Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች ለሁለት ሰዓታት ተቋረጡ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች ለሁለት ሰዓታት ተቋረጡ

ቀን:

ማክሰኞ ሚያዚያ 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠዋት በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና በአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሠራተኞች መካከል ተፈጥሮ በነበረ አለመግባባት፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡም ሆነ ከአገር የሚወጡ በረራዎች ለሁለት ሰዓታት ያህል ተቋርጠው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ወ/ሮ አንለይ እሸቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት ለበረራው መቋረጥ ምክንያት የሆነው ደግሞ፣ በሲቪል አቪዬሽን አስተዳደርና በሠራተኞች መካከል በተከሰተ ውስጣዊ አለመግባባት ነው፡፡

በሠራተኞቹና በአስተዳደሩ መካከል አለመግባባት የፈጠሩ ምክንያቶችን እንዲያስረዱ የተጠየቁት ወ/ሮ አንለይ፣ ‹‹ይኼ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን አስተዳደርና የሠራተኞች የውስጥ ጉዳይ ስለሆነ የተሟላ መልስ ከእነርሱ ማግኘት ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡ ምንም እንኳን በሠራተኞችና በአስተዳደሩ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት በረራዎች ተቋርጠው የነበረ ቢሆንም፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ተከስቶ የነበረው የበረራ መዘግየት ሙሉ በሙሉ ተቀርፎ፣ በረራዎች በመግባትና በመውጣት ወደ ተለመደው የዘወትር ተግባራቸው ተመልሰዋል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

 የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የሥራ ኃላፊዎችን ለማግኘት የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ሊሳካ አልቻለም፡፡

ሆኖም የኤርፖርት ኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ንጉሤ ሙሉጌታ በሰጡት መግለጫ፣ የበረራ ሠራተኞች ተቃውሟቸውን ማሰማት የጀመሩት ከሰኞ ዕለት ጀምሮ እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቧል፡፡

በዚህም ሳቢያ ዓለም አቀፍ በረራዎች ሙሉ በሙሉ መቋረጣቸውን ለኢቢሲ ገልጸው ነበር፡፡ የበረራ ተቆጣጣሪ ሠራተኞች የሚያቀርቡት ጥያቄ ከበዓል ቀናት አበል ክፍያና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዙ መሆናቸውን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ለኢቢሲ ተናግረው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፍፁም ጥላሁን ማክሰኞ ዕለት የተፈጠረው የበረራ መዘግየትና መስተጓጎል ሠራተኞች አድማ በማድረጋቸው የተከሰተ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. የጻፈው ደብዳቤ የፈጠረው እንደሆነ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በቁጥር ANS 05-001/1339/10 ተጽፎ የወጣው ደብዳቤ አፕሮች የሚባለው የሥራ መደብ መታጠፉን ይገልጻል ያሉት አቶ ፍፁም፣ በዚህ የተነሳ የበረራዎች መስተጓጎል ማጋጠሙን ጠቁመዋል፡፡

‹‹የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሠራተኞች ለሚሠሩት ሥራ በቂ ክፍያ አይፈጽምላቸውም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የሥራ ጥያቄና ጫና አለባቸው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሀል ከገንዘብ ሚኒስቴር መጣ በተባለ ደብዳቤ መሠረት የበዓል ዕለት የሥራ ላይ ክፍያ እንደማይፈጸም እንደተገለጸላቸው፣ ይህም በሠራተኞችና በማኔጅመንቱ መክፈል ውዝግብ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ‘አፕሮች’ የተሰኘውን የሥራ መደብን የማጠፍ ውሳኔ ምንም ዓይነት ሙያዊ መሠረት የሌለው በመሆኑ ችግሩን በማባባስ ሙያተኛውን አላስፈላጊ ጫና ውስጥ በማስገባት፣ ኢንዱስትሪውን ለከፍተኛ የአደጋ ሥጋት ሊያጋልጥ እንደሚችል፣ ስለሆነም የሚመለከተው አካል ችግሩን በሰከነና ሙያን መሠረት በማድረግ በጥልቀት በመመርመር የመፍትሔ አቅጣጫና የማስተካከያ ሥራ እንዲከናወን ማኅበሩ እንደሚያሳስብ አቶ ፍፁም ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...