Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኮማንድ ፖስቱ ታስረው የነበሩ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ ምክትል አዛዥና የፍትሕ ቢሮ ቃል...

በኮማንድ ፖስቱ ታስረው የነበሩ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ ምክትል አዛዥና የፍትሕ ቢሮ ቃል አቀባይ ተፈቱ

ቀን:

የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ተግባራዊ መሆን የሚገባቸውን ድንጋጌዎች ተላልፈዋል ተብለው በኮማንድ ፖስቱ ታስረው የከረሙት፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ አድማ በታኝ ፖሊስ ምክትል አዛዥ፣ የፍትሕ ቢሮ ኮሙዩኒኬሽን  ኃላፊና የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር ከእስር ተፈቱ፡፡

በኮማንድ ፖስቱ ተጠርጥረው ላለፉት 39 ቀናት በእስር ላይ የከረሙት ምክትል አዛዡ ኮማንደር ኢሳያስ አንጋሱ፣ የፍትሕ ቢሮ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ፣ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ መምህርና ጦማሪ ሥዩም ተሾመ ናቸው፡፡ የኦሮሚያ ክልል ልዩ አድማ በታኝ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ኮማንደር ኢሳያስ ለእስር የተዳረጉት፣ ከሶማሌ ልዩ ፖሊስ ጋር ያጋጠመውን ግጭት መልካም በሆነ መንገድ ለመፍታት ጥረት ባለማድረግና ከፌዴራል ፖሊሶችም ጋር በስምምነት ለመሥራት ፈቃደኝነታቸውን አላሳዩም ተብለው መሆኑን፣ ሪፖርተር ካገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኮማንደሩ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲሆን፣ በዕለቱ በሐረር የነበሩ ተፈናቃዮችን ወደ ተዘጋጀላቸው መጠለያ ለመውሰድ በሄዱበት ወቅት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኃላ ወደ አዲስ አበባ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ተወስደው ከቆዩ በኋላ፣ ማዕከላዊ ሲዘጋ በትውስት ለጊዜው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እስረኛ ማቆያ ውስጥ እንዳሉ፣ ሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ከእስር መፈታታቸው ተረጋግጧል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኦሮሚያ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ የታሰሩት፣ በሞያሌ ከተማ በመከላከያ ሠራዊት አባላት መጋቢት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ስለተገደሉ ወገኖች በሰጡት መግለጫ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል፡፡ አቶ ታዬ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ፣ በሞያሌ ነዋሪዎች ላይ የተፈጸመው ግድያ ሆን ተብሎና በፌዴራል መንግሥት የተፈጸመ መሆኑን በመናገራቸው መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ አቶ ታዬ ሕዝብንና መንግሥትን ሆን ብለው ለማጋጨት ያልተጣራ መረጃ  በማሠራጨትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌ ተላልፈዋል ተብለው ታስረው ከርመዋል፡፡ እሳቸውም ሚያዝያ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ከእስር ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል፡፡

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ካምፓስ መምህርና ጦማሪ ሥዩም ተሾመ፣ የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው በእስር ላይ ቆይተዋል፡፡ ‹‹የጦር መሣሪያ ቤትህ ውስጥ ሸሽገሃል፤›› ተብለው ቤታቸው በመከላከያ ሠራዊት ተከቦ መያዛቸውን የገለጹት መምህር ሥዩም፣ ቤታቸው ከተፈተሸና ምንም ዓይነት መሣሪያ እንደሌለ ሲረጋገጥ የተጠረጠሩበት ጉዳይ ወደ ሌላ መቀየሩን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹የጦር መሣሪያው ሲጠፋ መንግሥትንና ሕዝብን የሚጋጭ መጣጥፍ በማዘጋጀት ሁከት እየፈጠርክ ነው፤›› ተብለው መጀመርያ ሰበታ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ካምፕ መወሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡

በመቀጠልም ወደ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ተወስደው መታሰራቸውን የገለጹት መምህር ሥዩም፣ የካቲት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት እንደቀረቡ ጠቁመዋል፡፡ በወንጀል መጠርጠራቸውንና ቀሪ ምርመራ እንዳለባቸው መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሲጠይቅ እንደተፈቀደለትም አክለዋል፡፡ በቀጣይ ቀጠሮ ግን እሳቸው ሳይቀርቡ መርማሪው ፍርድ ቤት ቀርቦ ተጠርጣሪው የታሰሩት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌ ተላልፈው በመሆኑ፣ ጉዳዩ የሚታየው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት በሚቋቋመው ፍርድ ቤት እንደሆነ አስረድቶ መዝገቡን ማዘጋቱን መምህር ሥዩም ገልጸዋል፡፡

ከመጋቢት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በኋላ በማዕከላዊ ታስረው መክረማቸውንና አልፎ አልፎ ዘለፋና ማስፈራራቶች ቢደርስባቸውም አካላዊ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻ ሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ከኮማንድ ፖስቱ የተላከ ደብዳቤ መጥቷል ተብሎ በአደራ ከታሰሩበት አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እስረኛ ማቆያ ቦታ ተጠርተው (ማዕከላዊ በመዘጋቱ)፣ በምርመራ ወቅት የሰጡትን ቃል ‹‹ፈጽመሃል? አልፈጸምክም?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ‹‹አልፈጸምኩም፤›› በማለት መለቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡

መርማሪው ጥያቄ ያቀረበው ‹‹እኛ ጋ ነበር›› ለማለትና ለፎርማሊቲ እንጂ የተፈቱት በፖለቲካ ውሳኔ መሠረት መሆኑን አክለዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...