Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበእነ አቶ መላኩ ፈንታ ላይ የቀረቡ ምስክር አሥር ሚሊዮን ብር ጉቦ ተጠይቄ...

በእነ አቶ መላኩ ፈንታ ላይ የቀረቡ ምስክር አሥር ሚሊዮን ብር ጉቦ ተጠይቄ ነበር አሉ

ቀን:

‹‹በዚች አገር ወንጀል ሠርቷል ብሎ የሚያስበኝ አለ ብዬ አላምንም›› አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ በተመሠረተባቸው በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ ቁጥር 14/352 የተካተቱት፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ምክትል ዋና ዳይሬክተር (በሕግ ማስከበር ዘርፍ) አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ፣ አሥር ሚሊዮን ብር ጉቦ ጠይቀዋቸው እንደነበር፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ምስክር ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

ምስክሩ ሚስተር መሐመድ ሁሴን የተባሉ የውጭ አገር ዜጋ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተቋቋመ ኤ ኤንድ ጂ ግሎባል ኮንስትራክሽን የተባለ ድርጅትን በኃላፊነት የሚመሩ የነበሩ ናቸው፡፡ አቶ ገብረ ዋህድ አሥር ሚሊዮን ብር ጉቦ እንዲሰጧቸው የጠየቋቸው፣ በኢትዮጵያ ከ1999 ዓ.ም. እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ ተከስቶ በነበረው የሲሚንቶ እጥረት ጋር በተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንደገለጸው፣ ከ1999 ዓ.ም. እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ የሲሚንቶ እጥረት ተከስቶ ነበር፡፡ የሲሚንቶ እጥረትን ተከትሎ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በመከሰቱ፣ ዋጋ ለማረጋጋት ሲሚንቶ ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ከቀረጥ ነፃ የገባው ሲሚንቶ በዋናነት የሚውለው ለቤቶች ልማት ፕሮጀክት ቢሆንም፣ ሲሚንቶውን ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ እንዲጓጓዝ ያደረገው ድርጅት (ኤ ኤንድ ጂ ግሎባል ኮንስትራክሽን) ከአጓጓዦች ጋር በመመሳጠር ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፉ በክሱ ተብራርቷል፡፡ መንግሥት 21,602,608 ብር ጉዳት እንደደረሰበት ለአቶ ገብረ ዋህድ ጥቆማ እንደደረሳቸውም አክሏል፡፡ አቶ ገብረ ዋህድ በወቅቱ የባለሥልጣኑ የሕግ ማስከበር ዘርፍ ዳይሬክተር በመሆናቸው ሲሚንቶውን እንዲያጓጉዙ፣ ከኤ ኤንድ ጂ ግሎባል ኮንስትራክሽን ጋር ውል የፈጸሙትን ትራንስፖርተሮችና ባለቤቶቻቸውን ተከታትለው በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ሲገባቸው፣ አለማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡

አቶ ገብረ ዋህድ ከትራንስፖርት ድርጅቶችና ከባለንብረቶች ጋር ባላቸው ስውር የጥቅም ግንኙነት፣ የራሳቸውንና የሌሎችን ጥቅም ለማስጠበቅ በማሰብ፣ ሊከሰሱ ሲገባ እንዳይከሰሱ ማድረጋቸውንም ክሱ ያስረዳል፡፡ አቶ ገብረ ዋህድ በደረሳቸው ጥቆማ መሠረት ምስክሩን አቶ መሐመድ ሁሴንን በተደጋጋሚ በማስጠራት፣ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ሲመረምሯቸው እንደነበር ምስክሩ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናትን ስም በመጥራት ለመክሰስ እንደሚፈልጉ በመግለጽ አቶ መሐመድ ምስክር እንዲሆኑ ሲጠይቋቸው፣ ‹‹እኔ ሃይማኖቴ አይፈቅድም›› በማለት ጥያቄያቸውን እንደማይቀበሉ ሲነግሯቸው፣ ያስገቡትን ሲሚንቶ ሀይደር ለሚባል ግለሰብ ከ122 እስከ 155 ብር በኩንታል እንዲያስረክቡ እንዳዘዟቸው ምስክሩ ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ የሲሚንቶ ዋጋ በኩንታል 400 ብር የነበረ ቢሆንም፣ እሳቸው ከላይ በተጠቀሰው ዋጋ ለሀይደር እንዲያስረክቡ መገደዳቸውን መስክረዋል፡፡

አሥር ሚሊዮን ብር ጉቦ እንዲሰጡ ሲጠየቁ በተደጋጋሚ ሃይማኖታቸው እንደማይፈቅድ በመግለጽ ባለመስማማታቸው፣ ድርጅታቸው ኤ ኤንድ ጂ ኮንስትራክሽን፣ እሳቸው፣ ኃይሌ አሰፋ ትራንስፖርተር፣ ሸሚዛል ትራንስፖርትና ሌሎች ክስ ሲመሠረትባቸው፣ ከእሳቸው ጋር የጥቅም ግንኙነት አላቸው የተባሉት ነፃ ትራንስፖርት፣ ጌታስ ኢንተርናሽናል፣ ኮሜት ትራንስፖርትና የድርጅቶቹ ባለቤቶች ሳይከሰሱ መቅረታቸው ተገልጿል፡፡

አቶ መሐመድ ሁሴን ክስ ካልተመሠረተባቸው ትራንስፖርተሮች ጋር የጥቅም ግንኙነት እንዳላቸውና እንደሌላቸው ተጠይቀው፣ ትራንስፖርተሮቹ ባላቸው የማጓጓዣ ውል መሠረት ሲሚንቶውን አጓጉዘው ለኤ ኤንድ ጂ ኮንስትራክሽን ድርጅት ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ አዟዙረው በችርቻሮ ስለመሸጣቸው ተጠይቀው ‹‹የማጓጓዝ ሥራ ብቻ ሠርተዋል፤›› በማለት በሽያጭ ጉዳይ ምንም እንዳልሠሩ ተናግረዋል፡፡

አቶ ገብረ ዋህድ በመስቀለኛ ጥያቄ አቶ መሐመድ ሲሚንቶውን ያስገቡት ለራሳቸው የኮንስትራክሽን ድርጅት ተፈቅዶላቸው ስለመሆኑ ሲጠይቋቸው፣ ድርጅታቸው ከኮንስትራክሽን ጋር የተገናኘ ሥራ እንደሌለው በመናገር መልስ ሰጥተዋል፡፡ ይኼንን በሚመለከትም ክስ ተመሥርቶባቸው ነፃ መውጣታቸውን አክለዋል፡፡ የድርጅቱ ባለቤት ስለመሆናቸው ተጠይቀው፣ ድርጅቱ በሁለት የውጭ ባለሀብቶችና በአንድ ኢትዮጵያዊ የተቋቋመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ምን ያህል ሲሚንቶ እንዳስመጡ፣ የት እንዳቆሙ፣ ማን እንዳስቆማቸው፣ የት ፍተሻ እንደተደረገ ተጠይቀው ሁሉም በእሳቸው (አቶ ገብረ ዋህድ) ትዕዛዝ የተደረገ መሆኑን በመግለጽ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሽያጭን በሚመለከት ያስገቡትን ሲሚንቶ ሀይደር ለሚባል ግለሰብ ከ122 እስከ 155 ብር እንዲሸጡ እንዳስገደዷቸው፣ ነገር ግን ለአትራፊ ነጋዴ ቢሸጡ 180 ብር ሊሸጡ ይችሉ እንደነበር ለራሳቸው አቶ ገብረ ዋህድ ነግረዋቸዋል፡፡ ምስክሩ ሚስተር መሐመድ የሚመሰክሩት ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በተመደበ አስተርጓሚ አማካይነት ስለነበር፣ በአቶ ገብረ ዋህድና በፍርድ ቤቱ መካከል ከፍተኛ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ የፍርድ ቤቱ መጠቀሚያ ቋንቋ አማርኛ ነው፡፡ በመሆኑም ምስክሩ የሚናገሩትን እንግሊዝኛ አስተርጓሚው ወደ አማርኛ ለውጠው እስከሚያስረዱ ድረስ፣ አቶ ገብረ ዋህድ መጠበቅ እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ መቃወሚያ ካላቸውም ተርጓሚው ተናግሮ እስኪጨርስ መጠበቅ እንዳለባቸው ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ ቢገልጽም፣ አቶ ገብረ ዋህድ ምስክሩ በእንግሊዝኛ ተናግረው ሳይጨርሱ ተቃውሞ በማሰማታቸው ከፍርድ ቤቱ ጋር በተደጋጋሚ ኃይለ ቃል ተለዋውጠዋል፡፡

‹‹በዚች አገር ወንጀል ሠርቷል ብሎ የሚያስበኝ አለ ብዬ አላምንም፡፡ በአሉባልታ በተሞላ ጭብጥ ነው እየተመሰከረብኝ ያለው፤›› በማለት አቶ ገብረ ዋህድ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤቱ ሲያስቆማቸው የንዴት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ ሲያስቆማቸው ሊያቆሙ ባለመቻላቸው ‹‹ፍርድ ቤቱ የያዘው ቀልድ አይደለም›› ሲላቸው እሳቸውም፣ ‹‹እኔም የያዝኩት ቀልድ አይደለም››  በማለት ምላሽ ከሰጡ በኋላ ‹‹ፍርድ ቤቱ ከተቆጣ ለምስክሩ ጥያቄ ማቅረቤን አቆማለሁ፤›› የሚል ምላሽ አክለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ እሳቸውን እንደማይቆጣ፣ ነገር ግን ትዕዛዝ አክብረው ጥያቄያቸውን ማቅረብ እንዳለባቸው በመግለጽና፣ ስሜታዊ ሆነው ለፍርድ ቤቱ ሌላ ምሥል ለመስጠት በማሰብ ‹‹ፍርድ ቤቱ ከተቆጣ አቆማለሁ›› ማለት ተገቢ አለመሆኑን በማስረዳት፣ ተረጋግተው መስቀለኛ ጥያቄያቸውን ማቅረብ እንዳለባቸው ነግሯቸው ጥያቄያቸውን ቀጠሉ፡፡

አቶ ገብረ ዋህድ መስቀለኛ ጥያቄያቸውን ሲጥቀሉ የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በመጠናቀቁ ምስክርነቱ ተቋርጦ ለታኅሳስ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ተቀጥሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...