Tuesday, October 3, 2023

ተስፋ የሰነቀው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግርና በእንከን የተሞላው ዝግጅት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ አንድ ጊዜ ብዙ ሺሕ ሕዝብ ማስተናገድ የሚችለው የሚሊኒየም አዳራሽ ከተገነባና አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አሥረኛ ዓመቱን ደፍኗል፡፡ ግዙፉ አዳራሽ የተገነባው ኢትዮጵያ በራሷ አቆጣጠር የምታከብረውን ሚሊኒየሟን ለመቀበል ሲደረግ የነበረው የዝግጅት አካል አንዱ ሆኖም ነበር፡፡

ሙሉ ወጪውን የሸፈኑት ሼክ መሐመድ አል አሙዲ ሲሆኑ፣ በጀቱም ዘጠና ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ በወቅቱ አግራሞትን ፈጥሮ የነበረው ሙሉ ወጪው በባለሀብቱ መሸፈኑ ብቻ ሳይሆን፣ በአሥር ቀናት ውስጥ የአገሪቱ ግዙፍና ዘመናዊ አዳራሽ ተገንብቶ መጠናቀቁ በመቻሉ ነበር፡፡

አገሪቱ ሚሊኒየሙን በተቀበለችበት ዕለት በዚሁ አዳራሽ የተደረገው ሥነ ሥርዓት ደማቅ፣ ትልቅና በአብዛኛው ዜጋ ዘንድ ትውስታን ጥሎ ያለፈ ዝግጅት ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ከዋና ዋና ትዕይንቶች ውስጥ በቀዳሚነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት ትውስታዎች ውስጥ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ወትሮ ከሚታወቁበት፣ በሕዝብ ባሳዩት ውጫዊ ገጽታ ለየት ብለው መቅረባቸው ነበር፡፡ ምናልባትም በነጭ ባህላዊ አለባበስ ባልተለመደ የአነጋገር ለዛ ለሕዝብ የታዩበት ቀን እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ እንዲሁም በፊት ከሚታወቁበት አነጋገር በተለየ የኢትዮጵያን ጥንታዊነትና ታሪካዊነት በማውሳት በአንድነት፣ በፍቅር፣ በመቻቻልና በመዋደድ የመኖር አስፈላጊነት ንግግር ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ እንደሳቸው ሁሉ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በባህላዊው አለባበስ አጊጠው የታዩትም በዚሁ አዳራሽ ነበር፡፡

ባልተለመደ ሁኔታም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባለቤታቸውና የቀድሞዋ ቀዳማዊ እመቤት (ወ/ሮ አዜብ መስፍን) ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲደንሱ የታዩበት ታሪካዊ ምሽት ነበር፡፡ ለዚህም ታዋቂው ሱዳናዊ ድምፃዊ መሐመድ ወርዲ በአዳራሹ ተገኝቶ በማቀንቀን በዕለቱ የታደሙ ባለሥልጣናትን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን፣ ዲፕሎማቶችንና በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎችን በደስታና በተስፋ ሲያስጨፍር ነበር በዓሉ ያለፈው፡፡

ሌላው በዕለቱ ከማይዘነጉና ምናልባትም ባልተጠበቀ ሁኔታ ቀርበው ሕዝብን ካስደመሙት ውስጥ፣ በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር የነበሩት አልፋ ኦማር ኮናሬ ነበሩ፡፡

በዓሉ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ሚሊኒየም ጭምር እንደሆነ በማውሳት የኢትዮጵያን የሦስት ሺሕ ዘመን ታሪክ ወደ ኋላ በመዳሰስ ያቀረቡት አነቃቂ ንግግር ለብዙዎች አይረሴ ነበር፡፡ ሚሊኒየሙ ሲከበርም በዚያች ዕለት እንዲሁም ዓመቱን ሙሉ የኢትዮጵያ ትንስዔ ተደርጎ ስለፍቅር፣ ስለአንድነትና ስለብልፅግና ብዙ ተብሎለታል፡፡ ብዙሙ ተዚሞለታል፡፡ ‹‹በልዩነት አንድነት›› በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ ህዳሴ ተብሎ ተደስኩሮታል፡፡ ይኸው የሚሊኒየም በዓል የተበሰረበት ዘመናዊና ግዙፍ አዳራሽ ላለፉት አሠርት ዓመታት የተለያዩ ሕዝባዊና መንግሥታዊ ዝግጅቶች ሲቀርቡበት ቀጥሏል፡፡ አቶ መለስና እስካለፈው ወር ድረስ የተኳቸው አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተውበታል፡፡ ኮንሰርቶችና የተለያዩ ባህላዊ ዝግጅቶች እየቀረቡበት ሲቀጥል፣ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችና የንግድ ዓውደ ርዕዮችንም ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡ ሃይማኖታዊ ዝግጅቶችና ትምህርቶች ሲሰጡበትም ይታያል፡፡ በዚህ ምክንያት ሚሊኒየም አዳራሹ የመስተንግዶ ልምድ አካብቷል፡፡

አገሪቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት ካለፈችበት ፖለቲካዊ ክስተቶች አንፃር ለአብዛኛው ዜጋ እንደ መነጋገሪያም እንደ ሥጋትም ተደርጎ የሚቆጠር የአገሪቱ ሕዝብ አንድነት ጉዳይ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ከሚከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት መተግበር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ተስፋና የመከፋፈል ሥጋቶች እንደነበሩም ይታወቃል፡፡

በተለይም የሕዝቦች አንድነት ተሸርሽሮ ሥጋት ላይ ወድቋል ብለው ለሚያስቡ ዜጎች የተስፋ ብልጭታ ታይተውባቸዋል ከሚባሉ ክስተቶች መካከል በዚሁ አዳራሽ በ2000 ዓ.ም. የተደመጠው የወቅቱ መሪዎች ንግግር ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፉት አሥር ዓመታት አገሪቱ ያለፈችበት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያ እውነታዎች በሚሊኒየሙ አጥቢያ ከነበረው ተስፋ ፍፁም ተቃራኒ ነበር፡፡ ይልቁንም ተስፋ ቢስነት ነግሶ ሥራ አጥነት የተንሰራፋበት፣ ከአንድነት ይልቅ በብሔርተኝነትና በጎሳ ግጭት አገሪቱ ሐዘን ላይ የወደቀችበት አጋጣሚዎች ተከስተዋል፡፡ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት መስቀለኛ መንገድ ላይ ሆና ትልቅ አደጋ ተጋርጦባት መቆየቷ የሚታወቅ ነው፡፡

የአገሪቱ ሰላም ከሥጋት አልፎ ተናግቷል፣ ወይም ደፍርሷል የሚባል ደረጃም መድረሱን በቅርቡ የታዩ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችና ግጭቶችን ዋቢ ማድረግ ይቻላል፡፡ እነዚህን ክስተቶች ተከትሎም በአንድ ዓመት የጊዜ ልዩነት ብቻ ከአንድም ሁለቴ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ አሁንም አገሪቷ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ምናልባት ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ አንፃራዊ መረጋጋት ያለ ቢመስልም፣ አገሪቱ ሙሉ በሙሉ ወደቀደመው አንፃራዊ መረጋጋቷ ደርሳለች ብሎ ደፍሮ መናገር አይቻልም፡፡

ነገር ግን በቅርቡ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መመረጥ ጋር ተያይዞ ለበርካቶች ተፈጥሮ ከነበረው ሥጋት በመጠኑም የመተንፈስ ስሜትና ተስፋ ያጫረ ስሜት በርካቶችን አላብሷል፡፡

በተለይም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት (መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም.) በፓርላማው ያደረጉት ንግግር፣ በሕዝብ ውስጥ የአንድነት ስሜት ስለመጫሩ ይነገራል፡፡ ይኼንን ተስፋ ጫሪ ንግግራቸውን እሑድ መጋቢት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ከ25 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በታዋቂው የሚሊኒየም አዳራሽ በድጋሚ አሰምተዋል፡፡

ዕለቱም ከአዲስ አበባና ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንደመጡ የተነገረላቸው የመጡ ታዳሚዎች ጋር የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በአካል ተገኝተው ያደመጡ ሲሆን፣ ሚሊዮኖች በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት ተከታትለውታል፡፡

የዝግጅቱ ዝብርቅርቅ ተቃርኖ

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሁንም ድረስ መነጋገሪያና ታሪካዊ የተባለውን የመክፈቻ (የቅቡልነት) ንግግራቸውን በማሰማት በዓል ሲመታቸው ካለፈ ገና 17ኛ ቀናቸው ነው፡፡

ከእሑድ ዕለቱ (ሚያዝያ 7 ቀን 2010 ዓ.ም.) መሰናዶ ከተለያዩ የኅበረተሰብ ክፍሎች ጋር በሚሊኒየም አዳራሽ፣ በማግሥቱ ሰኞ ምሽት በሸራተን አዲስ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ እነዚህን ጨምሮ በመጀመርያዎቹ 15 ቀናት የሥልጣን ቆይታቸው በአጠቃላይ ስምንት ሕዝባዊ ውይይቶች ወይም መሰናዶዎችን ታድመዋል፡፡

በሲመታቸው ዕለት በፓርላማ፣ በዚያው ቀን በፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የተደረገላቸው የእራት ግብዣ፣ በጅግጅጋ፣ በአምቦና በመቐለ ያደረጓቸው ክልላዊና አገር አቀፍ ዝግጅቶች ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሰየሙበት  ቀን ጀምሮ በየሁለት ቀኑ ከሕዝብ ጋር ተገናኝተዋል ሊባል ይችላል፡፡

በበርካቶች ዘንድ እንደ ትዕይንት ተደርጎ ከሚቆጠረው የፓርላማው ንግግራቸው ቀጥሎ፣ የእሑዱ የሚሊኒየም አዳራሹ ዝግጅት ቀደም ብሎም ተጠባቂ ነበር፡፡ ይኸው በክልል ከተሞች ካደረጓቸው ሦስት ጉብኝቶች በኋላ አዲስ አበባ ላይ በሚደረገው ዝግጅት በርካቶች በጉጉት የጠበቁት ቢሆንም፣ በአዳራሹ የተስተዋለው የዝግጅት ችግር ግን የሚያበሳጭ እንደነበር ሪፖርተር በሥፍራው አስተውሏል፡፡

በዕለቱ የተስተዋሉት ችግሮችና እንከኖች ከአዳራሽ የውስጥ ችግሮች ብቻ የተወሰኑ ሳይሆን፣ ከአዳራሽ በፊት የነበረ የቅድመ ዝግጅት ድክመትንና መዘበራረቅን በግልጽ ያሳየ ነበር፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ከ25,000 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ቀድሞ የተነገረለት ዝግጅት፣ የታዳሚዎች ማንነትና በአዳራሽ የሚቀመጡበት ቦታ በአግባቡ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር ለማለት አይቻልም፡፡ ለአብነትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወጣቶች ጋር ይወያያሉ የሚል መረጃ ነበር፡፡ በተቃራኒው ግን ውይይቱ ከወጣቶች ጋር ሳይሆን፣ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር የሚል መረጃም ሲሰራጭ ነበር፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ መረጃዎች ሲወጡ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስብሰባው አዳራሽ ከተገኙም በኋላ የዕለቱን ዝግጅት በማስተዋወቅ ሲመሩ የነበሩ አንዴ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከመላው አገሪቱ የተወከሉ፣ አልፎ ተርፎም ከኢትዮጵያ ወጣቶች በማለት ታዳሚዎችን ግራ ሲያጋቡም ተስተውሏል፡፡

ተጠባቂው ጠቅላይ ሚኒስትር ምሽት 11፡35 ሰዓት አካባቢ በአዳራሹ ሲገኙ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ቢሆንም፣ የአዳራሹ በር ቀደም ብሎ ከቀኑ ከ6፡00 ሰዓት ጀምሮ ክፍት የነበረ በመሆኑ በርካታ ሰዎች ለረዥም ሰዓታት ለመጠበቅ ተገደው ነበር፡፡

ይኼ ደግሞ ዝግጅቱ የሚጀምርበት ሰዓት በአግባቡ ባለመገለጹ ችግር ሆኖ ታይቷል፡፡ ለዚህም ነው የስብሰባው ተሳታፊዎች ለስድስት ሰዓታት ያህል ለመጠበቅ የተገደዱት፡፡ በርካቶችም ተሰላችተው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መምጣት በፊት አዳራሹን ለቀው ሲወጡም መታዘብ ተችሏል፡፡ ብዙዎች መሰላቸታቸውን፣ የጊዜ አጠቃቀምና እርባና የሌለውን ጎጂ ልማድ በመጥቀስ ሲያማርሩም ተስተውለዋል፡፡

በርካታ ታዳሚዎች የት ቦታ ሆነው ዝግጅቱን እንደሚከታተሉ ባለማወቃቸው ሲተረማመሱና ግራ ሲጋቡ አምሽተዋል፡፡ ይኼ ትርምስ ደግሞ ለዝግጅቱ የተሰጠው ትኩረት ላይ ክፍተት መኖሩን ከማሳየቱ በተጨማሪ፣ በእንዲህ ዓይነት አገራዊ ዝግጅቶች ላይ ያለውን የብቃት ጥያቄ እንደሚያስነሳ ሌላው ማሳያ ነው፡፡

ከተጋባዣ እንግዶች በተጨማሪ ለሚዲያ ተቋማት ግብዣ ከማድረግ ባለፈ ምንም ትኩረት አለመሰጠቱ ሌላው አጠያያቂ የዝግጅቱ ክስተት ነበር፡፡ ከጥቂት የሚዲያ ተቋማት የመጡ ጋዜጠኞች በስተቀር በርካታዎቹ ለሥራቸው አመቺ ቦታ ሊሰጣቸው ባለመቻሉ፣ የሄዱበትን ሥራ ማከናወን አለመቻላቸውን በምሬት ሲገልጹ ነበር፡፡ የዚህ ችግር ሰለባ ከሆኑት የሚዲያ ተቋማት ውስጥ የሪፖርተር ዘጋቢና ፎቶግራፈር ሲገኙበት፣ ከበርካታ የግል ሚዲያ ተቋማት የተገኙ ደግሞ ዝግጅቱ ሳይጠናቀቅ ጥለው እስከ መሄድ ተገደዋል፡፡

በዝግጅቱም አመቺ ቦታ አግኝተው ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ የተመቻቸላቸው ኢዜአ፣ ኢቢሲና ጥቂት የመንግሥት ሚዲያ ተቋማት ብቻ ነበሩ፡፡ ይኼ ሁኔታ ሁልጊዜም የሚከሰት ሲሆን፣ በመንግሥት ተቋማት የግል ሚዲያ ተቋማትን እንደ እንጀራ ልጅ ማየት የተለመደ ማሳያ ነው፡፡

በቅርቡ በኢሕአዴግ ብሔራዊ ጉባዔና ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከታቃዋሚ (ተፎካካሪ) ፓርቲዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር በነበራቸው የእራት ግብዣ ላይ ተስተውሏል፡፡ በሸራተን አዲስ ሰኞ ዕለት በተካሄደው ውይይት ወቅት ይኼው ተመሳሳይ ችግር በድጋሚ ተከስቷል፡፡

በሚሊኒየም አዳራሽ ዝግጅት ከተስተዋሉት ለየት ያሉና ያልተለመዱ ክስተቶች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ቀደም ብሎ ለመጀመርያ ጊዜ፣ የሃይማኖት መሪዎች ዝግጅቱን በምርቃት እንዲከፍቱ መደረጉ ነው፡፡ ይኼ ሁኔታ በዕለቱ ከታዳሚዎች አድናቆት የተቸረውም ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ግን አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከስቶ መጠነኛ ድንጋጤ የፈጠረ ትዕይንት ታይቷል፡፡

ከበርካታ የሃይማኖት መሪዎች ምርቃት ቅድሚያውን በመውሰድ የጀመሩት የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ ሲሆኑ፣ ፀሎተ ቡራኬ መስጠት ሲጀምሩ ከቆሙበት ሥፍራ ትይዩ ከጣሪያው ላይ የኤሌክትሪክ ገመድ የፈጠረው የእሳት ብልጭታ ድንጋጤ ፈጥሮ ነበር፡፡ ምንም እንኳ እሳቱ ጉዳት ሳያደርስ ወዲያው ቢጠፋም ፓትሪያርኩ ንግግራቸውን ለመግታት ተገደዋል፡፡

በሌላ በኩል በርካታ ወጣቶች የአዳራሹን ዝግጅት በከፍተኛ ጩኸትና ጭብጨባ አድምቀውት አምሽተዋል፡፡ በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና የአቶ ለማ መገርሳ (የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት) የታተመ ፎቶግራፍ ከፍ አድርገው ሲያውለበልቡም ታይተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ‹‹ገዱ የታለ?›› ሲሉ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ለምን እንዳልተገኙ ሲጠይቁም ተሰምተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕቅድና ምኞት

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓል ሲመታቸው ወቅት ያቀረቡት ንግግር በቅርፁም ሆነ በይዘቱ አስደማሚ እንደነበር ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ በወቅቱ በእሳቸው የሥልጣን ዘመን የይቅርታና የዕርቅ ተግባራት እንደሚያከናውኑም ገልጸው ነበር፡፡ ሰፋፊ አገራዊ ጉዳዮችንም መዘርዘራቸው ይታወሳል፡፡ በእሑድ ዕለት ንግግራቸውም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ሐሳብ ቢያነሱም፣ ተጨማሪ አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችንም አካተው ነበር የቀረቡት፡፡  

ባለፉት ሦስት ዓመታት አጋጥሞ በነበረ ግጭት አገሪቱ ችግር ውስጥ ገብታ እንደነበር ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ችግሩ በሕዝቦች አብሮ የመኖርና የአንድነት ባህል መቀረፉን ጠቅሰዋል፡፡ የአገሪቱ ሀብት ሕዝቦቿ መሆኑን ጠቁመው፣ በሰላም ዕጦት ምክንያት በሕዝቦች መካከል አለመተማመን ተፈጥሮ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳይገታ፣ ሁሉም በአገራዊ ኃላፊነት ለአገሩ ዘብ እንዲቆም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ለኢኮኖሚው ዕድገት እንቅፋት የሆነውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍም ጠንካራ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ነው የተናገሩት። የማምረቻ ዘርፉን ማጠናከርና በተለይም የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን አቅም በማጠናከርና ምርቶችን በማብዛት፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ምርት ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል። በተጨማሪም ለውጭ ምንዛሪ ብክነት ምክንያት እየሆኑ ባሉ ግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ ክትትል በማድረግ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የእርምት ዕርምጃ እንደሚወሰድም አስረድተዋል።

መንግሥት አሁን በሕዝቡ ዘንድ የታየውን ተስፋ ዕውን ለማድረግ በፅናት እንደሚሠራ ጠቅሰው፣ ሕዝቡም ባለፉት ዓመታት በአንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለመካስ መሥራት ይገባዋል ብለዋል። በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚታዩ ቅሬታዎችን ለመፍታትም፣ የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሰና ሙስናና ብልሹ አሠራርን የሚጠየፍ ሠራተኛ ለመፍጠር ይሠራል ነው ያሉት።

በተቋማት የሚደረገው ምደባ ዕውቀትና ክህሎትን መሠረት ያደረገ እንደሚሆን ገልጸው፣ በዚህም የመንግሥት የማስፈጸም አቅም ይሻሻላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተንዛዛ ስብሰባ የሚባክን ጊዜና ሀብትን ለማስቀረትና የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ የሚያስችል፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጅ የታገዘ መንግሥታዊ አሠራር እንዲኖር እንደሚደረግም ገልጸዋል። ከትምህርት ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት የነበረው የትምህርት ሥርዓት የጥራት ጉድለት የነበረበት መሆኑን፣ አሁን ግን ጥራት ላይ ያተኮረ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት፣ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ጥረት እንደሚደረግም አውስተዋል።

በመስኖ ልማት፣ በአርሶ አደርናአርብቶ አደር አካባቢዎች፣ እንዲሁምታዳጊ ክልሎች ድጋፍ በማድረግ የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል ብለዋል። በዲፕሎማሲው መስክም፣ ‹‹መርህን መሠረት ያደረገ መልካም ግንኙነት በተለይምአፍሪካውያን አገሮች ጋር በመሥራት፣ በምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምንጫወተውን ሚና አጠናክረን እንቀጥላለን፤›› ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ እንዲጎለብት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መጠናከር እንደሚኖርባቸው ጠቅሰው ቀጣዩን ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ታማኝ ለማድረግ መንግሥት በቅንጅት እንደሚሠራ አስረድተዋል።ፍትሕ ሥርዓቱ ለውጥ የሚያመጡ የመፍትሔ ዕርምጃ እንደሚወሰድ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሥርዓቱ የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥበት፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳና ሕዝቡ ትክክለኛ ፍርድ የሚያገኝበት እንዲሆን እንደሚደረግ አስታውቀዋል። ከዚህ ባለፈም ለቅሬታ ምንጭ የሆኑ አንዳንድ ሕጎች ላይ ማሻሻያ እንደሚኖር ጠቁመዋል።

የፀጥታና የደኅንነት ተቋማትም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆነው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚጠብቁ እንዲሆኑ ይሠራል ሲሉም በመልዕክታቸው አስታውቀዋል። የሚዲያ ተቋማትም በአገር ግንባታ፣ ሰላምና ልማትን ከማረጋገጥ አኳያ፣ እንዲሁም ከወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል። የሃይማኖት መሪዎች ትውልድ በመቅረፅ፣ ሰርቆ የመክበር አካሄድንና ሙስናን በማውገዝ፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እሴቶችን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በማተኮር፣ እንዲሁም መምህራን ትውልድን በመቅረፅ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት ደግሞ ወጣቶች የአገሪቱ የለውጥ አንቀሳቃሾች መሆናቸውን ተረድተው፣ ለአገር ዕድገትና ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። ካለፉ ታሪኮች ለአገር ዕድገትና ግንባታ የሚበጀውን በመውሰድ መሥራት ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በወጣትነት ያለውን ልዩ ኃይል ሀብት ለማፍራትና አገራዊ ዕድገት ለማምጣት መጠቀም እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አካል ጉዳተኞችን በአገር ግንባታ በማሳተፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት ይሠራል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ30 ደቂቃ ንግግራቸው ውኃ ያልቀረበላቸው በመሆኑ ድካምና ዝለት ይታይባቸው ነበር፡፡ ንግግራቸውንም በትግል የጨረሱ ይመስሉ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -