Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ስንቱ ተነግሮ ይዘለቃል?

እነሆ መንገድ። ከፒያሳ ወደ አዲሱ ገበያ ልንጓዝ ነው። መንገድ ማጣሪያ እንጂ መቋጫ የለውም ይላሉ ጎዳናውያን ተራማጆች። የአረማመድ ቄንጥ ከነጫማ ቁጥራችን ተብጠርጥሮ በሚበረበሩት በዚህ ጎዳና፣ ተጓዥና አጓጓዥ ብዙ ይባባላሉ። “ታያታለህ እንዴት እንደለበሰች? አሁን ቢጫ ኮት በጥቁር ሱሪ ይደረጋል?” ይላል ከተሠለፍነው መሀል አንዱ። በሩቅ አውቶሞቢሏን በንቃት እየዘወረች መዓት የወረደባት የምትመስል ቀዘባን እየጠቆመ። “ኮቱንስ ይሁን፣ ሱሪዋን እንዴት ከዚህ ሆነህ ልታየው ቻልክ?” ይላል ወዳጁ። “ቀላል ነው። እንደኔ ተደራጅተህ ቡቲክ ስትከፍት ይገልጥለሃል፤” ይላል ያኛው። “እ? ደግሞ ቡቲክ ለመገለጥ ዕውቀትም ተደራጁ አሉ እንዴ?” ሳምሶናይት ያንጠለጠለ ጎልማሳ ጠየቀ። “አቤት? ማናቸው እነሱ?” ዓይኑ ከዚያች ባለቢጫ ኮት ወጣት አልነቀል ያለው ጠየቀ። ጎልማሳው በኮባ እንደተጠቀለለ ያልበሰለ ሊጥ መልሱ በጥያቄ ተሸፍኖ ተመለሰለት መሰል ዝም አለ። “ሰው በቃ በተውላጠ ስም እነሱ እኛ እያለ ማነካካቱን ‘ሙድ’ አረገው አይደል?” ይለኛል ከኋላዬ የተሠለፈ ቀጭን ጎልተው የሚንከባለሉ ዓይኖች ያሉት ወጣት።

 ትከሻዬን ሰብቄ የመሀል ሰፋሪ መልስ ስመልስለት ደግሞ፣ “ቆይ ለምን አንደኛውን መሀል ገብቶ አስቁሟት ‘ሊፍት’ አይጠይቃትም?” ይለኛል። ያ የቅርብ ሩቅ አዳሪው ሰምቶት ኖሮ፣ “ማን በሠራው መንገድ ነው ማን መሀል ገብቶ የሚገጨው?” ብሎ ዞረበት። ከጀርባዬ የቆመው ደፋር “አየህ? ወይ ማጥመድ አይችሉ ወይ መጥለፍ አይሳካላቸው ዝም ብለው ዳር ቆመው ቄንጥ ሲያወጡ ሰው ይመስላሉ፤” ብሎ ጎሸመኝ። “እኮ እነማ?” ብሎ ያኛው ሲያፈጥ፣ “ስለማን ነው የምናወራው? ስለኛና ስለነሱ ነዋ፤” ብሎት ደረቱን ነፋ። ባለሳምሶናይቱ ጎልማሳ ዘወር ብሎ “አቤት! አቤት! ተናግሮ ሞቷል እባክህ። እዚህ ቆሎ የማይደፋ ቅኔ ዘረፍን እያሉ ሰላማችንን የሚያደፈረሱብንን ምናለበት ቢያጣሩልን፤” አለ።  ሁላችንም እንዳሻን የገጠመ ያልገጠመውን ሁሉ ገጣጥማችሁ ትርጉም ካልሰጣችሁ በምንልበት ጊዜ አጣሪ ‘ኮሚሽን’ ቢቋቋም ማን ሊተርፍ ነው? እንዲያው እኮ!

ተሳፍረናል። ያ ከጀርባዬ ተሠልፎ ጆሮዬ ሥር ሲተነፍስብኝ የነበረው ደፋር መሀል መቀመጫ ላይ ከአንዲት ወይዘሮ ጋር ተሰይሟል። ወይዘሮዋ ደርባባነታቸው ልዩ፣ አለባበሳቸው ደግሞ ማራኪ ጥንቅቅ ያሉ ሴት ናቸው። “እማማ እባክዎ ይኼን ግርማ እንዲያየው ይዘውት እንዳይወርዱ አደራ፤” ይላል ወጣቱ። “ምን ላድርገው ታዲያ? ልስቀልልህ?” ይሉታል እያሾፉ። ተጫዋች ናቸው። “የለም ይፍቀዱልኝና ፎቶ ላንሳው፤” ዓይን አውጣው ፊት ሲሰጠው ያቀረበው ጥያቄ ነው። “እንዴ? እናንተ ልጆች የፎቶ አብዮት ነው የያዛችሁት የልማት? መንግሥት ልሙ አልሙ እያለ ይደርቃል። እናንተ ቴክኖሎጂ አገዘን ብላችሁ ቀጭ ቋ ያለችውን ሁሉ እንደ ፓፓራዚ በፎቶ ምች ስታሳድዱ መዋል ሆኗል ሥራችሁ።

ምን ይሻላችኋል?” ከናፍራቸውን አጣመው ጥርሳቸውን ብልጭ እያደረጉ ያዩታል። “ምን ይሻለናል እማማ። ይኼም እኮ ሥራ ፈጠራ ነው። ሥራ እስክናገኝ ሥራ መፈለግ ነው ሥራችን፤” ወጣቱ ሲናገር ይፈጥናል። “በል ሁለተኛ . . . ሁለተኛ ጊዜ እንኳን ብለኸኛል ይሁን፣ ሦስተኛ እማማ ብትለኝ እኔ ነኝ በጥፊ ጥሩ ፎቶ የማነሳህ፤” አሉት ኮስተር ብለው። “እሺ እማማ…” አለና አረፈው። “ድገማትና ታያለህ። የዘመኑ ወጣቶች የተፈቀደላችሁን ቃል በኃላፊነት ከመጠቀም ይልቅ፣ ያልተፈቀደላችሁን መደጋገም ትወዳላችሁ። የፈጃችሁን እሳት እንደመራቅ መልሳችሁ ትጠጉታላችሁ። ይብላኝላችሁ…፤” ብለው ትከሻቸው ላይ ጣል ያደረጉትን ባለፈርጥ ሻርፕ ማስተካከል ያዙ። “እኔ ምለው ግን …” አለ። “አንተ ምትለው?” ቀና ብለው አያዩትም። “እርስዎ በዚህ ዕድሜዎ እንዲህ ጥንቅቅ ብለው ሲለብሱ፣ የእኔ ትውልድ መላ ቅጡ የጠፋው አለባብስ ፋሽን ብሎ የተያያዘው ምን ነክቶት ነው?” ከማለቱ፣ “ነገረኛ! ‘የፖለቲካ ተፅዕኖ ነው’ እንድልህ ነው? አንዲያው መልሱ ጠፍቶህ ነዋ የጠየቅከኝ። በል ቶሎ አንሳኝ አሁን፤” ብለው ለፎቶ ተዘጋጁ። ቀጭ አደረጋቸው። እኒህ ‘ዋዘኛ’ ስልኮች እኮ ሰውን ሁሉ በሄደበት ዋዛ አስመሰሉት እናንተ!

ያንቀጫቀጫቸውን ፎቶዎች ሲያሳያቸው ወይዘሮዋ፣ ‘ይኼን ደልተው ይኼን በብሉቱዝ ላክልኝ’ እያሉ ሳሉ ወያላው “ሒሳብ” ብሎ ከፊታቸው ቆመ። “እስኪ መጀመርያ ከፊት የተቀመጡትን ተቀበል። ጉልበታችሁ መሀልና ዳር የተቀመጥነው ላይ ብቻ ነው?” አሉት ሽቅብ እያዩት። “የለም እርስዎ ተጨማሪ ክፍያ ስለሚከፍሉ ቅድሚያ ከዚህ ነው የምጀምረው፤” አለ ወያላው የምሩን። “እኮ ለምን? ማን ሾሞህ ነው ደግሞ አንተን ተጨማሪ እሴት ታክስ ከሌላው ነጥለህ እኔን ብቻ የምታስከፍለኝ? እናንተ ዘንድሮ እኮ ሿሚና ሻሪውን ማወቅ አቃተን፤” ወይዘሮዋ ተነሳባቸው። “የለም ይኼ ሹመት ምናምን አይደለም። ደግሞ ተጨማሪ እሴት ታክስ ክፈሉ አልወጣኝም። ያለፈቃድ ታክሲያችን ውስጥ ፎቶ ስለተነሱ ከታሪፉ ጋር አሥር ብር ይከፍላሉ…፤” ከማለቱ ተሳፋሪዎች በሳቅ አውካኩ።

ሁላችንም ቀልድ መስሎን ነበር። ወያላው ግን አምሯል። “እንዴ! ምን ለማለት ነው አንተ?” ሦስተኛው ረድፍ ላይ አጠገቤ የተሰየመው ባለሳምሶናይቱ ጎልማሳ ለወይዘሮዋ ተደረበ። “ምናልባት ፎቶው ለሽብር ተግባር እንዳይውል ሠግቶ ይሆናል፤” አለ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠው ያ . . . አለባበስ ሲተች የነበረው ወጣት። “ሥራው ገንዘብ መቀበል እንጂ መርማሪነት ነው ታዲያ?” ብሎ ጎልማሳው ወደ ወጣቱ ሲዞር፣ “እንዲያ ካልክ ‘ሳታማሃኝ ብላ’ን ጋብዘው፤” አለው። ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ወያላው ድርቅ ብሎ የጠየቀው አሥር ብር ባይከፈለውም ታሪፉን ግን ወሰደ። ወይዘሮዋ፣ “ዋ ጊዜ ብለን ብለን በገዛ ካሜራችን ትዝታን በዋጋ የምንሸምትበት ጊዜ ላይ ደረስን?” ሲሉ ጎልማሳው፣ “ይተውት በቃ በዚሁ ይለፍ። በዚህ ዓይነት እኮ የዜግነትም ክፈሉ ይመጣ ይሆናል፤” ቢል ሁሉም በጩኸት አፍጦ አየው። ይሆናል ብሎ ገመተ እንጂ መቼ ሆነ ወጣው? ለወሬና ለነገር ያለን ችኮላ እኮ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ ሁለት ሴቶች ሲያወሩ ቀሪዎቻችን አዳማጮች ነን። “ገና ለገና አሜሪካ ቪዛ ተመታልኝ ብላ እንዲህ ፀባዩዋ ይቀየር?” ትላልች ወደ መስኮቱ ጥግ የተቀመጠችው። “አትገርምሽም? ብርቅ ነው እንዴ አሜሪካ መሄድ? ባንሄድም ዕድሜ ለሆሊውድና ለሲኤንኤን የማናውቀው ነገር የለም፤” ትላለች ጫፍ ላይ የተቀመጠችው። “ውይ ሰው! ሰው ግን . . .”  ስታማትብ ቆየችና “ሳገኝ ከምከዳ አምላኬ ሆይ መጀመርያውኑም አትስጠኝ፤” ብላ አጉል ቃል ገባች። ይኼን ጊዜ ጎልማሳው ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ፣ “ምንድነው የምትለው ልጅቷ? ቪዛ አግኝቶ ይቅርና በባዶ መስሎኝ ሰው የይሁዳን መንገድ የተናነቀው። አይደለም እንዴ?” ይለኛል።

“አንቺ ግን . . . ” ሴቶቹ ጨዋታቸው ቀጥሏል። “እ?” ትላለች ሰሚዋ። “እንዲች ብለሽ ቅሬታችሽን ማሳየት የለብሽም። እንዲያውም እያደር እንዲነዳት ሽሮና በርበሬ. . . እ . . .  አንድ ኪሎ ቅቤ ምናምን ቋጥረሽ መስጠት አለብሽ፤” ስትባል፣ ተመካሪዋ እሳት ለብሳ እሳት ጎርሳ፣ “ማ እኔ ለእሷ! ከ15 ሚሊየን በላይ የሚሆን ወገኔ መራቡን እያወቅኩ ነው ገና ለገና አሜሪካ ልሄድ ነው ብላ ቀባሪ አልፈልግም ላለች ጉረኛ ሽሮና በርበሬ የምቋጥረው? ወየው የኑሮ ውድነቱን ተቋቁሜ ለራሴ መቋጠር በቻልኩ፤” ብላ ሐሳብ ገባት። “ምን ቸገረሽ? አንቺም እኮ ያ አሜሪካዊ ነው ያልሽው ልጅ ላግባሽ ብሎ ቢፈርምልሽና ብትሄጂ፣ አገሩን እስክተለምጂ ከእሷ ውጪ ምንም ሰው የለሽም፤” ስትላት ወዳጁዋ ቦግ ቦግ ስትል የነበረቸው ባለማህተብ “እሱስ ልክ ነሽ …” ማለት ጀመረች። ትርፍና ኪሳራን እያሰሉ በሚኖርበት በዚህ የራስ ወዳድነት ዘመን እንኳን እሷ ስንቱ የተጨበጨበለት ሲሸነፍ አላየንም? አዬ ሰው መሆን!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወይዘሮዋ በነገር እየተብሰለሰሉ፣ ቆስቁሶ ባለዕዳ አድርጓአቸው የነበረው ወጣት ድምፁን አጥፍቶ፣ ጎልማሳው ከቀበሌ እስከ ፓርላማ የሚታዘበውን እያወራ፣ እነዚያ ወጣት ጓደኛማቾች ማስጫን ስለሚፈልጉት የመኪና ሞዴል እየተወያዩ፣ ካጠገባቸው ደግሞ በዝምታ የተዋጡት ባልና ሚስት እንዳቀረቀሩ መጨረሻችን ቀረበ። ጋቢና ከተቀመጡት አንዱ የአርሴናል ደጋፊ ነኝ እያለ አጠገቡ ከተቀመጠው የቼልሲ ደጋፊ ጋር ደርቢ ገጥሟል። “እናንተ ምን አለባችሁ? እኛ እዚህ በጠራራ ፀሐይ በረባ ባረባው እንጋጣለን፣ እናንተ ህልውናችሁን እንኳ ዕውቅና ለማይቸሩ ተራጋጮች ታሸበሽባላችሁ፤” አሉ ወይዘሮዋ። “ምን እናድርግ? ‘ለራሳችሁ አልቅሱ’ ተብሎ ተጽፏል፤” ይላቸዋል ከጎናቸው የተቀመጠው። “ታዲያ ማርገጃ መሬት ጠፋ? ምን ሩቅ ያስኬዳችኋል?” ወይዘሮዋ ከፍቷቸዋል። “ስለመሬት ነክ ጉዳይ ባይወራ ደስ ይለኛል፤” ይለኛል ጎልማሳው። “ዳይፐር’ አልቆበታል እኮ ማሙሽ?” ትላለች ደግሞ ከኋላ ሚስት ለባሏ። ባል “ምናለበት ብትገዥለት? ከትናንት ወዲያ የሰጠሁሽን ገንዘብ ምን አደረግሽው?” ብሎ ያፈጣል።

 “አይደብረውም እንዴ ሰውዬው? በሰው መሃል ‘ሼም’ ያስይዛታል እንዴ?” ይባባላሉ ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙት ሴቶችት። የባልና ሚስቱን ንትርክ ከወይዘሮዋ ጎን የተቀመጠው ሲያዳምቅ፣ “ኳስ እኮ ነጋ ጠባ የሚደጋገም ፕሮፓጋንዳ የለው፣ ፖለቲካ ተኮር ዘገባ አያውቅ፣ የራሱን ድምፅ ለማሰማት ሲል የሰው ድምፅ አያፍን፡፡ በቃ ምን ልበልዎ ኳስ ኳስ ነው። ደግሞ የአውሮፓ ኳስ? ልዩ . . .”  ሳይጨርስ ወይዘሮዋ፣ “የአገርህስ?” ብለው ዞሩበት። ይኼኔ ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ከፈተ። “የአገርህስ ነው እኮ የምልህ?” ወይዘሮዋ አጥብቀው ይጠይቃሉ። “ነገርኩዎ እኮ!” ወጣቱ ተወዛገበ። ተሳፋሪዎች አንድ በአንድ መውረድ ጀመሩ። ኑሮ ፖለቲካ፣ መዝናኛው ፖለቲካ፣ ማዘኛው ፖለቲካ፣ ኳሱ ፖለቲካ በሆነባት ምድር እግር እርሙን በልቶ መርገጡን ቀጠለ። ችግሩን መዘርዘር ቢቀጥል ማቆሚያ ያለው አይመስልም ነበር፡፡ ስንቱ ተነግሮ ይዘለቃል? መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት