Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ውኃ አምራቹ ጥቅም ላይ የዋሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን እንደሚሰበስብ ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአበበ ድንቁ የታሸገ ውኃና ከአልኮል ነፃ መጠጦች አምራች ፋብሪካ ያስተዋወቀው ቶፕ ውኃ የተባለ አዲስ የውኃ ምርት ይፋ ተደረገ፡፡ ኩባንያው አካባቢን የሚበክሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶች የሚያደርሱትን ጫና ለመቀነስ ጥቅም ላይ የዋሉ ጠርሙሶችን ከመሰብሰብ ባሻገር፣ በየዓመቱ ከሚያከናውነው ሽያጭ ውስጥ ንፁህ የመጠጥ ውኃ ማግኘት ላልቻሉ ማኅበረሰቦች አስተዋፅኦ የሚያደርግበትን አሠራር እንደሚከተል አስታወቀ፡፡

ቶፕ ውኃ የተሰኘውን አዲስ ምርት ሐሙስ፣ ሚያዝያ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ያስተዋወቀው ኩባንያው፣ በአሁኑ ወቅት ለምርት ዝግጁ ያደረገው ፋብሪካ በሰዓት 18 ሺሕ ጠርሙስ የመሙላት አቅም አለው፡፡ የፋብሪካው መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ድንቁ እንዳስታወቁት፣ በ273 ሚሊዮን ብር ካፒታል በ11 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ፣ ከአዲስ አበባ 18 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ቡራዩ ከተማ አቅራቢያ፣ በተለይም በታጠቅ፣ ገፈርና ኖኖ አካባቢ የተገነባው ውኃ አምራቹ ፋብሪካ፣ የማስፋፊያ ግንባታዎችን በማካሔድ ተጨማሪ 24 ሺሕ ጠርሙሶችን በሰዓት የሚሞላ ማሽን ለመትከል ዝግጀቱን አጠናቋል፡፡

በጥቂት ጊዜ ውስጥ ይህ ማስፋፊያ ዕውን እንደሚደረግና አጠቃላይ አቅሙንም በሰዓት 42 ሺሕ ጠርሙስ እንደሚያደርሰው አብራርተዋል፡፡ ፋብሪካው የራሱን የፕላስቲክ ጠርሙሶች ከነክዳናቸው በማምረት የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር እንዳይገጥመው ከማድረጉም ባሻገር፣ ምርቶቹን ከ0.6 ሊትር ጀምሮ እስከ 20 ሊትር በሚይዙ ማሸጊያዎች ለገበያ ማቅረብ የሚያስችለው ዘመናዊ ማሽን መግጠሙን አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡ 

ቶፕ ውኃ የአገሪቱን የታሸገ ውኃ አምራቾች ሲቀላቀል ከጅምሩ ጀምሮ ለአካባቢ ተፅዕኖ የሚያጋልጡ አሠራሮችን ለመቀነስ መነሳቱን የገለጹት የኩባንያው የገበያና የሽያጭ ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ አጀማ፣ ኩባንያው የራሱን የፕላስቲክ ጠርሙሶች የሚሰበስብባቸውን አሠራሮች መዘርጋቱን ጠቅሰዋል፡፡

በዓመት 66.7 ሚሊዮን የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ፋብሪካው ሞልቶ እንደሚያሽግ የጠቀሱት አቶ ሽመልስ፣ ጥቅም ላይ የዋሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ከሚሰበስቡ 74 ማኅበራት ጋር አብሮ ለመሥራትና በገበያው ከሚከፈላቸው ዋጋ ላይ ጭማሪ በማድረግ የተሰበሰውን ጠርሙስ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ሥራ ላይ ለተሠማሩ የውጭ ኩባንያዎች እንደሚልክም አስታውቀዋል፡፡ ከሚያዝያ 4 ቀን ጀምሮ ምርቱን ወደ ገበያ እንዳስገባ ያስታወቀው ይህ ኩባንያ፣ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችለውን የፕላስቲክ ጠርሙሶች ማሰባሰብ ሥራም ከሚያዝያ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚተገብር ይፋ አድርጓል፡፡

ጥቅም ላይ የዋሉትን ፕላስቲክ ጠርሙሶች ከሚሰብስቡ 74 ማኅበራት ጋር አብሮ እንደሚሠራና፣ እስከ 300 ኪሎ ግራም ክብደት መሸከም የሚችሉ ከረጢቶችን በመኖሪያ አካባቢዎችና በመሰብሰቢያ አካባቢዎች በማስቀመጥ የፋብሪካው ጠርሙስ መሬት ላይ ተጥሎ እንዳይገኝ ለማድረግ መነሳቱን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በየዓመቱ ከሚያከናውነው ሽያጭ ውስጥ የ1.34 ሚሊዮን ብር አስተዋፅኦ የሚያደርግበትንና የኩባንያ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣበትን ዕቅድ መቅረጹንም አቶ ሽመልስ ጠቅሰዋል፡፡ ይኼም ከ66.7 ሚሊዮን ጠርሙስ ሽያጭ ውስጥ የ0.02 ሳንቲም መዋጮ ማድረግ የሚችልበት ስሌትን የተከተለው ቶፕ ውኃ፣ በየዓመቱ ከአራት እስከ አምስት የጉድጓድ ውኃ ማስቆፈር እንደሚያስችለው ተብራርቷል፡፡

ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት ኩባንያዎች እንዲህ ያሉ የማኅበራዊና የኮርፖሬት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ ቢያስታውቁም፣ በተለይ የታሸገ ውኃ በገበያው የሚሸጥበት ዋጋ የተጋነነ ሆኖ ይገኛል፡፡ አንድ ሰው የታሸገ ውኃ ለመጠቀም በወር የሚያወጣው ወጪ በአማካይ ከ400 ብር ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህም ማለት አንድ ቤተሰብ በወር በአማካይ ለቧንቧ ውኃ ስምንት ብር ይከፍላል ተብሎ ቢታሰብ፣ ለመደበኛው የቧንቧ ውኃ አገልገሎት የሚያወጣው ገንዘብ፣ ለታሸገ ውኃ ፍጆታ በወር ከሚያወጣው አኳያ ከአራት እጥፍ በላይ ያነሰ ሆኖ ይገኛል፡፡ በሌላ አባባል በወር ለታሸገ ውኃ የሚያወጣው ገንዘብ የአራት ዓመት የቧንቧ ውኃ ፍጆታውን ይሸፍናል እንደማለት ይሆናል፡፡

የኩባንያው አማካሪ አቶ ሔኖክ ነጋሽም ሆኑ አቶ ሽመልስ እንደሚገልጹት፣ አብዛኞቹ ውኃ አምራቾች ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ በማስገባት መጠቀማቸው የመሸጫ ዋጋቸው ላይ ተፅዕኖ አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በገበያው የሚታየው የሽያጭ ሰንሰለት መራዘም፣ ከአምራቹ እስከ መጨረሻው ቸርቻሪ ድረስ ያለው ቅብብሎች ሸማቹ ላይ የዋጋ ጫና ሲያሳድር እንደሚታይ አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ወደ ሥራ ለመግባት እየተጠባበቁ ከሚገኙት ሰባት ውኃ አምራቾች ባሻገር ከ67 የውኃ ፋብሪካዎች በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም በአገሪቱ የምርት ጥራትና ቁጥጥር ላይ አስገዳጅ ደረጃዎች ቢቀመጡም፣ ፋብሪካዎቹ ለሽያጭ ያዋሏቸው የፕላስቲክ ጠርሙሶች በአግባቡ እንዲሰበስቡ የሚያስገድድ አሠራር ባለመኖሩ፣ ከ600 እስከ 1,000 ዓመታት ለሚቆይ ጊዜ ሳይበሰብሱ መቆየት የሚችሉ የፕላስቲክ ውጤቶች አገሪቱን አጥለቅልቀውና በሜዳው ተጥለው ይታያሉ፡፡ የውኃ አምራቾቹ ብቻም ሳይሆኑ ሌሎችም የፕላስቲክ ማሸጊያዎችንና ግብዓቶችን የሚያመርቱና የሚጠቀሙ ድርጅቶች እንዲህ ያለው ግዴታ ስላልተቀመጠባቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፔትሮ ኬሚካል ውጤት የሆኑ የፕላስቲክ ምርት የኢትዮጵያን ጎዳናዎች አጥለቅልቀው ይታያሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች