Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትዓለም አቀፉ ፀረ አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲ የኢትዮጵያን እንቅስቃሴ ገመገመ

ዓለም አቀፉ ፀረ አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲ የኢትዮጵያን እንቅስቃሴ ገመገመ

ቀን:

የስፖርቱን መንደር የሚፈታተነው ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነው የኃይል ሰጪና አበረታች መድኃኒት ተጠቃሚነት መንሰራፋት አገሮችን ማዋረድ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ከአውሮፓ ሩሲያን የመሳሰሉ ታላቅ የስፖርተኞች አገር በአበረታች መድኃኒቶች ቅሌት መሳለቂያ በመሆን በዓለም አደባባይ ተብጠልጥላለች፡፡ የአገሪቱን ስም ያጎደፈው ይህ ተግባር ንፁኃን አትሎቶቿን አንገት አስደፍቷል፡፡ በቅርቡም ከወደ ኬንያ የተደመጠውና ሲደመጥ የቆየው ቅሌትም ነግ በኔን ያጭራል፡፡ ምክንያቱም ኬንያውያን በዓለም የስፖርት አደባባይ ታማኝነትን አጥተዋል፡፡ ስም ያላቸው ሯጮቿ በአበረታች መድኃኒት ጦስ የሰበሰቡትን ሜዳሊያ መልሱ ተብለዋል፡፡ ነገርየው እየከረረ በመምጣቱ ለኢትዮጵያ ሥጋት ከሆነም ሰነባብቷል፡፡

ኢትዮጵያ ምንም እንኳ ስመ ጥር አትሌቶቿ እስካሁን ከዚህ ቅሌት ጋር በተያያዘ ስማቸው ባይነሳም፣ በዓለም የሩጫ መድረክ እምብዛም እውቅና የሌላቸው አምስት አትሌቶች በአበረታች መድኃኒት ተጠርጥረው መታገዳቸው አይዘነጋም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የተገኙት በዓለም አቀፉ ፀረ አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲ ዋዳ የአፍሪካ ተወካይ ደቡብ አፍሪካዊ ሚስተር ሮዲኔይ ስዊንግለር ባለፈው ሰኞ ታኅሣሥ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ከመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም በኢትዮጵያ የፀረ አበረታች መድኃኒት ድርጅት ኃላፊዎች ጋር በሒልተን አዲስ ውይይት አድርገዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የፀረ አበረታች መድኃኒት ድርጅት ዶ/ር አያሌው ጥላሁን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲ (ዋዳ) የአፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር ሚስተር ሮዲኔይ፣ በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ዋናው ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ከፈረሙ አገሮች አንዷ እንደመሆኗ የገባችውን ቃልና ኃላፊነት ምን ያህል እየተወጣች ነው? በመከላከሉ ሒደት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ በተለይም አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስምና ዝና ያላቸው አትሌቶች አገር ስለሆነች በተለይም በዚህ ዘመን ለስፖርቱ ትልቅ ሥጋት እየሆነ ስላለው ኃይል ሰጪ አበረታች መድኃኒት ጉዳይ ለሁሉም ስፖርቶች አትሌቶች ትክክለኛውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በአግባቡ እየሰጠች ነወይ? የሚሉት ርዕሰ ጉዳዮችን በዝርዝር እንደተመለከቱና በተለይም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2011 እስከ 2015 ባሉት ዓመታት ውስጥ ልታከናውነው ያቀደችውን ስትራቴጂክ ፕላን ትኩረት እንዲሰጠው ማሳሰቢያ መስጠታውንም ገልጸዋል፡፡

በአፈጻጸም ረገድ ክፍተት እንዳይፈጠር መንግሥትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ለአገራዊው ኤጀንሲ ሙሉ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ፣ እስካሁን ባለው ግን የአገሪቱ መንግሥትም ሆነ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አትሌቶቻቸውን በመጠበቁ ረገድ ሊጠቀስ የሚችል ሥራ እንደሠሩ፣ ወደፊትም ይኼው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት፣ በተለይ በታላላቅ አትሌቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ክትትል ማድረግ የግድ እንደሚል ጭምር መግለጻቸውን ዶ/ር አያሌው አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የኦሊምፒክ ስርጸት ትግበራ አብይ የሥራ ሒደት ዳይሬክተር አቶ ታደለ ልዴቻ በበኩላቸው፣ በአገሪቱ እስካሁን የነበረው ክትትልና ቁጥጥር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የዓለም አቀፉ ፀረ አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲ (ዋዳ) የአፍሪካ ዳይሬክተር በሰጡት ማብራሪያ መሠረት ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በዋናነት ለስፖርት መምህራን፣ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖች፣ ለሙያተኞች፣ ለአትሌቶችና ለክለቦች፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ወጣቶች አካዴሚ፣ ለጥሩነሽ ዲባባ ማሠልጠኛ ማዕከል፣ ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ለሚገኘው ታዳጊ ወጣቶች አካዴሚና ለሚመለከታቸው አካላት በአገር አቀፍ ደረጃ በተለይም ከአበረታች መድኃኒት ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...