Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙስናን ተጠይፈው የመንግሥትን ነጋዴነት እንደሚያስቀጥሉ ያስታወቁበት የምክክር መድረክ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከንግዱ ማኅበረሰብ የመተዋወቂያ የምክክር መድረክ ሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. አካሂደዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነጋዴዎቹን በተዋወቁበት የመጀመርያው ንግግራቸው ‹‹ከሀብታሞች ጋር ትገናኛለህ ስላሉኝና ደሃ መንግሥት እንዳልሆንኩ እንድታውቁ በማለት ሽክ ብዬ ነው የመጣሁት፤›› በማለት ለፈገግታና ለተግባቦት እንዲያዋዛላቸው በማድረግ መድረኩን አስጀምረዋል፡፡

  የንግዱ ኅብረተሰብ በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት በኩል አንኳር ያላቸውን ጥያቄዎች በፕሬዚዳንቱ  መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) በኩል አቅርቧል፡፡ ከንግድ ምክር ቤቱ ጥያቄዎች ባሻገር፣ በምክክር መድረኩ የተገኙት የንግዱ ኅብረተሰብ አባላትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋባዥነት በርካታ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡ በዕለቱ ከንግድ ምክር ቤቱም፣ ከተሳታፊዎችም ከቀረቡት ውስጥ ሚዛን የደፉት የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የመሬት አስተዳደር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ መስተጓጎል፣ ብድር የማግኘት ችግር፣ የመልካም አስተዳደርንና የመሳሰሉትን የተመለከቱ ነበሩ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከአገር የወጡ ነጋዴዎች ወደ አገር ቤት ይመለሱ የሚሉ ጥያቄዎችም ተደምጠዋል፡፡ ‹‹እዚህ ፕሮግራም ላይ ከባለቤቴ ጋር እንድጠራ ለምን አልተደረገም?›› ያለ ነጋዴም ነበር፡፡ መንግሥት ከንግድ ሥራዎች ይውጣ የሚል ጥያቄም በመድረኩ ተስተናግዷል፡፡

  የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የጉምሩክ  አሠራሩን ሳይታሰብ ለውጦ ችግር ውስጥ ጥሎናል በማለት ወቀሳውን ያሰማ የኢንዱስትሪ ዘርፍም ነበር፡፡ ከቆዳ ኢንዱስትሪ የመጡት ባለሀብት ፍሳሽ ማስወገጃና ማጣሪያ ካልተከላችሁ ፋብሪካችሁን እንዘጋለን ተብለናል በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤት ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ትራክተር የሚቀረጥባት አገር ነች፡፡ እንዲህ መሆን አልነበረበትም፤›› በማለት ጥያቄ ያነሳ ተሳታፊም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽ ለመስማት ከሚጠባበቁት ወገን ነበር፡፡

  የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለግዥ ጨረታ ሲያወጡ የውጭ ዕቃ ካልሆነ በማለት ከጨዋታ ውጪ እንደሚያደርጓቸው የገለጹ የአገር ውስጥ አምራቾች ጥያቄም ተስተናግዷል፡፡ አንዳንዱ በግል የገጠመውን ችግር ሲናገር፣ ሌላው የተሰማራበትን ዘርፍ የተመለከተ ጥያቄ አስተጋብቷል፡፡ ‹‹የውጭ ባለሀብቶች እየደቆሱን ነው፤ መላ ይበጅላቸው፤›› ተብሎ ተጠይቋል ጠቅላይ ሚኒስትሩም ምላሽ አልነፈጉትም፡፡

  ከመድረኩ የቀረበው ጥያቄ ንግድ ምክር ቤቱ ካቀረባቸው በላይ በርካታ ነበሩ፡፡ ከእሳቸው ምላሽ አንፃር ሲታይ፣ ጥያቄው በርካታ ነበር፡፡ በዕለቱ ከተደረገው ውይይት የተወሰኑ ጥያቄዎችና ምላሾቻቸው እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

  ብድር

  ሁለቱ የመንግሥት ባንኮች ማለትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የፖሊሲ ባንኮች መሆናቸውን በመጠቆም ምላሻቸውን የሰጡት ዶ/ር ዓብይ፣ ጣልቃ በምንገባባቸው አካባቢዎች ፖሊሲያችንን የምናሳካባቸው ባንኮች ናቸው ብለዋል፡፡ የማበደር ብቃታቸው አሁን ካለው ከግሉ ዘርፍ አኳያ ገዘፍ ያለ አቅም እንዳላቸው ጠቁመው፣ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የግሉ ዘርፍ የሚበደረው ከእነዚሁ ባንኮች እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ በታዳጊ አገሮች መንግሥታት ድርሻቸውን የሚካፈሉት የቦንድ ሽያጭ በማከናወንና በሌላውም መንገድ እንደሆነ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የፖሊሲ ባንኮች ትልቅ ትኩረት የሚሰጣቸው ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ ሁኔታ ችግሮች እንደሚታዩ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ‹‹የሥራ ባህል ችግርና ሌብነት እየተጠናወተን ስለሆነ፣ በዘመድ አዝማድ ግንኙነት የምንሠራ ስለሆነ በዚያው ልክ በርካታ ችግሮች ያጋጥሙናል፡፡ ይህንን ችግር በአስተዳደራዊ ዕርምጃና በሕግ እንፈታዋለን፤›› ብለዋል፡፡ ችግሩ ተፈትቶም እንኳ የፖሊሲ ባንኮች የብድር ፍላጎትን ሙሉ ለሙሉ ይፈታሉ ብለው እንደሚያምኑ፣ ይህም የሚሆነውም የአቅም ውስንነት ስላለ ነው ብለዋል፡፡

  ‹‹ልማት ባንኮች የት ቦታ ጣልቃ ይግቡ? እነማንን ያግዙ የሚለውን ጊዜ ስጡንና አጥንተን ተወያይተን እንመልሳለን፡፡ ከፖሊሲ አንፃር የተነሳው ጥያቄ ግን በስብሰባ አይመለስም፡፡ በስብሰባ ይኼ ፖሊሲ ተቀይሯል፣ ታርዟል አይባልም፤›› በማለት ለማሻሻልም ለመቀየርም አዲስ ለማምጣትም ጊዜ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን አስተዳደራዊና ከሌብነት ጋር የሚያያዙት ችግሮችም በሚከናወኑ ሥራዎች እየተፈቱ ይሄዳሉ ብለዋል፡፡

  ‹‹የብድር አቅርቦትን ልክ እንደውጭ ምንዛሪው በቀላሉ የማንፈታው ችግር እንደሆነ ማወቅ አለባችሁ፡፡ አብዛኛው ሀብታም እያደገ ሲሄድ ሥጋትን እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ በባንክ ገንዘብ ስለሚሠራም የባንክ ብድር ፍላጎቱ ያድጋል፤›› ብለዋል፡፡

  ባደጉት አገሮች ብድር ተለምኖ የሚሰጥ ስለመሆኑ ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ባደጉት አገሮች እባክህ ተበድረህ ቤት ግዛ ይባላል፡፡ ብር ስላለና ክምችት ስላለ ነው፡፡ እኛ ጋ ከዚህ አልደረስንም፤›› ለሚለው ጥያቄ፣ ‹‹በተቻለ መጠን የማበደር ዘርፍ መረጣና ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን አካባቢዎች ለይተን ባለን አቅም ለማገዝ እንሞክራለን፤›› በማለት በዚህ መስክ ያለውን የአመራር ችግር እንደሚፈትሹ በመግለጽም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

  አገልግሎት

  ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች በተለያየ መንገድ ቀርበዋል፡፡ በተለይ በመሬት አቅርቦት፣ በኃይል፣ በኢንተርኔትና ስልክ አቅርቦት፣ በገቢዎችና በፍርድ ቤት ጭምር ተጠያቂነት የሌለበት ኢፍትሐዊ ሥርዓት እንደሚታይና የአገሪቱን ኢኮኖሚ እያሽመደመደው እንደሚገኝ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ገልጸው ነበር፡፡

  ‹‹ማገልገል የሚፈልግ፣ ወጣት፣ ምሁር፣ ባለሀብት፣ ባለሥልጣን የለም፤›› በማለት በዋቢነት ካነሱት ውስጥ ባለሥልጣናት በሳምንቱ መጨረሻ ቢያንስ አንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት ሄደው ያለክፍያ የማስተማር ወይም ገለጻ የመስጠት ባህል እንደሌለ ጠቅሰዋል፡፡ ሀብታም ብቻ ሳይሆን፣ ምርጥ ኮርፖሬት መሪ የሆኑ ሰዎች ልምዶቻቸውን ካላካፈሉ፣ ማስተማር ካልቻሉ ገንዘብ ብቻውን ችግር እንደማይፈታ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወጣቱን ብትመለከቱት ከተመረቀ በኋላ ቁጭ ብሎ ይጠብቃል እንጂ ሥራ እስከሚያገኝ ድረስ አካባቢ ማፅዳት፣ ማስጠናት የሚባል ነገር አይታሰበውም በማለት ኮንነዋል፡፡

  በቀደመው ጊዜ የነፃ አገልግሎት የመስጠት ልማድ እንደነበር በማስታወስ፣ አሁን ግን ይህ ነገር እንደማይታወቅ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹በትምህርቱ ከተመረቀ በኋላ አጎቱ በሆነ ባለሥልጣን የሥራ ልምድ አፅፎ ሥራ ይቀጠራል፡፡ በዚህ መንገድ አገር መቀየር አይቻልም፡፡ በነፃ ማገልገል መማር አለብን፤›› ብለዋል፡፡

  በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ያለውን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት መዘጋጀቱን በማመልከት፣ ችግሩን ለመቅረፍ ዝግጁ መሆኑን የሚያመለክት ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ መንግሥት አማራሪ በሚባሉ ቦታዎች ላይ የአመራር ለውጥ ይደረጋል ብለዋል፡፡

  መሬት

  ከመሬት አሰጣጥ ጋር የተገናኙ በርካታ ችግሮች በተለያዩ መንገዶች ቀርበዋል፡፡ ቦታ ለማግኘት ያለው ፍዳ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ ዘርፍ ያለው ሙስናም ጥግ ስለመድረሱ በመግለጽ ጭምር የመፍትሔ ያለ ሲባልበት ቆይቷል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ከመሬት ጋር የተያያዘ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ ‹‹መሬት ያባከንነው ሀብት ነው፡፡ ያልተጠቀምንበት ሀብት፤›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ‹‹እያንዳንዱ ባለመሬት መንግሥት አያውቀውም፡፡ ልክ እያንዳንዱን ዶላር እንደማያውቀው ሁሉ፡፡ ስንት ዶላር እንደገባ አናውቅም፡፡ የምናውቀው ባንክ ያለውን እንጂ፡፡ በመሆኑም በመሬት ላይ ትልቅ ሪፎርም ያስፈልጋል፤›› ያሉት ዶ/ር ዓብይ፣ ‹‹ለኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ የሶማሌና የአፋር በረሃ ያለውን እንዲሁም ከራያ ጀምሮ ወደታች ያለውን በረሃማ አካባቢ በመስኖ ማልማት ብንችል ኢትዮጵያ እንኳን ለራሷ ስንቱን ለመመገብ በቻለች ነበር፤›› ብለዋል፡፡ የመስኖና የሜካናይዜሽን ግብርና አስፈላጊነትንም አንስተዋል፡፡ ‹‹በእኛ ዕቅድ ውስጥ ቅድሚያ የሰጠነው፣ የምናሻሽለው መዋቅር፣ በጣም የተሻለ አመራር የምንመድብበትና ባለን አቅም በጀት የምንመድብበት ዘርፍ ግብርና ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ይህንን በጥቂት ቀናት ውስጥ መዋቅር ስናስተካከል የምታዩት ይሆናል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

  ኃይል

  በኃይል እጥረትና መቆራረጥ ሳቢያ የሚፈጠሩ ችግሮች በተደጋጋሚ ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መድረኮች ለዚህ ችግር ከመንግሥት ሲሰጥ የነበረው ምላሽ ተመሳሳይ ነበር፡፡ በአፍሪካ ከፍተኛውን ኢንቨስትመንት በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ላይ ያዋለው የኢትዮጵያ መንግሥት ስለመሆኑ የጠቆሙት ዶ/ር ዓብይ፣ ከኃይል ማመንጨት በኋላ ግን ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ ኃይል ማመንጨት ማለት የተሻለ ኃይል አለ ማለት እንዳልሆነና በባህሪውም ኃይል እንደ ውኃ እንደማይከማች አስረድተዋል፡፡ ኃይል አንዴ ከመነጨ በኋላ መጠቀም ግድ ነው ካልሆነ ይባክናል በማለት ኢነርጂ ለመቆጠብ የሚያግዝ ቀላል ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ የሚመረተውን ኃይል በአግባቡ ማሰራጨት ላይ ችግር እንዳለ ጠቅዋሰል፡፡ የኃይል ሥርጭትና ማስተላለፍ ላይ የሚታዩት ችግሮች በበቂ እንዳልተፈቱ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አገሪቱ የምታመነጨው ኃይል በማስተላለፍ ችግር ሳቢያ የምታባክነው ኃይል በጣም አስደንጋጭ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከምናመርተው አንድ መቶ ኪሎ ዋት ቢያንስ ከ30 እስከ 40 በመቶው ይባክናል፤›› ብለዋል፡፡ ተመርቶ አገልግሎት ሳይሰጥ የሚጠፋው ኃይል አስደንጋጭ መሆኑን ለማሳየት ያደጉ አገሮችን አፈጻጸም ገልጸዋል፡፡ ባደጉ አገሮች የኃይል ብክነቱ ከአራት እስከ ሰባት በመቶ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ኃይል ለማመንጨት ኢንቨስት በተደረገው መጠን ስርጭትና ማስተላለፊያዎች ላይ እንዳልተሠራ በማመን አገልግሎቱ ወደ ግሉ ዘርፍ መሄድ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ሽቦ መቀጠል የለበትም፡፡ ነገር ግን በብዙ ያደጉ አገሮች ውስጥ በኃይል ማመንጨት መስክ የግል ዘርፉ ሁለት ሥራ ይሠራል፡፡ አንደኛው ቁጠባ ሲሆን፣ ሁለተኛው አማራጭ ኃይል ይፈጥራል፡፡ ቤት ሲገነቡ መንግሥትን የኤሌክትሪክ ኃይል አይጠይቁም፡፡ ቢያንስ ሀብታሞች የፀሐይ ኃይል ነው የሚጠቀሙት፤›› በማለት ባለሀብቱ በአማራጭ ኃይል እንዲጠቀም አሳስበዋል፡፡

  ‹‹ባለሀብቶች ከቻላችሁ የፀሐይ ኃይል፣ ካልቻላችሁ ጄኔሬተር በመጠቀም የእናንተን ድርሻ ኮንዶሚኒየም እንድናበራበት መፍቀድ ይኖርባችኋዋል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አማራጭ ኃይል ለመጠቀም ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ሲስተጓጎሉ ቆሻሻ አከማችቼ ኢነርጂ ላውጣ ብለው በጣም ብዙ የሚሰቃዩ ሰዎች አሉ፡፡ እሱን እናስተካክላለን፡፡ በተለያዩ ከተሞች ያሉትን የቆሻሻ ክምችት ወደ ኃይል መቀየር የሚፈልግና ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልግ ካለ ያለፈውን ቢሮክራሲ ቆርጠን እናግዛቸዋለን፤›› በማለት መተማመኛ ሰጥተዋል፡፡

  የውጭ ኢንቨስተር

  በሰፊው የምክክር መድረክ በንግድ ምክር ቤቱ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል ያልተገባ የንግድ ወድድርን የተመለከተው ይጠቀሳል፡፡ ይህንንም ፕሬዚዳንቱ እንዲህ በማለት አቅርበውት ነበር፡፡

  ‹‹የአገራችን የንግድ አሠራር የአገር ውስጥ ባለሀብትን ከውጭ ከሚመጡ ባለሀብቶች ከፍተኛ ጫና ለመታደግ፣ አነስተኛ የንግድ ሥራዎችንና የተወሰኑ ስትራቴጂክ ዘርፎችን ለአገር ውስጥ ባለሀብት ብቻ ከልሎ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን አገራችን የአኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናና የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትና ትስስር አካል መሆኗ ስለማይቀርና ከለላው የማይቀጥል ሊሆን ስለሚችል፣ የመወዳደር ብቃታችንን ልናጠናክረው ይገባናል፡፡ በዚህም እኛም የራሳችንን የቤት ሥራ እንሠራለን፣ መንግሥታችንም ከጎናችን ቆሞ የመወዳደር አቅማችንን በቀጣይነት ሊያጠናክርልን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

  ሆኖም ግን አነስተኛ ቴክኖሎጂን በሚጠቀሙ ማምረቻ መጋዘኖች ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን በትላልቅ ኢንዲስትሪ ፓርኮች ውስጥ ጭምር በማምረት ለሕገወጥ ንግድ መስፋፋት የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ላይ የሚገኙ የውጭ ኩባንያዎች እንዳሉ ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሚያስተዳድሩ አካላትና በየአካባቢው የሚመለከታቸው የንግድ ዘርፍ መዋቅሮች እንዲህ ያለውን ጥሰት ሥርዓት ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

  በሺሕ የሚቆጠሩ ሠራተኞችን የሚያስተዳድሩና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያድኑ ምርቶችን በአገር ውስጥ የሚያመርቱ ድርጅቶች፣ ከአንድ ሺሕ ዶላር በታች የሚያወጡ መለዋወጫዎችን ለማስመጣት ሲጠይቁ በንግድ ባንኮች ያለወረፋ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የብሔራዊ ባንክ ሕግ ስለሚከለክላቸው ለወራት ምርት ሳያመርቱ ለመጠባበቅ የሚገደቡበት አጋጣሚ ይታያል፡፡ በአንፃሩ የውጭ ባለሀብቶች የሚያስተዳድሯቸው ድርጅቶች፣ ከውጭ በፍራንኮ ቫሉታ ማስመጣት ስለሚችሉ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቱን ከውድድር ውጭ የሚደርጉበት ሁኔታ ተንሰራፍቶ በውጭ ባለሀብቶች የሚመቱ ከፍተኛ ምርቶች ሳይቀሩ፣ ያለደረሰኝ ለገበያ እየቀረቡ የሽያጭ ገንዘቡ በጥቁር ገበያ በተጋነነ የምንዛሪ ዋጋ እየተገበየ ከአገር እንደሚወጣ የተብራራበት ጥያቄም ቀርቧል፡፡ በሌሎች ጥያቄዎችም የውጭ ኩባንያዎች አላሠራ እንዳሉ ተጠቅሷል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የውጭ ኢንቨስትመንት ለኢትዮጵያ ያለውን አስፈላጊነት አጠንክረው ገልጸዋል፡፡ ይሁንና የውጭ ኩባንያዎችን የተመለከተው አስተያየት ዕርምት ይደረግበታል ብለዋል፡፡ ቴክኖሎጂውን ለመውረስ የግድ ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡ የሥራ ባህልን በመቀየር ረገድ የውጭ ኩባንያዎች አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ ከውጭ ምንዛሪ አንፃርም እገዛ እንደሚያደርጉ በማስረዳት፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ያነሱትን አስተያየት ማስተካከል እንደሚገባቸው ጠይቀዋል፡፡ ‹‹እንደውም እየጋበዛችሁ ልታመጡዋቸው ይገባል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አብሮ በሽርክና መሥራቱም መልካም እንደሆነ መክረዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ሚዛኑ መጠበቅ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በእናንተ እንጂ በእነሱ አይደለም፡፡ እነሱን የምንፈልገው አሁን ባለን ችግር ነው፡፡ እናንተ እያደጋችሁና እየበዛችሀ ከሄዳችሁ የእነሱ ሚና እየቀነሰ ይሄዳል፤›› ብለዋል፡፡

  ሙስና

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ንግግራቸው ውስጥ የአገሪቱ ፈተና የሆነውን የሙስና ጉዳይ አንስተው ነበር፡፡ ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር ባደረጉት ውይይትም ይህንኑ አስመልክቶ ሐሳብ ሲሰነዝሩ፣ ‹‹ዛሬ ከእናንተ ጋር መነጋገር የምፈልገው የሙስናን ጉዳይ ነው፤›› በማለት የሚሰጡትን አጽንኦት ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ‹‹በጣም ብዙ የሠለጠነ ዘመናዊ ሌባ በውስጣችን ተሰግስጓል፤›› በማለት ችግሩን አብራርተዋል፡፡

  ‹‹ሌቦች ከእኛ የተሻለ ጭንቅላት ካላቸው፣ ከእኛ የተሻለ አልፈው መሄድ ይችላሉ፡፡ ዘመናዊ ሌባን በሕግ መያዝ ከባድ ነው፡፡ እናንተ ብታግዙን፣ አውራ አውራው መስመር እየያዘ ቢሄድ፣ ሌላው ይደነግጣል፡፡ ሌብነትን ዜሮ እንደማናደርግ አውቃለሁ፡፡ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት እንደሥራ ባይወሰድ፣ ቢያንስ ይህንን ሸጦ [የታሸገውን ውኃ እያሳዩ] ኮሚሽን መጠየቅ ለመንግሥት ባለሥልጣን እንደመብት ባይቆጠር መልካም ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ‹‹ሌባ ብር አይጠግብም፡፡ ዛሬ የሰጣችሁትን ይቀበላል፡፡ መስጠት ሲያቅታችሁ እናንተኑ ነው የሚበላችሁ፡፡ በቃኝ ትናንት ተሰጥቶኛል አይልም፡፡ ውለታ ብሎ ነገር አያውቅም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አንዴ ሰጥታችሁ አትገላገሉም፤ የሚቆም ነገር ስላልሆነ በተቻለ መጠን ሌብነት ነውር እንዲሆን ተባብረን እንሥራ፤›› በማለት ለንግድ ኅብረተሰቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

  መንግሥት መነገዱን ይቀጥላል

  መንግሥት በንግዱ ውስጥ እጁን ባያስገባ የሚለውን ጥያቄ አሁንም ለጥቂት አሥርታት አይሠራም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንዲህ እንዳትጠብቁ ብለዋል፡፡ መንግሥት እየመረጠ ይነግድ፣ ሽንኩርት መቸርቸር ውስጥ አይግባ ከሆነ ጥያቄው እንደሚስማሙበት የገለጹት ዶ/ር ዓብይ፣ ንግድ ተዉ የሚለው ነገር ግን አይሠራም በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

  ‹‹አሜሪካም፣ ቻይናም ይነግዳሉ፡፡ የአሜሪካ ፖስታ ቤት የመንግሥት ነው፡፡ መንግሥት የተመረጠ ቦታ ላይ ይገባል፡፡ ሊብራሊዝም የሚባለው ነገር ውሸት ነው፡፡ መነገድ አንተውም ግን እናንተ መነገድ የምትችሉትን እንተውላችኋለን፡፡ በዚህ እንስማማ፡፡ ብዙ የምንለቃቸው አካባቢዎች ይኖራሉ፡፡ ሆቴል አንፈልግም፡፡ ለቀቅን ማለት ግን ከንግድ ወጣን ማለት እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል፤›› በማለት ምላሻቸውን ሰጥተው መድረኩ ተዘግቷል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች