Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የተራቆተ የውጭ ምንዛሪ ካዝና ስለሚያገኙ የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ማውጣት ይኖርባቸዋል››

አቶ ፀጋዬ አበበ፣ የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎችና ማኅበር መሥራችና የመጀመርያው ፕሬዚዳንት

አቶ ፀጋዬ አበበ በኢትዮጵያ ውስጥ በአትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪነት ሥራ ላይ ከተሰማሩ የመጀመርያዎቹ ባለሀብቶች አንዱ በመሆን ይታወቃሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራች ኩባንያዎችን በአባልነት የያዘው የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር መሥራችና የመጀመርያ ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡ በአበባ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እርሻዎቻቸው ላይ ከ1,700 በላይ ሠራተኞችን አሠማርተዋል፡፡ በወጪ ንግድ ዘርፍ ብዙ ተሞክሮ ያላቸው አቶ ፀጋዬ፣ የንግድ ማኅበረሰቡን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ በመሆን ይታወቃሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የህዳሴ ነጋዴዎች ፎረም ሰብሳቢም ናቸው፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ኮሚቴ የቦርድ አባል በመሆንም አገልግለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦርድ አባል በመሆን ሠርተዋል፡፡ በቅርቡ ከተደረገው የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ ጋር ተያይዞ በኢኮኖሚው ረገድ ምን ዓይነት ለውጥ ሊኖር እንደሚገባ፣ በተለይ ከኤክስፖርትና ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዙ ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ዳዊት ታዬ አቶ ፀጋዬ አበበን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ አንድ የንግድ ማኅበረሰብ አባል አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ያደረጉት የመጀመርያ ንግግራቸው ምን አመላከተዎት? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነቱን ከተረከቡ በኋላ እያደረጉዋቸው ያሉ እንቅስቃሴዎችን እንዴት ያመለከታሉ?

አቶ ፀጋዬ፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግር  አገራዊ ስሜትን በጣም የሚቀሰቅስና ሁሉንም ዘርፎች የነካ ነው፡፡ ጥንታዊ ታሪካችንን የዳሰሰ፣ ቀድሞ የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ አሁን ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት የጠቀሰም ነው፡፡ ኢኮኖሚያችን ያለበትን ተግዳሮቶች ያሳዩበት ንግግር ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግሩንም ጭምር በሚገባ ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ በፓርላማ ያቀረቡት የመጀመርያው ንግግራቸው ያልዳሰሰው ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ ተቃዋሚ የሚለውን ለፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰጥቶ የነበረውን ስያሜ ተፎካካሪ በማለት ቃሉን ራሱ በመቀየር፣ ብዙዎችን በማስገረም ቀይረው ተጠቅመዋል፡፡ በአጠቃላይ ከአንድ መሪ የምንጠብቀው ንግግር ነው፡፡ የብዙዎችን ስሜት የነካ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ለብዙዎች ተስፋ የሰጠ ነው፡፡

በፓርላማ ካደረጉት ንግግር በኋላም የመጀመርያ የአገር ውስጥ ጉዟቸውን ጅግጅጋ በመሄድ፣ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መሀል የተፈጠረውን ችግር ለማቃለል ቅድሚያ መስጠታቸው በእርግጥም ትክክል ነው፡፡ ከሁለቱም ወገን ወደ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ አካባቢ ያለውን ችግር ቀድመው ለመፍታት መንቀሳቀሳቸው ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ ችግሩ ኢኮኖሚያዊ ጠባሳ ነበረውና አሁን በተደረገው ጥረት ወደ ሰላም መመለስ ተገቢ ነው፡፡ በወንድማማቾች መካከል የተፈጠረ ችግር መሆኑን በማስረዳት ወደፊት መመልከቱ በአካባቢው ሰላም ከማምጣት ባሻገር፣ በዚህ አካባቢ የተዳከመውን ኢኮኖሚ ያነቃቃል፡፡ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተከታታይ የሚያደርጓቸው ጉብኝቶችና በጉብኝቶቻቸው የሚያደርጓቸው ንግግሮች ነገን በተስፋ እንድናስብ አድርገውናል፡፡ እየተደረገ ያለው ጥረትም አገር በማረጋጋት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ ቀጣዩንም ጊዜ በጥሩ ተስፋ እንድንመለከት ዕድል የሚሰጥ መነቃቃትን  የሚፈጥር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በፓርላማ ካቀረቡት ንግግር ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተካተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ኤክስፖርት የተጠበቀውን ያህል ውጤት ማምጣት አለመቻላቸው ይጠቀሳል? ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ሐሳቦችን እንዴት ያዩዋቸዋል?

አቶ ፀጋዬ፡- ወደ ኢኮኖሚው ስትመጣ እሳቸው መጀመርያም የመንግሥት ሲስተም ውስጥ ስላሉ ብዙ ነገሮች ያውቃሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በተለያዩ ዘርፎች አድጓል፡፡ የግል ዘርፉ አድጓል፡፡ በመንግሥት በኩልም መሠረተ ልማቱ አድጓል፡፡ እዚህ ላይ የዚህን አገር ኢኮኖሚ እየተፈታተነ ያለውና መንግሥትም ያመነው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው፡፡ ይህ አሁንም ማነቆ ናቸው፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲፈቱ ባብዛኛው ሰው ከታሰረበት ቦታ እግሩ እንደተፈታ መንቀሳቀስ ይጀምራል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ዘርፍ ላይ ያሉ ችግሮች ምንድናቸው? ተብሎ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ በተለይ የአንድ አገር የጀርባ አጥንት ኤክስፖርት ነው፡፡ ትልቁ ለዚህ አገር ዕድገት ወይም መውደቅ ሚና የሚኖረው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ነው፡፡ ውጭ ምንዛሪ መኖር አለበት፡፡ ውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በዕርዳታና በብድር ሁልጊዜ መቆየት አንችልም፡፡ ዕርዳታውም ሆነ ሌላው ነገር አንድ ቀን ይቆማል፡፡ ራሳችንን የምንችልበት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ሊኖረን ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በተለይ በአሁኑ ወቅት ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ እንዴት ይቻላል? የወጪ ንግዱ ክፍተትስ ምንድነው?

አቶ ፀጋዬ፡- ችግሩን ካወቅነው እኮ መፍትሔውን 50 በመቶውን አውቀነዋል ማለት ነው፡፡ ከእኛ ዘንድ ችግሩም ሆነ ለችግሩ የሚሆን መፍትሔ ይቀርባል፡፡ ግን ወደ ተግባር ስንሄድ ተግባሩ የለም፡፡ የኤክስፖርት ማነቆዎች ምንድናቸው? በየዘርፉ ብትሄድ ችግሮቹ ይታወቃሉ፡፡ ለምሳሌ እኔ ባለሁበት የሆርቲካልቸር ዘርፍ ያሉት ችግሮች ይታወቃሉ፡፡ መፍትሔ የሚሰጠው ነው የጠፋው፡፡ የቅባት እህሎች፣ ቡናና ሰሊጥ ላይ ብትሄድ  ብዙ ችግር አሉ፡፡ ለእነዚህም ይሆናል የተባለ መፍትሔ ቀርቦ ነበር፡፡ ግን አልተተገበረም፡፡ ወደ ውጭ የምትሸጠው ብዙ ነገር ቢኖርም ኤክስፖርቱ እያደገ አይደለም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝታችን እየወደቀ ነው፡፡ አሁንም ከሦስት ቢሊዮን ዶላር የዘለለ የወጪ ንግድ የለንም፡፡

ሪፖርተር– ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ፀጋዬ፡- ምክንያቱም ለዘርፉ አለማደግ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ተለይተው፣ ለዚህ ይሆናሉ የተባሉ መፍትሔዎች አብረው የቀረቡ ቢሆንም ከማድመጥ ሌላ መፍትሔ ሊሰጣቸው አለመቻሉ ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም በዚህ የለውጥ ሒደት ውስጥ ለኤክስፖርት ማነቆ የሆኑ ነገሮች መፍትሔ ሊቀመጥላቸው ይገባል፡፡ ቁርጥ ያለ ነገር ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ከተቆጣጣሪነት ወጥቶ ወደ ልማት ደጋፊነት መሄድ አለበት፡፡ ቀላሉ ነገር ቁጥጥር ስለሆነ ዘርፉ የሚያድግበትን መንገድ ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡

ሪፖርተር– በአገሪቱ ተከስቶ ከነበረው ችግር ጋር ተያይዞ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ተሰይመዋል፡፡ ብዙዎች ለውጥ ይኖራል ብለው እየጠበቁ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለውጡ ለኢኮኖሚው ምን ያመጣል? አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ምን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል?

አቶ ፀጋዬ፡- አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የተትረፈረፈ የውጭ ምንዛሪ ካዝና አያገኙም፡፡ የተራቆተ የውጭ ምንዛሪ ካዝና ስለሚያገኙ የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ማውጣት ይኖርባቸዋል፡፡ የዚህ አገር አንደኛው ችግር ትልቁ ችግር የተማረውንም ሆነ ያልተማረውን ወጣት ሥራ ማስያዝ ነው፡፡ ሥራ ለመያዝ የሚያስችሉ ተግባራትን መፈጸም ደግሞ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የእያንዳንዱ የግል ዘርፍ ሚና የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ እያንዳንዱ ባለሀብት ሥራ ፈጣሪ መሆን አለበት፡፡ የተጀመሩ ነገሮች መቀጠል አለባቸው፡፡ አሁን ግን እየታየ ያለው ብዙ ፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃ ዕጦት ሥራቸው እየቆመ ነው፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች ነገ ጠዋት ወደ ሠራተኛ ቅነሳ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ሥራ ከመፍጠር ይልቅ ያሉትንም ወደ መቀነስ ስንሄድ ደግሞ የመንግሥት ችግሮች እየተባበሱ ነው የሚሄዱት፡፡ ስለዚህ የዛሬና የነገን መፍትሔ እንፈልግ ካልን መጀመርያ አሁን ላለው ችግር መፍትሔ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ እኔ እንደሚታየኝ ያሉትን ችግሮች ፈትቶ ወደ ተደላደለ የኢኮኖሚ ዕድገት ለመሄድ ጊዜ ይወስዳል፡፡ በአንድ ምሽት የሚሆን ነገር የለም፡፡

ስለዚህ አሁን ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከየትም ቦታ ከየትም አገር ብድር ተገኝቶ እዚህ ኢኮኖሚ ውስጥ የተወሰነ ቢሊዮን ዶላር ገብቶ እየተጠቀምን፣ ኤክስፖርታችንን የምናሳድግበት መንገድ መምጣት አለበት፡፡ ዛሬ ኤክስፖርቱን በ24 ሰዓት ማሳደግ አይቻልም፡፡ ዛሬ የጀመርነው ነገር ከአንድ ሁለት ዓመት በኋላ የተደላደለ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ሊያስገባን ይችላል፡፡ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ሊኖረን ይችላል፡፡ አሁን ግን መፍትሔው ሰባት ለስምንት ወራት የቆሙና የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሠልፍ የያዙ ፋብሪካዎች ያለምንም ውጣ ውረድ የሚፈልጉን አግኝተው፣ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ምንዛሪና የጥሬ ዕቃ እጥረታቸው ተቀርፎ በተንቀሳቀሱ ቁጥር አዲስ ሥራ መፍጠር ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የተንጠለጠሉትን ችግሮች ለማርገብ ከየትም ተብሎ  የውጭ ምንዛሪ ኢኮኖሚ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ እዚህ ላይ ከአበዳሪዎቻችን ምን ያህል ተበደርን? ምን ያህል እምነት አለን? ምን ያህል ከፍለናል? ጥሩ ከፋይ ነን ወይ? ራሱ አንድ ጥያቄ ነው፡፡ ግን መፍትሔው ይኼ ነው፡፡ 

ሪፖርተር– አሁን የነገሩኝ አገሪቱ ላለባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጊዜያዊ መፍትሔዎች ናቸው ያሉትን ነው፡፡ ዘላቂ መፍትሔውስ?

አቶ ፀጋዬ፡- ዘላቂው መፍትሔው ከግል ዘርፉ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህንን እንቅስቃሴ ለማጎልበት ደግሞ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከግሉ ዘርፍ በተለይ ከኤክስፖርተሩ ጋር ውይይት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ችግራችሁ ምንድነው? ማለት ይገባቸዋል፡፡ እስከ ዛሬ ችግራችንን በተደጋጋሚ ተናግረን መፍትሔ አልተገኘም፡፡ ስለዚህ ማነቆውን ነገ ሳይሆን ዛሬ መበጣጠስ ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዳችን ሌት ከቀን የምንሮጥበት አሠራር መዘርጋት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡ በአገር ውስጥ ንግድም በተመሳሳይ የሚታይ ነው፡፡ ራስን በምግብ ከመቻል አንፃርም መተግበር የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ ማስገባት ማቆም አለባት፡፡ ለስንዴና ለዘይት የውጭ ምንዛሪ ተመድቦ ከውጭ እያስገባን እስከ መቼ እንሄዳለን? ከዚህ አንፃር የረዥም ጊዜ ዕቅዳችንን ዛሬ ማስቀመጥ አለብን፡፡ ኢትዮጵያ ስንዴ ኤክስፖርት ማድረግ ያለባት አገር ነች፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ ካልተከሰተና ትልቅ ጥፋት ካልመጣብን በቀር፣ ይህች አገር አፍሪካን የሚመግብ አቅም አላት፡፡

ሁሉንም ነገር ወደ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መግፋታችን ሳይሆን፣ በእሳቸው ተቆጣጣሪነት ሥር ሆኖ የሚመለከታቸውን አካላት ጉሮሮ ይዞ የስንዴ ችግር በአገር ውስጥ ሊፈታ ይገባል፡፡ የሁለት ዓመት ጊዜ እሰጥሃለሁ መፍትሔን አምጣ መባል አለበት፡፡ የዘይት ችግር በአምስት ዓመት መቀረፍ አለበት ተብሎ በዕቅድና በቁርጠኝነት መሠራት ይኖርበታል፡፡ ከሰሊጥም ሆነ ከተልባ የሚመረት ዘይት እዚህ እንዲመረትና በውጭ ምንዛሪ የሚገባ ዘይት መቅረት አለበት ተብሎ መሠራት ይኖርበታል፡፡ የፓልም ዘይት እኮ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊመረት ይችላል፡፡ ስለዚህ ዕድሜ ልካችንን ለዘይትና ለስንዴ 500 ወይም 700 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማውጣት ለምን? ስኳርም እንዲሁ ነው፡፡ የስኳር ፋብሪካዎች በየቦታው ቆመዋል፡፡ እነዚህን ፋብሪካዎች አንቀሳቅሶ ለስኳር የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ መንግሥት ማስቀረት አለበት፡፡ መጀመርያ ያለህን ገንዘብ ቆጥበህ በአገር ውስጥ ምርቶች የምትተካበትን መንገድ መቀየስ የግድ ነው፡፡ ስለዚህ ለዘለቄታው እንዲህ ያሉና ሌሎች መፍትሔዎች ተፈልገው ሊተገበሩ ይገባል፡፡ ሌላው ኤክስፖርታችን ውጤታማ ሆኖ እንዲጓዝ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ የእኛ የኤክስፖርት ምርቶች ከማንኛውም አገር የሚበልጥ ዕድል ያላቸው በመሆኑ የተመቻቸ ነገር አለ፡፡ ውጤቱም ጥሩ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር– እንዴት?

አቶ ፀጋዬ፡- እዚህ ኬንያ የአበባና የአትክልት የወጪ ንግድ ገቢ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ እዚህ አገር ውስጥ ደግሞ 700 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ አንድ ቢሊዮን ዶላር እናደርሳለን ብለን እናወራለን፡፡ ግን የለም፡፡ ለምንድነው? ሁላችንም መሬት ይዘናል፡፡ ሁላችንም በያዝናት መሬት ላይ እንሠራለን፣ እንፍጨረጨራለን፡፡ ለእኔ በሆርቲካልቸር ያለው ችግር የመሬት ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን አንቆ የያዘ ነገር አለ፡፡

ሪፖርተር– ይህ እንደ ማነቆ የሚቆጠረው ችግር ምንድነው?

አቶ ፀጋዬ፡- አንደኛ ባለሀብቱ በምርታማነት ላይ ከፍ ብሎ ሄዷል ወይ? ሁለተኛ ዓለም አቀፍ ገበያዎችን ሁሉንም ዳሰናል ወይ? አንድ ሆላንድ ላይ ነው ሁሉም የአበባ ገበያ ያለው፡፡  አሁን ነው በተወሰነ ደረጃ ወደ ተለያዩ አገሮች መውጣት የጀመርነው፡፡ ሌላው አትክልትና ፍራፍሬ ላይ ያሉ ባለሀብቶች ብዙ አልተበረታቱም፡፡ ሥራው መሬት ይፈልጋል፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ እንደ አበባ በአንድ መሬት ላይ ሁልጊዜ የምታመርተው አይደለም፡፡ ማፈራረቅ (ሮቴሽን) ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ መሬት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ አንተ አንድ ቦታ ላይ የአትክልትና የፍራፍሬ እርሻ ቢኖርህ፣ የአካባቢውን አርሶ አደሮች አደራጅተህ በጋራ የምታመርትበት ጠንካራ የመንግሥት ሲስተም ያስፈልጋል፡፡ ኬንያ ኤክስፖርት ከምታደርገው አትክልትና ፍራፍሬ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው አነስተኛ አርሶ አደር ከግል ዘርፉ ጋር ባላቸው ግንኙነት ተመርቶ የሚወጣ ነው፡፡ ዛሬ ግን የአትክልትና የፍራፍሬ ምርቷ እየወረደ ነው፡፡

ሪፖርተር– ለምን? ኤክስፖርቱን ለማሳደግ አማራጭ መፍትሔዎቹስ?

አቶ ፀጋዬ፡- በአብዛኛው ኬሚካል ስለሚጠቀሙ ነው፡፡ ብዙ ተባዮች እየተራቡ መጡ፡፡ ይህንን እንደ ምሳሌ ጠቀስኩ እንጂ ቡናንም ልናነሳ እንችላለን፡፡ ቡና ባለቤት የለውም እያልን ቆይተናል፡፡ አሁን በቅርብ ባለቤት እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ይህ አሠራር ምን ያህል ኃይል አለው? ጠንካራ ነው ወይ? ቡናን ከማምረት ጀምሮ ገበያ ድረስ ጠንካራ ሰንሰለት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር የተጀመሩ ጥሩ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ቡና ተይዞ ለረዥም ዓመታት ተሄደበት፡፡ ቡና ቡና እያልን ለዘመናት ኖርን፡፡ አሁንም ግን ቡና መሪ ነው፡፡ ግን የበለጠ ውጤት እንዲያመጣ መሠራት አለበት፡፡

      ሁለተኛ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀማችንም ችግር አለው፡፡ አንድ ኤክስፖርተር አንድ ወቅት ላይ ያተርፋል፡፡ ሌላ ጊዜ ይከስራል፡፡ ግን አንተ የምታመጣውን የውጭ ምንዛሪ የሚጠቀምበት ሌላ ነው፡፡ አንተ ካመጣኸው የውጭ ምንዛሪ 30 ወይም 40 በመቶውን ይዘህ ሌላ ኩባንያ ከፍተህ የምትጠቀምበት፣ ኤክስፖርቱና ኢንፖርቱ ተደጋግፈው እንዲሄዱና ኤክስፖርቱ እንዲያድግ መደረግ አለበት፡፡ እዚህ አገር አምራችና ኤክስፖርተር በጣም መበረታታት አለበት፡፡ ከገበያ ገዝቶ ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው ሰውዬና አምርቶ ለውጭ ገበያ የማያቀርበው ሰው መካከል ያለው የአደጋ ተጋላጭነት ይለያያል፡፡ አምርቶ የሚልከው ለሁሉ ነገር የተጋለጠ ነው፡፡ ከገበያ የሚገዛውና የሚልከው ደግሞ የተመቻቸ ነገር መርጦ፣ ለቅሞና አፅድቶ ይልካል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ አመጣብኝ አይልም፡፡

ስለዚህ ለሁለቱ የሚሰጠው ድጋፍ መለየት አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ብዙ አምራች እንዲኖሩ ይገፋፋል፡፡ ስለዚህ ብዙዎች ወደ አምራችነት እንዲገቡ አምራች ላኪዎችን የሚያበረታታ ነገር ሊኖር ይገባል፡፡ እነዚህን የበለጠ ባበረታታናቸው ቁጥር ሰው ወደዚህ እንዲገባ ይገፋፋል፡፡ ምክንያቱም ከሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ 50 በመቶውን ተጠቅሞ ኢንፖርት ስለሚያደርግ ወደ ኤክስፖርት መግባት ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በመረዳት፣ አምራች ዘርፉን የሚቀላቀለው እየበዛ ይሄዳል፡፡ ወደ ኤክስፖርቱ ሲገባ ደግሞ ሁለት ነገር መደረግ አለበት፡፡ አንደኛ ራሱ አምርቶ እንዲልክ፣ ሁለተኛ ከአነስተኛ አርሶ አደሮች ሰብስቦ በጥምረት የሚላክበትን አሠራር መዘርጋት ነው፡፡  

      ማንም ሰው ዶላር ካገኘ እንደሚያተርፍ ያውቃል፡፡ አንድ ኮንቴይነር ካመጣህ እኔ 100 ሔክታር ላይ ከማገኘው ትርፍ በላይ ትርፍ ታገኛለህ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ነገሮች የት ጋ ነው እኩል የሚሆኑት? ማለት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትም የተሻለ ጥቅም ሊያስገኝ የሚችሉ ነገሮችን ለመለየት ላኪዎችን ያወያይ፡፡ የሚፈለገውን ዕድገት ለማምጣት መሥራት ይኖርበታል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም በዚህ ላይ ውይይት ማድረግ አለባቸው፡፡ ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ ፍቱን መድኃኒት ሊሆን የሚችለው ከግል ዘርፉ ጋር በመመካከር ሲሠራ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር– በተደጋጋሚ ኤክስፖርት ያሉበትን ችግሮች አቅርበናል፣ ለችግሩ የሚሆን የመፍትሔ ሐሳብም ጎን ለጎን ብንሰጥም አልተሳካም ብለዋል፡፡ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ዕድገት እንዳይኖረው ያደረጉት ማነቆዎች ምንድናቸው? የችግሩ ምንጭስ ምንድነው?

አቶ ፀጋዬ፡- ችግሩ እንደ ኤክስፖርት ዘርፉ ይለያያል፡፡ በጉምሩክ ዙሪያ ችግሮች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አካባቢም ሊስተካከሉ የሚገቡ ጉዳዮች አሉ፡፡ ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ በጥቅል ሲታይ የወጪ ንግዱን የተመለከቱ የተለያዩ አሠራሮች ሲተገበሩ ኤክስፖርተሩን ያላማከሉ ሆነው መገኘታቸው በየቦታው ክፍተት እንዲኖር አድርጓል፡፡ ሌላው ለአገር ውስጥ ባለሀብቱ የሚሰጠው ድጋፍ አነስተኛ ነው፡፡ እንዲያውም ከአገር ውስጥ ባለሀብቱ የበለጠ ለውጭ ዜጎች የሚሰጠው ድጋፍ የተሻለ ነው የሚያስብል አሠራር አለ፡፡ ለምሳሌ የአገር ውስጥ ባለሀብት አንድ ማሽን ቢበላሽበት፣ የተበላሸውን ማሽን ለመተካት የውጭ ምንዛሪ ቢፈልግ ወረፋ መጠበቅ ግድ ይለዋል፡፡ የውጭ ኩባንያ ከሆነ ግን ወዲያው የሚፈልገውን ዕቃ ወረፋ ሳይጠብቅ የሚያስመጣበት ዕድል አለው፡፡  

ሪፖርተር– እንዴት የዚህን ያህል ልዩነት ይፈጠራል? የውጭ ኩባንያ ምን የተለየ ነገር አግኝቶ ነው የሚፈልገውን ዕቃ ለውጭ ምንዛሪ ወረፋ ሳይጠብቅ የሚያገኘው?

አቶ ፀጋዬ፡- በራሱ የውጭ ምንዛሪ ያስመጣል፡፡ ያስመጣውን ዕቃም በካፒታል ያስመዘግባል፡፡ በፍራንኮ ቫሉታ ያስገባል፡፡

ሪፖርተር– ፍራንኮ ቫሉታ ይፈቀዳል?

አቶ ፀጋዬ፡- በካፒታል ስለሚያስመዘግቡ ይፈቀድላቸዋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ክፍተቶችም አሉ፡፡ ሥራ አቁሞ ወረፋ የሚጠብቀው የአገር ውስጥ ባለሀብት ለምርቱ የሚሆነውን ጥሬ ዕቃ ለማግኘት ጊዜ የሚወስድበት ከሆነ ደመወዝ እንዴት ይከፍላል? ፈጣን ምላሽ ካላገኘስ እንዴት ኢኮኖሚውን ያግዛል?

ሪፖርተር– አሁን እየታየ ነው ከሚባለው ለውጥ አንፃር የንግዱ ማኅበረሰብ ምን ይጠብቃል? ከዚህ በኋላ ምን መሆን አለበት? በአንፃሩ ደግሞ በአጠቃላይ ለግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴ መዳከም የሚፈለገውን ያህል የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻል፣ ወይም ኤክስፖርቱ የተጠበቀውን ያህል ባለመሆኑ መንግሥትን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል? የንግድ ማኅበረሰቡ አስተዋጽኦ የለበትም?

አቶ ፀጋዬ፡- የንግዱ ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች በአንድ ጀንበር የሚመለሱ አይደሉም፡፡ ግን የንግድ ማኅበረሰቡን የሚመለከቱ ነገሮች ላይ መምከርና መወያየት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ያስቀራል፡፡ አንዳንድ መመርያዎች ብዙ ነገሮችን ሊያበላሹ ይችላሉ፡፡ ቢመከርባቸው ኖሮ እንዲህ ችግር ባልተፈጠረ የምትልባቸው ነገሮች አሉ፡፡ አሁን እንኳን በቅርቡ አንድ እንደ ኢንቮይስ ለመቆጣጠር ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመርያ የፈጠረውን ችግር መመልከት እንችላለን፡፡ ዋጋ ትመና ላይ ገብቶ ብዙ ነገር ሲዘበራረቅ ዓይተናል፡፡ በኋላ ላይ እንዲቀር ተደረገ እንጂ ይህ መመርያ ብዙ ችግር እየፈጠረ ይቀጥል ነበር፡፡ አንዳንዴ ጥቂቶች የሚፈጽሙትን ችግር ለመቆጣጠር ሲባል የሚወጡ መመርያዎች፣ በአግባቡ የሚሠሩትን ብዙዎች ሲጎዱ ይታያል፡፡ ሁሉም የንግድ ማኅበረሰብ ንፁህና በአግባቡ የሚሠራ ነው ባይባልም፣ ከ95 እስከ 99 በመቶ በአግባቡ ይሠራል ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ የሚወጣው መመርያ አብዛኛውን የሚደገፍና የሚያሠራ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ መካከር የግድ ይላል፡፡ የተወሰኑትን ለመቆጣጠር ሲባል ብዙኃኑን መደቆስ አያስፈልግም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...