Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ የእህል ምርት ከተገመተውም የተሻለ ውጤት እንደሚያሳይ የአሜሪካው የግብርና መሥሪያ ቤት ይፋ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከ100 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ በቆሎ ወደ ውጭ እንደሚላክ ይጠበቃል

በአሜሪካው የግብርና መሥሪያ ቤት ዕውቅና ‹‹ግሎባል አግሪካልቸራል ኢንፎርሜሽን ኔትወርክ›› የተሰኘው ዓመታዊ ሪፖርት ውስጥ የተካተተው የኢትየጵያ የሰብል ምርት መጠን፣ የግብይትና የፍጆታ ትንታኔ፣ ከዚህ ቀደም አነስተኛ ምርት እንደሚኖር የተገመተውን ያሻሻለ ትንበያ ቀርቦበታል፡፡

የየአገሮቹን የግብርና ምርቶች በመተንተን ትንበያዎችን የሚያስቀምጠው ይኼው ሪፖርት፣ በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ እየታየ ካለው የተሻሻለ የአየር ጠባይ ሁኔታና የዝናብ ሥርጭት፣ ከተሻሻሉ ዝርያዎችና ከማዳበሪያ ተጠቃሚነት መስፋፋት አኳያ እንደ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ገብስ፣ ማሽላና መሰል ምርቶች የጨመረ ምርታማነት ሊኖር እንደሚችል በትንታኔው አቅርቧል፡፡ በተለይም ለተከታታይ ዓመታት የተቋረጠው የበልግ ዝናብ በዚህ ዓመት መምጣቱ ለምርት ዕድገቱ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

ይህም ሆኖ የአጭር ጊዜ ቆይታ ያለው የበልግ ዝናብ፣ በዚህ ዓመት የሚጥለው መጠን አስተማማኝ ባለመሆኑ ሊኖር የሚችለው የምርት መጠን ከፍተኛ እንደሚሆን መጠበቅ አዳጋች ስለመሆኑም ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ ዋናው የዝናብ ወቅት በመኸር ምርት ዘመን የሚታየው በመሆኑ የምርት ዕድገትን በአብላጫው የሚወስነውም ይኼው የዝናብ ወቅት ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የመጤው ተምች ወረርሽኝ (ፎል አርሚ ዋርም) በሰብል ምርቶች ላይ በተለይም በበቆሎ ምርት ላይ ያደረሰው ጉዳት እንደተፈራው ባለመሆኑም የዘንድሮ ምርት የተሻለ ውጤት ሊታይበት እንደሚችል የአሜሪካ ግብርና ባለሙያዎችና አማካሪዎች ያሰናዱት ሪፖርት ይጠቅሳል፡፡

ባለፈው ዓመት የተመረተው የስንዴ መጠን 4.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደነበር ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ በዚህ ዓመት የ300 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ተጨማሪ ምርት እንደሚኖር ይተነብያል፡፡ ይህ የሚሆነውም በሔክታር የሚመረተው 2.6 ሜትሪክ ቶን ምርት፣ እንዲሁም የታረሰው 1.6 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ከዓምናው ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ነው፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የስንዴ ምርት ዕድገት እያሳየ መምጣቱን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ ከምርጥ ዘር አጠቃቀም መጨመር ባሻገር ሜካናይዜሽን እየተበራከተ መምጣቱ፣ የተባይ ወረርሽኝ ብሎም የሰብል በሽታዎች ጫና መቀነስ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ያትታል፡፡

በፍጆታ ረገድም በዚህ ዓመት ከስድስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የስንዴ ፍላጎት እንደሚኖር ሲጠበቅ፣ እንደ ዳቦና ፓስታ ያሉ የስንዴ ውጤቶች ፍላጎት መጨመር ለፍጆታው ከፍተኛ መሆን አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡ ምንም እንኳ የስንዴ ፍላጎት እየጨመረ ቢመጣም አቅርቦቱ በሚፈለገው መጠን እንዳልሆነ ተጠቅሷል፡፡ በቂ አቅርቦት ባለመኖሩ ሳቢያም እስከ 40 በመቶ የሚሆውን የስንዴ ምርት ከውጭ ማስገባት አስፈልጓል፡፡ ይህም ሆኖ በፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ሳቢያ የስንዴ ዋጋ እየጨመረ በመምጣት በአሁኑ ወቅት በተለይ በአዲስ አበባ የአንድ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ዋጋ 12,420 ብር ገደማ ወይም 460 ዶላር እንደደረሰ ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡ ይህም በኪሎ ሲሰላ ዋጋው 12 ብር ከ42 ሳንቲም እንደሆነ ያመላክታል፡፡

ከዚህ ባሻገር በዚህ ዓመት ከውጭ የሚገባው የስንዴ መጠን ካለፈው ዓመት 100 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቅናሽ በማሳየት 1.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ቅናሹ እንደሚኖር የተገመተው መንግሥት ለመጠባበቂያ ከያዘው ክምችት ሊጠቀም ይችላል ከሚል መነሻ ነው፡፡ መንግሥት ለዕርዳታ ከሚገባው ስንዴ ባሻገር ያለውን የስንዴ የገቢ ንግድ ሲቆጣጠር ቢቆይም፣ እየተባባሰ ከመጣው ወጪ አኳያ የግሉ ዘርፍም በአስመጪነት እንዲሳተፍ ማድረግ መጀመሩን ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡ በተለይም ለዳቦና ለዱቄት የሚደረገው ድጎማ መንግሥት ላይ ያስከተለው የወጪ ጫና የግሉን ዘርፍ በአስመጪነት እንዲያሳትፍ ማስገደዱ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ዋናው ነው፡፡ ይሁንና የግሉ ዘርፍ በተለይም የዱቄት ፋብሪካዎች በስንዴ አስመጪነት እንዲሳተፉ የሚያስችላቸው በቂ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በወቅቱ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ሪፖርቱ ይጠይቃል፡፡

ይህ ይባል እንጂ ንግድ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በበላይነት የሚቆጣጠሩት የስንዴ የገቢ ንግድና የዳቦ ዋጋ ድጎማ ሒደት የአዲስ አበባ ዳቦ ቤቶችም ሆኑ ዱቄት አምራቾችን በተተመነላቸው ዋጋ መሠረት እንዲሸጡ ያስገድዳሉ፡፡ በ2003 ዓ.ም. ተግባራዊ የተደረገው የዋጋ ተመን ከአምስት ወራት ቆይታው በኋላ በ22 ምርቶች ላይ ተጥሎ ከነበረው የዋጋ ተመን ውስጥ እስካሁን ሳይነሳ የቆየው በዳቦና ዱቄት ምርቶች ላይ ብቻ ሆኖ ይገኛል፡፡

መንግሥት ድጎማ በማድረግ ለዱቄት ፋብሪካዎች የሚያቀርበውን ስንዴ ፋሪካዎቹ በመፍጨት ለተመረጡ ዳቦ ቤቶች በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ መንግሥት ይህንን የስንዴ ድጎማ፣ የዱቄትና የዳቦ ዋጋ ላይ የጣለውን ተመን ያላነሳው የምግብ ዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ከነበረው አቋም በመነሳት ሲሆን፣ በተለይ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል ለመደጎም ያለመ አካሄድ እንደሆነ በወቅቱ ሲገለጽ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከስንዴ ባሻገር በአገሪቱ ሰፊ የምርት ሽፋን እንደሚኖረው የሚጠበቀው በቆሎ ነው፡፡ በዚህ ዓመት 7.1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በቆሎ እንደሚመረት ሲገመት፣ ካለፈው ዓመት አኳያ 100 ሸሕ ሜትሪክ ቶን ምርት ጭማሪ እንደሚኖር ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ምርቱ እንደሚጨምር የታሰበውም በበቆሎ ዋጋ መጨመር ሳቢያ ተጨማሪ የእርሻ መሬት በቆሎ እንደተዘራበት በመታየቱና የመጤው ተመች ጉዳትም እንደተፈራው ያህል በቆሎ ላይ ያደረሰው ጉዳት ባለመኖሩ ነው፡፡ ይሁንና የበቆሎ ዋጋ ካለፈው ዓመት አኳያ የ40 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ተመልክቷል፡፡ ይህም በመሆኑ በአገር ውስጥ የሚኖረው ፍጆታ ሰባት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደሚሆን ሲጠበቅ፣ ካለፈው ዓመት አኳያ የ150 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ጭማሪ እንደሚያሳይ ይገመታል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ባለፈው ዓመት ወደ ውጭ ከተላከው 80 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በቆሎ አኳያ ዘንድሮ የ20 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ጭማሪ የታየበት የ100 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የወጪ ንግድ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡

ምንም እንኳ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ መንግሥት የበቆሎ የወጪ ንግድ እንዳይኖር ከልክሎ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም አንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ተጨማሪ የበቆሎ ምርት እንደሚኖር መንግሥት በመገመቱ ሳቢያ የወጪ ንግድ ዕገዳው እንዲነሳ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም መንግሥት በይፋ የጠቀሰው የበቆሎ የወጪ ንግድ መጠን 62 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ሲሆን፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ምርትም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ወደ ጎረቤት አገሮች እንደሚወጣ የሪፖርቱ ጸሐፊዎች እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ መንግሥት የጠቀሰው የአንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ትርፍ ምርትም የተጋነነ ግምት እንደሆነ ሪፖርቱ አስፍሯል፡፡ ይህም ሆኖ በዚህ ዓመት ከ100 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ያላነሰ የበቆሎ ምርት ወደ ውጭ እንደሚላክ ይጠበቃል ብሏል፡፡

ባለፈው ዓመት ኬንያን ጨምሮ በርካታ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ባጋጠማቸው የመጤው ተምች ወረርሽኝ ሳቢያ፣ ከፍተኛ የበቆሎ ምርት እጥረት አጋጥሟቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎም ይመስላል የምሥራቅ አፍሪካ የእህል ነጋዴዎች ምክር ቤት በአዲስ አበባ ስብሰባውን አካሂዶ በኢትዮጵያም ጽሕፈት ቤቱን እንደከፈተ አስታውቆ ነበር፡፡ በዚህ ወቅትም የኢትዮጵያ እህል ነጋዴዎችም በመሳተፍ የግዥ ስምምነቶችን ማድረጋቸውም የሚታወቅ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች