ታንዛኒያን ለሁለት ተከታታይ የሥልጣን ዘመን የመሩት ፕሬዚዳንት ጃካያ ኪኩዌቴ የሥልጣን ዘመናቸውን ጨርሰው ኃላፊነታቸውን ለተተኪው ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ በምርጫ ካስረከቡ ከ50 ቀናት በላይ ተቆጠሩ፡፡ ‹‹ቡልዶዘር›› በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁት የ56 ዓመቱ አዲሱ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ፣ ለአገራቸው ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ መሪዎችም ትምህርት የሚሆን ተግባር ይዘው ብቅ ማታቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ሕዝቡ የሚከፍለውን ታክስ ለሕዝቡ ቀጥታ ልማት ማዋልን ቀዳሚ ተግባራቸው እንዳደረጉ የተነገረላቸው ፕሬዚዳንቱ፣ በሕዝቡ ገንዘብ የየትኛውም የመንግሥት ባለሥልጣን የግል ፍላጎት እንደማይሟላ፣ አገሪቷን ለአላስፈላጊ ወጪ የሚዳርጓት በዓላት እንደማይከበሩና ለፕሬዚዳንት በዓለ ሲመት ተብሎ የሚወጣ ብዙ ገንዘብ እንደማይኖር ቃል የገቡትን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡
አብዛኞቹ የአፍሪካ መሪዎች በተለይም ከሰሃራ በታች የሚገኙትና በሙስናና በድህነት የተዘፈቁት፣ በችግር ወቅትም ቢሆን ሕዝባዊ በዓላትን ከማክበርም ሆነ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚገኙ ባለሥልጣናትን ለልምድ ልውውጥ እያሉ አውሮፓ፣ እስያና አሜሪካ ከመላክ አይቆጠቡም፡፡ ባለሥልጣናት በተለያዩ የአገራቸው ክፍሎች የሚገኙ ዜጐች ያሉበትን የኑሮ ደረጃ በየጊዜው እየጎበኙ ችግሮቻቸውን ከመፍታት ይልቅ፣ በስብሰባ ስም በትላልቅ ሆቴሎች ሲደግሱ የውሎ አበላቸውን የአንዱን ቀን እንደ ሁለትና ከዚያም በላይ ቀናት እያሰቡ፣ የሕዝቡን የታክስ ገንዘብ ሲቀራመቱ ማየት ለአፍሪካውያን አዲስ አይደለም፡፡
አፍሪካ ብዙኃኑ የሚራቡባት፣ የሚታመሙባት፣ በድህነት የሚማቅቁባትና ፍትሕ የሚያጡባት ስትሆን፣ ሥልጣንና ሀብት ያለው ደግሞ የሚፈነጥዝባት ናት፡፡ በሙስና መበልፀግ፣ በብሔር መቧደን፣ ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም፣ ፍትሕን መንፈግ፣ የታክስ ከፋዩን ገንዘብ ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ መዝረፍ ከሕግ አውጪው እስከ ታች ያሉ የአፍሪካ ባለሥልጣናት ተግባር ነው፡፡ ንፁኃን የሉም ማለት ባይቻልም ጎልቶ የሚታየው ከላይ እስከ ታች የሚገኙ ባለሥልጣናት በጥቅምና በብሔር መተሳሰር ነው፡፡
እያንዳንዳቸው የአፍሪካ አገሮች የተለያዩ ብሔሮች ባለቤቶች መሆናቸው፣ የአንድ ወይም የሁለት ብሔሮች የሥልጣን የበላይነት በየአገሮቹ መኖር፣ እንዲሁም ምርጫ በመጣና ችግር በተፈጠረ ቁጥር እንደ አንድ አገር ሳይሆን እንደ ብሔር ማሰባቸው አፍሪካውያን ካሉበት ድህነት እንዳይወጡ፣ የዲሞክራሲ ሥርዓታቸው ግንባታ በየምክንያቱ እንዲሽመደመድ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡
አዲሱ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ ግን ለዚህ የሚበገሩ አይመስሉም፡፡ ራሳቸውን ለሕዝባቸው አሳልፈው የሰጡ፣ ለአፍሪካ መሪዎችም ከሙስናና ከተንደላቀቀ ኑሮ ወጣ ብሎ ለሕዝብ ራስን አሳልፎ መስጠት እንደሚቻል ያሳዩ መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ አገሪቷ ከ120 በላይ ብሔሮች ያሏት ቢሆንም፣ በምርጫ ወቅት ብሔርተኝነት አልተንፀባረቀም፡፡ ይህም ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ሚና ተጫውቷል ተብሏል፡፡
ከጥቅምት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሥልጣን የያዙት ፕሬዚዳንቱ፣ በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ‹‹ድህነት ማለት ምን እንደሆነ አውቃለሁ፣ የእናንተ አገልጋይ እንድሆን ፍቀዱልኝ፤›› በሚለው የምርጫ ዘመቻቸው ይታወቃሉ፡፡ ከምርጫ በኋላም ጊዜ ሳያባክኑ የአገልጋይነት ተግባራቸውን አሳይተዋል፡፡ ሕዝቡን ለድህነት በዳረገው ሙስና ላይም መነሳታቸው ተሰምቷል፡፡
ሥልጣን ከያዙ ማግሥት ጀምሮ ታች ዝቅ ብሎ በመሥራት ጭምር ለሕዝባቸው ምን ያህል ቅርብና አርዓያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያሳዩ ሲሆን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትም የእሳቸውን አርዓያ እንዲከተሉ፣ ሕዝባቸውንም ዝቅ ብለው እንዲያገለግሉና ሙስናን እንዲፀየፉ እየቀየሱ ይገኛሉ፡፡
የዓለም አቀፍና የአፍሪካ ሚዲያዎች መነጋገሪያ የሆኑት ፕሬዚዳንቱ፣ በተለይም በአፍሪካ የሚዲያ ተቋማትና ተንታኞች ይሁንታን አግኝተዋል፡፡ አፍሪካውያን መሪዎች ከፕሬዚዳንቱ ሊማሩ ይገባል በማለትም በናይጄሪያ፣ በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካና በሌሎችም የአፍሪካ አገሮች የሚገኙ የሚዲያ ተንታኞች ከየአገሮቻቸው ባለሥልጣናት ጋር እያነፃፀሩ ዘገባዎች አስፍረዋል፡፡
ማጉፉሊ ሥልጣን በያዙ ማግሥት ማፅዳት የጀመሩት በቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኪኩዌቴ ዘመን ተንሰራፍቶ የነበረውን ሙስና ነው፡፡ ሙስና ከሚፈጸምባቸው መንገዶች አንዱ በአገሪቱ የሚከበሩ ብሔራዊ በዓላትን ተከትለው የሚዘጋጁ የተንዛዙ ዝግጅቶች በመሆናቸው፣ አገሪቷ የነፃነት በዓሏን የምታከብርበትን ኅዳር 29 በጭፈራና በድግስ ሳይሆን ከተሞችን በማፅዳት እንዲከበር አድርገዋል፡፡ ይህንን አስመልክቶም ‹‹ታንዛኒያውያን በኮሌራ እየሞቱ የነፃነት በዓልን ለማክበር ብዙ ገንዘብ ማውጣት ያሳፍራል፡፡ በበዓሉ ፋንታ አገሪቷን በማፅዳት እናሳልፋለን፤›› ነበር ያሉት፡፡
ዕለቱን ከዓለም በቆሻሻነቷ በዘጠነኛ ደረጃ የምትመደበውን አገራቸውን ለማፅዳት ጓንት አጥልቀውና መጥረጊያቸውን ይዘው ዳሬሰላም ጎዳና ላይ አሳልፈዋል፡፡ ከቤተ መንግሥቱ አቅራቢያ የሚገኘውንና በዓሳ ተረፈ ምርት ምክንያት የሚሸተውን የህንድ ውቅያኖስ የተወሰነ ዳርቻም ከግብረ ኃይላቸው ጋር አፅድተዋል፡፡ ሕዝቡም በየጎዳናው ወጥቶ ቱቦዎችንና መንገዶችን ሲያፀዳ ውሏል፡፡ ከተሞችን የማፅዳት ሥራው ከዚህ በኋላ የሚቀጥል ይሆናል ተብሏል፡፡ ፕሬዚዳንቱም ሁሉም ሕዝብ ወጥቶ አካባቢውን እንዲያፀዳ አዘዋል፡፡
በሙሂምቢሊ ሆስፒታል በቂ የሕሙማን አልጋ ባለመኖሩ ሕሙማን በየኮሪደሩ ወይም በአንድ አልጋ ለሁለት እንዲተኙ ይገደዳሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም የሆስፒታሉ የሕክምና ማሽኖች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፡፡ ሕሙማንም አገልግሎት በማጣት ይሰቃያሉ፡፡ ሆስፒታሉን የጎበኙት ፕሬዚዳንቱ ለአገሪቱ የፓርላማ አባላት ፓርቲ ለማዘጋጀት የተመደበን 200 ሚሊዮን የታንዛኒያ ሽልንግ በቀጥታ ለሆስፒታሉ ማደሻና ቁሳቁስ ማሟያ እንዲውል ወስነዋል፡፡ ይህን በወሰኑ በጥቂት ቀናት ውስጥም 300 የሕሙማን አልጋ ሆስፒታሉ ያገኘ ሲሆን፣ ተበላሽቶ የነበረው ኤምአርአይ ኤክስሬይ ማሽን ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ሆስፒታሉን ይመሩ የነበሩ የቦርድ አባላትም ከሥልጣናቸው ተነስተው በምትካቸው አዲስ ተሹመዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱን በዓለ ሲመት ለማክበር 100 ሺሕ ዶላር ተመድቦ የነበረ ቢሆንም፣ በሰባት ሺሕ ዶላር እንዲያልቅ በማድረግ 93 ሺሕ ዶላር ለሆስፒታሉ ማደሻና ቁሳቁስ ማሟያ እንዲሆን አድርገዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወደ ውጭ አገሮች የሚያደርጉትን ጉዞም አግደዋል፡፡ በዚህ ምትክ እያንዳንዱ የመንግሥት ባለሥልጣን በአገሪቱ ገጠራማ ሥፍራዎች ተከታታይና ቀጣይነት ያለው ጉብኝት በማድረግ ከሕዝቡ እንዲማር፣ ሕዝቡን እንዲረዳና ታንዛኒያውያን በየቀኑ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች እንዲፈታ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ ወደ ውጭ የሥራ ጉብኝትና ስብሰባ በሚኖርበት ጊዜም፣ ለዚህ ተብለው የተመደቡት ኮሚሽነሮችና አምባሳደሮች እንዲሳተፉና አገራቸውን እንዲያገለግሉም ወስነዋል፡፡
ወደ ውጭ በሚደረግ የአውሮፕላን ጉዞም ከፕሬዚዳንቱ፣ ከምክትል ፕሬዚዳንቱና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በስተቀር ማንኛውም የመንግሥት ባለሥልጣን የ‹‹ፈርስት›› ወይም የ‹‹ቢዝነስ ክላስ›› በረራ መጠቀም አይችልም፡፡ እንደ ማንኛውም ዜጋ ‹‹በኢኮኖሚ ክላስ›› ይጠቀማል፡፡ የታንዛኒያ ባለሥልጣናት በእሳቸው የሥልጣን ዘመን በዘመናዊ የሆቴል አዳራሾች ስብሰባ አያካሂዱም፡፡ ለስብሰባ አዳራሽ ተብሎ የሚወጣ ወጪም አይኖርም፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ባለሥልጣናት ስብሰባ የሚያካሂዱት በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ በሚገኙ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለተሰብሳቢዎች የውሎ አበል አይኖርም፡፡
ዳሬሰላም የሚገኘውን ወደብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካሲም ማጃሊዋ እንዲጎበኙና ማጣራት እንዲያደርጉ ካዘዙ በኋላ፣ በቀረበላቸው ሪፖርት በወደቡ ከተመዘገቡ ኮንቴይነሮች 350 ያህሉ ባለመኖራቸው፣ የታንዛኒያ የገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅና ተጨማሪ አምስት ኃላፊዎች ከሥልጣናቸው ተነስተዋል፡፡ ‹‹ለሙስናና ለታክስ ድበቃ ቦታ የለንም፤›› ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ሳምንት ከአገሪቷ ዋና ከተማ ዳሬሰላም 600 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ዶዶማ የሰሚገኘው ፓርላማ የመክፈቻ ንግግር ለማድረግ ያቀኑትም በአውሮፕላን አይደለም፡፡ በመኪና በመጓዝ ፓርላማውን ሥራ አስጀምረዋል፡፡ በተያዘው ሳምንት መጀመሪያ ደግሞ በመንግሥት በጀት የገና ካርዶች የማይታተሙ መሆኑን፣ ካርድ መለዋወጥ የሚፈልግ ባለሥልጣን በራሱ ወጪ እንዲጠቀምም አሳስበዋል፡፡
የማጉፉሊ ድርጊት ለአፍሪካውያን ባለሥልጣናት የሚዋጥ ባይሆንም፣ ሕዝቡ ግን የሚፈልገው ነው፡፡ አፍሪካውያን ከማንም በበለጠ በባለሥልጣናት፣ በወዳጆቻቸውና በዘመዶቻቸው እየተበዘበዙ ይገኛሉ፡፡ የቱንም ያህል በጀት ቢመደብም ሕዝቡን ከድህነት ለማውጣት ያልተቻለውም በባለሥልጣናትና በሰንሰለቶቻቸው ሙሰኝነት ነው፡፡ በአፍሪካ ሕዝቡ በሚከፍለው የታክስ መጠን ተጠቃሚ መሆን ያልቻለውም፣ ለሕዝቡ ይመለከተኛል የሚል መሪ በመታጣቱ ነው፡፡ የማጉፉሊ አንድ ዕርምጃ ግን ለአፍሪካ መሪዎች ትምህርት ነው፡፡ በኬሚስትሪ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ማጉፉሊ፣ አገሪቷን ለረጅም ጊዜ ይመራ የነበረው ቻማ ቻ ማፒንዱዚ (ሲሲኤም) ፓርቲ አባል ናቸው፡፡
‹‹በምርጫ ዘመቻ ወቅት ፓርቲያችን የገባውን ቃል ለመፈጸም ባለኝ አቅም ሁሉ እሠራለሁ፡፡ ሕዝባችን አምኖን ኃላፊነት ሰጥቶናል፡፡ በእግዚአብሔር መሪነት፣ በሕዝባችን ትብብርና መልካም ፈቃድ ታንዛኒያ ሀብታም ትሆናለች፤›› የሚለው ፕሬዚዳንቱ በበዓለ ሲመታቸው የተናገሩት ነው፡፡