Sunday, June 23, 2024

በወሰን ማስከበር ችግር በአዲስ አበባ መንገድ ግንባታ ማካሄድ አስቸጋሪ ሆኗል

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በወሰን ማስከበር ችግር ያቀዳቸውን መንገዶች መገንባት እንዳልቻለ ገለጸ፡፡ ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመቱ 900 ኪሎ ሜትር መንገዶችን ለመገንባት ቢያቅድም፣ በሚገነቡ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ቤቶች፣ አጥሮችና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን በወቅቱ ማንሳት ባለመቻሉ፣ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ ግንባታ ለማካሄድ አስቸጋሪ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ባለፈው ዓርብ ታኅሳስ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ጉዳዩ ከሚመለከተው አካላት ጋር በጉዳዩ ላይ መክሯል፡፡ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለፉት ስምንት ወራት በተለይ በወሰን ማስከበር በኩል ሥራዎች አልተከናወኑም፡፡

‹‹ባለሥልጣኑ ለሚያካሂዳቸው ፕሮጀክቶች 11.5 ቢሊዮን ብር በጀት ይዟል፡፡ የወሰን ማስከበር ችግር በመኖሩ በአምስት ወራት መውጣት ያለበትን ወጪ አላወጣንም፤›› በማለት ኢንጂነር ፍቃዱ የችግሩን ስፋት ተናግረዋል፡፡

በወሰን ማስከበር ምክንያት በተለይ በመሀል ከተማ የሚገኙ መንገዶችን ለማስገንባት የሚወጡ ጨረታዎች ዋጋቸው እየናረ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የባለሥልጣኑ የዲዛይን ዋና የሥራ ሒደት መሪ ኢንጂነር ሙሉጌታ አብርሃ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት፣ ከከተማ ወጣ ላሉ መንገዶችና በመሀል ከተማ ለሚገነቡ መንገዶች የሚቀርበው የጨረታ መወዳደሪያ ገንዘብ እጅግ የተራራቀ ነው፡፡

በመሀል ከተማ በወሰን ማስከበር ምክንያት ፕሮጀክቱን ለመጀመር ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ኮንትራክተሮች የጨረታ ዋጋውን ያንሩታል በማለት ኢንጂነር ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡

ለወሰን ማስከበር ትልቁ እንቅፋት ክፍላተ ከተሞች በቂ ትኩረት ሰጥተው ስለማይሠሩ እንደሆነ ኢንጂነር ሙሉጌታ ተናግረው፣ በተለይ በወሰን ማስከበር የሚነኩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ፈቃደኞች እንደማይሆኑ አስረድተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የተገኙ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የመሬት ልማትና ኮንስትራክሽን ክላስተር አስተባባሪ አቶ አባተ ሥጦታው፣ ክፍላተ ከተሞች ችግሩን ተቀብለው በኃላፊነት እንዲሠሩ መመርያ ሰጥተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በወሰን ማስከበር ምክንያት ለተጓተቱ ፕሮጀክቶች የከተማ አስተዳደሩ ክትትል እንደሚያደርግ አቶ አባተ ተናግረው፣ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ እንደሚጠናቀቁ አስታውቀዋል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -