Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየወልዲያ ስታዲየም ለአንድ ዓመት ውድድር እንዳያስተናግድ መታገዱን ክለቡ ተቃወመ

የወልዲያ ስታዲየም ለአንድ ዓመት ውድድር እንዳያስተናግድ መታገዱን ክለቡ ተቃወመ

ቀን:

  • አሠልጣኙና ተጫዋቾች ዕግድና የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የተመልካቾች አምባጓሮ በአብዛኞቹ ክልሎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ እየታየ ነው፡፡ በክልሎች በሚካሄዱ ውድድሮች ወቅት የተጫዋቾችንና የደጋፊዎችን ስም እየጠሩ መሳደብና ማንቋሸሽ፣ ብሽሽቁን ወደ ብሔር በመውሰድ ግጭት ማስነሳትና ድንጋይ መወራወር፣ ተጫዋቾችንና አሠልጣኞች ማስፈራራት በስታዲየሞች አካባቢ እየተለመደ መጥቷል፡፡ የአካል ላይ ጉዳት ማድረስና የንግድ ቤቶችን ማጥቃት እየተለመደ በመምጣቱ፣ ረብሻውን ለማረጋጋት አስለቃሽ ጋዝ እስከ መጠቀም ደረጃ ተደርሷል፡፡

በጨዋታዎች ወቅት የሚታዩ ግጭቶችን ተከታትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዕርምጃ ቢወስድም፣ ክለቦች ግን የሚጣለው ቅጣት ተመጣጣኝ አይደለም በማለት ቅሬታ ያሰማሉ፡፡

በቅርቡ በወልዲያና በፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለቦች መካከል በተካሄደው የ19ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ፣ በ89ኛው ደቂቃ ላይ ለፋሲል ከነማ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት በመቃወም የወልዲያ ከነማ ዋና አሠልጣኝ ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስ አልቢትሩን በማነቅና በመገፍተር፣ ተመልካቾችን ለብጥብጥ ዳርገዋል ተብሎ ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡  

- Advertisement -

በጨዋታው ወቅት የተከሰተውን የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ተከትሎ የፌደሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ በክለቡ፣ በተጨዋቾች፣ እንዲሁም በአሠልጣኙ ላይ ቅጣት ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት ለእንግዳው ፋሲል ከነማ ቡድን ሦስት ነጥብና ሦስት ጎሎች ሲሰጡት፣ የወልዲያው የሼክ መሐመድ አል አሙዲ ዘመናዊ ስታዲየም ለአንድ ዓመት ጨዋታ እንዳይካሄደበት የሚል ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡ ወልዲያ ከነማ በሜዳው የሚያከናውነውን አንድ ቀሪ ጨዋታ ከከተማዋ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ የትኛውም ስታዲየም እንዲያከናውን፣ የ250 ሺሕ ብር ቅጣት፣ የዳኛውን የሕክምና ወጪ እንዲሸፍን፣ አሠልጣኝ ዘማሪያም የአንድ ዓመት ዕገዳና የአሥር ሺሕ ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡  

የወልዲያ ከተማ አማካይ ሥፍራ ተጫዋች ብሩክ ቃልቦሬ ዳኛ ለመማታት በመቃጣቱ፣ ተጫዋቾችንና ደጋፊዎችን ለረብሻ በማነሳሳት ምክንያት ከማንኛውም እግር ኳስ ጨዋታ ለአንድ ዓመት እንዲታገድና የአሥር ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት ፌደሬሽኑ መወሰኑን አስታውቋል፡፡

በሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ወቅት በተፈጠረው ረብሻና ብጥብጥ ምክንያት በተመልካቾች ጉዳት የደረሰባቸውን ዳኞች እንዲያሳክም፣ ወደ ፊትም የሚኖረውን የሕክምና ወጪ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ድረስ በመቅረብ የወልዲያ ክለብ እንዲከፍል ተወስኖበታል፡፡

በተላለፈው ቅጣት ሳቢያ ግን በዲሲፕሊን ኮሚቴው ላይ ቅሬታ መቅረቡ አልቀረም፡፡ በተለይም በክለቡ ላይ የተጣለው ቅጣት ተመጣጣኝ እንዳልሆነና ከሌሎች ክለቦች ጥፋት ይልቅ በወልዲያ ላይ የከረረ ውሳኔ እንደተላለፈበት አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ የወልዲያ ዘመናዊ ስታዲየም ለአንድ ዓመት ከውድድር ውጪ መደረጉ ተገቢ እንዳልሆነም፣ የእግር ኳስ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡

የወልዲያ እግር ኳስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገረመው ካሳ፣ በተላለፈው ውሳኔ ላይ ቅሬታቸውን በማሰማት ተገቢ አይደለም ብለውታል፡፡ አቶ ገረመው፣ ‹‹ፌደሬሽኑ ተመሳሳይ ችግሮች ሲፈጠሩ እንዲህ ያለ ውሳኔ ወስኖ አያውቅም፡፡ በተገቢው መንገድ መወሰን አለበት፤›› በማለት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በክለቡ ላይ ከተወሰኑ ውሳኔዎች ባሻገር ስታዲየሙን ለአንድ ዓመት ምንም ዓይነት ውድድር እንዳያከናውን ማገድ፣ የአካባቢውን ስፖርት ወዳድ ሕዝብ ከስፖርት ማራቅ በመሆኑ በተወሰኑት ውሳኔዎች ላይ ይግባኝ እንጠይቃለን ብለዋል፡፡

በዕለቱ የተከሰተው ረብሻ የጥቂቶች ድርጊት እንጂ የሁሉም ተመልካቾች ተግባር እንዳልሆነ በመጥቀስም ውሳኔውን ተችተዋል፡፡ በአንፃሩ በስታዲየሞች አካባቢ የሚከሰቱትን ከስፖርታዊ ጨዋነት ያፈነገጡ ድርጊቶች መከላከል የሚያስችል ተመጣጣኝ ቅጣት እንደሚስፈልግ፣ ፌዴሬሽኑም ቆራጥ አቋም በመያዝ የእግር ኳስ ሜዳውን ከብጥብጥ አውድማነት የመታደግ ኃላፊነት እንዳለበት በርካቶች ሲገልጹት የከረመ ሐሳብ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...