድሶ ወቅት እንኳን በተነሱ ዜጎች መሬት ላይ (የአምናውን የሃና ማርያም ሁኔታ ልብ ይሏል) ሥልጣንን መከታ አድርገው በጉልበታቸው በመስፈር የኤሌክትሪክ ኃይል አስገብተው የግንባታ ግብዓት ማምረት ጀመሩ፡፡ ዕውን ይህ አካሄድስ አገርን የሚያቆም ተግባር ነውን ብሎ መጠየቅ በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አመራርና ከታደሰው ኢሕአዴግ በአፋጣኝ የሚጠበቅ ነው፡፡  

በአገሪቱ የግብርና የታክስ፣ የንግድ ሥርዓቱና የግብይት ምኅዳሩ ሁሉ ለሙስና ይበልጥ የሚጋለጠው  በከተሞች እንደሆነ ጥናቶችም አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከተሞች የያዟቸው ከገጠር በተሻለ የተማሩ፣ የተሻለ ገቢ ያላቸውና ለዓለም አቀፉ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት የቀረቡ ሰዎችን መሆኑም የራሱን አስተዋፅኦ ያሳድራል፡፡ በእኛም አገር የከተማው አራዳና ጮሌ ሁሉ ወደ ጉዳይ ገዳይነትና የመሬት ደላላነት ወይም ወደ ሕገወጥ ስደት አስተባባሪነትና ኮንትሮባንዲስትነት ተቀይሮ ስናይ አደጋው ምን ያህል እንደ ሰደድ እሳት እየለበለበን እንደመጣ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ የአዲሱ አመራር አንዱ ቀዳሚ ፈተናም ይኸው ነው፡፡

በእርግጥ በእኛ አገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰና ዓይን እያወጣ መጣ እንጂ፣ ሙስና ዋነኛ መገለጫችን አልነበረም፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ በአንድ ጀንበር፣ በንፋስ አመጣሽ ሀብት የቅንጦት ጣሪያ ላይ የሚያወጣ የምጣኔ ሀብት መሰላልም አልነበረንም፡፡ ምንም ተባለ ምን ግን አሁን ባለችው አገራችን በተለይ በከተሞች ያለውን ሙስናና የመልካም አስተዳዳር ብልሽት በተጠናከረ መንገድ በመቅረፍ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና የዴሞክራሲ ሥርዓትን ማጠናከር ካልተቻለ አደጋው ለአገር መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ የትውልድ ተወቃሽነትን የሚያሰከትል ብቻ ሳይሆን በጋራ አብሮ ለመኖርም የሚያውክ አደጋ እንደሆነ መገንዘብም ያስፈልጋል፡፡

በመሠረቱ ሙስና የትም ቢሆን ሁለት ዓይነት ነው፡፡ ግለሰባዊና ሥርዓታዊ (Individual and Systemic Corruption) በአፍሪካ ደረጃ እንደ ኬንያ፣ ዛየር፣ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ግብፅ፣ ሊቢያ፣ ናይጄሪያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ… የመሳሰሉ አገሮች ውስጥ ያለው ሙስና ሥርዓታዊ (Systemic) ነው፡፡ ከላይ እስከታች ያሉ ባለሥልጣናትና በየደረጃው የሚገኙ ሹመኞችና ሠራተኞቻቸው ጭምር እከሌ ከእከሌ ሳይባል በሙስና የተዘፈቁበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ የራሴ የሚሏቸውን ሰዎች፣ ቡድኖችና ድርጅቶችም በልዩ ሁኔታ በመጥቀም ሙስናን  የፖለቲካ መሣሪያ እስከ ማድረግ ይሄዳሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የእኛም ሁኔታ ወደዚህ ዓይነቱ ገጽታ የመሄድ ዝንባሌ ሲያሳይ የሚደነግጡ ሰዎች መብዛታቸው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ምልክቶች ስላሉ ነው፡፡

በተጨባጭ የእኛ አገርና መሰል ታዳጊ አገሮችን እየፈተነ ያለው ግን በዋናነት ግለሰባዊ ሙስና (Individual Corruption) ስለመሆኑ ልንጠራጠር አንችልም፡፡ በመሠረቱ በመርህ ደረጃ ወይም ሕጐቻችን ሙስናን አይፈቅዱም፡፡ ከየትኛውም ብሔር ይምጡ፣ በየትኛውም ዕድሜ ይገኙ በርከት ብለው በሥልጣን ላይ ያሉና ሆን ብለው የቁጥጥር ሥርዓቱን ያዳከሙ ሰዎች በብዛት ዘርፈው በልፅገው ሊሆን ይችላል፡፡ በልፅገዋልም፡፡ ይህንን ድርጊት አዲሱ አመራር በፍጥነት ሕዝቡን አነቃንቆ ካልታገለው የሚፋጠነው አገራዊ ውድቀታችን ብቻ ነው፡፡

በተለይ አዲስ አበባን በመሰሉ ከተሞች ሙስና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በባሰ ሁኔታ  እየታየባቸው ያሉ አዳዲስ ዘርፎች አሉ፡፡ ሌላው ይቅር በማኅበራዊ ዘርፍ የጤናው ሴክተር ላይ ከተመዘገቡ ውጤቶች በላይ የከፋ ሙስናና መጠቃቀም መንገሡን  መረጃዎችና የሕዝብ ቅሬታዎች እያስገነዘቡ ነው፡፡ ለምሳሌ ብንወስድ መጀመርያ ዘውዲቱ፣ በቅርቡ ደግሞ ምኒልክ፣ አሁን ደግሞ የካቲት 12 ሆስፒታሎች፣ ከዚያም ብሶ በኤችአይቪ/ኤድስ ዕርዳታዎችና የመንግሥት በጀቶች ላይ፣ ከመንግሥት ግዥ፣ የአገልግሎት ጨረታና ፋይናንስ ወጪ ጋር በተያያዘ አደገኛ ዘረፋ እየተፈጸመባቸው መሆኑን የቅርብ ታዛቢዎች እየገለጹ ነው፡፡

ጤና ጣቢዎችን ጨምሮ በዘርፉ ከሰው ኃይል ቅጥርና ዝውውር ጋር ያለው ብልሽት ግልጽነትና ተጠያቂነት አልባ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በተለይ በፋይናንስና በግዥ ዘርፍ እየተመደቡ ያሉ ሰዎች በድርጅት አባልነት ስም ለዘረፋው ተስማሚ የሆኑ የኔትወርክ ውጤቶችም ናቸው፡፡ በተመሳሳይ በትምህርቱ ዘርፍ በተለይ የግሎቹን ከማስተዳዳር አንፃር ያለው ብልሽትም ሕዝቡን ለከፋ ምሬት እየዳረገው ነው፡፡ ትግሉ መጀመር ያለበት እንግዲህ ከእነዚህ ውድቀቶች አንስቶ መሆን አለበት የሚሉ ትንታኔዎች ዋጋ ሊያገኙ ግድ ይላቸዋል፡፡

 አስገራሚው ነገር ደግሞ በከተማዋ ምክትል ከንቲባ የሚመራው ይህ ዘርፍ  አደገኛ የኔትውርክ ትስስር ያለበትና በሙስናም የተጠረጠሩ ሰዎች ለጊዜው ከቦታቸው  ይነሱ እንጂ፣ ዘወር ተደርገው እስከ ሚኒስቴር ‹‹አማካሪነት›› የሚመደቡበት ድራማ  መቀጠሉና መነካካቱ እስካሁንም የዘለቀ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁኔታም እስከ ዛሬ የሙስና ቀጣናዎች ሲባሉ ከነበሩት እንደ መሬት፣ ግብር፣ መሠረተ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ሌሎችም ውጪ ተጠናክሮ የመጣ ፈተና ሆኗል፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ መንግሥት በራሱስ ቢሆን ምርር ያለ ሕዝባዊ የፀረ ሙስና ትግል እንዲዳረግ ይፈልግ ይሆን? የሚለውን የብዙዎችን ሥጋት የዶ/ር ዓብይ አቅጣጫ ካላስቀየረው ውድቀቱ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ አገርንም ዳግም ሌላ ዋጋ የሚያስከፍል ነው፡፡

አሁን አሁን በተለይ በከተሞቻችን (የአዲስ አበባ የለየለት ነው) የሚሰማው አንዳንዱ ሙስና አስፈሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ በነገራችን ላይ በአገሪቱ የፈለገው ንፋስ አመጣሽ ገንዘብ ቢያጥለቀልቀን ማነህ የሚል ባለመኖሩ እንጂ፣ ከአምስት ሺሕ ብር የማይበልጥ ወርኃዊ ደመወዝተኛ በሚሊዮን የሚገመት ተሸከርካሪ፣ መኖሪያ ቤት ወይም ሌላ ንብረት ባለቤት ወይም ዕቁብተኛ መሆኑን የምንሰማው እንደ ቀልድ መሆን ነበረበት? ይኼ ችግር በሁሉም ዘርፍ ያው በመሆኑ እዚህ ላይ መወሰድ ያለበት ዕርምት ምንድነው ብሎ መፈተሸም አለበት፡፡

ዛሬ በየመስኩ የሙስና ጨዋታው ተቀይሮ  በሚሊዮን ብሮች ሆኗል፡፡ ተራ ፖሊስና የከተማ ደንብ አስከባሪ ሳይቀር ሕገወጥ ንግድ፣ ሕገወጥ ግንባታ፣ ሕገወጥ የተሸከርካሪ አቋቋም… በሚል ኪሱን የሚያደልብባቸው የኑሮ መደጎሚያዎች ተፈጥረውለታል፡፡ በፖሊስ የምርመራ መዝገብና በፍርድ ችሎት የመነገድ ያህል የሚሞስኑ ጅቦች እየተጠናከሩ መምጣታቸውስ ምን ያህል የተጠናከረ ትግልና ቁርጠኝነት ያስፈልገዋል መባልም አለበት፡፡ የፈለገው የግምገማና አውጫጭኝ በረዶ ቢዘንብ መነካካት ተዘንግቷል፡፡ እየተድበሰበሱ ሕዝብን ለማማረር ማሰብ ግን ሊገታ ይገባል፡፡

በመሠረቱ ጉቦ የለመደ ሠራተኛ ገንዘብ ይዞ ላልመጣ ተገልጋይ ጉዳዩን ሊፈጽምለት አይችልም፡፡ አበሳጭቶ፣ አመላልሶና አማርሮ በመላክም ዜግነቱን እንዲጠላ ያደርገዋል፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲማረር ይገፋዋል፡፡ መረጃ ቢኖርህ እንኳ ማስረጃ አምጣ  እያለ እንደ ውኃ ቀጅ ያመላልሳዋል፡፡ ይኼም ተገልጋዩ ሳይወድ በግድ በእጁ ለመሄድ፣ በእጅ መንሻ ለመኖር እንዲገደድ ያደርገዋል፡፡ የግልጽነትና የተጠያቂነት ሥርዓቱ በርትቶ ጥበቃና ዋስትና ካልሰጠው የሚፈጸመው ሙስና በሥርዓት ደረጃ እየመሰለ ሕዝቡ ከመራድ ሊወጣ አይችልም፡፡ (ይህን መሬት ላይ ያለ እውነት ነው የድኅረ ተሃድሶው ኢሕአዴግም ሆነ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርና አመራራቸው መገንዘብ አለባቸው!!)

በመሠረቱ አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ የተስፋፋ ሙስናና ዕላፊ የመጠቀም ችግር ለመንሰራፋቱ ማስረጃው የሹመኛው ወይም የአንዳንዱ ሠራተኛ የኑሮ ሁኔታ  ነው፡፡ ሳይነግድ፣ ሳይሸጥ፣ ሳይለውጥ በአጭር ጊዜ ይኼን ሁሉ ሀብት ማግኘቱ እንደ ማስረጃ ተቆጥሮ ጥያቄ ሊቀርብበት በተገባ ነበር፡፡ አንዳንድ በቅርብ የምናውቃቸው ቱባ የሚባሉ የፌዴራልና የክልል መንግሥት ባለሥልጣናት፣ በተለይ በአዲስ አበባ አንዳንድ ቢሮዎች የሚገኙ አመራሮችና ሙያተኞች በስማቸው ቢቀር በዘመድና የሚስቶቻቸው ወገኖች የካበተ ሀብት እንዳላቸው በይፋ እየታየ ነው፡፡ ከአገር ሀብት የሚያሰድደውም ጥቂት አይደለም፡፡ የሕዝቡን የአደባባይም ሆነ የቡና ላይ ጨዋታን በቅጡ ላዳመጠው ማጠንጠኛው ይኼው እየሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ውኃ የበላው የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሀብት ምዝገባ ጉዳይ አቧራውን አራግፎ መነሳት የሚኖርበት ጊዜ አሁን መሆኑ ሊጤን ይገባዋል፡፡

በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ ከትልልቅ ሕንፃዎች ጀርባ የሚነሱ ስሞች መፈተሽ ይኖርባቸዋል (ይህን ጉዳይ ተሃድሶውም እንደሚያጣራ መግባባት ላይ መደረሱም ይታወቃል)፡፡ በአጭር ጊዜ በኮንትሮባንድ፣ በቀረጥ ነፃና በመሬት ወራራ ቁንጮ በለሀብት መሆን የጀመሩ ጥገኞች አሁንም ቁጭ ብለው ኪራይ ለመሰበሰብ የሚስገበገቡት ተቆጪ ባለማግኘታቸው ነው፡፡ ወይም በእነርሱ መዘዝ አገርና ሕዝብ የከፈሉትን ውድ ዋጋ ችላ ብለው ነው፡፡

እዚህ ላይ እስካሁን መንግሥትም ቢሆን ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን አምርሮ እንደሚታገል ከመግለጽ አልፎ ዋነኛውን የችግሩን ቀፎ መነቅነቅ የቻለ አይመስልም፡፡ በተሃድሶ ጥልቅ ግምገማ ከጥገኛ ግለሰብ አልፎ ያልበላውን በስመ የብሔር ተወላጅ ሁሉም የበላይ፣ የበታች እያስባለ ሲያባላው የከረመውም ይኼው የትግል መዳከም ነበር፡፡ እውነት ለመናገር እስካሁን በሙስና ተከሰው በተያዙት ላይ የሚበየነው ፍርድስ አስተማሪ ነውን ሊባል ይችላልን?  ከዚህ አንፃር ዶ/ር ዓብይ፣ ‹‹ኢትዮጵያችን አንዱ ሠርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆን እንጠብቅ፤›› ያሉትን መሪ ሐሳብ ፈጥኖ መተግበር ግድ ይለናል፡፡

ይህን እውነታ ለመረዳት በቀላሉ በመሬት ካርታ ማውጣት፣ በግብር መሰብሰብና ቅሬታ ምላሽ፣ በግንባታ ፈቃድ፣ ዕድሳትና የኮንትራት ግዥ፣ በማዕድን ማውጣት ሥራና መሰል መስኮች ላይ ያለውን እንግልትና አሻጥር መፈተሽ በቂ ነው፡፡ እንደ አሽዋና የጠጠር ድንጋይን ማውጣና ማምረት፣ የብሎኬት ምርት ማዘጋጀትና ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃን ማቅረብ ሳይቀር በርካታ ወጣቶች ተሰማርተው ሀብት ሊያፈሩበት ሲቻል፣ ጥቂት ጥገኞች ከባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር እየቦጠቦጡ (የቀረጥ ነፃ ሕገወጥ ተጠቃሚም እየሆኑ በመንደላቀቅ) በአቋራጭ መበልፀጋቸው ብቻ ሳይሆን፣ መልሰው የሥርዓቱ ጠላት በመሆን ላይ ናቸው፡፡ ሀቀኛውን ትጥቅ እያስፈታው ያለው እውነታም ይህ ዓይነቱ ድርጊት ነው፡፡ እንግዲህ ቢያንስ  ኦሮሚያ ላይ የተጀመረውን ለውጥ አዲሱ አመራር እውነተኛ የሕዝብ ተቆርቆሪነት ካላው፣ በየክልሉ  ትግል ማቀጣጣል ያለበት በዚህ ላይ ነው፡፡

ሌላው አሳዛኝ ነገር ደግሞ ዜጋው እየተቸገረም ቢሆን በሚያወጣውና በተሰበሰበ ገንዘብና የመንግሥት በጀት ላይ የሚፈጸመው ውንብድና ነው፡፡ ብዙዎቹ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ከምክር ቤቶች ግምገማና የክዋኔ ኦዲት በኋላ መሻሻል ቢያሳዩም ቀላል ቁጥር የሌላቸው በስፔሲፊኬሽንና በሚፈለገው ጥራትና መጠን መሠረት ግዥ አይፈጽሙም፡፡ እውነተኛና ተዓማኒ የሆነ ግልጽ የጨረታ አሠራርና ቁጥጥር የላቸውም፡፡ በገንዘብ አወጣጥና አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ችግር ይታይባቸዋል የሚለው ሕዝባዊ ቅሬታ አዳማጭ ሊያገኝ  ግድ ይለዋል፡፡

እስካሁን እንደታየው ኃላፊውና ፖለቲከኛው ሁሉ በሙስና ጉዳይ በግምገማና ስብሰባ መቀመጫውን ሲፈትግ ይውላል፡፡ ነገር ግን  በየመስመሩ ከፍተኛና መካከለኛ ኃላፊ እየተመሳጠረ ዘረፋውን ያጧጡፋል፡፡  መልሶ ደግሞ ሙስና በዝቷል እያለ ከላይ ባለው ላይ ጣቱን ይቀስራል፡፡ ይህን ያህል ሀብት አለው እያለ ያስወራል፡፡  እንግዲህ  መንግሥት መፍትሔው ሕዝቡን ማታገል፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባትና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሆነ ተገንዝቦ ካልዘመተበት በምንም ተዓምር በለብ ለብ ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል በጥሞና መጤን አለበት፡፡   

በእርግጥ  እስካሁንም ቢሆን በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ በሙስና ጉዳይ ላይ ዝም ያለ የለም፡፡ መሪዎቻችን ይናገራሉ፡፡ ጋዜጦቻችን ይጽፋሉ፡፡ ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ ያወግዛሉ፡፡ የሃይማኖት አባቶች ይመክራሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ እየሆነ ለውጥ በተፈለገው መጠን ማምጣት ግን ለምን አልተቻለም ብሎ መፈተሸ ወቅቱ የሚጠይቀው ወሳኝ ተግባር ሆኖ ይገኛል፡፡ በዋናነት ሕዝቡን ወዳልተፈለገ የእርስ በርስ ግጭትና አለመተማመን እየከተተው ያለው ተግዳሮት ይኼው መሆኑም ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባዋል፡፡

በመጪው ጊዜም ቢሆን ሕዝቡም ሆነ መንግሥት ሙስናን ማጥፋት ባይቻል እንኳ መቀነስ በሚቻልበት ዘዴ ላይ ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ ልጆቻችንን በሥነ ምግባርና ሞራል ከማስተማር ጀምሮ፣ ሙሰኛን እጁን በመቁረጥና የዘረፈውን የሕዝብ ሀብት ወደ መንግሥት በማስመለስ፣ በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ ባለሀብት ወይም ባለሥልጣን ቢሆንም በሕግ የበላይነት መርህ በማጋለጥ፣ ዴሞክራሲያዊነትን በማስፋት (የሐሳብ ነፃነት፣ የመደራጀት፣ የሕግ የበላይነት…) የሙስናን ሥሩን መንቀል ባይቻል እንኳን በእርግጠኝነት ማዳከም ይቻላል፡፡

በእርግጥ ‹‹የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ›› የሚባለው ብሂል እየተረትን የእኛ ሙስና የከፋ አይደለም ስንል መኖራችንም ክፉኛ አዘናግቶናል፡፡ በተለይ በከተሞች ያለው የመሬት ወረራ፣ የግብር ማጭበርበር፣ የኮንትሮባንድና የቀረጥ ነፃ ማጭበርበር፣ የሞኖፖልና የንግድ ብልሽት፣ ሰው ሠራሽ የገበያ እጥረትና ቅሸባ… በዚሁ ከቀጠሉ በአጭር ጊዜ ከሌሎች የአፍሪካ ሙሰኛ አገሮች ተርታ መሠለፋችን የማይቀር ነው፡፡ ጨለምተኛ ካልተባልኩ ሁከት፣ ብጥብጥና መፈራራስም ሊቀርልን አይችልም፡፡

በክልሎችም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ጠቅላይ ዓቃብያነ ሕግና የፀረ ሙስና ኮሚሽኖችም በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚካሄዱ ሙስናዎችን ለመከላከልና ለመቀነስ ከመቼውም ጊዜ በላይ መትጋት አለባቸው፡፡ በእርግጥ የትኛውም ምሁርና የምርምር ሰነድ ሙስናን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያስወግድ ተዓምራዊ ቀመር (Magic Formula) የለውም፡፡ ከመፍትሔ ሐሳቦች ውስጥ ግን ዋነኛው የድርጅትና የመንግሥት አመራሩን ሥነ ምግባር፣ ሕዝባዊነትና ዴሞክራሲያዊ ትግል ባህል ማነፅና  ማስተካከል ነው፡፡ የመንግሥት ውሳኔና ዕርምጃ የመውሰድ አቅምም ወሳኝ ነው፡፡

‘ዓሳ የሚገማው ከጭንቅላቱ ነው’ እንደሚባለው በየደረጃው ያሉ የክልል አመራሮች፣ በየደረጃው ያሉ ባለሥልጣናትና ሹመኞች ሙስናን ለመዋጋት ተነሳሽነትና ቀና መንፈስ (Initiated and Inspired transformational Leaders) ያላቸው መሆናቸውን ደግሞ ደጋግሞ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ዘመድና ብሔርን ነጥሎ ለመጥቀም ከመሻት ይልቅ፣ ለመላው ሕዝብና ለአገር የቆሙ መሆናቸውም በጥብቅ ሊመዘን ይገባዋል፡፡ በተለይ አሁን ባለው ሁኔታ ሌባው አመራር ሲነካ በብሔርና በክልል ባርኔጣ እየነገደ፣  ከመነካካት ይልቅ በመሸፋፈንና በአድርባይነት መንጎድ መጀመሩ መጨረሻው አገርን ወደ አረንቋ እንደ መገፍተር የሚቆጠር ነው፡፡ የተደከመበትን መልካም ጅምር ሁሉ በዜሮ አባዝቶ በውርደት መውደቅንም ያስከትላል፡፡ ስለሆነም በሁሉም በኩል ቢሆን የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጠንካራ ጥሪ እንደ የተሃድሶ አቅጣጫ ወስዶ መታገል ያስፈልጋል እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...