Wednesday, February 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የአስከሬን ምርመራ ዘርፉን ፌዴራል ፖሊስ ቢቀበለን እንመርጣለን››

አቶ ክበበው ወርቅነህ በዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ

ዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል የተቋቋመው በ1889 ዓ.ም. በዓድዋ ጦርነት ወቅት ነው፡፡ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወታደሮች ሕክምና የሚሰጥ ሆስፒታል ባለመኖሩ፣ ተቋቋመ ኢትዮጵያዊ ባለሙያ ባለመኖሩም የሕክምና አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ከሩሲያ በመጣ የቀይ መስቀል ቡድን ነበር፡፡ ቡድኑ የተወሰኑ ኢትዮጵያውያንንም በሙያው ማሠልጠን ችሏል፡፡ በዚህ መልኩ እርምጃውን አንድ ብሎ የጀመረው ሆስፒታሉ፣ በጦርነት የቆሰሉ አርበኞችን በማከም ደጀንነቱን አስመስክሯል፡፡ ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላም የአገሪቱ ብቸኛ ሆስፒታል በመሆን ለረዥም ጊዜ አገልግሏል፡፡ የተለያዩ ሆስፒታሎች በተቋቋሙበት በአሁን ወቅትም አገልግሎቱን በስፋት እያቀረበ ይገኛል፡፡ የሆስፒታሉን አጠቃላይ ገፅታ እና የተለያዩ ተግዳሮቶች በተመለከተም የሆስፒታሉን ሥራ አስኪያጅ አቶ ክበበው ወርቅነህን፣ ሻሂዳ ሁሴን አነጋግሯቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ሆስፒታሉ ሲመሰረት ምን ዓይነት አገልግሎት ይሰጥ ነበር?

አቶ ክበበው፡- እንደተመሠረተ ሕክምና ያጠኑ ብቁ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አልነበሩም፡፡ በመሆኑም የሜዲካል ዳይሬክተር እና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ይሠሩ የነበሩት ነጮች ናቸው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን መንግሥት ባለሙያዎችን ውጭ እየላከ በማስተማር ኢትዮጵያውያን ሙያተኞችን ማፍራት ችሏል፡፡ በወቅቱ ብቸኛ ሆስፒታል እንደመሆኑ ብዙ ጫና ነበረበት፡፡ በመሆኑም የባለሙያዎችን ቁጥር ማሳደግ ግድ ነበር፡፡ ይሰጣቸው የነበሩ አገልግሎቶችንም እንዲሁ፡፡ በወቅቱ ጠቅላላ ሕክምና፣ የአጥንት ሕክምና፣ የእናቶችና ሕፃናት ሕክምና ይሰጥ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ሆስፒታሉ በአሁኑ ሰዓት ምን ዓይነት ሕክምናዎችን ይሰጣል?

አቶ ክበበው ፡- ከእናቶችና ሕፃናት ሕክምና በስተቀር ጠቅላላ የቀዶ ሕክምና እንዲሁም፣ የአጥንት ሕክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በዋናነት የምንታወቅበት በዓይን ሕክምና ነው፡፡ ሆስፒታሉ ከሚሰጣቸው የሕክምና አገልግሎቶች 60 በመቶ የሚሆነውን የሚይዘው በዓይን ሕክምም ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም የአገልግሎቱን ጥራትና ተደራሽነት ማስፋት ተችሏል፡፡ ይኼንንም አጠንክረን ለመቀጠል ብዙ እየጣርን እንገኛለን፡፡ እንደ አጠቃላይ የሆስፒታሉ የአገልግሎት ተደራሽነትም ሰፍቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በጣት የሚቆጠሩ ባለሙያዎች የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ላይ ቁጥራቸውን 800 ማድረስ ተችሏል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ታካሚዎች ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ ብዙ ሠርተናል፡፡ በተለይም የባለሙያዎችን ሥነ ምግባር በማሻሻል በኩል ተሠርቷል፡፡ ለውጥም ማግኘት ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕክምና መሣሪያዎች በተገቢው መጠን አላችሁ?

አቶ ክበበው፡- ትላንት እንጠቀምባቸው የነበሩ መሣሪዎች ጊዜ አልፎባቸዋል፡፡ ሌላ የተሻለ መሣሪያ መጠቀም ግድ ይላል፡፡ መንግሥትም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተለይም የከተማው መስተዳድርና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ብዙ እየረዱን ይገኛሉ፡፡ ለዓይን ሕክምና የሚውሉ የጊዜው ቴክኖሎጂ ያፈራቸው መሣሪያዎች በማቅረብ ረገድ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ለቀዶ ሕክምና የሚያገለግሉ ዘመናዊ መሣሪያዎችም ማግኘት ችለናል፡፡ በፊት የነበሩ የኤክስሬይ ማሽኖች አሁን በዲጂታል ተቀይረዋል፡፡ በዚህ ሆስፒታል ውስጥ የሲቲ ስካን ማሽን የማይታሰብ ነበር፡፡ ዛሬ ግን የሲቲስካን ማሽን ባለቤት መሆን ችለናል፡፡ ዘመናዊና ምቹ አልጋዎችም አሉን፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ የሚያጋጥሟችሁ ተግዳሮቶች ምን ምን ናቸው?

አቶ ክበበው፡- ሰፊ የግብዓት ችግሮች ነበሩብን፡፡ አገልግሎቶቻችንን ለማስፋት የሚያስፈልገው በቂ የሰው ኃይልም አልነበረንም፡፡ እነዚህ ደግሞ በበቂ ካልተገኙ  አገልግሎት ማስፋት ቀርቶ ያለውንም ለማስቀጠል ከባድ ነው፡፡ በዚህ ላይ የተለያዩ ሥራዎች እየሠራን እንገኛለን፡፡

ከውኃ፣ ከመብራት ከፍሳሽ ማስወገጃ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችም አሉ፡፡ እድሳት የሚያስፈልጋቸው ዕድሜ ጠገብ ሕንፃዎች ነበሩ፡፡ ተጨማሪ ሕንፃም ያስፈልገን ነበር፡፡ የነበረብን የሕንፃ ችግር የከተማ መስተዳድሩ በ230 ሚሊዮን ብር ባለ ስምንት ወለል ሕንፃ ገንብቶልን ችግሩ ተቀርፏል፡፡ ባለሙያዎቻችን ጋር የሚታይ የአመለካት ችግርም ነበር፡፡

የፖሊሲ አቅጣጫው እንደሚያስቀምጠው ማንኛውም የሕክምና ተቋም የሕዝብን ባለቤትነት ያረጋግጣል ይላል፡፡ የሕዝብ ባለቤትነትን ለማረጋገጥም ደግሞ ሕዝቡና ባለሙያው መገናኘት እና መወያየት አለባቸው፡፡ በዚህም በየሦስት ወሩ የሚዘጋጅ ባለሙያውና ሕዝቡ የሚገናኝበት የውይይት መድረክ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህ መሠረት ባለሙያው ጋር ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ባለሙያዎቹ መልካም ሥነ ምግባር እንዲላበሱ መንግሥት የተለያዩ ሥራዎች ሠርቷል፡፡ አዲስ በተገነባው ሕንፃ ላይ አስፈላጊ የሆኑ እንደ ላይብረሪና መዝናኛ ያሉ አገልግሎቶች ተሟልተዋል፡፡ በመንግሥት ተቋም ውስጥ የግል ሕክምና መስጫ ሰዓት በመዘርጋትም በሆስፒትሉ ከሥራ ሰዓት ውጪ በክፍያ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ በእዚህም የሚያገኙትን ወርሐዊ ገቢ ለማሳደግ በሥራቸው ደስተኛ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል፡፡ የተለያዩ የሕክምና ግብዓቶች እጥረት መኖርም ትልቅ ችግር ነበር፡፡ በተለይ ለዓይን ሕክምና የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እጥረት ነበረብን፡፡ በፍሳሽ በኩል የሚታየውን ችግርም ለመቅረፍ እየሞከርን ነው፡፡ ከፍሳሽ ማስወገጃ ጋር የተያያዘ ችግር ለዓመታት የዘለቀ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለመሥራት ተሞክሮ አልተሳካም፡፡ በሆስፒታሉ የሚገኙ ዶክመንቶችን በማደራጀት ላይ ሳለን አንድ ደብዳቤ አገኘሁኝ፡፡ በ1940 ዓ.ም. ለጤና ሚኒስቴር የተጻፈው ደብዳቤው ሆስፒታሉ ያለበትን የፍሳሽ ችግር ሴፕቲክ ታንክ በመገንባት እንዲስተካከል የሚጠይቅ ነበር፡፡ ደብዳቤውን የጻፉት በወቅቱ የሆስፒታሉ ኃላፊ የነበሩ ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ነበሩ፡፡ ጥያቄው ምላሽ ሳያገኝ ቆይቶ  ሲንከባለል መጥቶ እኔ ላይ ወደቀ፡፡ አጠቃላይ የግቢውን ፍሳሽ በዘመናዊ መልኩ ማስወገጃ ሥርዓት የማስተካከል ሥራው ተጀምሯል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የሕንፃው መገንባት በተለይ የሚያቃልልላችሁ የትኛውን ችግር ነው?

አቶ ክበበው፡- ሕንፃው በመሠራቱ የምናገኛቸው በርካታ ጥቅሞች አሉ፡፡ የአልጋ ችግር አንዱ ጥያቄ ነበር፡፡ በርካታ ታካሚዎች በአልጋ እጦት ይንከራተቱ ነበር፡፡ አሁን ላይ ችግሩ ተቀርፏል፡፡ በፊት ተቋሙ የነበረው የአልጋ ብዛት 200 ብቻ ነበር፡፡ ሕንፃው ተጨማሪ 356 አልጋዎች ይዟል፡፡ በአጠቃላይ 556 አለን ማለት ነው፡፡ የነበረው ሰፊ የአልጋ እጥረት ችግር ተፈትቶልናል፡፡  

ሪፖርተር፡- የአልጋ እጥረት በነበረበት ወቅት ታካሚዎችን በምን መልኩ ነበር የምታስተናግዱት?

አቶ ክበበው፡- በነበረው የአልጋ ችግር ታካሚው እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ ቀጠሮ ይሰጠው ነበር፡፡ በተለይም በቀዶ ሕክምና እና በአጥንት ሕክምና ዙሪያ የሚመጡ ታካሚዎች በረዥም ቀጠሮ ይሰቃዩ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜም በሚሰጠው የተራዘመ ቀጠሮ ሕክምናውን ሳያገኙ የሚሞቱ ብዙ ናቸው፡፡ ተራ ደርሷችኋል ብለን ስንደውልላቸው ሕይወታቸው እንዳለፈ የተገረን ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ዛሬ ይኼ ሁሉ ቀርቷል፡፡ ባጣም በዛ ቢባል የሦስት ቀን ቀጠሮ ቢሰጥ ነው፡፡ ይኼ ቀላል ለውጥ አይደለም፡፡ ይኼንን ያመጣልን የግብዓቱ መስተካከልና የሕንፃው መሠራት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዓይን ሕክምና ረገድ ካለው የግብዓት እጥረት ባሻገር ከቦታ ጋር የተያየዙ ችግሮች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ክበበው፡- የዓይን ሕክምናው ትልቅ የቦታ ችግር አለበት፡፡ ሐኪሞች የተለያዩ ሕክምናዎችን ለመስጠት ይቸገራሉ፡፡ የዓይን የቀዶ ሕክምና የሚሰጥበት ቦታም በጣም ጠባብ ነው፡፡ ያለውን ችግር ለመቅረፍም ራሱን የቻለ ሕንፃ ለማስገንባት ከሳምንታት በፊት ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ በ120 ሚሊዮን ብር ለማስገንባት የመሠረት ድንጋይ ጥለናል፡፡ ግንባታው በ2011 ዓ.ም. ተጠናቆ ሥራ ይጀምራል ብለን ተስፋ አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለሆስፒታሉ ማስፋፊያ የተገነባው ሕንፃ የግንባታው ጊዜ መጓቱን፣ በተለያየ ጊዜያት መቋረጡንና የመልካም አስተዳደር ችግር እንደነበረበት ይነገራል፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

አቶ ክበበው፡- የሕንፃው ግንባታ የተጀመረው በ2004 ዓ.ም. ሲሆን፣ በ2006 መጨረሻ ላይ ግንባታው ተጠናቀቆ ሥራ ይጀምራል ተብሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች በተባለበት ጊዜ ሳይደርስ ቀርቷል፡፡ ግንባታውን በዋናነት ያዘገየው ከአካባቢው ተፈጥሯዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ያጋጠመ ችግር ነው፡፡ መሠረት ለማውጣት ወደታች ሲቆፈር ውኃ ይፈልቅ ነበር፡፡ ትልልቅ አለቶች ያጋጥሙም ነበር፡፡ በሌላ በኩል በዙሪያው የነበሩ መነሳት የነበረባቸው ሰዎችን ለማንሳት ረዘም ያለ ጊዜ ፈጅቷል፡፡ ከአጥሩ ግንባታ ጋር በተያያዘ ችግሮች በመኖራቸው ተገኝተው በወቅቱ የነበሩ አመራሮች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአስክሬን ክፍል ጋር በተያያዘ ብዙ ቅሬታዎች ይስማሉ፡፡ አስፈለጊው ምርመራ በጊዜ እንደማይከናወን፣ የሠራተኛ እጥረት እንዳለ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም ጋር የሚነሱ ችግሮች መኖራቸው ይነገራል፡፡ የችግሮቹ መንስኤዎች ምን ምን ናቸው? ለመፍታት የምታደርጉት ጥረትስ ምን ይመስላል?

አቶ ክበበው፡- ሆስፒታሉ የአስክሬን ምርመራ ሲሠራ 40 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡   ይሁን እንጂ በዘርፉ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ የባለሙያ እጥረትም ዋነኛው ነው፡፡ ዘርፉ በሚፈልገው ሙያ ሰዎችን ለማስተማር ያደረግነው ጥረትም አልተሳካልንም፡፡ ደፍሮ የሚገባበትም ጠፍቷል፡፡ በመሆኑም የውጭ ዜጎችን ለመቅጠር ተገድደናል፡፡ እስካሁን አገልግሎት የሚሰጡትም የኩባ ሐኪሞች ናቸው፡፡ ክፍያውን የምንፈጽመውም በዶላር ነው፡፡ ሆስፒታሉ በቀን እስከ 50 የሚሆኑ አስከሬኖች ይቀበላል፡፡ የተለያዩ ኬዞች ስለሚመጡም ሙሉ ምርመራ መደረግ አለበት፡፡ ይሁን እንጂ ካለው የሥራ ጫና፣ የባለሙያ እጥረትና የቋንቋ ችግር አንፃር በተፈለገው ጊዜ ለማደረስ ያስቸግራል፡፡ ከሠራተኞች ጋር ተያይዘው የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ነበሩ፡፡ አስከሬን ጫኝና አውራጆች ገንዘብ ይቀበሉ ነበር፡፡ ይህን የሚያደርጉትን ከሥራ እሰናብተናል፡፡ ከቀጠሮ መራዘም ጋር የሚነሱ ቅሬታዎችም እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ይህም ካለው የሰው ኃይል እጥረት የሚፈጠር ነው፡፡ ያለንን የሰው ኃይል እንዳናሳድግ ደግሞ ሲቪል ሰርቪስ ለመደቡ ያስቀመጠው ደመወዝ የሚስብ አይደለም፡፡ እስካሁን ያልተቀረፈ ችግራችንም ይኼ ነው፡፡ በተቻለን አቅም ያለውን ችግር ለመፍታት የክፍሉን ሠራተኞች በትርፍ ጊዜያቸው በአበል እያሠራን ነው፡፡ በአስከሬን ክፍል ያለው ጫና በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ለወራት ተቀብሮ የሰነበተ አስከሬን ለምርመራ ይመጣ ነበር፡፡ አጋጣሚው ሠራተኞቹ በኢንፌክሽን እንዲጠቁ ያጋልጥ ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ አጋጣሚውን ለመቀነስ ተችሏል፡፡ ያለውን አጠቃላይ ችግር ለመቅረፍ ሁሉም ክልሎች የራሳቸው የአስከሬን ምርመራ ተቋም ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- አስከሬን ለማቆየት የሚረዳ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ትጠቀማላችሁ?  

አቶ ክበበው፡- የሚሰነብቱ አስከሬኖችን ለማቆየት ማቀዝቀዣዎች (ዲፕፍሪዝ) መጠቀም ግድ ይላል፡፡ ሆስፒታሉም በቅርቡ አንድ ማቀዝቀዣ መግዛት ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ በቂ አይደለም፡፡ ሌላ ሁለት ተጨማሪ ማቀዝቀዣዎች ያስፈልጉናል፡፡ የአስከሬን ክፍሉን ዘመናዊ ለማድረግ ማቀዝቀዣ ብቻም በቂ አይደለም፡፡ ክፍሎቹን ማስፋት ይጠበቃል፡፡ ይኼንን ለማድረግም ልዩ ልዩ ሥራዎች እየሠራን እንገኛለን፡፡ ነገር ግን ካለው ጫና አንፃር የአስከሬን ምርመራ ዘርፉን ፌዴራል ፖሊስ ቢቀበለን እንመርጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሆስፒታሉ በቀን ምን ያህል ሕመምተኞችን ያስተናግዳል?

 አቶ ክበበው፡- ከዚህ ቀደም በቀን ከ200 እስከ 300 ታካሚ ያስተናግድ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን እስከ 600 የሚደርሱ ታካሚዎችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡ ሕንፃው አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም በቀን እስከ 800 ታካሚዎች ማስተናገድ ይቻላል፡፡ በቀን ማስተናገድ የሚችለውን የታካሚ ቁጥር ከማሳደጉ ጎን ለጎንም የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ ካርድ ክፍል ይታይ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ በሙያው የሠለጠኑ ሰዎች ቀጥረናል፡፡ የእናቶችና ሕፃናት ሕክምና ቀድመን እንሰጥ የነበረ ቢሆንም፣ በተለያዩ ሆኔታዎች አቋርጠናል፡፡ ይሁን እንጂ በቅርብ ጊዜ ውስጥ አገልግሎቱን መስጠት እንጀምራለን፡፡ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ለመጀመርም ልዩ ልዩ ሥራዎች በመሥራት ላይ እንገኛለን ቦታውም ቀደም ተብሎ ተዘጋጅቷል፡፡ ወተር ትሪትመንት ማሽንም ገዝተናል፡፡

 

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...

‹‹በአሁኑ ሰዓት እየፈተነን ያለው እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን መሥራት አለመቻላችን ነው›› አቶ ልዑል ሰገድ መኮንንን፣ አይሲዳ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

አይሲዳ አገር በቀል የዕርዳታ ድርጅት በኤችአይቪ ሥርጭት ቁጥጥር ላይ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ራሱን እንደ አዲስ አዋቅሮ በተለይ ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ...

‹‹ማንም ያለ ምክንያት አልተፈጠረምና ዜጎች እንዳይባክኑ እንሠራለን›› አቶ አብዱልፈታህ ሁሴን፣ የብሬክስሩ ትሬዲንግ ሥራ አስፈጻሚ

ብሬክስሩ ትሬዲንግ ‹ባለራዕይ፣ ቅን፣ ጤናማና ባለፀጋ ትውልድን ለመፍጠር የሚል ዓላማን ሰንቆ ቅን በተሰኘና አሥራ ስድስት አባላት ባሉት ቡድን ከአራት ዓመት በፊት የተመሠረተ ድርጅት ነው፡፡...