Sunday, February 16, 2025
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ የሕንፃ መገንቢያ መሬት ተከለከልኩ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቅብር ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ በሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ተመራጭ እየሆነ በመጣው ሠንጋ ተራ አካባቢ ዋና መሥሪያ ቤቱን ለመገንባት፣ የመሬት ጥያቄ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያቀረበው የኦሮሚያ ኢንተርናሸናል ባንክ ተቀባይነት ማጣቱ ቅር እንዳሰኘው ገለጸ፡፡

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በሠንጋ ተራ የፋይናንስ ተቋማት ኮሪደር ውስጥ አምስት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጠውና በቦታው ላይ 40 ፎቅ ከፍታ ያለው ግዙፍ ሕንፃ ለመገንባት፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡

ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ በሚደነግገው አዋጅ መሠረት ቦታ በድርድር መስጠት እንደማይችልና ለተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ቦታ የሚቀርበው በሊዝ ጨረታ እንደሆነ ለባንኩ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የፋይናንስ ኮሪደሩ በዋነኛነት የሚገኝበት የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አዱኛ ወንድሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አካባቢው ለፋይናንስ ኮሪደር ተብሎ የተከለለ አይደለም፡፡

አስተዳደሩ ቦታውን የሚያውቀው ለቅይጥ አገልግሎት እንደሚውል ነው፡፡ ነገር ግን በርካታ ባንኮች በቦታው ላይ ዋና መሥሪያ ቤታቸውን መገንባታቸውን አቶ አዱኛ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ግን ምንም ዓይነት ክፍት ቦታ በአካባቢው የለም ብለዋል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት ለአብነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዘመን ባንክ፣ አዋሽ ባንክ፣ ዳሸን ባንክና ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክን ጨምሮ በርካታ ባንኮችና የኢንሹራንስ ተቋማት በዚህ ቀጣና ውስጥ ግንባታቸውን አካሂደዋል፡፡

እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት ቦታውን ያገኙት በድርድርና ከባለይዞታዎች በመግዛት ነው፡፡ ነገር ግን የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እንደ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ዋና መሥሪያ ቤቱን በዚህ የፋይናንስ ኮሪደር መገንባት እንዳለበት አቋም ይዟል፡፡

ባንኩ ለአስተዳደሩ በጻፈው ደብዳቤ ይህ ቀጣና የፋይናንስ ኮሪደር እንደመሆኑ መጠን፣ በአካባቢው የተጠናው የአካባቢ ልማት ዕቅድ ከ35 ፎቅ በላይ እንዲገነባ የሚያዝ በመሆኑ አቅሙ ታይቶ ሊፈቀድለት እንደሚገባ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አበራ ቶላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጎማ ቁጠባ አካባቢ ባንኩ 1,900 ካሬ ሜትር ቦታ ነበረው፡፡ ነገር ግን ባንኩ ላቀደው ግዙፍ ግንባታ ቦታው በቂ ባለመሆኑ ግንባታውን ለማካሄድ የግድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡

የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር መልካሙ ትርፌ በበኩላቸው፣ 1,900 ካሬ ሜትሩ መስቀለኛ ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑና እንደ ፓርኪንግ ላሉ አገልግሎቶች በቂ ባለመሆኑ ፕሮጀክቱን ማካሄድ አልተቻለም፡፡

የባንኩ የቦታ ጥያቄ አገራዊ ፋይዳ እንዳላቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ታይቶና እንዲሁም አካባቢው የፋይናንስ ተቋማት ቀጣና መሆኑ ከግምት ገብቶ ሊስተናገድ እንደሚገባ፣ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ባለሙያዎች ዕምነታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን የፋይናንስ ኮሪደሩ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ዕውቅና ውጪ የለማ በመሆኑና በሊዝ አዋጅ፣ ደንብና መመርያው ላይ የባንኮችና የኢንሹራንስ ተቋማት በልዩ ሁኔታ እንዲያስተናግዱ የተቀመጠ ነገር ባለመኖሩ አስተዳደሩ የባንኩን ጥያቄ ለመቀበል መቸገሩን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የከተማው ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ አስተዳደር የሊዝ ደንብና መመርያን ለማሻሻል የወሰነ በመሆኑ፣ በቀጣይነት የባንኩ ጥያቄ ሊታይ እንደሚችል እኚሁ ባለሥልጣን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ኢንጂነር መልካሙ አስተዳደሩ ቦታውን እንደሚሰጥ ምልክት በማሳየቱ ተስፋ አድርገው ብዙ መቆየታቸውን ገልጸው፣ አስተዳደሩ አሁንም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የመሬት ልማትና ኮንስትራክሽን ክላስተር አስተባባሪ አቶ አባተ ሥጦታው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመሬት ጥያቄ የሚስተናገደው በሊዝ አዋጅ መሠረት ነው፡፡ የሠንጋ ተራ አካባቢ በፋይናንስ ተቋማት ተመራጭ እየሆነ መምጣቱን የአዲስ አበባ አስተዳደር ዕውቅና መስጠቱን አቶ አባተ ገልጸው፣ አስተዳደሩ ለተመረጡ ፕሮጀክቶች ልዩ ጨረታ እንደሚያወጣ አስረድተዋል፡፡

‹‹በሠንጋ ተራ አካባቢ ከዚህ በኋላ የሚወጣው ልዩ ጨረታ ለፋይናንስ ተቋማት ብቻ ነው፤›› በማለት የገለጹት አቶ አባተ፣ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በዚሁ ልዩ ጨረታ ተሳትፎ ቦታ ማግኘት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስካሁን ድረስ ሁለት ጊዜ ልዩ ጨረታ አውጥቷል፡፡ ልዩ ጨረታው ለሆቴል፣ ለሪል ስቴትና ለትምህርት ተቋማት ለሚውሉ ግንባታዎች ብቻ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች