Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርታሪካዊ አጋጣሚውና ሰዋዊ ስሜቶቻችን

ታሪካዊ አጋጣሚውና ሰዋዊ ስሜቶቻችን

ቀን:

በብሩክ ፈለቀ

ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት ጀምሮ ስለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ብዙ ተብሏል፡፡ በተለይም እንደ አሜሪካዊው ዶናልድ ሌቪን የመሳሰሉ የጥናትና የጽሑፍ አትኩሮታቸውን በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያደረጉ ‹‹የመከኑት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዕድሎች›› የሚሉ ሐተታዎችን ብዙ አንብበናል፡፡ ከእነዚህ ዕድሎችም ውስጥ ብዙዎች የሚስማሙበት የወንድማማቾቹ የመንግሥቱና የግርማሜ ነዋይ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ፣ የ1966 ዓ.ም. አብዮት፣ የ1981 ዓ.ም. የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ፣ የ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥና የ1997 ዓ.ም. የምርጫ ውድድርን ከሞላ ጎደል ብዙ ምሁራን ኢትዮጵያ ያመከነቻቸው ብሩህ ዕድሎች እንደነበሩ ይስማሙባቸዋል፡፡

ይህን የመነሻ ሐሳብ እንዳነሳ ምክንያት የሆነኝ በ27 ዓመታት የኢሕአዴግ አገዛዝ ውስጥ ከፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ባለፈ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ቀልብ የሳበው፣ ‹‹በራሳቸው ፈቃድ›› የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ይበቃኛል ብለው የለቀቁትን አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ለመተካት በተደረገው ውድድር አሸናፊ ሆነው ብቅ ያሉት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሥልጣን ርክክቡ ዕለት የተናገሩት ንግግር ነው፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት ብዙ ዕድሎች አምልጠዋል፣ ይህን አጋጣሚ ግን ልንጠቀምበት ይገባል›› በማለት በንግግራቸው መሀል በአጽንኦት የተናገሩት ሐሳብ ነው፡፡ ይህ ሐሳብ ከላይ እንደ መነሻ እንዳነሳሁት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በእጃችን ገብተው እንዳመከንናቸው ዕድሎች፣ ይህን አጋጣሚ በጥሩ ሁኔታ ሳንጠቀምበት ሊያልፈን አይገባም የሚል አቋም ያለው ንግግር ይመስለኛል፡፡

በእርግጥም ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ለንባብ ትበቃ ከነበረችውና የአብዛኞቹ ጋዜጠኞቿ መጨረሻ ስደት የሆነባት ‹‹አዲስ ነገር ጋዜጣ›› ላይ ያነበብኳት፣ ‹‹የኢትዮጵያ የፖለቲካ ህዳሴ ከወዴት ይመጣል?›› የምትል ጥናታዊ መሰል ጽሑፍን እንዳስታውስ ተገድጃለሁ፡፡ ልጆቹ ጽሑፉን ሲያዘጋጁ ሙሉ በመሉ የጥናታዊ ሥራዎች መሥፈርቶችን በመጠቀም ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ላይ ከመንግሥት አካላትና ደጋፊዎች ጀምሮ እስከ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች (ይቅርታ ይደረግልን የዚህ ቃል ዘመን ማለፉን ጠቅላይ ሚኒስትራችን አብስረውናል፡፡ ለአገር የሚበጅ የተለየ ሐሳብ ያላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሚለው ይተካልኝ) እና የተለያዩ ምሁራንን ሐሳብ በጽሑፍ መጠየቅ፣ በቃለ መጠይቅና  ወቅታዊ የሆኑ የጥናት ወረቀቶችን በመመርኮዝ የተዘጋጀ ጽሑፍ ነበር፡፡ ለማንኛውም የዚህ ጥናት መሰል የመጨረሻ ውጤት ‹‹የኢትዮጵያ የፖለቲካ ህዳሴ ከኢሕአዴግ ከራሱ ውስጥ ይፈጠራል›› የሚል እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ እናም የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የመጀመሪያ ታሪካዊ ንግግራቸውን ላዳመጠ ኢትዮጵያዊ፣ የአዲስ ነገር ጋዜጣ ከዓመታት በፊት ትንቢት አዘል ጽሑፍ መፈጸሚያዋ ዛሬ ይሆን እንዴ ማለቱ አይቀርም፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም የስሜታችንን ትክክለኝነት በሚደግፍ ሁኔታ፣ ይህንን አጋጣሚ ልናመክነው አይገባም የሚል ጠንካራ አቋም ማንፀባረቃቸው እሰየው የሚያስብል ነው፡፡

በእርግጥም ይህንን አጋጣሚ ለመጠቀም የሚያበቁ በተለይም በልዩነት ለአንዲት ኢትዮጵያችን አብረን እንሥራ የሚል ጥሪ ለሁሉም አካላት ማቅረባቸውን እንደ አንድ ዕድል ልንቆጥር ይገባል፡፡ ይህም መልካም ሐሳብና ጅማሮ በዕውን እንዲታይም ሁሉም ከተለያየ አቅጣጫ አጨብጭቦላቸዋል፡፡ ብዙዎችም ይህ ንግግር በተስፋ ብቻ እንዳይቀር ብዙ ትግልና ተግዳሮቶች እንደሚጠብቋቸው ፍርኃታቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ሆኖም ሥራቸውን ዛሬ ነገ ሳይሉ እንዲጀምሩና ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በተለያዩ ሚዲያዎች የቀረቡ ምሁራን፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላትና የማኅበረሰቡ አካላት አውስተዋል፡፡ እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የተፈጠረውን መነሳሳት መከታ በማድረግ የድርሻዬን ለማለት ሞክሬያለሁ፡፡ ከዚህ በታችም የቅድሚያ ሥራቸው ቢሆን ወይም ከፍተኛ ተግዳሮት ይሆኑባቸዋል ያልኳቸውን ሐሳቦች እነሆ፡፡

ከመጠን ያለፈ የብሔርተኝነት ስሜት

ባለፉት 27 ዓመታት ከብሔራዊ አንድነታችን ይልቅ ልዩነታችንና ክፍተታችን፣ በዘመኑ በነበሩ አስተሳሰቦች፣ ትምህርት፣ ሥልጣኔና አስገዳጅ ሁኔታዎች ምክንያት የተፈጠሩ ታሪካዊ ጠባሳዎች፣ ሲልም የፈጠራ ታሪኮች እንደ ተረት ሲነበነቡልን መክረማቸውንና በተለይም ካለፈው 30 ዓመት ወዲህ የተወለደ ‘ኢትዮጵያዊነት፣ እናት አገራችን፣ አንድነት ጥንካሬ ነው’ የተሰኙና መሰል አባባሎች ተረት የሚመስለው አዲስ ትውልድ መኖሩ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አንዱና ዋነኛ ፈተናቸው እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም፡፡ ይህ የመለያየት፣ በብሔርና በጐሳ በጐሪጥ የመታየት ስሜት ሥር የሰደደ በሽታችን መሆኑን መካድ ታሞ እየማቀቁ መድኃኒቱን አለመፈለግ ይመስለኛል፡፡ ይህንን አባዜ ከኢሕአዴግ ራስ ውስጥ መንቀል የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ትልቁ የቤት ሥራ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ፈተና እንደማረጋገጫ ዶ/ሩ ሊቀመንበር ሆነው ከተመረጡ በኋላ በሸራተን አዲስ በተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ላይ፣ ከጠዋት ጀምሮ በጥናት አቅራቢዎችም ሆነ በተሳታፊዎች ሕዝባችንን አንድ በሚያደርግና በሚያስተሳስር ጉዳይ ላይ አለመሠራቱን ከመተማመን ባለፈ ሐሳቦቹ በጭብጨባ ድጋፍ ሲሰጣቸው  ተስተውሏል፡፡ በውይይቱ መቋጫ ላይ ግን ዕድል የተሰጣቸውና በኢሕአዴግ የግምገማና የተሃድሶ ሒደት ላይ ትልቅ ሚና የነበራቸው አንጋፋው አቶ በረከት ስምኦን፣ ‹‹በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ባለፉት ዓመታት የብሔር ብሔረሰቦች አንድነት ተፈጥሯል፤›› በማለት መናገራቸውን እንደ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡

ይህን የመለያየት ስሜት ግን በቢሮ፣ በባንክ፣ በንግድ ተቋማት፣ በምግብ ቤቶች፣ በካፌዎችና በመጠጥ ቤቶች የሚስተዋል ከሆነ ቆይቷል፡፡ የመንግሥት ቢሮዎች ብንሄድ ከላይ የተቀመጠው ባለሥልጣን ዘሮች፣ ሲወርድም በጐሳ ደረጃ የአንበሳውን ወንበር ተቆናጠው መገኘታቸው ድንቅ ያልሆነባት አገር ሆናለች፡፡ በግሉ ዘርፍ ሳይቀር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከሙያ ብቃት በላይ ብሔር ተኮር ቅጥሮች መከናወናቸው የበሽታችን ሥር መስደድ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህንንም የተወሰነ ወይም ከግማሽ በላይ በሚሆኑ የግል ባንኮች፣ ትልልቅ ሆቴሎቻችንና የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች መመልከት ይቻላል፡፡ ለማንኛውም ከቤተ መንግሥታቸው ጀምሮ እነዚህ መሰል ስሜቶችን መቀበል የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዋነኛ የቤት ሥራቸው መሆን እንዳለበት የሁላችንም ስሜት ይመስለኛል፡፡ በንግግራቸውም ከ30 ጊዜ በላይ ስለኢትዮጵያዊነትና ስለአንድነት መናገራቸው በትክክልም ይህንን ሥር የሰደደ በሽታችንን የማከምን ሥራ፣ በዕለተ ሲመታቸው ላይ አንድ ብለው ጀምረውታል ለማለት ያስችላል፡፡ በእርግጥም ይህንን ሐሳባቸውን በዙሪያቸው ያሉት ሰዎች ውስጥ ማስረፁና ሐሳባቸውንም እንዲገዛቸው ማድረግ ካልቻሉ ፈተናቸው ከባድ ይሆናል፡፡

ሹመት

ባለፉት አሥርት ዓመታት ተንሰራፍቶ የከረመው የሹመት አሰጣጥ ወይም የካቢኔ አወቃቀር ብዙ ገጽታዎች ነበሩት፡፡ እንደኔ ዕይታ ግን ሦስት ዓይነት ሹመቶች ጎልተው የወጡበት ጊዜያት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ አንደኛ በደጋፊነት፣ ታማኝነትና ታዛዥነት የተመረኮዘ ሹመት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሹመኞች ወደ ላይ አንጋጠው የማይጠይቁ፣ ሁሉንም ነገር ወደ ታች የሚያወርዱ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ሁለተኛው ብሔር ተኮርና ኮታዊ አሠራርን ተመርኩዘው የሚሾሙ ሹመኞችን ያካትታል፡፡ እነዚህም ታማኝ የፓርቲው አገልጋዮች ከመሆናቸው ባሻገር እንደ ብቃት ማረጋገጫ ከሚቀርቡላቸው ዶክመንቶች ባሻገር፣ ታሪካዊ ዳራቸው ቢመረመር ውጤታማ የሚባል ሥራቸውን በባትሪ ፈልገን ልናገኝላቸው የምንችል አይመስለኝም፡፡ ሦስተኛው ሹመት ሰንሰለትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ እነዚህ ከኢንቨስትመንት፣ ከግሉ ሴክተር፣ ከመሬት፣ ከፋይናንስና ከመሳሰሉት ወሳኝ የሚኒስቴርና የመሳሰሉት መሥሪያ ቤቶች የቤት ሥራ ተሰጥቷቸውም ሆነ ለክፉ ጊዜ መደገፊያ እንዲሆኑ ታስበው የሚሾሙ ታማኞች ናቸው፡፡

በእንደዚህ መሰልና በሌሎች መሥፈርቶች ሚኒስትር ዴኤታ፣ ቢሮ ኃላፊ፣ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ ክፍል ኃላፊ፣ ፋይናንስ ኃላፊ እየተባለ ወደ ታች ሹመኛ ሲዘረጋ ደግሞ ብዙ ቀመሮች ይሠራሉ፡፡ አንደኛው ቀመር ራስ ላይ የተቀመጠው ሹመኛ ቦታው ላይ የሚያነጣጥር እንዳይኖር የሚሸፍን ብሔር ተኮር ምልመላዎች ያካሂዳል፡፡ ከብሔር ቢዘል እንኳን በተለያየ አጋጣሚ ታማኝነታቸውን ያስመሰከሩ ወዳጆች ዋና ዋና ቦታዎችን ይይዛሉ፡፡ እንዲያውም በቅርቡ በአንድ ጥናት ጉዳይ ብዙ በመመላለሴ በመግባባት በአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሰማሁት ወሬ የሰንሰለቱን እውነታነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ለምሳሌም በእነሱ ቋንቋ ‹‹የሚኒስትሩ ክሊክ ነው››፣ ‹‹የሚኒስትር ዴኤታው ግሩኘ ነው›› በማለት መሥሪያ ቤቱ ውስጥ ቡድኖች እንዳሉ ነግረውኛል፡፡ እዚህ ሰንሰለት ውስጥ የገቡ ሠራተኞች በሹመት ላይ ሹመት ባይሰጣቸው እንኳን ‹‹ሹመት ያዳብርላችሁ!›› ተብለውና ተመርቀው የተቀመጡ አይነኬዎች የመሆን ዕድላቸው በጣም ሰፊ ይሆናል፡፡

የዚህ ሁሉ ትርምስ ሐሳብ ሲሰላ ግን የመሥሪያ ቤቱን ውጤታማነት ዜሮ ያደርገዋል፡፡ በጣም ሙያተኛ የሚፈልጉ ቦታዎችን በፍራቻ ምክንያት ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች እንዲያሽከረክሩዋቸው ይደረጋል፡፡ ይህም የመልካም አስተዳደር፣ የሙስና፣ የብሔርተኝነትና የመሰሳሰሉት ችግሮች በአገሪቱ ላይ እንዲንሰራፉ ትልቁ ምክንያት ሆኗል፡፡ የተማረው የሰው ኃይል በአገሩ ተስፋ እንዲቆርጥ አድርጓል፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንን አሠራር መታገል ካልቻሉና ታች ወረዳ ድረስ ያለውን መዋቅር በትምህርት፣ በብቃት፣ በልምድና ሁሉን አሳታፊ የሆነ መዋቅር የሚዘረጋበትን ድልድይ መዘርጋት ካልቻሉ ልፋታቸው ሁሉ ‹‹አልሸሹም ዞር አሉ›› ዓይነት ይሆንባቸዋል፡፡ ማኅበረሰቡም መልሶ ፊቱን ማዞሩ አይቀሬ ይሆናል፡፡ የተማረው የሰው ኃይል የበኩሉን እንዲወጣ በር ሊከፈትለት ይገባል፡፡ የሥራ ማስታወቂያ አውጥቶ የመግቢያ ፈተናውን አግላይ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ ለጤና ባለሙያ የወጣ የሥራ ማስታወቂያ ፈተና ላይ በኢሕአዴጋዊ መዋቅር ውስጥ ያለፉ ወጣቶች ብቻ ሊመልሱት የሚችሉትና ሙያዊ ያልሆነ ጥያቄ ማውጣት ኢፍትሐዊነት ነው፡፡ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ ረገድ ተስፋ እንድናደርግ የሚያስችሉን በነበሩባቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተከሏቸው አሠራሮችና በተለያዩ አጋጣሚዎች በዕውቀት፣ በወጣትነት፣ በአገር አንድነት ላይ ያደረጓቸው ንግግሮች ናቸው፡፡

ለምሳሌም ፓርቲያቸው ሊቀመንበር አድርጐ ከመረጣቸው በኋላ በአውሮፓ የዶክትሬት ዲግሪውን እየሠራ የሚገኝና የእሳቸው የሚገርም አሻራ ያረፈበት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሠራተኛ የነበረ ሰው በማኅበራዊ ድረ ገጽ ገጠመኙን አካፍሎን ነበር፡፡ በተለያዩ ቦታዎች በእርሱ ሙያ (የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ) ማስታወቂያ ወጥቶ ፈተናዎቹ ከ50 በመቶ በላይ ፓርቲ ተኮር የነበሩ ስለነበሩ፣ በዚህ መሥሪያ ቤትም ተመሳሳይ ገመኝ ይገጥመኛል ብሎ አስቦ እንደነበር ያትታል፡፡ የሆነው ነገር ግን መቶ በመቶ ሙያዊና ሳይንሳዊ ፈተና ነበር፡፡ የጽሑፉን ፈተና ሲያልፍም የቃለ መጠይቅ ፈተናው ላይ ራሳቸውን ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ተቀምጦ ማየቱ ቢያስደነግጠውም፣ ‹‹አገርን የሚያሳድገው ዕውቀት ነው፡፡ ስለዚህም ዋነኛ ሥራችን የሰው ልማት ላይ መሥራት ነው፤” የሚል አስደማሚ ንግግራቸውን መስማቱን ያስታውሳል፡፡ በእርግጥም ከእሳቸው ጋር በሠራበት ዘመን የሰው ልማት ላይ በተለይም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ብዙ እንደሠሩ ገልጿል፡፡

ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ ልዩነታቸውን በሚያሳይና በጥንቃቄ መሆን ይኖርበታል፡፡ በሚኒስትር ደረጃ ፖለቲካዊ አንድምታው ከፍ ቢል እንኳን በምክትልና ወደ ታች ያሉ መዋቅሮች ላይ የሚመረጡ ሰዎች ከመሥሪያ ቤቱ ተግባርና ኃላፊነት ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ሙያተኞች መሾማቸውን ልብ ሊሉ ይገባል፡፡ እንዲያ ከሆነ ሙያተኛም ክብር ያገኛል፡፡ የመማርም ጠቀሜታ ይጎላል፡፡ ወጣም ወረደ ግን የዶ/ር ዓብይ ዋነኛ ፈተናም ይህንን የተዘበራረቀ ሰንሰለት ለመበተን በሚያደርጉት ጥረት የሚገጥማቸው ይመስለኛል፡፡

ሙስና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በመክፈቻ ንግግራቸው በዋነኛነት እንታገለዋለን ያሉት ሙስናን ነው፡፡ ነፍሳቸውን ይማርና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሙስናን በየትኛውም የመንግሥት መዋቅር መንሰራፋቱን ሲገልጹ፣ ‹‹ሁሉንም እንፈትሽ ካልን መንግሥት ይፈርሳል፤›› ነበር ያሉት፡፡ የዶ/ር ዓብይ ትልቁም ፈተና ይህ ጉዳይ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በአገራችን ትናንት ምንም ያልነበሩ ሰዎች የትልልቅ ኢንቨስትመንት ባለቤት፣ የብዙ መቶ ሚሊዮን የባንክ ባለድርሻዎች፣ የብዙ ሕንፃዎች ባለቤቶች፣ የቡና፣ የሰሊጥ፣ የማዕድን ላኪዎች፣ በአጠቃላይ በአገሪቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ ንግሥና አግኝተዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ደግሞ ከእነዚህ ባለሀብቶች ጀርባ የእነማን እጅ እንዳለበት ያውቃል፡፡ ሁሌም ጥያቄው ‹‹ከማን ጋር ነው የሚሠራው?››፣ ‹‹ከመድረክ ጀርባ ያለው የሀብቱ ባለቤት ማን ነው?›› የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ‹‹በአነስተኛና ጥቃቅን ጀምሬ፣ ተበድሬና ተለቅቼ ዛሬ ባለሀብት ለመሆን በቅቻለሁ፤›› የሚለውን ተረክ የሚሰማም አይገኝም፡፡ ለማንኛውም ‹‹ተጠያቂነትን›› በትክክል ለማስፈን የሚተጉ ከሆነ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በአንድ ሌሊት ጠላተ ብዙ ሆነው ማደራቸውን ልብ ይሏል፡፡ ከፈተና አውጣኝ፡፡

የልማት ድርጅቶች

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔር ተኮር የሀብት ክፍፍል፣ ፉክክር፣ ጡንቻ ማዳበር ሩጫ ውስጥ ከተውን ያለፉት እነዚህ የልማት ድርጅት ተብዬዎች ናቸው፡፡ በፓርቲው ውስጥ እርስ በርስ አለመተማመንና ኅብረት ማጣት ውስጥ ለመግባቱ የነበራቸው ሚና በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ ማኅበረሰቡም ቢሆን የፓርቲው ቁንጮ ሰዎች ከቦርድ ሰብባቢነት ጀምሮ እስከ ታችኛው ሰንሰለት ታማኞቻቸውን ደርድረው የግል ጥቅማቸውን የሚያሮጡባቸው ተቋማት አድርጐ ይቆጥሯቸዋል፡፡ ድርጅቶቹ ለኦዲትም የታደሉ እንዳልሆኑ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ የግሉ ሴክተርም ቢሆን ገበያውን የሚያዛቡና በተለያየ ሰበብ አስባብ በቀጥታና ያለጨረታ ሥራ የሚሰጣቸው የእናት ልጆች አድርጐ ነው የሚቆጥራቸው፡፡ የቀረጥ፣ የግብርና የመሳሰሉት ሕጐችም ቢሆኑ ድጋፍ የሚሰጣቸው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ተፃራሪ መሆናቸውን ነው የሚያምነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በከፍተኛ አመራሮችም ዘንድ ሳይቀር በደማችን ላይ የሚል አቋም የሚያራምዱ በመሆናቸው፣ መላ መላ ሊሏቸው ቢነሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚገጥማቸው የመልስ ምት በግምት የሚለካ አይመስለኝም፡፡ ማኅበረሰቡ ግን ከአዲሱ ተስፋ ውስጥ በእነዚህ የልማት ድርጅቶች ዙሪያ የሆነ ነገር እንደሚያደረግ የሚጠብቅ ይመስለኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በኢኮኖሚ ሥርዓቱ ዙሪያ ከሚያከናውኑዋቸው ሥራዎች እንደ አንዱ ዕቅዳቸው የተቀመጠና ለመጋፈጥም የቆረጡበት አንዱ አጀንዳቸው እንደሚሆን የብዙዎቻችን እምነት ነው፡፡

የመከላከያውና የደኅንነቱ የሥልጣን ገደብ

የመከላከያውና የደኅንነት አካላቱ ለአንድ አገር ጥንካሬ፣ የውጭ ጠላትን ለመከላከልና የማኅበረሰቡን በሰላም ወጥቶ የመግባት ሒደቱን አሳማኝ ደረጃ ከማድረስ አንፃር ያላቸው ሚና በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ እንደ ሕገ መንግሥታችን አባባልና እንደ 21ኛ ክፍለ ዘመን የአስተሳሰብ ደረጃ ለመንግሥት አካላት፣ ለገዥው ፓርቲም ሆነ ለሌላ አካል ድጋፍ የሚሰጡ ሳይሆን ውክልናቸው ለሕዝብና ለአገር መሆን አለበት፡፡ የሁለቱ አካላት መዋቅራዊ ውክልናና መወገን ግን በገሃድ የሚታይ መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ የሥልጣን ገደባቸውም ሥልጣኑ ለተወሰነ ቡድን እንዲያጋድል ትልቅ ሚዛን መሆንም መናገር ለቀባሪው ማርዳት ይመሰለኛል፡፡ ወጣም ወረደም ሁለቱ አካላት በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊውም ሆነ በሁነኛ አገራዊ ክስተቶች ላይ ያዳበሩትን ጡንቻ ማላላት አንዱና ትልቁ የማኅበረሰቡ ጥያቄ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ይህንን ሁኔታ ወደ ትክክለኛው መንገድ መግፋት የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ትልቁ የቤት ሥራ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

ይህንን ጉዳይ እልባት መስጠት ካልተቻለ አዲሱ መንግሥት የፈለገ ቢሠራ የሕዝብን እንባ ማበስ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ከፍተኛ የአገሪቱን ሀብት የሚያስተዳድረው መከላከያም በጀቱ ምን ያህል እንደሆነ፣ ምን ያህል ሠራተኞችና ሀብት እንደሚያስተዳድር የአገር ሚስጥር በሚል ከአሉባልታዎች ለመገላገል፣ ዋና ኦዲተር በሚያደርገው ፍተሻ የሆነ ነገር ቢገኝ ምንም የማይባል ተቋም አለመሆኑን ከአዲሱ መንግሥት አዲስ ነገር መስማት እንሻለን፡፡ ‹‹ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው››፣ ‹‹በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት›› የመሳሰሉት ተረቶችን እንዳትተርቱብኝ ሠጋሁ፡፡ እሳቸውም ‹‹እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!›› ብለው የለ፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ብርታቱን ይስጣቸው››፡፡

ባለሀብቱና ማኅበረሰቡ

በዚህ ሰሞን አንዱ ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ? ‹‹የድሮ ባለሀብት እኮ ለሠፈሩ አድባር ነበር፡፡ የዘንድሮዎቹ ግን ለሠፈሩ ባዳ ናቸው፡፡ የድሮ ባለሀብት ዕድር፣ ዕቁብ፣ ማኅበር፣ ከማኅበረሰቡ ጋር ይሳተፋል፡፡ ሌሊት ሰው ቢታመም ቤቱ ይንኳኳል፡፡ ምክንያቱም መኪናው ሠፈሩን አገልጋይ ነችና፡፡ በገንዘብም ሠፈርተኛውን ይደግፋል፡፡ አብሮ ይበላል፣ ይጠጣል፡፡ የአሁኑ ባለሀብት ግን ደሃ ሲያይ ዓይኑ ደም ይለብሳል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ቦታ ላይ ያለ መሬት ለደሃ ምን ያደርግለታል ብሎ ያስባል፡፡ ማኅበረሰቡም ያሁኑን ባለሀብት እንደ ሙሰኛና ከጉሮሮው ላይ ነጣቂ አድርጐ ነው የሚቆጥረው፡፡›› ይህንን ማኅበራዊ አስተሳሰብና ክፍተት ማከም ካልተቻለ በአገሪቱ ባህል፣ እምነትና ታሪክ ተሰምቶ የማይታወቅ ጠባሳ ጥለን ማለፋችን ሀቅ ነው፡፡ ይህንን ክፍተት የሚያስታርቁ የመፍትሔ ሐሳቦች ማምጣት፣ ሰርቆና በአቋራጭ በመጓዝ ሳይሆን በላብና በወዝ የሚታደርባት አገር ለማድረግና ለማንደርደር ጥረት ማድረግ፣ የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሌላ የቤት ሥራና ተግዳሮት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

‹‹አበስገበርኩ እቴ!›› አሉ እናቶች፡፡ ድክም ድክም አለኝ፡፡ የወጣቱ ሥራ አጥነት፣ የመሠረታዊ ፍላጐቶች እጥረት፣ የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሒደት፣ የመናገር ነፃነት፣ ጨቋኝ የሆነም ሕጐችና መመርያዎችን ማሻሻል፣ የሚዋዥቀውን ኢኮኖሚ መምራት… ኧረ ስንቱ፡፡ የተባረከ ቃል መናገር ግን መልካም ነገርን እንደ መዝራት ነው፡፡ በበዓለ ሲመታቸው ቀን የተባረኩና ቅዱስ ሐሳቦችን ለቀውብናል፡፡ አምላክ ሐሳባቸውን ይባርክ! እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...