የናታኒያሁ ውሻ ፖለቲከኞችን ነከሰች
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን የታኒያሁ ከቤታቸው አዘጋጅተውት በነበረው የአይሁዶች ሃይማኖታዊ በዓል ዝግጅት ላይ ከተጠሩ እንግዶች ሁለቱን በመንከስ የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት የሳበችው ውሻቸውን እንዲህ ያለ ባህሪ የሚያሳዩ ውሾች ተገልለው ከሚቀመጡበት መጠለያ ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ምንም እንኳ ብ…. ሕግ እንደሚያዘው ካያን ከመጠለያ ለማስገባት ተገድደናል›› ብለዋል ታንያሁ በፌስቡክ ድረገጻቸው፡፡ የውሻቸው ቀጣይ ዕጣ ምን ሊሆን እንደሚችል ግን ያሉት ነገር የለም፡፡ አሥር ዓመት የሆናት የናታኒያሁ ውሻ የነከሰችው የአገሪቱን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ሌላ የፓርላማ አባልን እንደሆነ በሮይተርስ ዘገባ ተመልክቷል፡፡ አንደኛው ተነካሽ ጉዳዩ ለመገናኛ ብዙኃን ፍጆታ የማይበቃ ተራ ነገር ነው ሲሉ የእሥራኤሉ ቻናል 10 ቲቪ ደግሞ ሁለቱ ሰዎች ተነከሱ በተባለበት ምሽት ናታኒያሁ ራሳቸውም መነከሳቸውን ዘግቧል፡፡
**********
ጉልበትና ውበት
ባንድ ወጥተው ሳለ – ጣይና ጨረቃ
ውበት ጥሙን ላይቆርጥ – ዐይኑ ላይጠረቃ
ዓለሙ በመላ – በጨረቃ ውበት – እየነሆለለ
በፀሐይ ዝንጋዔ – ፍጥረት ተቸገረ፡፡
(ኋላም) ጨረቃና ፀሐይ – ድርድር ጀመሩ
ፀሐይዋ ውሎዋን – ጨረቃ ሌሊቱን – ላለም እንዲያበሩ፡፡
*****************
(ያኔ) ዘረ አዳም በሙሉ – ቀን ሲባዝን ውሎ – ቁጭ ይልና ማታ
‹‹ታምር ነው!›› እያለ – ዓይነርግቧን ገልጦ
– ፍጥረቷን ያደንቃል፤ ሩቧን ጨረቃ፡፡
******************
ቅናት ያናወጣት – ፀሐይ ተበሳጭታ
ዓለሙን በመላ – በንዳድ ብትመታ
ዛላ ጠወለገ፤ ቡቃያው አረረ
ያዳም ዘር በሙሉ – ጦሙን ውሎ አደረ
ችግር አስተምሮት – ሁሉን መረመረ
ተመራመረናም – ሳይንስን ፈጠረ
(ኋላም እንዲህ አለ)
‹‹በጨረቃ ፍቅር ዓለም ቢነሆልል፣ ፍጥረታት ቢንጫጩ
የፀሐይ ብርሃን ነው፣ ለውበቷ ምንጩ፡፡››
- በአካል ንጉሤ፣ ፍላሎት፣ 2006 ዓ.ም.
**************
አንደበትን አትለጉሚ
አንደበት፣ ነፍስ ዓለምን ለመድረስ እጇን እምትዘረጋበት መንገድ ነው፡፡ ይህ ቃል ይሆን ይሆናል፤ ዝምታም ይሆን ይሆናል፡፡ በልብሽም በነፍስሽም መናገር አቁሚና አድምጪ፡፡
ምስባክ መድረኩን በቁጥጥርሽ ስር ለማድረግ አትሞክሪ፡፡ ድምፅ የተነፈጉቱ እንዲናገሩ ፍቀጂ፡፡
ነፍሶች ሁሉ እኩል ናቸው፡፡ እኩልነት ማለት፣ ሰዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ አስቀምጦ የልባቸውን እንዲናገሩ ማድረግ ብቻ እንዳይደለ ግን እውቂ፡፡
ይልቅ፣ ልበ-ንፁሃን የሚናገሩ፣ በአዋቂነት ማን-አለብኝነት ጉድፍ ተሸፍኖ በልብሽ ጥልቀት ውስጥ የተደበቀውን የዛ ራስሽን እውነት እንዲሁ በመረዳት፣ እነሱ እልብሽ ውስጥ እንዲቀመጡ መፍቀድ ነው፡፡ አዎን፣ የነሱ አንደበት ያንቺም አንደበት ነው፡፡ ከዚያ ሁሉም ነፍሳት በጋራ ከሚዋኙበት ውቂያኖስ የፈለቀ አንድ ጠብታ፡፡ የራስሽን እውነት የምትይዢውን ያህል ያንንም እንዱያ አጥብቀሽ ያዢው፡፡
ይህ፣ እጅግ ጥልቅ በሆነ ደረጃ ሌሎችን መድረስ፣ ሌሎችም እንዲደርሱሽ መፍቀድ፣ ውሳኔ ሆኖ ሲወለድ፣ በልብሽም በነፍስሽም አክብሪው፡፡ ያ ውሳኔ ያንቺም ውሳኔ ነውና፡፡
የገዛ ልብሽ እንዲናገር ስትፈቅጂም እንዲሁ አድርጊ፣ አዕምሮሽን ዝም አስብዩና አድምጪ፡፡
የሚናወጠውን ባህር ለመግታት ከሞከርሽ፣ በውስጡ አትዋኚበትም፡፡ ትሰጥሚያለሽ፡፡
- አንደበትን አትለጉሚ፣ ኦታም ፑልቶ፣ የፈላሱ መንገድ፣ 2006 ዓ.ም.
*************
አፎቻና ዕድር
‹‹አፎቻ›› በአማርኛ ‹‹ዕድር›› ከምንለው የመረዳጃ ስብስብ ጋር ይቀራረባል፡፡ ጥንካሬውንና የእንቅስቃሴ አድማሱን ብናይ ግን ዕድርና ‹‹አፎቻ›› በእጅጉ የሚለያዩ ተቋማት መሆናቸውን መመስከራችን አይቀርም፡፡
አዎን! ‹‹አፎቻ›› በማንኛውም ማኅበራዊ ሕይወታችን ውስጥ አለ፡፡ ሙታንን ከመቅበር ባሻገር በርካታ ማኅበራዊ ኃላፊነቶችንም ይከውናል፡፡ ዕድር የሚቋቋመው ግን በቀብር (ለቅሶ) ወቅት ለመረዳዳት በሚል ዓላማ ነው፡፡
ዕድርን በሌሎች አጋጣሚዎች የመጠቀም ልማድ እምብዛም ነው፡፡ ኅብረተሰቡም ቢሆን ከዕድሩ የሚጠብቀው የተወሰኑ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ሠርግን በመሳሰሉ የደስታ አጋጣሚዎች በዕድሩም ሆነ በዕድርተኛው ላይ የሚጣል ማኅበራዊ ግዴታ የለም፤ ዕድርተኞቹ ደጋሹን ሰው (ቤተሰብ) በፍላጎታቸው ካልረዱት በስተቀር፡፡
‹‹አፎቻ ›› ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ ሠርግና ለቅሶ በ‹‹አፎቻ›› አባላት በእኩል ዓይን ይታያሉ፡፡ ማንኛውም ‹‹ጌይ ኡሱእ›› ያለ በቂ ምክንያት ከሠርግና ከለቅሶ መቅረት አይችልም፡፡ ከ‹‹አፎቻው›› አባላት መካከል አንዱ በክፉ ደዌ ተይዞ የአልጋ ቁራኛ ከሆነም ሌሎች አባላት ገንዘብ አዋጥተው ያሳክሙታል፡፡ የተጣሉ ጎረቤታሞች ካሉም ‹‹አፎቻ›› በአስቸኳይ እንዲታረቁ ያዛቸዋል፡፡ ሰዎቹ ‹‹እምቢ! አንታረቅም!›› የሚሉ ከሆነም ‹‹አፎቻ›› አስገዳጅ ዕርምጃ ሊወስድባቸው ይችላል፡፡
ባለቤቷ በቂ ‹‹መስሩፍ›› (የቤት ወጪ) የማይሰጣት ‹‹ጌይ ቀሐት››ም ስሞታዋን ለ‹‹አህሊ›› አቅርባ አጥጋቢ ውሳኔ ካላገኘች (ወይም በውሳኔው ቅር ከተሰኘች) ለ‹‹አፎቻ›› ይግባኝ ማለት ትችላለች፡፡ ከዚህ እልፍ ሲልም ‹‹አፎቻ››ን የሕዝቡ የማንነትና የሞራል እሴቶች ጠባቂ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ‹‹ጌይ እሱአች›› የባህል፣ የሥነ ምግባር፣ የታሪክና የትውፊት እሴቶቻቸውን ከሐረሪ አባቶች/እናቶች የሚማሩበት መድረክ እንደሆነም በኩራት ይናገራሉ፡፡
- አፈንዲ ሙተቂ፣ ሀረር ጌይ፣ 2004 ዓ.ም.
***********
ሊቀ መንበር
የዛሬን አያድርገው እንጂ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በአውሮፓ ወንበር በጣም ውድ ነበር፡፡ ዲታ ዲታው ብቻ ነበር ወንበር የነበረው፡፡ በየመኖሪያ ቤቱ እንኳ ያለው ወንበር አንድ ብቻ ነው፡፡ አባወራው ብቻ የሚቀመጥበት፡፡ ሚስትን ጨምሮ ቤተሰቡ በሙሉ የሚቀመጠው መሬት ወይም አግዳሚ ወንበር ላይ ነው፡፡ በርጩማ ቢጤ ከተገኘም ይሆናል፡፡ በተረፈ ከበድ ያለ እንግዳ ካልመጣ የአባወራውን ወንበር ማንም አይደፍረውም፡፡ ቼርማን የምትለዋ እንግዲህ እንዲህ ነው የጀማመራት፡፡ የሃይማኖት መሪው መቀመጫ እንኳ በላቲን ‹‹ካቴድራ›› ይባል ነበር፡፡ አንዳንድ የሃይማኖት ተቋማትም ‹‹ካቴድራል›› መባላቸው ከዚሁ ጋር ይያያዛል፡፡ የእኛም አገር የታቦት መቀመጫ ስፍራ ወንበር መባሉን ልብ እያልን፡፡ ‹‹ሊቀ መንበር›› መባሉ ከታቦት መወዳደሩን እያስተዋልን፡፡
***********
የናንተን ያህል አንበላም
አንዳንድ እንስሳት ለብዙ ቀናት ሳይመገቡ መቆየት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ እባብ የሚመገበው በሳምንት አንዴ ነው፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ከዚያም በላይ መቆየት ይችላል፡፡ ለመገረም አትቸኩሉ፡፡ ቀንድ አውጣ አለላችሁ ለሦስት ዓመታት የእህል ዘር ሳያይ የቆየው፡፡
**************
ዓሣዎች ይተኛሉ
ለአፍታ ያህል አረፍ ይሉ እንደሆን እንጂ አይተኙም፡፡ እንቅልፍ ብሎ ነገር አያውቁም፡፡
***********
መጽሐፈ ሰይጣን
ዴቭልስ ባይብል ወይም የሰይጣን መጽሐፍ የሚባለው መጽሐፍ የተጻፈው በአህያ ቆዳ ላይ ነው፡፡ ጸሐፊው በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ጽፎ እንዲጨርስ በሰይጣን የተገደደ በመሆኑ፣ ሕይወቱን ለማቆየት ሲል ነው የጻፈው የሚል አፈ ታሪክ አለ፡፡ የሰይጣን መጽሐፍ መባሉም ለዚሁ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ ተገድጄ ነው የጻፍኩት ባዩ ጸሐፊም የኋላ ኋላ የሰይጣን ደቀመዝሙር ሆኗል ይባላል፡፡ ያዳቆነ ሰይጣን … መሆኑ ነው፡፡
- ‹‹እፎይታ›› (1985)
**************