‹‹በምንም መልኩ ሕዝብ ያላመነበትንና ያልተቀበለውን ጉዳይ ለመተግበር አይሞከርም››
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ፣ አዲስ አበባን በዙሪያዋ ካሉ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ጋር በጋራ ማስተር ፕላን ለማስተሳሰር የተዘጋጀውን ዕቅድ በመቃወም በተለያዩ ስፍራዎች የተፈጠረውን ሁኔታ አስመልክቶ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡ አዲስ አበባን በዙሪያዋ ካሉ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ጋር ለማስተሳሰር ዕቅዱ የተወጠነው በ2006 ዓ.ም. ሲሆን፣ በወቅቱ ተቃውሞ አስከትሎ ነበር፡፡ ዳግም አገርሽቶ ከኅዳር 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተቃውሞ እየተናጡ ነው፡፡ በተቃውሞ ሠልፉም በሰዎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል፡፡ የማስተር ፕላኑን ጠቀሜታ በግልጽ ለማስረዳት ውስንነት እንደነበረ ያመለከቱት የክልሉ ፕሬዚደንት አቶ ሙክታር ከድር፣ በማስተር ፕላኑ ላይ ከሕዝብ ጋር መግባባት ካልደረሰ በቀር እንደማይተገበር ቃል ገብተዋል፡፡