Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የኢንቨስትመንት ተቋም ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በየዓመቱ በዱባይ አዘጋጅነት በሚካሄደው ዓለም ዓቀፉ የኢንቨስትመንት ጉባዔ፣ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ውጤታማ አፈጻጸም ያሳዩ አገሮች ተወዳድረው በሚሸለሙበት መድረክ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ የዘንድሮውን ሽልማት ማሸነፍ ችሏል፡፡

በተመረጡ ዘርፎች የሚሳተፉ የውጭ ባለሀብቶችን በመመልመል፣ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ፣ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚያስገኙ የሚታመንባቸው ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት ውጤት ላስመዘገቡ አገሮችና የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ተቋማት የሚበረከተውን ሽልማት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን መውሰድ የቻለው የሩዋንዳ አቻውን በመቅደም እንደሆነ ታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ሚያዝያ 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ እ.ኤ.አ. በ2018 በተዘጋጀው ውድድር ኮሚሽኑ ከሩዋንዳው የልማት ቦርድ ጋር ምሥራቅ አፍሪካን በመወከል ለሽልማቱ የታጩ ተፎካካሪዎች ነበሩ፡፡ ሆኖም ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምሥራቅ አፍሪካን በመወከል ውጤታማ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ተቋም በመባል በተባብሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ዱባይ ከተማ ከሚያዝያ 1 እስከ 4 ቀን 2010 ዓ.ም በተካሄደው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ጉባዔ ላይ ተሸላሚ ሆኗል። በተባበሩት የዓረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ወ/ሮ እየሩሳሌም ዓምደማርያም ኮሚሽኑን በመወከል ሽልማቱን ተቀብለዋል፡፡

መንግሥት የውጭ ኢንቨስትመንቶች የአካባቢ ጥበቃን ባማከለ፣ የወጪ ንግድ ዘርፉን በሚያበረታታ፣ ከአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በሚያፋጥን መልኩ የውጭ ኩባንያዎች አብረው እንዲሠሩ ለማድረግ ባሳየው ውጤታማ አፈጻጸም ለሽልማት እንደበቃ ተጠቅሷል።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በጉባዔው የቤልጂየም፣ የህንድ፣ የሰርቢያ፣ የግብፅ፣ የጋና እንዲሁም የስዋዚላንድ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ተቋማት ከየመጡባቸው አኅጉራት ቀዳሚ በመሆን ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የጉባዔው አዘጋጅ ኮሚቴ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳውድ አል ሼዛዊ እንደተናገሩት፣ ሽልማቱ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ተቋማቱ አገራቸውን በማስተዋወቅና መልካም ስም በመፍጠር ኢንቨስትመንትን ወደየአገራቸው በመሳብ የአገራቸውን ኢኮኖሚ በማሳደግና ሥራ ፈጠራን በማስፋፋት ረገድ ላደረጉት ውጤታማ እንቅስቃሴ የሚሰጥ ነው። በዘንድሮው ጉባዔ ተሸላሚ የሆኑት አገሮች ያሳዩት ውጤት ለሌሎችም ተምሳሌት እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ የኢንቨስትመንት ጉባዔ፣ በየዓመቱ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ምሁራንና ሙያተኞች እንዲሁም የተለያዩ ተቋማትን የሚመሩ ኃላፊዎች የሚሳተፉበትና በኢንቨስትመንት ዘርፉ ዕውቅና የተቸረው ጉባዔ ነው።

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ሩዋንዳን አሸንፋ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ተሸላሚ ለመሆን የበቃችበት የኢንቨስትመንት ተቋም ቢኖራትም፣ የዓለም ባንክ በየዓመቱ በሚያወጣው ‹‹ኤዝ ኦፍ ዱዊንግ ቢዝነስ›› በተሰኘ ሪፖርት ያላት ደረጃ ዝቅተኛው ሲሆን፣ በአንፃሩ ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ከአፍሪካ ከሚጠቀሱ ግንባር ቀደም አገሮች የመጀመሪያዎቹ ተርታ ትመደባለች፡፡ በዓለም ባንክ ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ በርካታ ማሻሻያዎችን እንዳደረገ፣ መንግሥትም በመስኩ ለውጦችን ለማስመዝገብ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራ የሪፎርም ፕሮግራም፣ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን አማካይነት መተግበር እንደጀመረ ይታወቃል፡፡ ይሁንና በዓለም ባንክ ሪፖርት ውስጥ ከፍተኛ ለውጦችና መሻሻሎች ካሳዩ አገሮች ተርታ ለመሠለፍ ብዙ የሚቀራት አገር ሆናለች፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች