Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዝም ያሉ አንደበቶች

ዝም ያሉ አንደበቶች

ቀን:

በሰላሳዎቹ መጀመሪያ የምትገኝ ነች፡፡ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው፡፡ ከችግረኛ ቤተሰብ የተገኘችው ሒሩት አሳምነው (ስሟ ተቀይሯል) እንደ ዕድሜ እኩዮቿ ልጅነቷ የጨዋታና የቡረቃ አልነበረም፡፡ የቤተሰቧ ኑሮ በእንክብካቤ እንዳታድግ፤ ከልጆች ተቀላቅላ እንዳትጫወት አደረገ፡፡ ዕድሜዋ ከፍ እያለ ሲሄድ የተለያዩ ችግሮችን ታስተናግድ ጀመር፡፡ ብዙ ጊዜ የተለያዩ ፆታዊ ትንኮሳዎች ይደርሱባታል፡፡ ይሁን እንጂ የሚከታተላት ባለመኖሩ ከሚደርስባት ነገር የሚታደጋት አልተገኘም፡፡ በአንድ ወቅትም ተደፈረች፡፡ ቤተሰቦቿ ግን መደፈሯን ያወቁት ሆዷ ሲገፋ ነበር፡፡ በወቅቱ ሁኔታውን አሜን ብሎ ከመቀበል ባለፈም ምንም ለማድረግ አለመቻላቸውን የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባት እናቷን ሕይወት የ14 ዓመት ልጇ ትተርካለች፡፡

ብዙዎች ‹‹ሴት ልጅ እናት፣ እህት፣ ሚስት ናት›› በሚለው ይስማማሉ፡፡ ሴት ልጆች ላይ የሚፈጸመው ጥቃቶች እንዲሁም የማኅበረሰቡ ምላሽ ሲታይ ግን ይህ ምን ያህል ከአባባል የዘለለ ነው? ያሰኛል፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ከሚያወግዙ መልዕክቶች መለቀቅ ባለፈም የፆታ እኩልነት በሥርዓተ ትምህርት እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በተለያዩ ዘጋቢ ፊልሞች፣ ቴአትሮች፣ የቴሌቪዥን ድራማዎች ስለሴቶች እኩልነት ብዙ ይባላል የተወሰነ ለውጥም ለማምጣት ተሞክሯል፡፡

በዚህም በማኅበረሰቡ እንደ ባህል ይቆጠሩ የነበሩ ጠለፋና የሴት ልጅ ግርዛት ላይ ብዙ መሥራት ቢቻልም በተለያዩ መልኩ የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶች አሁንም በስፋት ይስተዋላሉ፡፡ ለዚህም በቅርቡ በደረሰባት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ሕይወቷ ያለፈው ሐና ላላንጎን ማንሳት ይቻላል፡፡ በየጊዜው የሚሰሙ የአስገድዶ መደፈር ዜናዎች እንደ ሒሩት ባሉ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ባለባቸው ሴቶች ላይ እንደሚያይል ነገር ግን ተሸፋፍኖ በዝምታ እንደሚታለፍ በተደጋጋሚ ይገልጻል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ብዙዎች በተለያዩ ጥቅማ ጥቅም ሊያታልሉን ይሞክራሉ፡፡ መሰል አጋጣሚዎች በብዛት ስለሚገጥመን አይሆንም እንላለን፡፡ በዚህም ለእኛ የተለየ ውለታ መዋል እንደሆነና ሌላ ሰው ዞር ብሎ እንደማያየን በንቀት የሚናገሩን ብዙዎች ናቸው፤›› የምትለው ወ/ሮ ብዙዬ አስማማው የእግር ጉዳት አለባት፡፡ የ30 ዓመቷ ወይዘሮ ብዙዬ ትውልዷ በሰሜን ወሎ ሲሆን አዲስ አበባ ከመጣች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከአካል ጉዳት ጋር የተወለደችው ብዙዬ በቤተሰቡ ዘንድ እንደ ክፉ ዕድል ትቆጠር ነበር፡፡

እንደ እሷ ገለጻ የቤተሰብ ፍቅር ብርቋ ነበር፡፡ ያፍሩባታልም፡፡ አካል ጉዳተኛ መሆኗን እንደ እግዜር ቁጣ በመቁጠር ከማጀት ወጥታ ከእኩዮቿ ጋር እንድትቀላቀል አይፈቅዱም፡፡ ‹‹በድብቅ መያዝ ነው የሚፈልጉት›› ስትል ዕድሜዋ ለትምህርት ቢደርስም የቤት ውስጥ ሥራ ከመሥራት ባለፈ ትምህርት ቤት እንዳልሄደች ትናገራለች፡፡ የነበረችበት ሁኔታ በእጅጉ ቢከብዳት የትውልድ ቀዬዋን ጥላ ከ20 ዓመታት በፊት ወደ አዲስ አበባ መጣች፡፡

በአዲስ አበባ የተሻለ ሕይወት እንደሚገጥማት አስባ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከበፊቱ የከፋ ችግር ይገጥማት ጀመር፡፡ በመጀመሪያ ያገኘችው ሥራ ሰው ቤት ተቀጥሮ መሥራት ነበር፡፡ በዚህም ብዙ ፈተና ከፊቷ ይጋረጥ ጀመረ፡፡ ከነበረው የሥራ ጫና ባሻገር ድብደባና ተግሳጽ ያማርራት ነበር፡፡ ቤት ቀይራ ለመሥራት ብትፈልግም አሠሪዎቹ ከቤት እንድትወጣ አይፈቅዱላትም፡፡ እዚያው ከመሥራት ውጪ ሌላ አማራጭ ጠፋ፡፡ ከዚህ ባሻገርም በሥራዋ የሚታሰብላት ወርሀዊ ክፍያ አልነበረም፡፡ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል በዚህ መልኩ ከሠራች በኋላ ሌላ ቤት የምትቀጠርበት አጋጣሚ አገኘች፡፡ በወር 100 ብር እየተከፈላት ትሠራም ጀመር፡፡ በዚህ መልኩ ጥቂት ከሠራች በኋላ በጥቃቅንና አነስተኛ በመደራጀት የቆዳ ውጤቶችን በማቅረብ ላይ ትገኛለች፡፡  

ከዚያ በፊት የተለያዩ ፆታዊ ትንኮሳዎች ይደርሱባት እንደነበር ትናገራለች፡፡ ‹‹የአሠሪዎቼ ባለቤትና ልጆች ሊደፍሩኝ ይሞክራሉ፡፡ ሮጬ ማምለጥ ቢያቅተኝ የወር አበባ ላይ እንደሆንኩ ዋሽቼ አመልጥ ነበር፤›› ስትል ሰው ቤት በሠራችባቸው ጊዜ ያጋጥማት የነበረውን የመደፈር ሙከራ ታስታውሳለች፡፡ ከዚህ ባሻገርም በተከራዮችና በጎረቤቶች የመድፈር ሙከራ ይደርስባት ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የገጠማትንም እንዲህ ትናገራለች፡፡ ‹‹አሠሪዎቼ ለአንድ ጉዳይ ወጣ ብለዋል፡፡ ግቢውም ጭር ብሎ ነበር፡፡ ይህንን ከርቀት ሲያስተውል የነበረ ጎረቤት የሚኖር አንድ ወጣት ድንገት ያዘኝ፡፡ ብጮህም የሚደርስልኝ አልነበረም፡፡ አለቀልኝ ያልኩበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ነገር ግን በከባድ ልመናና ለቅሶ ሐሳቡን አስቀየርኩት፡፡››

መሰል ፆታዊ ጥቃቶች የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ባለባቸውና መናገር በማይችሉ ሴቶች ላይ እንደሚበረክት ሀንዲ ካፕ ኢንተርናሽናል ከሁለት ዓመታት በፊት ያወጣው ጥናት ያመለክታል፡፡ በጉዳዩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ምሕረት ንጉሤ እንደሚሉት የማዕከሉ አባል የሆኑ ብዙ ሴቶች ለፆታዊ ጥቃት የተጋለጡ ናቸው፡፡

‹‹ከቅርብ ጊዜ በፊት አንዲት የማኅበራችን አባል የሆነች የ24 ዓመት ወጣት ተደፍራ ወልዳለች፤›› በማለት በጎረቤት ስለተደፈረች የማኅበሩ አባል ይገልጻሉ፡፡ ሰዎች በአንድ ግቢ ውስጥ ተሰባስበው በሚኖሩበት አካባቢ መሰል ድርጊቶች በስፋት ይፈጸማሉ፡፡ ስለመደፈራቸው ማስረዳት ስለሚቸገሩም የደረሰባቸው ጥቃት ሳይታወቅላቸው የሚቀሩ ጥቂት እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ የሚታወቀው ሆዳቸው ሲገፋ ነው፤›› በማለት የሚደርሰውን ችግር የከፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የማዕከሉ አባል የሆኑ ጥቂት የማይባሉ ወንዶችም የመደፈር አደጋ እንደሚያጋጥማቸው ብዙዎቹም ችግራቸው ሳይታወቅ እንደሚቆይ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቤተሰብ ማን ያስባቸዋል በሚል አስፈላጊውን ጥንቃቄ አያደርግላቸውም፤›› የሚሉት ሥራ አስኪያጇ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ወንጀል እንደፈጸሙ ሳይሆን የተለየ ውለታ እንደዋሉላቸው ሁሉ ይሰማቸዋል ይላሉ፡፡

ችግሩ አሳሳቢና ተገቢውን ትኩረት የሚሻ መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ብርሃኔ ዳባ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የመደፈር አደጋ ያጋጠማቸው ሴቶች የራሳቸው ጥፋት እንደሆነ ሁሉ በራሳቸው ያፍራሉ፡፡ ራሳቸውንም ለሥነልቦና ጫና ያጋልጣሉ፡፡

በማኅበሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በመሥራት ራሳቸውን እንዲገልጹና ጥቃት አድራሾችን ከሕግ ለማቅረብ ይሞክራል፡፡ ይሁን እንጂ በብዛት የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑ መናገር የማይችሉ ሴቶች የደረሰባቸውን ፆታዊ ጥቃት ለፍርድ ቤት ማስረዳት እንደሚቸገሩ በዚህም ብዙ ጊዜ ወንጀለኛው ሳይቀጣ እንደሚቀር ወ/ሮ ብርሃኔ ይናገራሉ፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...