አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በመከላከያ ምስክርነት ስለመቅረባቸውና አለመቅረባቸው ትርጉም እንደሚሰጥበት በማስታወቅ፣ የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አገደው፡፡
በሽብር ተግባር ወንጀል ተጠርጥረው ክስ በተመሠረተባቸው እነ ዘመኑ ካሴ መዝገብ፣ በመከላከያ ምስክርነት መቅረብ እንዳለባቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ያገደው ሰበር ሰሚ ችሎቱ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከወንጀል ሕግ አንቀጽ 123 (ሀ) አንፃር መከላከያ ምስክር መሆን ስለሚችሉበት ወይም ስለማይችሉበት ሁኔታ መርምሮ፣ የሕግ ትርጉም ሊሰጥበት እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡
ሕጉ እንደሚያብራራው ወንጀለኛው ከሕዝባዊ መብቶቹ ማለትም ከመራጭነት፣ በምርጫ ተካፋይ ከመሆንና ለሕዝብ አገልግሎት ሥራ ከመመረጥ፣ ለማዕረግ ከመመረጥ፣ በሰነድ ወይም በውል ስምምነት ላይ ምስክር ወይም ዋስ ከመሆን፣ ለፍርድ ሥራ ልዩ አዋቂ ሆኖ ከመሥራት መብቱ መሻሩን ይገልጻል፡፡
ችሎቱም ከላይ በተጠቀሰው ሕግ ላይ ትርጉም መስጠት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቶ አንዳርጋቸው መከላከያ ምስክር መሆን እንደሚችሉ አስታውቆ፣ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን በማፅደቅ የዓቃቤ ሕግን አቤቱታ ውድቅ ያደረገበት ውሳኔ ሳይፈጸም እስከ ጥር 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ታግዶ እንዲቆይ አዟል፡፡