Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር በታዋቂ ግለሰቦች ማንነት መነገድ

 በታዋቂ ግለሰቦች ማንነት መነገድ

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

ሰዎች ያዩትንና የተገነዘቡትን በተፈጥሮ ባገኙት የተፈጥሮ ዕውቀት፣ ወይም በትምህርት በቀሰሙት ጠቅላላ ዕውቀት፣ ወይም በልዩ ሥልጠና በተማሩት ሙያዊ ዕውቀት አስድግፈው ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ በሦስቱ ዕውቀቶች አማካይነት የሚነገሩ ነገሮች ልዩነት ያለመርቀቅ ጥሬነትና የመርቀቅ ብስለት ደረጃ ብቻ ነው፡፡

በተፈጥሮ ዕውቀት አማካይነት የሚናገሩት በሌጣ ዓይን በሚያዩት ላይ ያተኩራሉ፡፡ በጠቅላላ ዕውቀት አማካይነት የሚናገሩት ዓይናቸውንና አዕምሮአቸውን ይጠቀማሉ፡፡ በሙያ ዕውቀት አማካይነት የሚናገሩት ዓይናቸውንም አዕምሮአቸውንም የሙያ ዕውቀታቸውንም ሦሰቱን አመዛዝነው ይጠቀማሉ፡፡

ሰዎች ስለኢኮኖሚ ሙያ ሲናገሩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሰሚ ብቻ የሆኑበት፣ እኛም እንናገር ያላሉበት፣ የሚነገረውንና የሚጻፈውን ለመቀበልም ላለመቀበልም ያልፈለጉበት ምክንያት ብንናገርም ሰሚ ስለማናገኝ መናገር የሚገባን ጊዜ እስከሚደርስ በዝምታ መጠበቅ ያስፈልጋል ብለው ስላመኑ ይመስለኛል፡፡ ይኼ የባለሙያዎች ዝምታ ግን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አመንምኖ ገዳይ በሽታ እየሆነ ነው፡፡

በታዋቂ ኢኮኖሚስቶች ብርታትና ጥረት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባሳየው ዝምታ እንደ ሰው ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንዳይላክ የፈራ መስሎበታል፣ ወይም ከሌሎች እኩል ባህሩ ውስጥ ገብቼ አልንቦጫረቅም ብሎ ትቶም ይሆናል፡፡ የአንድ ሰው ዕድሜ ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት እርጅናው ይሁን ምኑ ባይታወቅም አፉን ገጥሟል፣ ዓይኑንም ከድኗል፣ ከሌሎች እኩል ባህሩ ውስጥ ገብቼ አልንቦጫረቅም ብሎ ትቶም ይሆናል፡፡

እነዚህ ሁለት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የኑሮ ደረጃ መሻሻልና አለመሻሻል፣ ማደግና አለማደግ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በተተነተኑ መረጃዎች ሙያዊ ምስክርነት በመስጠት በዕውቀት የማሳመን ተስፋዎች የነበሩ ተቋማት በሙያቸው ውስጥ ሳይገባቸው ጣልቃ ገብተው የሚነግዱትን የፖለቲካ ካድሬዎች በተሳሳተ መረጃ ከማሳሳት ከሕዝብ ጀርባ ላይ ውረዱ ማለት አልቻሉም፡፡

የኢኮኖሚስቶች ዝምታ በተፈጥሮና በጠቅላላ ዕውቀት ለሚናገሩ ሰዎች እንደ ልብ ለመፈንጨት ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡ ደጋፊዎችና ነቃፊዎች ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ሁለት ጽንፍ የረገጡ አመለካከቶችን እንዲያንፀባርቁ በር ከፍቶላቸዋል፡፡

ኢሕአዴጎችና የኢሕአዴግ ደጋፊዎች የሆኑ በተፈጥሮና በጠቅላላ ዕውቀት የሚናገሩ ኢኮኖሚው ማደጉንና ያሳደገውም የኢሕአዴግ ፖሊሲ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የመረጃ ምንጫቸውም በሌጣ ዓይን የሚታዩ የተሠሩ ሥራዎችና የተገነቡ ተቋማት፣ የመንግሥት ስታትስቲካዊ መረጃዎችና የዓለም አቀፍ ድርጊቶች ምስክርነት ናቸው፡፡ ምርቱን ብቻ ይለካሉ እንጂ ምርቱን ለማምረት ጥቅም ላይ የዋሉትን ግብዓተ ምርቶች ምን ያህል እንደሆኑና ከየት እንደመጡ፣ ወደፊት የሚከፈሉ የዕዳ ሸክም መሆን አለመሆናቸውን አያገናዝቡም፡፡

ኢሕአዴግን የማይደግፉና የሚቃወሙ በተፈጥሮና በጠቅላላ ዕውቀት የሚናገሩ በዓይን የሚታየው የጥቂቶች ሀብት ነው፣ ለደሃው ምኑም አይደለም ይላሉ፡፡ በወረቀት ላይ ቁጥር ተቆለለ እንጂ ሕዝቡ በእጁ ዳስሶ በምላሱ ቀምሶ አልረካም ከማለትም ባሻገር፣ በደሃው አካባቢ ያለው የመሻሻል ለውጥም በጊዜ ብዛት ከሚመጣ ተራ ለውጥ በላይ በፖሊሲ ምክንያት ልዩ ዕድገት አልመጣም ይላሉ፡፡ የመረጃ ምንጫቸውም ገበያ ውስጥ የሚታዩ ሁኔታዎችና የአብዛኛው ሕዝብ የኑሮ ደረጃዎች ናቸው፡፡ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ምስክርነትም ‘የአይጥ ምስክሯ ዲንቢጥ’ ብሎ ከማጣጣል በላይ አምኖ ለመቀበል ይከብዳቸዋል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ቢናገሩ ኖሮ በዓይን የሚታየውን እውነትና በስታትስቲክስ የቀረበውን ጥሬ መረጃ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ የሒሳብ መዝገብ ያዥ ባለሙያ የሀብትና የዕዳ መጠን ሠንጠረዥን መርምረው ምክንያትና ውጤትንም አዛምደው ነበር የሚናገሩት፡፡

ለምሳሌ ለቻይና ኢኮኖሚ ዕድገት ዋናው ምክንያት ከሶሻሊስት ኢኮኖሚ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ መሸጋገሯ ነው? ወይስ ከሶሻሊዝም ብዙም ፈቀቅ በማይለው በልማታዊ ኢኮኖሚ የመንግሥት ይዞታ በመብዛቱ ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች ኢኮኖሚስቶች ምክንያትና ውጤትን አገናዝበው፣ ቢያስፈልግም በሒሳብ ሥሌት ተዛምዶዎችን አጥንተው ይናገራሉ እንጂ የመላ ምት ግምታዊ መልስ አይሰጡም፡፡

የኢኮኖሚያዊ አስተዳደር ሥርዓትን ሳይንሳዊ ለማድረግ የአገር መሪዎች በሊቃውንት ተጠንተው በተተነተኑ ጽንሰ ሐሳቦች ላይ ተመርኩዘው አገራዊ ራዕያቸውንና ፖሊሲያቸውን መቅረፅ እንደሚኖርባቸው፣ ጥናቶችና የሌሎች አገሮች ተሞክሮዎች ያረጋግጣሉ፡፡ በየሦስት ወሩ በአማርኛ ቋንቋ በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ዓለም አቀፋዊና ድርጅታዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ የምትሰጠው የኢሕአዴግ መጽሔት ‹‹አዲስ ራዕይ›› ግን ከዚህ ሳይንሳዊ ማረጋገጫ የተለየ ሐሳብ ታቀርባለች፡፡

ከመስከረም እስከ ጥቅምት 2010 ዓ.ም. ‘የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ስኬቶች ተግደሮቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች’ በሚል ርዕስ በፌዴራሊዝም ሥርዓት አማካይነት ልዩነቶችን ማቻቻል አንድ ፖለቲካዊ ሥርዓት የመፍጠር ጉዳይ እውነተኛ መለኪያው የራሱ የሥርዓቱ ክንውኖችና ሒደቶች እንጂ፣ አፍአዊ ጽንሰ ሐሳቦች (Theoretical Concepts) አይደሉም በማለት በኢሕአዴግ ፍልስፍና ጽንሰ ሐሳብ ቦታ እንደሌለው መጽሔቷ ትገልጻለች፡፡

ይሁንና ግን መጽሔቷ ይኼንን ባለች በአራት ወራት ውስጥ የሥርዓቱ ክንውኖችና ሒደቶች የተቀስቀሰውን የሕዝብ አመጽ አባብሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ገፍትሮ እስከ መጣል ስለደረሰ፣ መቼም ቢሆን ኢሕአዴግ በተግባር ክንዋኔ ሊመፃደቅ እንደማይችል አረጋግጧል፡፡ 

በዚህ ሰሞን በአገሪቱ ያንዣበበውን አደጋ በውይይትና በንግግር ለመፍታት የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስለአንድነትና የብሔር ፌዴራሊዝም አተገባበር፣ እንዲሁም ስለኢኮኖሚያዊ ስኬትና ችግሮች አራትና አምስት ሰዎችን እየጋበዙ ማወያየትና አመለካከታቸውን መጠየቅ ስለጀመሩ ማዳመጥ ጀምሬአለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ውይይቶች ከአመለካከት ያለፉ ጽንሰ ሐሳቦች ባይሆኑም፣ ጠቃሚ መረጃና ዕውቀትን ሲያስተላልፉ አንዳንዶቹ በግትር አቋሞችና የሚታወቀውን መልሶ መላልሶ በመደጋገም ጊዜዬን በከንቱ አባክነዋል፡፡

አንዳንዶቹ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች የተያያዙት አዋቂ ሰዎችንና ባለሙያዎችን ማወያየት ሳይሆን በታዋቂ ሰዎች መነገድን ነው፡፡  የቴሌቪዥንና የሬድዮ ፕሮግራሞች ለአገር አንድነት እየሠሩ ቢመስላቸውም፣ አሁንም ልባቸው ገበያቸው ላይ ብቻ ነው፡፡ በሌላም በኩል በመጽሔቶችና በጋዜጦች ከሙያቸው ውጪ በሆኑ ጉዳዮች ቃለ መጠይቅ የሚደረግላቸውና ፎቶግራፋቸው በሽፋንና በውስጥ ገጽ የሚወጣላቸው ሰዎችም ቁጥር ከአሥር አይበልጥም፡፡

ታዋቂ ስፖርተኛውን፣ ታዋቂ ሙዚቀኛውን፣ ታዋቂ ፖለቲከኛውን ስለኑሮ ውድነት ስለዋጋ ግሽበትና ስለሥራ አጥነት ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ሲጠይቁ ሰምቼአለሁ፡፡ ከቀረቡት ታዋቂ ሰዎች ሁሉ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ብቻ ከኢኤንኤን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር ባደረገው ውይይት ከእኔ ይልቅ ባለሙያው ተጋብዞ ቢናገር ይሻላል ሲል ሰምቼአለሁ፡፡ 

ዓርብ መጋቢት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ‘ኑሮና ቢዝነስ’ የተባለ የኢቲቪ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ታዋቂ ሰዎችን ስለኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ሲያወያይ፣ በፖለቲካ ተሳትፏቸው ዕውቅ የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው የሕዝቡን ገንዘብ አወጣጥ በመመልከት ከሥርዓቱ ውጪ ገንዘብ የሚገኝበት መንገድ እንዳለ የሚያመለክቱ ሁኔታዎች አሉ የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረው ነበር፡፡

አቶ ልደቱ የኢኮኖሚ ባለሙያ ስላልሆኑ በሥርዓቱ ውስጥ መንግሥት የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ከልክ በላይ እንዲሆን ፈቅዶ የዋጋ ንረትን እንደሚፈጥር፣ ከመንግሥት ሌላ ብር አሳትሞ ሊያሰራጭ የሚችል አካል እንደማይኖር  አልተገነዘቡም፡፡ ሸቀጥን የሚያገበያይ ጥሬ ገንዘብ ብሔራዊ ባንክ አሳትሞ የሚያሰራጨው ብር ብቻ ሳይሆን፣ ንግድ ባንኮችም በብድር አሰጣጣቸው ብርን አርብተው ብዙ ጥሬ ገንዘብ ፈጥረው ሸቀጥ እንደሚያገበያዩ አላወቁም፡፡

የዋጋ ንረት ትንታኔ ጥያቄ በፕሮግራሙ አዘጋጅ ሊቀርብላቸውም አይገባም ነበር፡፡ ሙያና ባለሙያን በማገናኘት ሕዝብን ከማስተማር ይልቅ ከቢራ አምራች ኩባንያዎች ለማስታወቂያ የአየር ጊዜን ለመግዛት ቢሚያገኙት ስፖንሰርሺፕ፣ በታዋቂ ሰዎች ማንነት የንግድ ፕሮግራሞቻቸውን አድምቀው እያደናገሩ ያሉ የኤሌክትሮኒክስና የኅትመት ሚድያ ፕሮግራም አቅራቢዎች ፕሮግራማቸውን መሸጥ ዋናው ዓላማቸው እየሆነ ነው፡፡

ከሁለት ወይም ከሦስት ሳምንታት በፊትም ስለብሔር ፌዴራሊዝም በባለሙያዎች ከቀረበ ውይይት ውስጥ አንዳንዶቹን አድምጬያለሁ፡፡ ለብሔር ፌዴራሊዝሙ ጠንቅ የሕገ መንግሥቱና የሕጎቹ ችግር ሳይሆን፣ የአፈጻጸም ችግር ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎችም ኢሕአዴግ ማስፈጸም አልቻለበትም እንጂ እኔ ብሆን ኖሮ እችል ነበር ዓይነት መልዕክት እያስተላለፉ ግራ አጋብተውኛል፡፡ ኢሕአዴግ መተግበር ያቃተው ለመተግበር ስለሚከብድ ይሆን እንዴ ብሎ ለአፍታም ያሰበ የለም፡፡

በእኔ እምነት ግን በዓለም ላይ ብዙ ሊተገበሩ የማይቻሉ ቆንጆ ነገሮች አሉ፡፡ ሊተገበር የማይቻል ሆነ እንጂ ኮሙዩኒዝም ከካፒታሊዝም ይልቅ የሚያሰጎመዥ የሆነውን ያህል፣ የብሔር ፌዴራሊዝም ምንም ያህል የሚያስጎመዥ ቢሆንም እንደ ኮሙዩኒዝም ሊተገበር የማይችል የሰው ልጅን የስግብግብነት ተፈጥሯዊ ሥነ ልቦና የሚቀሰቅስ ሐሳባዊና ስሜታዊ እምነት ሊሆን ይችላል፡፡ በጣም ተምረው የዶክተርነትና የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙትም ጭምር የዚህ የስግብግብነት ስሜት ሰለባ ሆነው ለጠባብ ቡድናዊ ጥቅም ብቻ እየተሯሯጡ እንደሆነ እየተመለከትን ነው፡፡

ኮሙዩኒዝም ከመክሸፉ በፊት በሶቭየት ኅብረት ለሰባት ዓመታት ተቀምጬ እንዳየሁት፣ ከፖለቲካዊና ከኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ባሻገር የሰው ልጅ ተፈጥሮዓዊ ባህሪይ የሆነው የመበላለጥ ውድድር የግለኝነት ስሜትና ሥነ ልቦና ከሰባ ዓመታት ማኅበራዊ የጋራ ብልፅግና ትምህርትና ስብከት በኋላም አገርሽቶ ለውድቀቷ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ በዓይኔ አይቼአለሁ፡፡

ጠቢባን የሰው ልጅ የራስ ወዳድነትና የስግብግብነት ሥነ ልቦናዊ ባህሪይን ከአንድ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ግንባታ ፍላጎት ግንኙነት ጋር ቢመረምሩ የሰው ልጆች በባህሪያቸው የማይገባቸውን፣ ያልለፉበትን፣ ከሌሎች ያልተወዳደሩበትን ግላዊ ጥቅም ለማግኘት የብሔር ቡድናዊ ማንነታቸውን መሣሪያ አድርገው ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ሊያጠኑ ይገባል፡፡ ይህ የሰዎች ሥነ ልቦናዊ ስሜትም የኢኮኖሚ ጥቅም ሊሆን ይችላል፡፡ በሌሎች አንቱ ከመባል መደነቅም አልፎ የመመለክ አባዜ መጠናወት ስሜትም ሊሆን ይችላል፡፡

ዋልታ ቴሌቪዥን ከሁለት ወይም ከሦስት ሳምንታት በፊት ከባለሙያዎች ጋር በፌዴራሊዝሙ ትግበራ ጉዳይ ላይ ባደረገው ውይይት፣ የብሔር ፌዴራሊዝሙ በመሬት ጥያቄ ያጋጠመውን ችግር የሕግ ባለሙያው አቶ በሪሁ ተወልደ ብርሃን፣ የአፈጻጸም ችግር እንጂ ሕገ መንግሥቱ እንከን የለበትም ብለው መከራከራቸውን ሰምቼአለሁ፡፡ ሕገ መንግሥት የሕግ ጉዳይ ቢሆንም የመሬት ይዞታ ግን የኢኮኖሚ ጉዳይም ነው፡፡ የመሬት ጥያቄ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቅ ውዝግብ ያስከተለ ጉዳይም ነው፡፡ በኢኮኖሚ ሙያ መነጽር አንዳንድ ያላሳመኑኝ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አነሳቸዋለሁ፡፡

መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው ሲባል የመንግሥት የሚለው የሚመለከተው የማዕከላዊ መንግሥትን ብቻ እንጂ፣ የክልል መንግሥታትን አይደለም በማለት የክልል መንግሥታት ከማስተዳደር በላይ የባለቤትነት መብት ሕገ መንግሥቱ አልሰጣቸውም፡፡ ሆኖም የክልል መንግሥታት ባልተሰጣቸው መብት መሬትን እንደ ባለቤት ሆነው ሰጪና ነሺ ሆነዋል በማለት አቶ በሪሁ ተከራክረዋል፡፡

ማዕከላዊ መንግሥት ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚመረጥ የሕዝብ ተወካይ ሆኖ ለተመረጠበት ጊዜ ብቻ ከማስተዳደር በላይ፣ ከሕዝብ እኩል ወካይና ተወካይ በአንድ ላይ የመሬት ባለቤት ሊሆኑ የሚችሉበትን የሕገ መንግሥት አንቀጽ የአስተሳሰብ ትክክለኛነት ግን አላብራሩም፡፡

እኔ እንደሚመስለኝ ደርግ መሬትን ከግለሰቦች ወርሶ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ሲያደርግ፣ ሕዝብ ባለቤት መንግሥት ግን እንደ የሕዝብ ወኪልነቱ አስተዳዳሪ ማድረጉ ነበር፡፡ ደርግ ባለቤት እንዳለመሆኑና እንደ አስተዳዳሪነቱ ብቻ መሬትን በነፃ ለመጠቀም ያከፋፍል ነበር እንጂ የመሸጥ መብት እንደሌለው ያውቅ ነበር፡፡

ረቂቅ የኢኮኖሚክስ ጽንሰ ሐሳብ ሆኖ ባለሙያ ላልሆኑ ሰዎች በቀላሉ አይገባም እንጂ  ካፒታል፣ የሰው ኃይልና መሬት በጥቅል ኢኮኖሚያዊ አጠራራቸው የምርት ግብረ ኃይሎች ወይም የማምረቻ መሣሪያዎች በራሳቸው የፍጆታ ጥቅም ስለሌላቸው እንደ ሸቀጥ አይሸጡም፡፡ የሚሸጠውና የፍጆታ ዋጋ የሚያወጣው ምርት ለማምረት የሚፈለገው አገልግሎታቸው ነው፡፡

ሰው አይሸጥም፡፡ ከሰው ውስጥ የሚፈሰው የጉልበትና የዕውቀት አገልግሎት የፍጆታ መሸጫ ዋጋ አውጥቶ ይሸጣል፡፡ የካፒታል ዋጋ የሚወሰነው ከውስጡ በመፍሰስ የገቢ ምንጭ የሚሆነው የፍጆታ አገልግሎቱ ነው፡፡ የመሬት የፍጆታ መሸጫ ዋጋም የሚወሰነው ከውስጡ በመፍሰስ የገቢ ምንጭ የሚሆነው አገልግሎቱ ነው፡፡   

ለምሳሌ አንድ ማሽን በአሥር ሚሊዮን ብር ቢሸጥ ማሽኑ ምንም የፍጆታ ጥቅም አይሰጥም፡፡ የማሽኑ ዋጋ የሚወሰነው ለገዥው በጊዜ ብዛት በሚያስገኘው ተከታታይ ለፍጆታ የሚውሉ ገቢዎች አገልግሎት ልክ ነው፡፡ የማሽኑ ዋጋም የወደፊት ተከታታይ ገቢዎች የተጣራ አሁናዊ ካፒታላዊ ዋጋ (Net Present Capitalized Value of future Streams of Incomes) ይባላል፡፡

መሬትን ለ99 ዓመታት በሊዝ የተከራየ ሰውም የሚከፍለው የኪራይ ዋጋ የመሬቱን አገልግሎት ለ99 ዓመት በፍጆታ በመጠቀም የሚያገኘውን የገቢ መጠን የሚያህል ነው፡፡ የመሬት አገልግሎት ለዘጠና ዘጠኝም ሆነ ለመቶ ዓመት ከተሸጠም ለዚያን ያህል ጊዜ መሬት የገዥው ግለሰብ መጠቀሚያ ንብረት ስለሚሆን የሕዝብ መጠቀሚያ ንብረት መሆኑ ይቀራል፡፡ ኢሕአዴግ  ለዘጠና ዘጠኝ ዓመት አከራየሁ እንጂ አልሸጥኩም ቢል፣ አባባሉን ከላይ የተመለከትነው የምርት ግብረ ኃይሎች ወይም ማምረቻ መሣሪያዎች አገልግሎት ሽያጭና ግዥ ግብይት ጽንሰ ሐሳብ አይደግፈውም፡፡ 

ይህ በኢኮኖሚ ጥናት የምርት ግብረ ኃይሎች ወይም ማምረቻ መሣሪያዎች መሬት ካፒታል ወይም የሰው ጉልበት አለመሸጥና የሚሸጡት ከውስጣቸው የሚፈሱት አገልግሎታቸው መሆኑን ማወቅ፣ የገበያ ኢኮኖሚ ውጣ ውረድ ውጥንቅጦችን ለመረዳትና የዋጋ አወሳሰን ሥርዓትን ለመገንዘብ ቢያገለግልም፣ ኢኮኖሚክስ በኢኮኖሚያችን ውስጥ ስላልሰረፀ ያሻንን እንናገራለን፡፡ በሕገ መንግሥት ውስጥ የምናካትታቸው አንቀጾች ሳይቀሩ የትርጉም ስህተት ላይ ይወድቃሉ፡፡

ምንም ነገር አገልግሎትንም ሆነ ቁሳዊ ሸቀጥን ለመሸጥ ባለቤት መሆን ያስፈልጋል፡፡ ወኪል ከባለቤት ፈቃድ ሳያገኝ ምንም ነገር መሸጥም አይችልም፡፡ ኢሕአዴግ በምርጫ 97 ከቅንጅት ጋር ሲወዳደር መሬት ወይም የመሬት አገልግሎት አይሸጥም አይለወጥም ብሎ የተከራከረበትን አቋሙን ቀይሮ፣ እንደ የሕዝብ ወኪል አስተዳዳሪነት ከማከፋፈል በላይ እንደ ባለቤት ለራሱ የመሸጥ መብትም ሰጠ፡፡ የካሬ ሜትሩን ዋጋም በሞኖፖል ሽያጭ አዛብቶ በአዲስ አበባ አንዳንድ ሥፍራዎች ሦስት መቶ ሺሕ ብር አደረሰ፡፡ ማዕከላዊ መንግሥቱም ክልላዊ መንግሥታትም ይህን የመሬት ባለቤትነት ሥልጣን ለራሳቸው ሰጥተው፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በጥቂት ግለሰቦች የመሬት ሽያጭ መስገብገብ አተረማመሱ፡፡ የገበያ ዋጋ አወሳሰን ሥርዓትን አወዛገቡ፡፡

ደርግ የከተማ ቦታን በማኅበር አደራጅቶ ከሞርጌጅ ባንክ መኖሪያ ቤት ሠሪዎች በዝቅተኛ ወለድ እንዲበደሩ በማድረግ በማከፋፈል፣ የገጠር መሬትንም በአምራቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት አደራጅቶ በግልና በወል ይዞታ እንዲጠቀሙ አደረገ እንጂ መሬትን ለሽያጭ አላቀረበም ነበር፡፡

ኢሕአዴጎች ያደረጉት ግን በብሔረሰብ ክፍፍል ተወላጅ በተወላጅነቱ፣ ባለሥልጣን በባለሥልጣንነቱ ከመንግሥት ተመርቶ ወይም በርካሽ ገዝቶ ለሌላ ብሔረሰብ ተወላጅ ወይም ለእውነተኛ ተጠቃሚው በውድ ዋጋ እንዲሸጥ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ከተሞች የመገበያያ ዋጋው በሻጭና በገዥ የገበያ ስምምነት መሆኑ ቀርቶ፣ መንግሥት በሔክታር ይህን ያህል እያለ እስከ መወሰን ደርሷል፡፡ የተሸጠውን መልሶ መቀማትም አጋጥሟል፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ሻጩ መንግሥት ራሱ ብቻ በመሆኑም በሞኖፖል ገበያ ዋጋው ሰማይ የነካው፣ የመሬት አገልግሎት ወደ ፊት የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር ዋጋው ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ሲታሰብ በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡

እቴጌ ጣይቱ አዲስ አበባን ሲቆረቁሯት የአዲስ አበባ መሬት አገልግሎት ዋጋ በካሬ ሜትር ምናልባትም ከጥቂት ሣንቲሞች በላይ አይሄድም ነበር፡፡ ስለሆነም መንግሥት ከፈጠረው የሞኖፖል አርቲፊሻል ዋጋ ጎን ለጎን የአዲስ አበባን መሬት አገልግሎት ከፍተኛ ዋጋ የፈጠሩት፣ አዲስ አበባን ለኑሮና ለንግድ ተፈላጊ ከተማ ያደረጉት የአዲስ አበባ የቀድሞና የዛሬ ነዋሪዎች ናቸው፡፡

አዲስ አበባን ከአዲስ አበቤዎች ጋር ለመጋራት የኦሮሚያ ክልል የመብት ጥያቄ አንስቶ በተወካዮች ምክር ቤት በይደር እንደተላለፈ ይታወቃል፡፡ ጥያቄው ተቋማዊ ተጠቃሚነትን ብቻ ሳይሆን ግለሰቦችም በተወላጅነታቸው፣ የክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ስለሚያገኙበት ሁኔታም የተመለከተ ነው፡፡

አዲስ አበባን የፈጠሯትና ትልቅ ዋጋ ያሰጧት የአዲስ አበባ ኗሪዎች በመሆናቸው፣ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች በተወላጅነታቸው ከአዲስ አበባ ኗሪዎች የበለጠ የኮታ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ዜጎችን በተወላጅነታቸው ልዩ የመሬት ተጠቃሚ ማድረጉ ትክክል ካለመሆኑም ባሻገር፣ የተወላጅነት ተጠቃሚነት ጣይቱ በቆረቆሯት ወቅት ያወጣ በነበረው በሣንቲሞች የአንድ ካሬ ሜትር ዋጋ ደረጃ ነው? ወይስ አሁን የአዲስ አበባ ኗሪዎች በፈጠሩት ተፈላጊነት ምክንያት ሦስት መቶ ሺሕ ብር በደረሰው የአንድ ካሬ ሜትር ቦታ ዋጋ ልክ ነው የሚል ኢኮኖሚያዊ ጥያቄም ያስነሳል፡፡

ጉዳዩን ለማብራራት በምሳሌ ተጠቀምን እንጂ ዋናው ጉዳይ የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የመሬት ተጠቃሚነት ሳይሆን፣ የመሬት ይዞታ ሥሪትና የመሬት አገልግሎት ዋጋ አወሳሰን በኢኮኖሚያዊ ጽንሰ ሐሳብ ደረጃ በሳይንሳዊ መንገድ የሚመለከቱት እንጂ፣ ጽንሰ ሐሳብ ምን ይሠራልኛል የሚል ሥልጣን የያዘ መንግሥት የፈለገውን አዋጅ የሚያውጅበት እንዳልሆነ ለማስገንዘብ ነው፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታን ለማብራራት እንደገለጹት፣ የክልል መንግሥታት መዋቅሮች የመሬት ወረራን መከላከል አቅቷቸው ከሕጋዊ ሥርዓት ውጪ በሆነ መንገድ የሰዎችን እንቅስቃሴ መቆጣጠር አስፈልጓል፡፡ ግን እስከ መቼ ነው በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ የምንተዳደረው?

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የአገሪቱን ኢኮኖሚ ችግር እንደሚፈቱ ትልቅ እምነት ተጥሎባቸዋል፣ በዕውቀት አምናለሁ ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ቃላቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ አያስፈልገኝም በሚለው የኢሕአዴግ መስመር ከመሄድና ያለጽንሰ ሐሳብ መጓዝ አይቻልም ከሚለው ሳይንሳዊ ማረጋገጫ አንዱን መምረጥ ይኖርባቸዋል፡፡

በተለይም ለአገሪቱ ከባድ የኢኮኖሚ ነቀርሳ የሆነውን የመሬት ጉዳይ በሳይንሳዊ ጽንሰ ሐሳብ መፍታት? ወይስ በአዲስ ራዕይ የኢሕአዴግ ልሳን እንደ ተጠቀሰው በዘፈቀደ እየተጓዙ ተግባርን መፈተሽ? ከሚለው የኢሕአዴግ አካሄድ ሊመርጡ ይገባል፡፡ ለመምረጥም ባለሙያዎች በሙያቸው ዕውቀት እንዲናገሩ በማበረታታት አመለካከታቸውን መስማት ያስፈልጋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዳሉት ታዋቂነት አዋቂነት ስላልሆነም ታዋቂንና አዋቂን መለየት ያስፈልጋል፡፡

ለዚህ ነው የሚዲያ ሰዎች ዓላማቸው ፕሮግራማቸውን ከመሸጥ ባሻገር፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግር ለማስወገድ ከሆነ ከታዋቂነት ይልቅ አዋቂነት ላይ አትኩረው እንዲሠሩ የማሳስበው፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻሉ የአገር ፍቅር ስሜትን የሚነጥቁ ቢሆንም፣ እንደ ወትሯቸው የስፖርትና የሙዚቃ ፕሮግራማቸውን ቀጥለውበት ሰውን ቢያዝናኑ ይመረጣል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...