Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የ45 ነጋዴዎችን የባንክ ሒሳብ ማገዱ ተቃውሞ አስነሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በንግድና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ 45 ኩባንያዎች በ18 ባንኮች የሚያንቀሳቀሱትን ሒሳብ በሙሉ ማገዱ ተቃውሞ አስነሳ፡፡ ባለሥልጣኑ የባንክ ሒሳባቸውን ያገደው ሕግን ባልተከተለ መንገድ መሆኑን የገለጹ ኩባንያዎች ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

      የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሞጆ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ በአቶ አዲስ አየለ ፊርማ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. የወጣው ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክና ለ16 የግል ባንኮች ደርሷል፡፡

      በባለሥልጣኑ ትዕዛዝ መሠረት ባንኮቹ የደንበኞቻቸውን ሒሳብ ማገድ የጀመሩ ሲሆን፣ 45 ኩባንያዎች ባለሥልጣኑ ከሚፈልገው ገንዘብ በላይ የታገደባቸው በመሆኑ እንቅስቃሴያቸው እንደተገደበ ገልጸዋል፡፡

      “በባንካችሁ ከሚገኙ ደንበኞች ሒሳብ ቁጥር ላይ ተቀንሶና ታግዶ እንዲገለጽ ስለመጠየቅ” በሚል ርዕስ ባለሥልጣኑ ለ18 ባንኮች በጻፈው ደብዳቤ፣ የተጠቀሱት አስመጪዎች በሞጆ ጉምሩክ በኩል ቀሪ ቀረጥና ታክስ እንዲከፍሉ የተጠየቁ ቢሆንም፣ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ውስጥ ክፍያውን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆኑም ይላል፡፡

ደብዳቤው በመቀጠልም ‹‹በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 122 ንዑስ አንቀጽ 6 እንዲሁም፣ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/08 አንቀጽ 43 ምክንያት በደንበኞች ስም የተቀመጠ ገንዘብ ወይም ሊከፍሉት የሚገባ ማናቸውም ዓይነት ክፍያ ለታክስ ባለሥልጣኑ ገቢ እንዲደረግ ወይም በባንኮቹ እጅ የሚገኝ የግብር ከፋይ ማናቸውም ንብረት ለግብር ታክስ ዕዳ አሰባሰብ እንዲውል፤›› በማለት በደብዳቤው አስታውቋል፡፡

      ‹‹በባንካችሁ ከሚገኘው ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ላይ በትይዩነት የተገለጸው ሒሳብ መጠን ታግዶ ስለዕገዳው ለሞጆ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንድትገልጹ በማለትም በደብዳቤው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

      የ45 ኩባንያዎች የተቃውሞ ማጠንጠኛ በሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የመጀመሪያው ባለሥልጣኑ የሚፈልገው ገንዘብ በአንድ ባንክ ውስጥ ሊሟላ እየቻለ በሁሉም ባንኮች የሚገኙ አካውንቶች መዝጋቱ አግባብ አይደለም የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ኩባንያዎች ይህን ያህል ገንዘብ ልንከፍል አይገባንም በማለት ክርክር ውስጥ እያሉ ያላግባብ ሒሳቦቻቸው እንዲታገዱ መደረጉ አግባብ አይደለም የሚል ነው፡፡

      የባንክ ሒሳብ ከታገደባቸው መካከል ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ባለሀብት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ በአብዛኛው የሚፈልገው ገንዘብ በአማካይ ከአንድ ሚሊዮን ብር በታች ነው፡፡

      “እኛ በተለያዩ ባንኮች አካውንቶች አሉን፡፡ ባለሥልጣኑ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር ተነጋግሮ የሚበቃውን ያህል ገንዘብ ማገድ ሲችል፣ ሁሉንም አካውንታችንን አግዷል፡፡ ይህ ፍጹም ሕገወጥ ተግባር ነው፤” ሲሉ ባለሀብቱ አስረድተዋል፡፡

      ከዚህ በተጨማሪም የባለሥልጣኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የጠየቀው ገንዘብ ገና ስምምነት ላይ ያልተደረሰበትና በክርክር ሒደት ላይ የሚገኝ ሆኖ እያለ፣ ወደ አጠቃላይ ዕገዳ መሄዱ ከሥራ ውጪ ያደረጋቸው መሆኑን ባለሀብቶቹ ገልጸዋል፡፡

      በዚህ ጉዳይ ላይ የሞጆ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች