Monday, June 24, 2024

አሁንም ሕዝብን ማዳመጥ ይቅደም!

መንግሥት የሚደመጠው ሕዝብን ማዳመጥ ሲችል ብቻ ነው፡፡ ሕዝብን የማያዳምጥ መንግሥት ማንም አያዳምጠውም፡፡ መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት የሚጨምረውም የሚቀንሰውም፣ ከሕዝብ ካለው ቅርበትና ርቀት አንፃር ነው፡፡ በተለይ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ‘በ2007 ዓ.ም. በተካሄደ ምርጫ መቶ በመቶ የፓርላማ መቀመጫዎችን የተቆጣጠርኩት አብላጫው ሕዝብ በሰጠኝ ድምፅ ነው’ ሲል በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡ ነገር ግን ይህ የሕዝብ ድጋፍ በትክክል መሬት ላይ ይታያል ወይ ሲባል ደግሞ፣ በርካታ ጥያቄ የሚያስነሱ ልዩነቶች ይታያሉ፡፡ ሕዝብን ውስጡ ገብቶ የልብ ትርታውን ማዳመጥና በሩቅ ሆኖ ‘የሕዝብ ድጋፍ አለኝ’ ማለት ልዩነቱ በጣም ሰፊ ነው፡፡ የችግሩን ማሳያዎች እንያቸው፡፡

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ሥፍራዎች፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን ዝግጅትን በተመለከተ ሁከት ተፈጥሯል፡፡ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በአካልና በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል፡፡ ከዓመት በፊት በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ በተነሳ ሁከት የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ ከፍተኛ የንብረት ውድመትም አጋጥሟል፡፡ ተመሳሳይ ችግሮች እየተከሰቱ ዜጎች ሲሞቱና ጉዳት ሲደርስባቸው፣ ሕዝብን በማወያየት መፍትሔ መፈለግ ሲገባ በስህተት ላይ ስህተት እየታየ ነው፡፡ ዜጎች ምንም ይሁን ምን በሚመለከታቸው ጉዳይ ላይ ጥያቄ የማቅረብ ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው፡፡ መንግሥትም ተገቢውን ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ይህ በአግባቡ ተግባራዊ ባለመደረጉ ግን ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡

ለአዲስ አበባና ለኦሮሚያ ልዩ ዞን ተዘጋጀ የተባለው ማስተር ፕላን ከመፅደቁ በፊት፣ የሚመለከታቸው ወገኖች በጥልቅ ውይይት አድርገው ሳያበስሉት ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ የተቃውሞው ምክንያት ደግሞ ‘የአዲስ አበባ መሬት ሲያልቅ የኦሮሚያን ገበሬዎች ለማፈናቀል የተደረገ ደባ ነው’ የሚል ነው፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ እንደሚከናወን፣ ይህም አሠራር ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ መንግሥት አሠራሩ ግልጽና ሕዝብን አሳታፊ ካልሆነ ግን ሁከትና ብጥብጥ የማይቀር ነው፡፡ ማስተር ፕላኑ ለሕዝብ ይጠቅማል ሲባል ለሕዝቡ በሚገባው ቋንቋ ተብራርቶ ሊነገረው ይገባል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ሁከት የሚያሳየው ሕዝቡና የክልሉ መንግሥት በተዘጋጀው ማስተር ፕላን ላይ አለመወያየታቸውንና የጋራ ግንዛቤ አለመያዛቸውን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ያላግባብ ደም ይፈሳል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙክታር ከድር ዓርብ ታኅሳስ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ለውስን የመንግሥት ሚዲያዎች ብቻ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሁከቱ ሊከሰት የቻለው ዕቅዱን ግልጽ ለማድረግ ውስንነት በመኖሩ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህም በክልሉ በኅብረተሰቡ ውስጥ በጋራ ማስተር ፕላኑ ላይ ጥርጣሬና ጥያቄ እንዲፈጠር ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ ዕቅዱን በተመለከተም ግልጽነት፣ የጋራ መግባባትና መተማመን ከሕዝቡ ጋር ሳይፈጠር በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው ዕቅድ ተግባራዊ እንደማይሆን ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ ከሕዝቡ ጋር የመወያየት ሥራ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ ይህ የዘገየ ውሳኔ ቢሆንም፣ የክልሉ መንግሥት ከሕዝብ ጋር እመክርበታለሁ ማለቱ ጥሩ ነው፡፡ ግን አንድ ዓመት ሙሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ጊዜ መባከኑ ያሳዝናል፡፡ እሳቸው እንዳሉት ከሕዝብ ጋር የሚደረገው የጋራ መግባባትና መተማመን ወሳኝ ስለሆነ ይህ ተግባር ቅድሚያ ይሰጠው፡፡

መንግሥት በተደጋጋሚ ከሚተችባቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ከሕዝብ ጋር ያለው ግንኙነት ነው፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሙ የሚወሰዱት የኃይል ዕርምጃዎች ለዜጎች ሞት፣ መቁሰልና መፈናቀል ምክንያት ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ ወደ ኃይል የሚያስገባ አጋጣሚ ቢፈጠር እንኳ ተመጣጣኝ መሆን ሲገባው፣ የዕርምጃው መክፋት ሕዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ ያደርጋል፡፡ አመፅና ብጥብጥ የሚፈጠረውም በእንዲህ ዓይነት ቁርሾዎች ምክንያት ነው፡፡ ከሕዝብ ጋር ተቀምጦ በአገር ዙሪያ ገባ ጉዳዮች ላይ መምከር ቢቻል ኖሮ የመብት ጥያቄዎች ሰላማዊ ይሆናሉ፡፡ ምላሾቻቸውም ዴሞክራቲክ ይሆናሉ፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሲራራቁ ግን ችግሩ የከፋ ይሆናል፡፡ ለአላስፈላጊ መስዋዕትነት ይዳርጋል፡፡ ሕዝብ ከተደመጠ ግን ሰላም ይሰፍናል፡፡

በጋራ ማስተር ፕላኑ ላይ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር ያልተቻለው ለምንድነው? ከዚህ በፊት ከክልሉ ሕዝብ ጋር ውይይት መደረጉ ተሰምቶ ነበር፡፡ በእርግጥ ተደርጎ ነበር? ታዲያ ዛሬ ምን አጋጠመ? ከዓመት በፊት ጥያቄ ተነስቶበት ለዜጎች ሕልፈት ምክንያት የሆነ ጉዳይ፣ ከዚያ በኋላ በተገቢው መንገድ ግልጽ ባለመደረጉና ውይይት ባለመካሄዱ እንደገና አመፅ እንዲያገረሽ አድርጓል፡፡ መንግሥት ከሕዝብ ጋር በቅርበት ካልተነጋገረና የሕዝቡን አቤቱታ ካላዳመጠ ችግሩ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ ሕዝብ በቀጥታ ከመንግሥት ጋር በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች አማካይነት ጥያቄዎቹንና ጥርጣሬዎቹን ማቅረብ አለበት፡፡ መንግሥትም አዳምጦ ተገቢውን ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ የሕዝብን ቅሬታና አቤቱታ በቀጥታ አለማዳመጥ ውጤቱ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በመልካም አስተዳደር ጉዳይ በተዘጋጀ መድረክ ላይ እንደተናገሩት፣ በአደረጃጀት አማካይነት የሚደረጉ ‘ሕዝባዊ’ የሚባሉ ውይይቶች አሰልቺ ሆነዋል፡፡ ሕዝቡ እየተደመጠ ባለመሆኑም በመንግሥት ላይ ያለው መተማመን መሸርሸሩን ነው የገለጹት፡፡ አሁንም ሕዝብን በቀጥታ አወያይቶ ለችግሮች መፍትሔ መስጠት መቅደም አለበት፡፡ የመንግሥት አሠራርን ለሕዝብ ግልጽ ባለማድረግ ምክንያት የሚፈጠሩ ቀውሶች ለአገር ህልውና ጠንቅ ናቸው፡፡ መንግሥት ኃላፊነቱም ተጠሪነቱም ለሕዝብ እስከሆነ ድረስ ሕዝብን ያዳምጥ፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ ካልቻለ ግን ‘ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ፣ አለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይወረውሩሃል’ የሚባለው ተረት ተግባራዊ ይሆናል፡፡

መንግሥት በተደጋጋሚ በተለይ ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ በተነሳው ሁከት ላይ፣ ፀረ ሰላም ኃይሎች እጃቸውን ማስገባታቸውን አስታውቋል፡፡ ከድርጊታቸውም እንዲታቀቡ አስጠንቅቋል፡፡ እነዚህ ያላቸው ኃይሎች የበላይነቱን አግኝተው አመፅ መምራት ከቻሉ፣ መንግሥት ማዘን ያለበት በራሱ ነው፡፡ በእርግጥም በሕዝብና በመንግሥት መካከል አለመተማመንና ጥርጣሬ የሚፈጠረውና ሌሎች ኃይሎች ጣልቃ የሚገቡት ክፍተት ሲያገኙ ነው፡፡ ይህ ክፍተት የሚፈጠረው ደግሞ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መሠረት አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ ሳያደርግ ሲቀር ነው፡፡ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበት መንግሥት አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ ሳያደርግ ሲቀር፣ ሌሎች ወገኖች ለራሳቸው ዓላማ ማሳኪያ እንደሚጠቀሙበት መጠራጠር አያስፈልግም፡፡ ይህም ትኩረት ያሻዋል፡፡

አሁንም ደግመን ደጋግመን የምንለው ሕዝብ ይደመጥ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ይከበር ነው፡፡ ዴሞክራሲ ይስፈን ነው፡፡ ሰብዓዊ መብት ይከበር ነው፡፡ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት የደነገጋቸው መሠረታዊ መብቶች ይከበሩ ነው፡፡ በተለይ ሕገ መንግሥቱ ያለምንም መሸራረፍ ተግባራዊ ሲደረግ ሕዝብ ይደመጣል፡፡ የሕዝብ ፍላጎት ገዥ ይሆናል፡፡ የመንግሥት አሠራሮች በሙሉ ግልጽ ይሆናሉ፡፡ ፍትሕ ለሁሉም ተደራሽ ይሆናል፡፡ የአገሪቱ ሀብት ለሁሉም ዜጎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይከፋፈላል፡፡ ልማትና ብልፅግና የጋራ አጀንዳ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በሚደረግ ጉዞ ግን ሕዝብ ይቆጣል፡፡ ሰላማዊው ድባብ ይደፈርሳል፡፡ ይህ ዓይነቱ ጉዞ የሚፈለግ ስላልሆነ አሁንም ሕዝብን ማዳመጥ ይቅደም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎችን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መጠበቅ፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከለላ መስጠትና በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል...

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...