የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ወርኃ ጥቅምትን የሚገልጹበት ጠባይ ከቅዝቃዜው ጋር አቻ ይገጥማል፡፡ በጥቅምት ወር አየሩ ብቻም ሳይሆን ንግድም ይቀዘቅዛል ይላሉ፡፡ አንድም ለአዲሱ ዓመት ሲባል ሸማቹ በልዩ ልዩ ፍጆታዎች ገንዘቡን ጥቅም ላይ በመዋሉ ምክንያት የጥቅምት ወር ገበያ ይቀዘቅዛል፡፡
አንድም ነጋዴው በአብዛኛው ግብር የሚከፍለው በጥቅምት ወር በመሆኑ ገንዘብ የሚባል ነገር ከነጋዴ ተጠራርጎ ወደ መንግሥት ካዝና የሚገባበት ወቅት ስለሆነ አሁንም ለገበያ መቀዛቀዝ ጥቅምት ወር ከዓመቱ ወራቶች ሁሉ ይጠቀሳል፡፡ ነገሩ ከዚህም ይግፋ ከተባለ ለገበያው መፍዘዝ ሌላም ምክንያት ይቀርባል፡፡ የገበሬው ምርት በጥቅምት ወር ስለማይደርስ ገበያ ላይ የሚገላበጥ ገንዘብም እህልም እንደልብ አይገኝም ይባላል፡፡
ይሁንና የጥቅምት ወር አልፎ ህዳር ሲጋመስ፣ አሻግሮ ታኅሳስን በተስፋ የሚጠብቀው ነጋዴ እንደምንም መደብሩን ሞልቶ፣ ያለውን አብቃቅቶ ለበዓል ገበያ ዝግጅት ይጀምራል፡፡ እርግጥ በኢትዮጵያ የትኛውም በዓል ለሸመታ የተመቸ፣ የደራና የሞቀ ገበያ እንዳለው ይታመናል፡፡ መጪው ገናም ለዚህ አይታማም፡፡ ገናውም ሲያልፍ ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› የተባለለት በዓለ ጥምቀት ከበራፍ ደርሷል፡፡
በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች እየተስፋፋ የመጣው የገበያና የግብይት ሥርዓት ለአገሬውም ለውጭውም ሰው ተስማሚ የገበያ ማዕከላት ሲከፈቱለት ማየት እየተመለደ መጥቷል፡፡ ደንበል ሲቲ ሴንተር፣ ኤድና ሞል፣ ጌቱ ኮሜርሺያል እያለ የቀጠለው የዘመናዊ ሕንፃዎች የግብይት ማዕከልነት አሁን አሁን እነ ዘፍመሽን አምጥቷል፡፡ ካለፈው ዓመት ኅዳር ወር ጀምሮ ደግሞ ሞርኒንግ ሰን ሞል የተባለውንና በቦሌ፣ ከኤድና ሞል ጀርባ የተንሰራፋውን አዲስ ሕንፃ ለዚሁ አስተዋውቋል፡፡
ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ግብይትን ለማቀላጠፍ የሚያስችሉ፣ ለመዝናኛነት የሚመቹ ሕንፃዎች እየተለመዱ የመጡት ከአሥር ዓመት ወዲህ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በአንፃሩ ከጎረቤት ኬንያ እስከ ደቡብ አፍሪካ በትልልቅና ሰፋፊ ሕንጻዎች ውስጥ በርካታ ግብይት የሚካሄድባቸው ማዕከላት እንደልብ ይገኛሉ፡፡ ሕንፃው 140 መኪኖችን ለማቆም የሚያስችል ከምድር ቤት በታች ሁለት ፎቅ ያለው ሲሆን፣ በ2400 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈና ለተለያዩ የንግድ አገልግሎቶች የንግድ ማዕከል ይሁነኝ ተብሎ የተሠራ መሆኑን የገበያው ማዕከል ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡
አዲስ አበባ በውጭ የበዓል ድባብ ከምትደምቅባቸው ወቅቶች አንዱ የሆነው የገና በዓል ነው፡፡ ገና በኢትዮጵያ በዓመት ሁለት ጊዜ መከበር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በሚከበረው፣ በአገርኛ የሚዘወተረው የገና በዓል ወቅት የቤት ውስጥ ማስዋቢያዎች፣ የገና ዛፎች፣ ብልጭልጭ መብራቶችና ሌሎችም ጌጣጌጦች ሕንፃዎችን የሚያደምቁበት ይህ በዓል በሞርኒንግ ስታርም ለየት ያለ ዝግጅት ተደርጎለታል፡፡ ሰሎሜ አሰፋ የሞርኒንግ ስታር ሞል የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ ናቸው፡፡ በገበያ ማዕከሉ ዝግጅት ከተደረገባቸው መካከል ሁለቱን ይናገራሉ፡፡
ወደ ሕንፃው ሲገባ ከምድር እስከ ሁለተኛ ፎቅ ድረስ የሚረዝም 12 ሜትር ቁመት ያለው ትልቅ የገና ዛፍ አሸብርቆ ቆሟል፡፡ አናቱ ላይ እየሱስ የተወለደበትን ቦታ ለሰብዓ ሰገል እያመላካተ የመራቸውን ኮከብ የሚያመስል ኮከብ የተሰካበት የገናው ዛፍ ሁለት መልክ ይዟል፡፡ የውጮቹን ገና ከኢትዮጵያዊ የገና በዓል አከባበር ይዘት ጋር አዳምሮ የቆመው ዛፍ፣ ከበታቹ ጎጆ ቤትና የጌታን ግርግም የሚያሳዩ ምስሎች የተካተቱበት ነው፡፡ በስፋቱም ስድስት ሜትር ወገቡ ይዞራል፡፡
እንደ ሰሎሜ ማብራሪያ የገበያ ማዕከሉ ለጎበኝዎች አዲስ ነገር ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ በቀን እስከ 200 ለሚደርሱ የገበያው ማዕል ጎብኝዎች የቤተሰብ ፎቶ በነፃ አንስቶና አጥቦ የመስጠት ሥነ ሥርዓት ከመጪው ቅዳሜ፣ ታኅሳስ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. እስከ በዓሉ መቋጫ ድረስ እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡
እንደ ሰሎሜ ማብራሪያ የገበያ ማዕከሉ ሌላም ሥነ ሥርዓት ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ለግብይትም ሆነ ለመዝናናትም ወደ ሕንፃው የሚመጡ ሰዎች፣ ፈቃዳቸው ቢሆን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚሰጥ ማንኛውንም ስጦታ የሚሰጡበት ሥነ ሥርዓት ተሰናድቷል፡፡
ሕንፃው አምስት ፎቅና ሁለት ከምድር በታች ያሉ የመኪና ማቆሚያዎችን ጨምሮ ቢገነባም፣ ወደፊት ወደላይ የመቀጠል ፍላጎት እንዳለ የሕንፃው ባለንብረቶች ይገልጻሉ፡፡ ከምድር ቤት እስከ ሦስተኛ ፎቅ ያሉት ቤቶች ለቢሮ አገልግሎት ውለዋል፡፡የገበያ ማዕከል ለቢሮ ግልጋሎት የሚውል ከሆነ ምኑን የገበያ ቦታ ሆነ ብለው የሚከራከሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡
የሞርኒግ ስታር አስተዳደር ግን ሕንፃዎች የገበያ ማዕከልነታቸው አሁን ካለው በላይም እየተለመደ ሲመጣና ከዚህም በላይ ሲለመድ፣ ጥያቄው ቢነሳ ተቀባይነት እንደሚኖረው ይገልጻሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ለገበያ ማዕከልነት ሳይታሰቡ የሚሠሩ ሕንፃዎች ድንገት ሲያመቻቸው ከተሠሩበት ዓላማ ውጭ የገበያ ማዕከልና ሆቴል ወዘተ. በሚደረጉበት አገር፣ ከመነሻው ጀምሮ ለሆቴልና ለገበያ ማዕከልነት አስቦ መሥራትም እየተለመደ መጥቷል፡፡ ሞርኒንግ ስታር ለመጪዎቹ ሃያና ሰላሳ ዓመታት በዚህ ዘርፍ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ መገንባቱም ተነግሯል፡፡