Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ሕብረት ባንክ የ12 ዓመታት የስትራቴጂክ ዕቅድ እንዲያዘጋጅለት ድሎይት የተባለውን የውጭ አማካሪ ቀጠረ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የአገሪቱ የግል ባንኮች ለተወዳዳሪነት የሚያበቋቸውን የተለያዩ ስትራቴጂዎች በመቅረጽ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የውጭ ተወዳዳሪ የሌለባቸው የኢትዮጵያ ባንኮች የእርስ በርስ መወዳደሪያ ሥልቶቻቸው ጠንካራ እንዳልሆኑ ይነገራል፡፡

  ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን በኪሳራ የተዘጋ ባንክ ቤት ባይኖርም፣ አንዱ ከሌላው ያለው የውድድር ደረጃ ዝቅተኛ ሆኖ እንደቆየም ይገለጻል፡፡ ይሁን እንጂ የአገሪቱ ባንኮች ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታዩ፣ የሚገኙበት ደረጃ ዝቅተኛ ከመሆን አልፎ እዚህ ግቡ የሚያሰኛቸው ባለመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት ያሉት የመንግሥት እንቅስቃሴዎች ከአገር ውስጥ አልፈው ወደ ውጭ ተቋማት እንዲመለከቱም ፍንጭ እየሰጣቸው ነው፡፡

  አቅማቸውን ለማጎልበት በየግላቸው ከሚያደርጉት ጥረት ውስጥ አንዱ ስትራቴጂክ ዕቅድ የመንደፍ ልምድ ያላቸውን ኩባንያዎች ቀጥሮ ማሠራት እየተለመደ መጥቷል፡፡ የባንኮቹን የወደፊት የጉዞ አቅጣጫ አመላካች ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ከወዲሁ ተወዳዳሪ ሆነው ለመገኘት የሚችሉበትን ዝግጅት ማድረግም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እየጎላ የመጣ ልምድ ሆኗል፡፡ እንዲህ ያለውን አሠራር በመከተል ዝግጅት እያደረጉ ከሚገኙት ውስጥ አንጋፋዎቹ የግል ባንኮች ቀዳሚ እየሆኑ ነው፡፡

  አዋሽ ባንክና አቢሲኒያ ባንክ ለተወዳዳሪነት የሚያበቃቸውን የስትራቴጂክ ዕቅድ ኬፒኤምጂና ድሎይት የተባሉ የውጭ ኩባንያዎችን ቀጥረው ማሠራት ጀምረዋል፡፡

  ከአንድ ሳምንት በፊትም ንብ ባንክ ተመሳሳይ ተግባር ለመፈጸም ኬፒኤምጂን በመምረጥ ስምምነት አድርጓል፡፡ ቅዳሜ ሚያዝያ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በተከናወነ ሥነ ሥርዓት፣ 18ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ሕብረት ባንክ፣ ዋና መሥሪያ ቤቱ በኒውዮርክ ከሆነውና በኬንያ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ ከሚገኘው ድሎይት ኩባንያ ጋር በመዋዋል የ12 ዓመታት ስትራቴጂ እንዲነድፍለት ተስማምቷል፡፡ በሕብረት ባንክና በድሎይት ኬንያ መካከል የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ በየተሰጠ መግለጫ፣ ጊዜው የሚጠይቀውን የአሠራር ሥልት በመከተል ለተወዳዳሪነት ለመብቃት በዘርፉ ከታወቁ የውጭ አማካሪ ኩባንያዎች ጋር መሥራት ስላስፈለገ ድሎይት ተቀጥሯል ተብሏል፡፡

  አማካሪው ኩባንያ ባንኩ ወደፊት እንደሚደርስበት ለሚያስበው ግብ ስትራቴጂ እንዲቀርጽ በጨረታ ውድድር አሸንፎ ሥራውን መረከቡም ተጠቅሷል፡፡ የሕብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ እንደገለጹት፣ ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ሆነ ከዓለም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አኳያ ሕብረት ባንክ በሚለፈገው ደረጃ እንዲያድግ የረዥም ጊዜ ዕቅድ መተለም ስላስፈለገው የተወሰደ እርምጃ ነው፡፡

  በአፍሪካ አዳዲስ ክስተቶች ብቅ እያሉ መሆናቸው ለባንኩ ስትራቴጂክ ዕቅድ ማውጣት አንዱ ምክንያት ስለመሆኑ አቶ ታዬ በምሳሌነት የጠቀሱት፣ በቅርቡ በአፍሪካ መሪዎች የተፈረመውን የአፍሪካ የጋራ ገበያ ስምምነት ነው፡፡

  ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚፈልገው የፋይናንስ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፣ የባንክ ዘርፉም ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራር እየተቀየረ ወደ አውቶሜትድ አሠራር እየሄደ መሆኑና የደንበኛውም ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ፣ ባንኮች ራሳቸውን ማዘመን የውዴታ ግዴታ እየሆነባቸው መምጣቱን አብራተዋል፡፡ ይኼንን ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ ለማውጣትም ድሎይት ያካበተውን ልምድ ተጠቅሞ ፍኖተ ካርታ እንዲሠራ በማድረግ ባንኩን ተወዳዳሪ ማድረግ እንዳስፈለገ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለተመሳሳይ ሥራ ባንኩ ኬፒኤምጂ መርጦ የነበረ ሲሆን፣ አማካሪው ጨረታውን ካሸነፈ በኋላ ከባንኩ ጋር ስምምነቶችን ሊያደርግ ባለመቻሉ የተገባው ውል ሳይፈጸም ቀርቷል፡፡ የድሎይት ኬንያ ኩባንያ፣ የአማካሪ ቡድን ኃላፊ ሮጀር ጆርጅ በበኩላቸው፣ ባንኩን ብቁ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያግዙ ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል፡፡

  እርስ በርስ የሚወዳደሩ ባንኮችን የዕቅድ ሥራዎች አንድ አማካሪ ወይም ጥቂት አማካሪ ኩባንያዎች መሥራታቸው ግጭት አይፈጥርም ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የድሎይቲ ፓርትነር (ቴክኖሎጂ አማካሪ) አቶ አመኃ በቀለ፣ የአንዱ ባንክ ሥራ ከሌላው ጋር የሚያጋጨው ነገር አይኖርም በማለት ሁሉም የየራሱ አሠራር ስላለው ይኼ ችግር አይሆንብንም ብለዋል፡፡ ሚስተር ጆርጅም አንድም ኩባንያ በዚሁ አሠራር የተነሳ ችግር ገጥሞኛል ብሎ አልጠየቀም ብለዋል፡፡

  ድሎይት እ.ኤ.አ. በ2017 ብቻ ከ39 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያካበተ ግዙፍ አማካሪ ድርጅት ሲሆን፣ በዓለም ላይ ከ263 ሺሕ በላይ ሠራተኞች የሚያስተዳድር፣ በምሥራቅ አፍሪካም ከ1,000 በላይ ሠራተኞች ያሉት ኩባንያ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ ዘመን አንጋፋ ከሚባሉት የግል ባንኮች ተርታ የሚመደበው ሕብረት ባንክ በበኩሉ ከ230 በላይ ቅርንጫፎችን መክፈት የቻለና ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ባንክ አገልግሎቶችን በማቅረብ ወደ ዘመናዊ የፋይናንስ አገልግሎት በሚደረገው ሽግግር ውስጥ የሚሳተፍ ተቋም ነው፡፡ 

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች