Saturday, September 23, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በውጭ ምንዛሪ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮች ይወገዱ!

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከመቼውም ጊዜ በላይ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል፡፡ ለዓመታት ነዳጅ ከሌላቸው አገሮች በላቀ ሁኔታ ዕድገት እያስመዘገበ የመጣው ኢኮኖሚ፣ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከባድ ችግር ገጥሞታል፡፡ ለኢኮኖሚው መቀዛቀዝና መዳከም በዋነኛነት ከሚነሱ ችግሮች መካከል አንዱ ሥር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ የአገሪቱ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ኤክስፖርት፣ ሐዋላ፣ ብድርና ዕርዳታ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትና ከፕራይቬታይዜሽን የሚገኙ ገቢዎች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉም ድርሻ አለው፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው በዓመት አገሪቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ አገር ውስጥ ከሚገቡ የውጭ ምርቶች ወጪ ጋር ሲነፃፀር፣ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ነዳጅን ጨምሮ በርካታ የኢንዱስትሪ ውጤቶች ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ከፍተኛ የሆነ የንግድ ሚዛን መዛባት ተፈጥሯል፡፡ ለአገሪቱ የጀርባ አጥንት መሆን የሚገባው ኤክስፖርት አፈጻጸም በጣም በመዳከሙና የገቢ ንግድ ፍላጎት ደግሞ በጣም በመለጠጡ፣ አገሪቱ ለውጭ ምንዛሪ ጠኔ ተጋልጣለች፡፡ የውጭ ምንዛሪ አያያዝና አጠቃቀሙ ደግሞ ከፍተኛ እርምት ይፈልጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ምን ያህል እንደሆነ አለመታወቁ የችግሩን ግዝፈት ያመለክታል፡፡ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ከፊታችን አደጋ ይጠብቀናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለተወከሉ ተሳታፊዎች በሚሊኒየም አዳራሽ ባደረጉት ንግግር፣ የአገሪቱን ሰላም ይበልጥ በማረጋገጥ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት መንግሥት እንደሚተጋ ተናግረው፣ ለውጭ ምንዛሪ ብክነት ምክንያት እየሆኑ ባሉ ግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ ክትትል በማድረግ ችግሮችን ለመቅረፍ ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡ ከንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ጋር በሸራተን አዲስ ሲወያዩ ባደረጉት ንግግር ደግሞ፣ ለውጭ ምንዛሪ ብክነት የሚዳርጉ አሠራሮችን ለማሻሻል እንደሚሠሩና የውጭ ምንዛሪ በሚያሸሹ አካላት ላይ ጠንካራ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ ያሸሹ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትም እንዲመልሱ ጠይቀዋል፡፡ አገሪቱ በካፒታል ፍልሰት ምክንያት ከፍተኛ ሀብት እንደሚባክንባት ይታወቃል፡፡ በአንዳንድ ሪፖርቶች በዓመት በአማካይ 3.4 ቢሊዮን ዶላር በሕገወጥ መንገድ እንደሚፈልስባት ተመልክቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለፉት 40 ዓመታት 25 ቢሊዮን ዶላር እንደፈለሰባት ይነገራል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ ባጋጠሙ ሁከቶች ምክንያት በፋብሪካዎችና በእርሻዎች ላይ ጉዳት በመድረሱ ኢንቨስተሮች መተማመኛ በማጣታቸው፣ ከፍተኛ የካፒታል ፍልሰት እንዳጋጠመ ይታወቃል፡፡ የአገሪቱ ጥቁር ገበያዎችም ለዚህ ፍልሰት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው ካሳ ባለማግኘታቸው ወይም ማካካሻ ባለመደረጉ ተስፋ መቁረጣቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ መንግሥት የንግዱን ማኅበረሰብ በራስ የመተማመን ስሜት በፍጥነት ማሳደግ ካልቻለ ችግሩ በስፋት መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ ብልሹና ኢፍትሐዊ አሠራሮች መወገድ አለባቸው፡፡

በግብርና ምርቶች ላይ የተንጠለጠለው የኤክስፖርት ገቢ በፍጥነት በኢንዱስትሪ ምርቶች ካልተቀየረ የውጭ ምንዛሪ ረሃቡ ተባብሶ ይቀጥላል፡፡ መንግሥት በቅድሚያ ዕድሜ ያስቆጠሩ ፖሊሲዎቹን ሊፈትሽ ይገባል፡፡ ላለፉት 26 ዓመታት ተግባራዊ የሆኑ ፖሊሲዎች አሁን ከተፈጠረው ፍላጎትና አስቸጋሪ ሁኔታ አንፃር ሊቃኙ የግድ ይላል፡፡ በደካማ አፈጻጸም እየተመካኘ መቀጠል አይቻልም፡፡ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነፃ ገበያ ነው እየተባለ የመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ሲሄዱ ተቃርኖ ይፈጠራል፡፡ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ሞተር መሆን የሚገባው የንግዱ ክፍለ ኢኮኖሚ በብዛት ወደ አምራችነት ተሸጋግሮ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት ካልተቻለ፣ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በስፋት እያመረተ ኤክስፖርት ማድረግ ካቃተ፣ ከውጭ ምንዛሪ ችግር መቼም መላቀቅ አይቻልም፡፡ ይኼ ይሆን ዘንድ ደግሞ በአምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚያሠራ ፖሊሲና ስትራቴጂ ማውጣት፣ በፋይናንስ አቅርቦት መደገፍ፣ ጤናማ የውድድር ሜዳ ማመቻቸት፣ የቢሮክራሲ ውጣ ውረዱን ማስወገድ፣ ተገቢውን ዋስትና በመስጠት በራስ የመተማመን መንፈሳቸውን ማጎልበት የግድ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት 15 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ይነገራል፡፡ ነገር ግን አሁን እየተገኘ ባለው 6.4 ቢሊዮን ዶላር የት መድረስ ይቻላል? ይህ የንግድ ሚዛን ጉድለት የችግሩን መጠነ ሰፊነት ያሳያል፡፡

አገሪቱ ስንዴ፣ ስኳር፣ ዘይትና የመሳሰሉ ምርቶችን ከውጭ ማስገባቷ ከፍተኛ ጉዳት ነው፡፡ ሰፊ ለም መሬት፣ ውኃና ከምንም ነገር በላይ ሠራተኛ ሕዝብ ያላት አገር ስንዴ ስትሸምት ወይም ስትመፀወት እንደማየት የሚያሳፍር ነገር አለ? ስንዴ አምርታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ባለመቻሏ የግብርና ፖሊሲዋ መፈተሽ የለበትም? በአንድ ጊዜ አሥር የስኳር ፕሮጀክቶችን ዘርግቶ ግራ ከመጋባት እነ ተንዳሆን በወጉ አንቀሳቅሶ፣ በላያቸው ላይ አንድ ሁለት ፋብሪካዎችን እየገነቡ በሥርዓት መሥራት ቢቻል ኖሮ የአገር ሀብት አይባክንም ነበር፡፡ ቢያንስ ከነባሮቹና ከሚጨመሩት ፋብሪካዎች ከአገር ውስጥ ፍጆታ በላይ አምርቶ ኤክስፖርት ማድረግም ይቻል ነበር፡፡ በአንዴ ዘጠኝ ድስት ጥዶ አንዱንም ማማሰል ያልተቻለ የሚመስለው በስኳር ዘርፍ የታየው ውድቀት ያንገበግባል፡፡ የባከነው የውጭ ምንዛሪ ደግሞ የዕቅድና የአፈጻጸም ብቻ ሳይሆን ብልሹ አሠራርንም ያሳያል፡፡ ይህም አፋጣኝ መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ ዘይት ከውጭ እያስገቡ መቀጠልም እንቆቅልሽ ነው፡፡ ሰፊ ለም መሬትና የውኃ ሀብት ባለባት አገር የምግብ ምርቶችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገባት ያሳፍራል፡፡ ይኼ ሁሉ ችግር የአፈጻጸም ብቻ ሳይሆን የፖሊሲ ጭምር መሆኑን በመገንዘብ ለመጠነ ሰፊ ማስተካከያ መዘጋጀት ይገባል፡፡ በአገር ውስጥ መመረት ሲገባቸው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች መብዛት ለሥራ ፈጣሪዎችና ለፈጠራ ሰዎች ትኩረት አለመስጠት ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡ አሁንም አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ ምርቶች እንዲተኩ አስፈላጊው ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት ነው፡፡ ለዚህም የዘርፉ ተዋንያንና ባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ ይደመጥ፡፡ ከተሠራ ከራሷ አልፋ ለሌሎች የምትተርፍ አገርን በማያሠሩ ፖሊሲዎችና ብቃት በሌላቸው ሰዎች መበደል የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡

በውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ የሚስተዋለው ኢፍትሐዊ ድርጊት ሌላው የትኩረት አቅጣጫ መሆን አለበት፡፡ ሕይወት ለማዳን እጅግ በጣም መሠረታዊ የሚባሉ መድኃኒቶች እጥረት ተፈጥሯል፡፡ ከገበያ የጠፉም አሉ፡፡ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ኩባንያዎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ እየተዘጉ ነው፡፡ በጣም አንገብጋቢ የሚባሉ ምርቶች ከገበያ ውስጥ እየጠፉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለአስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ በቅደም ተከተል የሚሰጡበት መመርያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ይህ አሠራር አንገብጋቢ ለሆኑ ምርቶች ቅድሚያ የሚሰጥ ቢሆንም፣ በተለይ የመንግሥት ፕሮጀክቶች የቅድሚያ ቅድሚያ የሚያገኙ በመሆናቸው ችግሩ ተለጥጧል፡፡ በዚህ ላይ ‹‹ልዩ ተጠቃሚ›› የሆኑ ደግሞ ችግሩ የበለጠ እንዲገዝፍ አድርገዋል፡፡ ኢፍትሐዊነት እንዲንሠራፋ ምክንያት ሆነዋል፡፡ አምራቾች ለጥሬ ዕቃ አቅርቦት የውጭ ምንዛሪ አጥተው ‹‹ልዩ ተጠቃሚዎች›› ግን እዚህ ግባ ለማይባሉ ነገሮች ይንበሻበሻሉ፡፡  በዚህ መሀል በርካታ ሠራተኞችን ቀጥረው የሚያሠሩ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ለኪሳራ እየተዳረጉ ነው፡፡ ብዙዎቹ በኪሳራ እየሠሩ ደመወዝ እየከፈሉ ነው፡፡ ከአቅማቸው በላይ ሲሆን ግን በመጨረሻ ይዘጉና ሠራተኞችን ይበትናሉ፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚም በእንብርክክ ከመሄድ አልፎ በአፍ ጢሙ ይደፋና የአገር ሰላም ይደፈርሳል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ አደጋ እስከዚህ ድረስ ነው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

በውጭ ምንዛሪ ዕጦት ምክንያት አደጋ ውስጥ የገቡ አምራቾችን መታደግ ይገባል፡፡ ጉዳት የደረሳባቸውን በብድር አቅርቦትና በተለያዩ ድጋፎች ማበረታታት ይጠቅማል፡፡ ኢፍትሐዊ የሆነ የውጭ ምንዛሪ አሰጣጡን በፍጥነት ማስቆም ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡ በገቢና በወጪ ንግዱ ውስጥ የሚታዩ ለብክነት የሚዳርጉና  በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ብልሹ አሠራሮች፣ እንዲሁም ብቃት አልባነት መወገድ አለባቸው፡፡ የውጭ ምንዛሪ አያያዝና አጠቃቀም ደካማነት፣ ከባንኮች ውጪ የሚደረገው የውጭ ምንዛሪ ዝውውር መብዛት፣ ከአገር በሕገወጥ መንገድ የሚፈልሰው የውጭ ምንዛሪ ብዛት አስፈሪነት፣ በሐዋላ መገኘት የሚገባው የውጭ ምንዛሪ የጥቁር ገበያ ሰለባ መሆኑ፣ በኤክስፖርት ላይ የሚታየው አሳሳቢ የአፈጻጸም ድክመት፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት፣ ወዘተ በእጅጉ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት የኢንቨስተሮችና የንግድ ማኅበረሰቡ አባላት በራስ መተማመናቸው መጥፋቱ ለካፒታል ፍልሰት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በሁከቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ተመጣጣኝ ካሳ ወይም በቂ ማካካሻ አለመሰጠቱ የራሱን አሉታዊ ሚና ተጫውቷል፡፡ በውጭ ምንዛሪ አያያዝና አጠቃቀም ላይ የታዩ ብልሹና ኢፍትሐዊ አሠራሮችና በመንግሥት ውስጥ የሚስተዋሉ አደናቃፊ ተግባራት መሠረታዊ ለውጥ ይሻሉ፡፡ በገቢ ንግድ ላይ ጥገኛ የሆነ ኢኮኖሚ የትም መድረስ ስለማይችል ለኤክስፖርት ትልቅ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ ብድርና ዕርዳታ አያዛልቁም፡፡ በውጭ ምንዛሪ ላይ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮች ደግሞ ከሥር መሠረታቸው ይወገዱ!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...