የአገሪቱ ከፍተኛ ችግር እየሆነ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማርገብ መንግሥት ከሚወስዳቸው ዕርምጃዎች በተጨማሪ፣ ባለሀብቶችም በዱባይና በቻይና ያከማቹትን እንዲመልሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የንግድ ኅብረተሰቡን አሳሰቡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት ለመጀመርያ ጊዜ ከንግድ ኅብረተሰቡ ጋር ሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ተገናኝተው፣ ከሁለት ሰዓት ተኩል የፈጀ ቆይታ ባደረጉበት የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡ በዚህ የምክክር መድረክ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትና ከሌሎች ተሳታፊዎች ከቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን የተመለከቱ ጉዳዮች ጎልተዋል፡፡ በዕለቱ ጥያቄ ለመጠየቅና አስተያየት ለመስጠት ዕድል ካገኙት ውስጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የፈጠረባቸውን ችግር በተለያዩ መንገዶች የገለጹ ሲሆን፣ በተለይ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ ቢሠራም ሊሳካ አለመቻሉን በማስታወስ፣ ችግሩ ፋብሪካዎችን እስከማቆም የደረሰና ኢንሱሊን ለመግዛት እንኳን ያላስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አነስተኛ መለዋወጫዎች እንኳን ለማስመጣት የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ ባንኮች ያለወረፋ ለመስጠት የብሔራዊ ባንክ ሕግ እንደሚከለክላቸው፣ በአንፃሩ የውጭ ባለሀብቶች የሚያስተዳድሯቸው የማምረቻ ድርጅቶች ከውጭ በፍራንኮ ቫሉታ ማስመጣት ስለሚችሉ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከውድድር ውጪ ያደርጋሉ በማለትም ችግሩን አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሁሉም የውጭ ምንዛሪ ግኝት የሚሰበሰበው ከ6.4 ቢሊዮን ዶላር እንደማይበልጥ ጠቁመው፣ አገሪቱ የምትፈልገው የውጭ ምንዛሪ መጠን ደግሞ 15 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን በማስታወስ በአቅምና በፍላጎት መካከል ያለውን ልዩነት አመላክተዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ችግር በአንድ በብሔራዊ ባንክ መመርያ የመጣ አለመሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ኮንትሮባንድ፣ የጥቁር ገበያና የመሳሰሉት ለችግሩ እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡
‹‹አሁን የውጭ ምንዛሪ ችግር አለ ብቻ ሳይሆን ብዙዎቻችሁን መጠየቅ የምፈልገው ዱባይና ቻይና ያስቀመጣችሁትን እንድትመልሱ ነው፤›› በማለት ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹እንደ መንግሥት ሳይሆን እንደ አገር ችግር አለብን፤›› ያሉት ዶ/ር ዓብይ፣ ‹‹በዚህ ረገድ ባለሀብቱ አሁን እንዲያግዘን እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ለምድነው እንዲህ የምትለን የምትሉኝ ከሆነ እናት ስትታመም ስትቸገር ጎንዋ መሆን ያልቻለ፣ ስትሞት ለመቅበር የሚመጣ ዋጋ የለውም፤›› በማለት የሁኔታውን አሳሳቢነት አስረድተዋል፡፡
‹‹በውጭ ምንዛሪ ረገድ መንግሥት የሚያመጣውን እንደሚያመጣና የንግድ ኅብረተሰቡ ግን ከዘመድም ከአዝማድም፣ ከተቀመጠውም በከፍተኛ ደረጃ እንድትመልሱ፤›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ ‹‹እንድትመልሱ ስል ያው ይገባችኋል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ መደረግ ካልቻለ አሁን ባለው ሁኔታ ችግሩ በቀላሉ እንደማይፈታ አሳስበዋል፡፡ በዕለቱ ከንግድ ኅብረተሰቡ ጋር መገናኘት ያስፈለገውም ‹‹ችግር ውስጥ ነው ያለነው አግዙን›› ለማለት እንደሆነም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ብሩን ስጡን ሳይሆን መልሱት! አሁን ካገዛችሁን ያኔ አግዘን ነበር ብላችሁ ደግሞ አንድ ቀን ትጠይቃላችሁ፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹እናንተ ችግር ሲሆን ጠይቃችሁ እኛ ስንቸገር አለን የማትሉን ከሆነ ይኼ መልካም ጉርብትናም አይደለም፤›› በማለት በውጭ አለ ያሉት ሀብት እንዲመለስ ጠይቀዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አሁን እየተሰማ ባለው ሮሮ ብቻ ችግሩ እንደማይፈታ አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ችግር በመረባረብ የማይፈታ ከሆነ አደገኛ እንደሚሆን የተሰጠውን አስተያየት እንደሚጋሩ አስታውቀዋል፡፡ መንግሥት ይህንን ችግር ለመፍታት የሚወስዳቸውን ዕርምጃዎች ሥራ ላይ ካዋለ በኋላ ቢገልጽ ይሻላል በማለት፣ መንግሥት ችግሩን ይፈቱልኛል ብሎ ያመነባቸውን ዕርምጃዎች እንደሚተገብር አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ረገድ ሊስተካከል ይገባል ብለው የጠቆሙት ጥቁር ገበያን ነው፡፡ ይህንንም፣ ‹‹የብላክ ማርኬት መናኸሪያ እዚህ ኢትዮጵያ ሆቴል ጀርባ መሆኑን እያወቅን ዝም ብለን ያየንበት መንገድ ይቀየራል፤›› ብለዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የኮንትሮባንድ ማከማቻዎች ጉዳይም ለውጥ ይደረግባቸዋል ከተባሉት ዋነኛ ጉዳዮች መካከል የተጠቀሰ ሲሆን፣ ነገር እንዲህ ባሉ የለውጥ ሒደቶች ላይ የመንግሥት ጥረት ብቻ ሙሉ ስለማይሆን የንግዱ ኅብረተሰብ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አሁን አገሪቱ ያለችበትን የውጭ ምንዛሪ ችግር አስመልክቶ ከንግድ ምክር ቤቱ የቀረበውን ጥያቄ በማስታወስም፣ ንግድ ምክር ቤቱ ሊተገብር ይገባዋል ያሉትንም ጠቁመዋል፡፡
ለንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት በሰጡት ማሳሰቢያም ንግድ ምክር ቤቱ የሚጠይቅበት፣ እያንዳንዱን ሰው በማወያየት የተከማቸውን የውጭ ምንዛሪ እንዲመለስ ማድረግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዱባይና በቻይና ከፍተኛ ክምችት ያለው የውጭ ምንዛሪና ከፍተኛ ሀብት ስላላት እሱን መልሱ ብሎ ማስተማር እንደሚገባ፣ በተጠቀሱት አገሮች አለ የተባለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ወደ አገር እንዲመለስ ለንግድ ምክር ቤቱ የቤት ሥራ ሰጥተዋል፡፡
‹‹በነገራችን ላይ እንደ ቻይና ያሉ አገሮች በተለይ ባለሥልጣናት በውጭ አገር የውጭ ምንዛሪ ሲያከማቹ፣ ባላቸው ኃይል ከዚያ አገር ጋር ተደራድረው አዘግተው ይመለሳሉ፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹እኛ እዚያ ጋ አልደረስንም፡፡ ግን ደግሞ እንደርሳለን፡፡ እዚህ እየዘረፉ የሆነ ቦታ የሚከማቹ ሰዎች የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ምላሽ ያገኛሉ፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን የሚታየው የውጭ ምንዛሪ ችግር በቀጣይ 15 እና 20 ዓመታት ሊቀጥል እንደሚችል፣ ይህም የሚሆነው ፍላጎት እየጨመረ ስለሚመጣ እንደሆነ አሳስበዋል፡፡
በዚህ የምክክር መድረክ የንግድ ምክር ቤቱም ሆነ በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የባንኮች የብድር አሰጣጥ ችግር ያልተፈታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መሬት የማግኘት ችግርም አሁንም ያልተፈታ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በአገልግሎት አሰጣጦችም ቢሆን እየደረሱ ያሉት ችግሮች አልተፈቱም ብለዋል፡፡
ለእነዚህ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በዕለቱ ምላሽ ያልተሰጣቸውና መረጃ ፈልግባቸዋለሁ ያሏቸውን ጉዳዮችና በግል ደርሶብናል የተባሉ ችግሮችን ለመመልከት፣ በተለይ የመሬት ጉዳይ ንግድ ምክር ቤቱ ከከንቲባው ጋር እንዲመክሩና በአንድ ሳምንት ውስጥ ያለውን ችግር የሚያመለክት መረጃ እንዲቀርብ አዘዋል፡፡
እነዚህ ውይይቶችም ጋዜጠኞች በተገኙበት እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡ በዚህ የምክክር መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለንግዱ ማኅበረሰብ በተለየ ያስተላለፉትና ልታደርጉ ትችላላችሁ ብለው ያቀረቡት ሐሳብ ነው፡፡ ‹‹በትክክል እናንተ ዘንድ ሠርተፊኬት ያልተሰጠው ዕውቀት አለ፡፡ ይህ ዕውቀት ፖሊሲ ስናወጣና ችግር ሲገጥማችሁ ብቻ ሳይሆን፣ በየማኅበራችሁ እያጠናችሁ የፖሊሲ ሐሳብ ማቅረብ ትችላላችሁ፤›› በማለት የንግዱን ማኅበረሰብ ጠይቀዋል፡፡ እንዲህ በማድረግ የጥናቱን እውነተኝነት በማረጋገጥ እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል፡፡
የንግድ ማኅበረሰቡ በፖሊሲ ቀረፃ ላይ ተሳትፊ ማድረግ የሚቻልበት ዕድል ክፍት እንደሆነ ገልጸው፣ በዚህ የምክክር መድረክ ሰፊ ማብራሪያ የተሰጠባቸው በርካታ ጉዳዮች ስለተነሱ በአግባቡ ለመመለስ ግን የንግዱ ኅብረተሰብ እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡