Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሳምንት ክራሞት

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ከተመረጡ ሁለት ሳምንታት ያስቆጠሩት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣናቸውን በተረከቡ በቀናት ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሥራ ጉብኝት በማድረግ፣ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በመገናኘት ውይይት እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን የለቀቁትን አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ተክተው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ከተሰየሙ በኋላ፣ ተከታታይ ሁለት ሳምንታትን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የማነጋገር መርሐ ግብር ይዘው የሥራ ጉብኝቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

  ይህ ታሪካዊ ነው የተባለ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት፣ መጀመርያ የሥራ ጉብኝታቸው የነበረው ወደ ሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅግጅጋ የተደረገ ሲሆን፣ በዋናነት ዕርቀ ሰላም የመፍጠር አጀንዳን ያነገበ ነበር፡፡ የመጋቢት 29 ቀን 2010 ዓ.ም.  የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት፣ በተለይም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ሥፍራዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለማርገብ ያለመ ሲሆን፣ በሁለቱ ክልሎች ያጋጠመውን ግጭት አውግዘው፣ ‹‹ያልተገባ፣ ከባህላችን ያፈነገጠና የሁላችንንም አንገት ያስደፋ የሽንፈት ታሪካችን ነው፤›› በማለት ኮንነውት ነበር፡፡

  በጉብኝቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከክልሉ ከተውጣጡ ሹማምንት፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከሁለቱ ክልሎች ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ተወያይተዋል፡፡ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ፣ ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ያቀፈ ልዑካን ቡድን ይዘው ነበር የተጓዙት፡፡

  በዋናነት በሁለቱ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውንና አንድ ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት ለነበረው ግጭት መፍትሔ ለማምጣት ያለመ የሥራ ጉብኝት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁለቱ ክልሎች ርዕሰ ብሔሮች ለሰላም እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

  ‹‹አቶ አብዲ ሙሐመድ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት፣ አቶ ለማ መገርሳ የኢትዮ ሶማሌ ክልል ፕሬዚደንት፤›› ብለው አቀያይረው በመጥራትም ያለውን ልዩነት እንዲፈቱና በሕዝባዊ ስብሰባው ተሳታፊዎች ፊት እጅ እንዲጨባበጡ አድርገዋቸዋል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በጅግጅጋ የነበራቸው ቆይታ የሰላም ተልዕኮን ያዘለ ሲሆን፣ በሁለቱ ክልሎች ነዋሪዎች መካከል ተከስቶ የነበረው ግጭት በድጋሚ እንዳይከሰት በቀጣይነት ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ፣ ጥል ቢከሰት እንኳን ለልማት የሚውሉትን ትራክተርና ዶዘር በመዋዋስ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

  ቀጣይ ጉዞቸውን ወደ ኦሮሚያ ክልል አምቦ ከተማ ያደረጉት ዶ/ር ዓብይ፣ በከተማዋ ተገኝተው በስታዲዮም ለተሰበሰበው የአምቦና አካባቢው ማኅበረሰብ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ከኅብረተሰቡ ጋር በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ከተለያዩ አካላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

  ከጅግጅጋው ጉብኝታቸው መልስ በአምስተኛው ቀን ረቡዕ ሚያዝያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በነበረው የአምቦ ጉብኝት፣ ቁጥራቸው 50 ሺሕ የሚጠጉ የአምቦና የአካባቢው ነዋሪዎች በአምቦ ከተማ ስታዲዮም ተገኝተው ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቀባበል ማድረጋቸውን ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ ለማየት ችሏል፡፡

  ገና ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ መትመም የጀመረው ሕዝብ የኦሮሚያ ክልልና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማዎች በያዙ ወጣቶች፣ እንዲሁም በዋናነት ዶ/ር ዓብይና አቶ ለማን የሚያሞግሱ መፈክሮችን ባነገቡ ወጣቶች የታጀበ ነበር፡፡ በተጨማሪም ከአዲስ አበባ አምቦ ባለው 100 ኪሎ ሜትር መካከል በሚገኙ ትንንሽ ከተሞች በተሽከርካሪዎች ታጅቦ ወደ አምቦ ያቀናው ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናትን ያቀፈው የልዑካን ቡድን የ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ›› መልዕክት በያዙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አቀባበል ሲደረግለት ተስተውሏል፡፡

  መነሻውን አዲስ አበባ ያደረገው የልዑካን ቡድን ወደ ሦስት ሰዓት አካባቢ አምቦ ከተማ የደረሰ ሲሆን፣ ወደ አምቦ ስታዲዮም ከመግባቱም በፊት በአንድ ሆቴል የደቂቃዎች ዕረፍት አድርጓል፡፡

  አምቦ ከተማና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች ከሦስት ዓመት በፊት የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞና አመፅ ዋና መነሻዎችና ማዕከል እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ በጊንጪ ከተማ በትምህርት ቤቶች የተከሰተ ሕዝባዊ ተቃውሞ መዳረሻውን በማስፋት መላ ኦሮሚያን ማጥለቅለቁና ለበርካቶች መሞት፣ እንዲሁም ለአገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ መግባት ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡

  ሚያዝያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በአምቦ ከተማ የተገኙት ባለሥልጣናት፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አምቦንና የአካባቢውን ነዋሪ፣ እንዲሁም ሕዝቡን አሞግሰዋል፡፡

  ‹‹ይህ ቀን ታሪካዊ ነው፤›› ያሉት አቶ ደመቀ፣ ‹‹ቄሮ የኢትዮጵያ ለውጥ ባለቤት ናችሁ፤›› ሲሉ የኦሮሞን ወጣት አሞግሰዋል፡፡ ‹ኢትዮጵያ አገራችን› በሚለው ዜማ በኦሮሚያ ፖሊስ እግረኛ ባንድ የተጀመረው መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርና በአባ ገዳዎች ምርቃት የታጀበ ሲሆን፣ ቀጥሎም የዕለቱ እንግዶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ጨምሮ አቶ ደመቀና አቶ ለማ ለሕዝቡ ንግግር አድርገዋል፡፡

  የንግግር ሥርዓቱን የጀመሩት አቶ ለማ፣ ‹‹የተሰጠን ትልቅ ኃላፊነት ክልሉንም አገሪቱንም ይመለከታል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የኦሮሞ ሕዝብ ሌላውን ሕዝብ አቅፎ የመሄድ እሴቱን መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

  በስታዲዮሙ የተገኙ የአምቦና የአካባቢዋ ነዋሪዎችም ለአቶ ለማ ሞቅ ያለ አቀባበልና ሙገሳ ሲያሰሙ ነበር፡፡ በመጨረሻ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹እናንተ ወጣቶች የኦሮሞ ሕዝብ ጋሻና መከታ ናችሁ፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

  ‹‹በአምቦ ከተማ በመገኘቴ ደስተኛ ነኝ፤›› ያሉት ዶ/ር ዓብይ፣ ‹‹ከሰሞኑ የተደረገው የሥልጣን ሽግግር አገራችን ያለችበት ቁመና ከማሳየት አልፎ የገዳ ሥርዓታችንን ሕግ አውጥቶ ለበርካታ ዘመናት ያደረገው እንቅስቃሴ ማሳያ ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ‹‹መደማመጥ፣ መከባበር፣ አንቺ ትብሽ፣ አንተ ትብስ ተባብለን መኖር አለብን፤››  ሲሉም ተናግረዋል፡፡

  የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን በከተማው መገኘት ምክንያት በሥፍራው ከተገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት መኮንን በዳዳ አንዱ ሲሆን፣ በነበረው ሁነት ደስተኛ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

  የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የአንደኛ ዓመት አካውንቲንግ ተማሪ የሆነው መኮንን፣ አሁን ከወራት በፊት የነበረው አለመረጋጋት ተወግዶ በሰላም ትምህርቱን እየተከታተለ እንደሆነ ገልጿል፡፡

  በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው የነበሩት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የሆኑ ሁለት ህንዳውያን ቻንድራ ሴልቸር (ዶ/ር) እና መሐመድ ፋቂር (ዶ/ር) ሕዝቡ ለመሪዎቹ ያለውን ፍቅር በዓይናቸው ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ አሁን ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው ሲሉም የነበረው አለመረጋጋት እንደሰከነ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

  በክልሉና በአገሪቱ በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት አምቦ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ለተከታታይ ሳምንታትና ወራት ትምህርት ተቋርጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡

  ሌላው በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ከከተማዋ የተውጣጡ ግለሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈረስ ሽልማት ሲሰጡ ተስተውሏል፡፡ በተጨማሪም በወቅቱ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ደስታቸውን በዝላይ ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡

  ግማሽ ቀን በፈጀው በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹አንድነታችንን አጠናክረን የአገራችንን ዕድገት ማፋጠን አለብን፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ የተገኙት አቶ ዓለማየሁ እሬንሶ የተባሉ ግለሰብም፣ ‹‹አሁን ያየሁት ሕዝብ ምን እንደሚፈልግ ማሳያ ነው፡፡ ይህች አገር የሁሉም የጋራ አገር ናት፤›› ብለዋል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአምቦ ጉብኝት ከተመለሱ በኋላ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል አካላት ጋር በምኒልክ ቤተ መንግሥት ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጨባጭ የፖሊሲ አማራጮችን በመያዝ ትክክለኛ ተፎካካሪነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል፡፡

  ‹‹አገሪቷ በቀጣይ በምታካሂደው አገራዊ ምርጫ ፓርቲያችንና መንግሥታችን ከልብ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነፃ እንዲሆን አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል፤›› ሲሉም በዝግጅቱ ላይ ለተሳተፉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ቃል ገብተዋል፡፡

  ከአምቦው ጉብኝት ሁለት ቀናት በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዳረሻ የነበረው መቐለ ከተማ ሲሆን፣ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

  በቅድሚያ በሐውልቲ የሰማዕታት መታሰቢያ ተገኝተው የአበባ ጉንጉን ያስቀመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የትግርኛ ቋንቋ ይችላሉ ቢባሉም፣ በሕዝብ ፊት ሲናገሩ ተደምጠው በማያውቁበት ቅልጥፍ ባለ ትግርኛ ንግግር ሲያደርጉ በአዳራሹ የተገኙ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሐውልቲ የሰማዕታት መታሰቢያ አዳራሽን በጭብጨባ አናግተውታል፡፡

  ‹‹የተከበራችሁ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች . . . ›› ብለው ንግግራቸውን በትግረኛ ሲጀምሩ፣ ያልጠበቁት ነገር ያጋጠማቸው በመሰለ ሁኔታ ነበር አዳራሹ ውስጥ የተሰበሰቡት ተሳታፊዎች ጭብጨባቸውን ያስተጋቡት፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመቐለው ንግግራቸው የትግራይን ሕዝብ የኢትዮጵያ ዋልታና ማገርነት፣ የአገር ኩራት የሆኑ ዓድዋን፣ የዘርዓ ያዕቆብንና የቅዱስ ያሬድ መገኛነት፣ ብሎም ለአገር ለፃነትና ለኢትዮጵያ መታነፅ ሲሉ ራሳቸውን ቤዛ ያደረጉ ሰማዕታት፣ በተለይም መለስ ዜናዊን ያስገኘች ክልል መሆኗን በማውሳት ሙገሳቸውን አዝንበውታል፡፡

  እያንዳንዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የንግግር አንቀጽ በጭብጨባ የታጀበ ነበር፡፡ ‹‹ትግራይ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መሠረት ከመሆን አልፋ፣ የሚያኮራ ታሪክና ሥልጣኔ የያዘች፣ የአገራችን ታሪክ እንደ እንጀራ የተጋገረባት ክልል ናት፤››፣ ‹‹እንደነ ስሑል፣ ፀሐዬ፣ ማርታ፣ ሙሴ፣ ዶ/ር አታኸልቲ፣ ብረሃነ መስቀል፣ አሞራው፣ ሃየሎም፣ ቀሽ ገብሩና ሌሎች በሺሕ የሚቆጠሩ ጀግኖች አሁን ላለንበት ሥርዓት ሲሉ ክቡር ዋጋ የከፈሉትን የወለደች ክልል ነች፡፡ ለዚህ ነው ትግራዋይን በቀላል ቋንቋ ኢትዮጵያዊ ብለን የምንገልጸው ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን የፈጠረ ነው የምንለው፤›› ሲሉ ለክልሉ ሕዝብ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

  በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው ግጭት መጥፎ ጠባሳን ይዞ የመጣ ክስተት መሆኑ ካሁን በፊት በተደጋጋሚ ሲገለጽ የቆየ እውነታ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመቐለው ንግግራቸው እንዲህ ዓይነት ጥፋቶች እንዳይደገሙ ለመሥራት ቃል ገብተዋል፡፡

  ‹‹ባለፉት ጊዜያት ባጋጠመን ሁከትና ግርግር በተለይ በኦሮሚያናአማራ ክልሎች በትግራዋይ ላይ ለደረሰው በደል ይቅርታ እየጠየቅኩኝ፣ የተበደለውን ለመካስ ፌዴራል መንግሥት እንደሚሠራ ቃል እገባለሁ፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ገብተዋል፡፡

  ከዚህም ባለፈ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ያለውን ልዩነት ለመፍታት ጠንክረው እንደሚሠሩ፣ የቀድሞ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲመለስ በድጋሚ ለኤርትራ መንግሥት ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

  በትግራይ ክልል የሚኖራቸውን ቆይታ በአንድ ቀን አጠናቀው የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ እሑድ ሚያዝያ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ከ25 ሺሕ ወጣቶች ጋር፣ ሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ደግሞ ከባለ ሀብቶች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ዕቅድ ተይዟል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -