- በጂቡቲ በኩል ያለው የመንገድ ብልሽት የከባድ ተሽከርከሪ ባለንብረቶችን አስመርሯል
- የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ እንዲሚደረግ ይጠበቃል
የዘጠኝ ወራት የዘርፉን አፈጻጸም ለመምከር የትራንስፖርት ሚኒስቴር በጠራው ስብሰባ ላይ የግል አቪዬሽን ኦፕሬተሮች ያደረባቸውን ቅሬታ አሰሙ፡፡ አውሮፕላኖች በሚንቀሳቀሱበት ወይም በምድረ አየር ክልል (በበረራ መነሻና ማረፊያ) ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች፣ የአሥር ሚሊዮን ዶላር የመድን ሽፋን ግቡ መባላቸውን ተቃውመዋል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታዎች በቀረበው ቅሬታ ላይ እንደሚነጋገሩበት አስታውቀዋል፡፡
በግላቸው የአቪዬሽን አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ ባለሙያዎችና ግለሰቦች መካከል አንዱ መሆናቸውና ለ39 ዓመታት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ባልደረባነት ማገልገላቸውን የጠቀሱት ካፒቴን ሙላት ለምለምአየሁ፣ ቅሬታቸውን ካሰሙ የዘርፉ ተዋንያን መካከል አንዱ ናቸው፡፡ እንደ ካፒቴን ሙላት ከሆነ መንግሥት መደበኛ ባልሆነው የአቪዬሽን አገልግሎት ወይም ጄኔራል አቪዬሽን እየተባለ በሚጠራው ዘርፍ ውስጥ ያለው ግንዛቤ ደካማ ነው፡፡ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ጠቀሜታውን ያገዘናበ አሠራር የለም ያሉት ካፒቴን ሙላት፣ የኢትዮጵያ የአየር መንገድ በማይደርስባቸው 20 ቦታዎች በመብረር በተለይ በተፈጥሮ ጋዝና በነዳጅ ፍለጋ ቦታዎች፣ በወርቅ ማውጫ አካባቢዎችና በሌሎችም የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በመንግሥት ትኩረት ማጣቱ ሳያንስ፣ ‹‹ለአንድ መኪና አሥር ሚሊዮን ዶላር መድን ገብታችሁ ካልሆነ ተብለናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሕግ አንድ ኢትዮጵያዊ በሌላ ኢትዮጵያዊ ላይ ያወጣው ሕግ ነው ብሎ መቀበል ከባድ ነው፤›› በማለት ኮንነውታል፡፡ ካፒቴን ሙላት በቻይና ለመድን 3,000 ዩዋን ወይም 377 ዶላር በዓመት እንደሚከፈል በመጥቀስ፣ ለመድን ሽፋን የተጠየቀው ገንዘብ የተጋነነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ባቋቋሙት የአየር አምቡላንስ መስክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያደርጉት እንቅስቃሴም ድጋፍ እያገኘ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ሳያበቃም ለጄኔራል አቪዬሽን አገልግሎት የሚያግዙ የቢሮ መሰል አቅርቦቶች ባይኖሩም በራሳቸው የኮንቴይነር ቢሮ ሠርተው ሲጠቀሙም፣ ‹‹ከከተማ ዋጋ ያነሰ ስለምትከፍሉ ተብለን የ3,500 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎብናል፤›› በማለት ካፒቴኑ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
የኢቢሲንያ አቪዬሽን አካዴሚና የበረራ አገልግሎት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካፒቴን አማረ ገብረሃና በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም 2,000 ብር ይከፈልበት የነበረውን የኪራይ አገልግሎት ወደ 8,500 ብር እንዲጨምር ሲደረግም ሆነ ተቋማቱ ለመድን ሽፋን አሥር ሚሊዮን ዶላር ዋስትና ግቡ መባላቸውን ትራንስፖርት ሚኒስቴር ያውቃል ወይ በማለት ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ይህ የሆነው በትራንስፖርት ሚኒስቴር ፀድቆ ነው? ፀድቆ ከሆነ ብዙ ጥያቄ ያስነሳል፤›› ብለዋል፡፡ ካፒቴን አማረ የካፒቴን ሙላትን ሐሳብ አጠናክረው፣ መንግሥት የጄኔራል አቪዬሽን ዘርፉን በሚገባ አላወቀውም ለማለት የበቁበትን ምክንያቶች አሰምተዋል፡፡
በዚህ አገልግሎት የሚስተናገዱ መንገደኞች ለጊዜ ትኩረት የሚሰጡ ባለሀብቶችና ቱሪስቶች በመሆናቸውና በመጡበት ፍጥነት ጉዳያቸውን ጨራርሰው በዚያው ቀን ወደመጡበት መመለስ የሚፈልጉ በመሆናቸው፣ የጄኔራል አቪዬሽንን አገልግሎት ሲፈልጉም የበረራ ተቆጣጣሪዎች ግን ከሁለትና ከሦስት ሰዓታት ጥበቃ በኋላ ለአውሮፕላኖቻቸው የበረራ ፈቃድ የሚሰጧቸው በመሆኑ የአገልግሎቱ ጽንሰ ሐሳብ እየተፋለሰ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ የአውሮፕላን ሞተር ውጭ ለማስጠገን ሲልኩም የተቀናሽ ወይም ዊዝሆልዲንግ ታክስ ቁረጡ እየተባሉ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡
እንዲህ ያሉ ቅሬታዎችን፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አብዲሳ ያደታና በቅርቡ ሚኒስቴሩን የተቀላቀሉት ሌላው ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በመሩት መድረክ ወቅት ምላሽ ከሰጡት የየዘርፉ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ፣ የኤርፖርቶች ድርጅትን በመወከል ምላሽ ለመስጠት የሞከሩ ኃላፊ በሚኒስትር ዴኤታዎቹ ተተችተዋል፡፡ ‹‹እንዲህ ያለው ጉዳይ በሕዝብ ስብሰባ ወቅት የሚነሳ አልነበረም፡፡ ምላሾቹም በቂ አይደሉም፤›› ያሉት አቶ አብዲሳ፣ ምላሽ ለመስጠት የሞከሩት መካከለኛ አመራሮችና ባለሙያዎች በመሆናቸው፣ አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጥበት ሌላ መድረክ እንደሚኖር አስታውቀዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የመጡ ተወካይ የወጣው የመድን ዋጋ የኤርፖርቶችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሲባል የወጣና ዓለም አቀፍ አሠራር እንደተከተለ አስታውቀው፣ ገንዘቡ በዝቷል ከተባለ መነጋገር እንደሚቻልና ሌሎችም አማራጮች እንዳሉ፣ የቢሮና የቦታ ኪራይም ለብዙ ጊዜ ሳይሻሻል እንደቆየና አሁን የተደረገው ማሻሻያም ከከተማው ዋጋ አኳያ እንደሚታይ ለማብራራት ሞክረው ነበር፡፡ በአቪዬሽን ዘርፉ ላይ የታዩት ችግሮች በጽሑፍ ለመንግሥት ቀርበው ምላሽ እንዲሰጥባቸው አቶ አብዲሳ ሐሳብ ጠይቀዋል፡፡
ከአቪዬሽን ዘርፉ ባሻገር የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎችም በርካታ ቅሬታዎችን አሰምተዋል፡፡ በተለይም በጂቡቲ በኩል የሚገኘው መንገድ ባለመሠራቱ መኪኖቻቸው ለብልሽትና ለከፍተኛ የመለዋወጫ ወጪ እየተዳረጉ እንደሚገኙ ደጋግመው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ በጂቡቲ ድንበር ውስጥ አደጋ የሚደርስባቸው የኢትዮጵያ ተሽከርካሪዎች በወቅቱ እንደማይነሱና የክሬን አገልግሎት ችግሮች እንደሚታዩ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
የድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት ማኅበራት ተወካዮች ሲገልጹ እንደተደመጠው፣ አሁን ያለው ታሪፍ የአንድ የከባድ መኪና ጎማ 6000 ብር በነበረበትና የነዳጅ ዋጋም በሊትር 12 ብር በነበረበት ወቅት የወጣ ነው፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ለአንድ የቻይና ጎማ 13,000 ብር እንደሚከፈል፣ የነዳጅ ዋጋም ከ17 ብር በላይ እንደሆነ በመጥቀስ መንግሥት ታሪፍ እንዲያሻሽል ጠይቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የሥራ መቀዛቀዝ በመኖሩ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በወር አንድ ጊዜ እንኳ ወደ ጂቡቲ መሄድ ስላልተቻለ ሠራተኞችን ማሰናበት እንደጀመሩ የገለጹ ተወካዮች፣ የጭነት መኪኖች መቆሚያ መናኸሪያ እንዲገነባ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ተደጋግመው የተስጋቡ ነበሩ፡፡
በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አመራር ወቅት መንግሥት በጂቡቲ በኩል ያልተገነባውን የ100 ኪሎ ሜትር መንገድ በራሱ ወጪ ለመገንባት ፍላጎት እንደነበረውና ጥያቄ እንዳቀረበ ያስታወሱት አቶ አብዲሳ፣ መንገዱ ሊጠገን ወይም ሊገነባ የሚችልበት ዲፕሎማሲያዊ መግባባት እንደተደረገ ገልጸዋል፡፡ በትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የቀረበው የታሪፍ ይሻሻል ጥያቄ በመንግሥት መታየቱንና ለውሳኔ እንደሚቀርብ አቶ አብዲሳም ሆኑ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ አብዛኞቹ በዘርፉ ተዋናዮች የተነሱ ጥያቄዎች እስከ መጪው ሰኔ ወር ማብቂያ ድረስ ምላሽ እንደሚያገኙ አቶ አብዲሳ አስታውቀዋል፡፡