Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአገሪቱ የተከሰተው ድርቅ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል

በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል

ቀን:

– ተስፋ የተጣለበት ጊቤ ሦስት ያላለቁ ሥራዎች አሉት

በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች የውኃ መጠን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ እጥረት አጋጥሟል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ጊቤ ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተስፋ ቢጣልበትም ፕሮጀክቱ ያላለቁ ሥራዎች አሉት ተብሏል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ላይ የሚገኙ ግድቦች በድርቁ ምክንያት መያዝ ያለባቸውን ያህል ውኃ እንዳልያዙ እየተነገረ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 420 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣና በለስ ነው፡፡

ጣና በለስ ከጣና ሐይቅ በግዙፍ ካናል በሚያገኘው ውኃ የሚሠራ የኃይል ማመንጫ ነው፡፡ ዓባይ ወንዝ ጣና ሐይቅን ሰንጥቆ በማለፍ 30 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀው ለሚገኙት ጢስ ዓባይ ቁጥር አንድና ጢስ ዓባይ ቁጥር ሁለት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ኃይል እንዲያመነጩ ያደርጋል፡፡

ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት ጢስ ዓባይ፣ የዓባይ ወንዝ አቅጣጫ ቀይሮ 300 ሜትር ርዝመት ባለው ካናል ተጉዞ በድምሩ 84 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የሚመነጭባቸው ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የግድቦች ዳይሬክተር አቶ አንዳርጌ እሸቴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዘንድሮ ለጢስ ዓባይ ኃይል ማመንጫዎች የሚሆን ውኃ አልተገኘም፡፡ በሌሎች ጊዜያት ቢያንስ ለ110 ቀናት የሚሆን የውኃ መጠን ይኖር ነበር በማለት አቶ አንዳርጌ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

‹‹ጢስ ዓባይ ከሚያመነጨው ኤሌክትሪክ ኃይል ይልቅ ጣና በለስ የሚያመነጨው ከስድስት እጥፍ በላይ ነው፤›› በማለት፣ የጢስ ዓባይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ሥራ እንዲያቆሙ የተደረገበትን ምክንያት አቶ አንዳርጌ አስረድተዋል፡፡

ከድርቁ ጋር በቀጥታ ባይያያዝም በጊቤ አንድ ኃይል ማመንጫ ግድብ ችግር አለ፡፡ ይህ ግድብ በክረምት ወራት የሚያገኘው ውኃ ከመስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በኋላ እየቀነሰ መጥቷል በማለት አቶ አንዳርጌ ገልጸዋል፡፡

አቶ አንዳርጌ እንዳሉት፣ የጊቤ አንድ ግድብ ውኃ የሚያርፈው 55 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ ነው፡፡ ይህ ውኃ ከሌሎች ግድቦች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑን አቶ አንዳርጌ ገልጸዋል፡፡ የጊቤ አንድ ኃይል ማመንጫ ግድቡ ከደለል ጋር ስሙ በየጊዜው መነሳቱን አቶ አንዳርጌ አይስማሙበትም፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሁለት ዓመት በፊት የባዞ ሜትር ጥናት አካሂዷል፡፡ በተካሄደው ጥናት የጊቤ አንድ ግድብ በደለል ተጠቂ ነው ማለት እንደማያስችል አቶ አንዳርጌ ገልጸዋል፡፡ ግድቡ በክረምት ቢሞላም ከሌሎች ግድቦች ሲነፃፀር ለምሳሌ ጣና ሐይቅ ሦስት ሺሕ ካሬ ኪሎ ሜትር፣ ቆቃ 300 ካሬ ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ጊቤ አንድ ግድብ ግን 55 ካሬ ኪሎ ሜትር ብቻ ነው በማለት ችግሩ የግድቡ ባህሪይ ውኃ በብዛት መያዝ አለመቻል መሆኑን አቶ አንዳርጌ ተናግረዋል፡፡

የድርቅ ተፅዕኖ በተከዜ ኃይል ማመንጫ ላይ ተስተውሏል፡፡ በ2002 ዓ.ም. ተመርቆ ሥራ የጀመረው ተከዜ 300 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡

በድርቁ ምክንያት ግድቡ መያዝ ያለበትን ውኃ እንዳልያዘ ታይቷል፡፡ በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይህንኑ ሀቅ ተናግረዋል፡፡ ተከዜ በድርቁ ምክንያት ውኃ መያዝ ባለመቻሉ እያመረተ የሚገኘው አሥር ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቃለ ምልልሳቸው፣ ከተከዜ ባሻገር የቆቃ ኃይል ማመንጫ ችግር ውስጥ መግባቱና መልካ ዋከና ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ ኃይል ማመንጨት አቁሟል ማለት እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

‹‹ድርቁ ራሱ በፈጠረው የውኃ ችግር የኤሌክትሪክ እጥረት አጋጥሟል፤›› በማለት የችግሩን ስፋት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ የሚገኙ ኃይድሮ የኤሌክትሪክ ኃይል ግድቦች በድርቁ ምክንያት አቅርቦታቸው ከመቀነሱም በላይ በተለያዩ የቴክኒክ ችግሮች፣ በሰው ኃይል ብቃት ማነስና በአሻጥር ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ በየጊዜው እየተስተጓጎለ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ተቋማት በተለይ ድርቁ ባስከተለውና ወደፊትም በሚያስከትለው የኃይል አቅርቦት ችግር ከወዲሁ ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ አማራጮችን እየመረመሩ መሆኑ ታውቋል፡፡

በዋነኛነት እንደ አማራጭ የታየው የጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ግድብ ነው፡፡ ጊቤ ሦስት በደቡብ ክልል በዳውሮና በወላይታ ዞኖች መካከል ላይ የተገነባ ኃይል ማመንጫ ግድብ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታ በታኅሳስ 1999 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፣ ከሦስት ዓመት በፊት ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለት ነበር፡፡

የጣሊያኑ ግዙፍ ኩባንያ ሳሊኒ ኮንስትራክስንና የቻይናው ግዙፍ ኩባንያ ዳንግ ፋንግን ጨምሮ 24 ኩባንያዎች የተሳተፉበት ይህ ፕሮጀክት 14 ቢሊዮን ብር ወጥቶበታል፡፡

ፕሮጀክቱ አሥር ኃይል ማመንጫ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ አንዱ ተርባይን 187 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አለው፡፡ ፕሮጀክቱ በድምሩ 1,870 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡

በአሁኑ ወቅት ሁለት ተርባይኖች ማመንጨት የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውንና ሦስተኛው ተርባይን ደግሞ በሙከራ ላይ መሆኑን አቶ አንዳርጌ ገልጸዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቡ መሠረት ያደረገባቸው በጥቅጥቅ ደን ከተሸፈነው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚነሱት ጎጀብና ጊቤ ወንዞች በመሆናቸው፣ እነዚህ ወንዞች የተሻለ ፍሰት ስላላቸው የጊቤ ሦስት ግድብ የውኃ መጠን እየጨመረ ነው፡፡

አቶ አንዳርጌም እንዳረጋገጡት፣ የጊቤ ሦስት ግድብ የውኃ መጠን በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል፡፡ ግድቡ የሚያመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስተላልፈው ባለ 400 ኪሎ ቮልት ማስተላለፊያ መስመር ተገንብቷል፡፡ በወላይታ ሶዶና በአዲስ አበባ አቃቂ አካባቢ የሚገኙት ማከፋፈያ ጣቢያዎች ተገንብተዋል፡፡

ከሞላ ጎደል እነዚህ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን የሚናገሩት የሪፖርተር ምንጮች፣ የኃይል መቆጣጠሪያ ከፕሮጀክቱ ጋር ተያይዞ እኩል ባለመገንባቱ ጊቤ ሦስት በአሁኑ ወቅት ማመንጨት የሚችለውን የኤሌክትሪክ ኃይል በዋናው መስመር ማስገባት አልቻለም፡፡

አቶ አንዳርጌ እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት አንዱ ተርባይን ብቻ የሚያመነጨውን 70 ሜጋ ዋት ኃይል ከአዲስ አበባ-ወላይታ ሶዶ ድረስ በተዘረጋው ነባሩ ባለ 132 ኪሎ ቮልት ማስተላለፊያ መስመር እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡ በ400 ኪሎ ቮልት መስመር ኤሌክትሪክ ለማስተላለፍ የግድ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎቹ መገንባት እንዳለበቸውም ተነግሯል፡፡

‹‹ያልተጠናቀቁ ሥራዎች በመኖራቸው ዋናውን መስመር መጠቀም አልተቻለም፤›› በማለት አቶ አንዳርጌ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ያልተጠናቀቁ ሥራዎች በአስቸኳይ ተጠናቀው ጊቤ ሦስት ኢኮኖሚውን እንዲረዳ መደረግ አለበት የሚል መመርያ መስጠቱ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ተቋማት በጥምር፣ ከስኳር ፕሮጀክቶችና ከንፋስ ኃይል ተጨማሪ ኃይል በሚገኝበት መንገድ ላይ እየመከሩ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኃይል ቆጣቢ የኤሌክትሪክ መሣሪያዎች በሰፊው ለገበያ በሚቀርቡበት ሁኔታ ላይም እየተመከረ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግሩ ተባብሶ የሚቀጥል ከሆነና አማራጭ መፍትሔ መቅረብ ካልተቻለ፣ የማምረቻ ተቋማት ለከባድ ችግር ይዳርጋሉ ተብሏል፡፡ ሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የመሳሰሉ ግዙፍ ፋብሪካዎች ከቀኑ 11፡00 እስከ ምሽቱ 4፡00 ሰዓት ድረስ ኃይል እንዳይጠቀሙ ተነግሯቸዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ የማይሻሻል ከሆነ ይህ ሰዓት ሊጨምር የሚችል በመሆኑ ከፍተኛ ሥጋት ተፈጥሯል፡፡ መንግሥት ለዚህ ሁሉ ችግርና የአገሪቱን የማምረቻ ተቋማት ለማነቃቃት ጊቤ ሦስት ላይ ተስፋ ተጥሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...