Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየአገር ወዳድነት ብልኃት አጣዳፊነት

የአገር ወዳድነት ብልኃት አጣዳፊነት

ቀን:

በአብዱል መሐመድ

አንድን ሕዝብ ወደ አዲስ የፖለቲካ ሕይወትና ዘመን ለመምራት ለየት ያለ የለውጥ አስተሳሰብ ያለው ፓርቲና እውነተኛ መሪ ያስፈልጋል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በመጀመርያ ሕዝባዊ ንግግራቸው ይኼን አስቸጋሪነቱ የታወቀ ጀብድ ለመፈጸም ትክክለኛውን መልካም ነገር አስቀምጠዋል። ቁርጠኝነትና ትህትና በተሞላው ንግግራቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ቅርብ ጊዜያት ለተሠሩት ስህተቶችና ቀውሶች ይቅርታ በመጠየቅ፣ በኢትዮጵያዊነታቸው እንደሚኮሩ ተናግረዋል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሕግ የበላይነትና ሕገ መንግሥቱን በማስከበር ጠንካራ ዴሞክራሲና ለውጥ ያለጥርጥር እንደሚመጣ አረጋግጠዋል።

ዓብይ አህመድ ስለእናታቸውና ስለባለቤታቸው በማውሳት ሕይወታቸውን የኮተኮተውን ሥነ ምግባር በጨረፍታ አካፍለውናል ማለት ይቻላል።

በተጨማሪም ብዙ ጊዜ በፖለቲካ ውስጥ ይረሳ የነበረን አንድ መሠረታዊ እውነት ወደ መድረክ አምጥተዋል። የኢትዮጵያ እናቶች የባሎቻቸውንና የልጆቻቸውን ፍላጎት ያለምንም ቅሬታ ከትውልድ ትውልድ መሸከም ችለዋል።

በአብዮትም ሆነ በጦርነት ዓመታት ለራሳቸው ምንም ነገር ሳያተርፉ ሁለ ነገራቸውን ለመሰዋት ዝግጁ ነበሩ። እናቶቻችን ራሳቸው በጭራሽ ጠይቀውት የማያውቁትን፣ ነገር ግን የሚገባቸውን ዕውቅና በመጨረሻ ማግኘት አለባቸው።

እኔም ራሴ በኩራትና በትህትና እናቴን ከነዚህ ብፁዓን ነፍሶች በመደመር ይኼን እውነት መመስከር እችላለሁ። የእነሱ ሽልማት ግልጽ ነው። የእነሱ ሽልማት ቤተሰቦቻቸው ገላቸውን ሰደው መኖራቸው፣ ያለ ረብሻና ያለ ብጥብጥ ዕድገት መገኘት መቻሉና ልጆችና የልጅ ልጆች ያለሥጋት የፖለቲካ መሪዎች ሕይወታቸውን እንዲሰው ሳያስገድዷቸው ማደግ መቻላቸው ነው።

አገራችን በገባችበት ማንኛውም ለውጥ ውስጥ ወጣት ኢትዮጵያውያን ግንባር ቀደምት ናቸው። መሣሪያ፣ ድንጋይ፣ ወይም መፈክር በማንሳት ሁሉም ፊታውራሪዎቻችን ናቸው።

የዛሬ የፖለቲካ ሥርዓት የተፀነሰው በወጣቶቻችን ነው። አሁን ችቦው ወደ አዲሱ ትውልድ ተሸጋግሯል። በአርበኞች ብልኃትና ጥበብ እየተመሩ ወደፊት ያራምዱናል። ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መልካሙን ሁሉ ሊመኝላቸው ይገባል። እሳቸው ከተሳካላቸው እኛም ተመሳሳይ ዕድል እንጎናፀፋለን።

ዛሬ በአገራችን ያለውን ሁኔታ አንድ ብልህ አገር ወዳድ እንዴት ሊገነዘበው ይችላል? እውነታው ባለፉት ሁለት ትውልዶች የሚያሰቃዩ ግን እጅግ ጠቃሚ ትምህርቶችን አግኝተንባቸዋል ብዬ አምናለሁ። ለስኬቶቻችን ዕውቅና የምንሰጠውን ያህል ድክመቶቻችንንም እኩል መገንዘብ ይገባናል። ድሎቻችንም ውድቀቶቻችንም በግልጽ የትም ቦታ የሚታዩ ናቸውና ሊሳቱ የሚችሉ አይደሉም።

ዋናው ትልቁ ትምህርት የሕዝብ ጉዳይ የዜሮ ድምር ጨዋታ አለመሆኑ ነው። የአንዳንዶቻችን ማግኘት የግድ የሌሎቻችን ማጣት አይደለም። በተቃራኒው ሁላችንም ኢትዮጵያውያን አንድ ላይ እንነሳለን ወይም አንድ ላይ እንወድቃለን። ምናልባት የተሻለ ነገር ሊመጣ ይችላል በሚል ምኞት ያለንን የሚያበላሽና የሚያጠፋ የፖለቲካ አጀንዳ በፍፁም አምነን መቀበል የለብንም።

ወደፊት መራመድ የሚቻለው ተከባብሮ በመነጋገር መግባባትን በምፍጠርና በመታደስ ነው። ህዳሴው ግን ምናልባት ፈጣን፣ በጣም ሩቅና ሰፊ ሊሆን ይችላል።  ግን በፍፁም የሆነ ቀኖናን በግድና በጭካኔ የሚተገብር መሆን የለበትም። በምትኩ ለልዩነትና ለብዙኃንነት በማሰብ ሰፊ ሜዳ የሚሰጥ መሆን አለበት። የቅርብ ጊዜ ሥልጣኔዎች ያረጋገጡት ነገር ቢኖር የሕዝቦችን ድምፅ እንዳልሰማ ሰምቶ ማለፍ እንደማይቻልና ያን ማድረግ ለፓርቲዎቹ ለራሳቸው አደጋ መሆኑን ነው።

ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ መሠረታዊ እውነት እንደሚያረጋግጠው ሕዝብ ሊመራ የሚችለው ፈቃደኛ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው። ይህም ከመጀመርያ ጀምሮ ስኬቶችን በሕዝብ ድጋፍ ላገኘው ኢሕአዴግ በፍፁም ባዳ ሊሆን አይገባም። መሽቶ በነጋ ቁጥር የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዙኃንነትን ወደሚያስተናግድ አዲስ ዘመን እየገባ ይገኛል። እርግጥ አንዳንድ የማኅበረሰብ ሚዲያዎች ዛሬም በፅንፈኛ ድምፆች የተዋጡ፣ መደበኛ ሚዲያዎችም በብቃት እየተንቀሳቀሱ አለመሆኑ እውነት ነው።

የሕዝባዊ ፖለቲካ ክርክሮች በኢሕአዴግ ውስጥ ብቻ መወሰናቸው በቂ ነው ሊባል የሚችል አይደለም። የፖለቲካ ፓርቲዎችን (መሪውም ሆነ ተፎካካሪዎች) እንደ ተቋም በሽግግር ወይም በመሻሻል ሒደት ያልተቃኙ ናቸው።

ይሁንና ማኅበረሰባዊ ሀብታችን ጠንካራ መሆኑ እያካካሰው ይገኛል። የትኛውም አገር ቢኖረው የሚኮራባቸው ሕዝቦች እንዳሉን ለመረዳት መወዛገብ የለብንም። ዕድለኛነታችን ከዚህ ይጀምራል፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ደግሞ እጅግ የተሻለና የሚመቻቸው መንግሥት ያስፈልጋቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በንግግራቸው ላይ የኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ ትስስር ጥንካሬ ምን ላይ እንደ ተመሠረተ በጠንካራ ስሜት አሳይተዋል። ይህ ጠቃሚ ነገር ነው። ይኼ ሽግግር ሊበላሽ አይችልም።

ኢትዮጵያ የዓረብ አገሮች [የፀደይ አብዮት] በሄዱበት መንገድ ተጉዛ ቢሆን ኖሮ ታላቅ ታሪካዊ ውድቀት ይከሰት ነበር። ግብፅ ወደ አምባገነናዊ ሥርዓት ተመልሳለች። የመን፣ ሶሪያና ሊቢያ ቀውስ ውስጥ ናቸው።

ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ተስፋ የሚሰጥ ነው። ሠራዊቱና ደኅንነቱ ከፖለቲካ ጨዋታው ገለል ብለው ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን ድርሻ ብቻ መወጣት ይገባቸዋል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለውጥ ለማምጣት ፖለቲካዊ ማሻሻያ ያስፈልጋል የሚል ሐሳብ ወደ ፖለቲካው መድረክ አምጥተዋል። ይኼ የፖለቲካ ማሻሻያ አጀንዳ መግባባትን በሚገነባ መንገድ መመራት አለበት።

አገራችን የምትገኘው ችግር በበረከተበት የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየጊዜው ተጨማሪ አገሮች በዚህ ቀንድ ጉዳዮች ውስጥ እጃቸውን እያስገቡ ይገኛሉ። እንደሚታወቀው ምንም እንኳን የውስጥ ችግሮች ቢኖሩብንም፣ ኢትዮጵያ ለአካባቢው ቀውስ ማረጋጊያ ማማ ሆና ቆይታለች። ዛሬም ለጎረቤት አገሮች ግጭቶች  የሰላም አስከባሪ ወታደሮችና አደራዳሪ ዲፕሎማቶች እናዋጣለን።

በተጨማሪም በአፍሪካ ኅብረትም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ገንቢ ሚና እየተጫወትን እንገኛለን። ለሃያ ዓመታት ያህል አንዳንዶች እንደምንበታተን ሲተነብዩልን ቆይተዋል። ይኼ ግን እስካሁን ድረስ አልሆነም፣ ወደፊትም መሆን አይገባውም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ  ለኤርትራም የሰላም እጃቸውን ዘርግተዋል። አስመራ የሚገኙ ወዳጆቻችን ይኼን ጥያቄ እንዲቀበሉት በጥሞና ይመከራሉ። ይኼም ኢትዮጵያ ስትፈራርስ የሚጠበቁ ፖሊሲው እስከ ዛሬ እንደታየው የተሳሳተ በመሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን ማናችንም ብንሆን በጋራ ትልልቅ ችግሮቻችንን ልናስወግድ ስንችል፣ በግጭትና ባለመተማመን መቆየታችን የማንችለውና የማይበጀን በመሆኑ ነው። ይሁንና አሁንም ተመልሶ ያው መሆኑ ያሳዝናል። አንዳንድ ቀዳሚ ምልክቶች እንደሚጠቁሙት በዚህ ረገድ ምንም ተስፋ የሚሰጥ ነገር የለም። በአገራችን የፖለቲካ ማሻሻያ ለማድረግ ያለው ታላቁ ፈተና ይኼን ለማካሄድ ያለን ልምድ ውስን መሆኑ ነው።

ከፖለቲካ ተቀናቃኙ ጋር ተግባብቶና ተስማምቶ የሚሠራ፣ በሐሳብ ከማይጣጣሙ ጋር ለጋራ ውጤት አብሮ ለመጓዝ የመደራደር ልምዱ ያለው እጅግ በጣም ጥቂቱ የፖለቲካ ክፍል ነው።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን እጅግ አስቸጋሪ ፈተናዎች ይጠብቋቸዋል። የሕዝቡ ለለውጥ ያለው ከፍተኛ ጉጉት፣ ከእነዚህ ጉጉቶች አንዳንዶቹ ጊዜ የሚፈልጉና አሁን ሊተገበሩ የማይችሉ መሆናቸው፣ በዚህ ምክንያት ያለመርካት ስሜትና ቅሬታ ሊፈጥር ይችላል። ችግር ቢያጋጥም ወይም ትንሽ መደነቃቀፍ ቢፈጠር ችግሮቹን አጋነው በማጮህ ተስፋ ሊያስቆርጡና በፍርኃት ሊያስደነብሩ የተዘጋጁ ብዙ ኃይሎች አሉ፡፡

አሁን ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ትልቅ ሀብት አላቸው። ፓርቲያቸው ህዳሴ ለማድረግ ራሱን አዘጋጅቷል። የመንግሥት ተቋማት ሥራቸውን እየሠሩ ነው። ኅብረተሰባችንም ፅናቱን አረጋግጧል። የሃምሳ ዓመት ግብዓታዊ ጉዞ የኢትዮጵያን ማኅበራዊ ትስስር ሀብት አላዳከመም፣ እንዲያውም ይበልጥ አጠናክሯል እንጂ።

ኢትዮጵያውያን ሴቶችና ወንዶች ላገኙት ፀጋ ማለትም ተረጋግተው በሰላም አብረው በፅናት ለመኖራቸው፣ እርስ በራሳቸውና ለሕግ ባላቸው ከበሬታና ወደ አደጋ የሚወስዷቸውን የተሳሳቱ መንገዶች በጥልቀት በማወቃቸው ትልቅ አድናቆት አላቸው።ኅብረተሰባችን ከፖለቲከኞቻችን የተሻለ ትልቅና ጠንካራ፣ እንዲሁም ከእነሱ በላይ ብልህ ነው። ብልህ አገር ወዳድም ይኼንን ያከብራል።

ይኼ ወቅት ለኢትዮጵያውያን አገራቸው ወደ ተሻለ ጎዳና ስትቀየር ለማየት እጅግ አስፈላጊ ቅጽበት ነው። ለሚዛናዊና የተረጋጋ አገር ወዳድ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር ምን አስተዋፅኦ ልናበረክት እንችላለን? በሚል በጥሞና የምንወያይበትም ሁነኛ ቅጽበት ነው።

ፍላጎታችንን በማጋነንና አገሪቱን በማጨናነቅ ዓላማችን ሳይሳካ እንዳይቀር መጠንቀቅ አለብን። ይኼን  የሽግግር ጊዜ ማበላሸት የለብንም። መከባባር፣ መግባባት፣ ትዕግሥትና ሰጥቶ መቀበል የሰፈነበት የፖለቲካ ባህል ልናበለፅግ ይገባናል።

ለዚህም ምን ዓይነት ኢትዮጵያ ነው የምንፈልገው? እንዴት ያለ ችግር እዚህ መድረስ ይቻላል? በማለት ጤናማ ብሔራዊ የፖለቲካ ውይይት በማድረግ መጀመር ይቻላል። ነገር ግን አንድ መወሰን ያለበት ነገር ይኼንን ያህል የተጋነነና የተንዛዛ ክርክር አስፈላጊ አይደለም።

ኢሕአዴግ በአገራችን ካሉ የማስተዳደር አቅም ካላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አንዱ ሆኖ፣ የፈቃደ ዓመቱ ሥልጣን የኢትዮጵያ መራጮች ለሚሆኑበት የፖለቲካ ምዕራፍ ኢትዮጵያ ሳትውል ሳታድር በፍጥነት ማስረከብ አለበት። ያን ጊዜ ነው ይህቺ ጥንታዊት አገር ይህቺ ለጥቁር ዘር የተስፋ ምሳሌ የሆነች አገር ዘለቄታ ያለው ሰላም፣ ዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ብልፅግና የምታገኘው እላለሁ።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...