Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለስድስት ወራት ታሽገው የከረሙት የቢሾፍቱ ልኳንዳ ቤቶች ሥራ ጀመሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የቢሾፍቱ ልኳንዳ ነጋዴዎች በታክስ ዕዳ ለስድስት ወራት ታሽገው ከቆዩ በኋላ በቅርቡ መከፈታቸውንና ሥራ መጀመራቸውን ገለጹ፡፡ መንግሥት ወደ ኋላ ውዝፍና ያልተከፈለ የታክስ ዕዳ ያላግባብ ተጠይቀናል የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበርና መንግሥትም ዕዳው ሊከፈለኝ ይገባል በሚል ተፋጠው እንደነበር ይታወሳል፡፡ 

ኮሎኔል ነጋ ቢራቱ የቢሾፍቱ ከተማ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ፣ ‹‹በከተማው ከ2002 ዓ.ም. በፊት የተቋቋሙ ወደ 36 የሚጠጉ ልኳንዳ ቤቶች ወደኋላ ተመልሶ በተጠየቀ የግብር ዕዳ ሳቢያ ለስድስት ወራት ያህል ታሽገው ቆይተው ነበር፡፡ ነገር ግን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኅዳር 17 ቀን 2008 ዓ.ም. የግብር ዕዳ እንዲነሳ በማድረግ የታሸጉ ልኳንዳ ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ወስኗል፤›› ብለዋል፡፡

ልኳንዳ ቤቶች ለስድስት ወራት ያህል ተዘግተው በመቆየታቸው እስከ አንድ ሺሕ የሚሆኑ ሠራተኞች የተበተኑ ሲሆን፣ መንግሥትም በዚሁ ሳቢያ እስከ 60 ሚሊዮን ብር አካባቢ አጥቷል፡፡ የክልሉ መንግሥት ልኳንዳ ቤቶቹ እንዲከፈቱ ያደረገው ማኅበሩ ለረዥም ጊዜ ያቀረበውን አቤቱታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ችግሩን በጥልቀትና በጥናት ከገመገመና ከተመለከተ በኋላ ነው፡፡

አሁን ያለውን የገቢ ሥርዓት መልክ በማስያዝ ሁሉም አባላት ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታና ክብር መሆኑን ማወቅ እንደሚኖርባቸው፤ በሕገወጥ መንገድ ለመበልፀግ ከሚሯሯጡ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ደላላዎች ጋርም መተባበር እንደሌለባቸው በገቢዎች ባለሥልጣን የአዳማ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲበራ ፋፉ አሳስበዋል፡፡ ነፃ የንግድ መርህ በመከተል ገበያን ማረጋጋት፣ የሸማቾችን መብት የጥበቃ ሕግን ማክበር፣ የገበያ ንረትን በመግታት በተመጣጠነ የዋጋ አቅርቦት ዜጎች የሚጠቀሙበትን መንገድ ማመቻቸት የነጋዴው ትልቁ ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

አቶ ዲበራ ‹‹የልኳንዳ ነጋዴዎች የ2005 እና የ2006 በጀት ዓመት ግብር በአዲሱ መመርያ መሠረት እንዲከፍሉ ተደርጎ ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ አከፋፈል ከነጋዴዎቹ አቅም በላይ ሆኖ በመገኘቱ አዲሱን በመተው በ1996 ዓ.ም. በወጣውና በነባሩ ወይም በቀድሞው መመርያ መሠረት እንዲከፍሉ፣ አዲስ መመርያ ግን ከ2008 በጀት ዓመት ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውል የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና የክልሉ ገቢዎች ባለሥልጣን ወስኗል፤›› ብለዋል፡፡

ከእንግዲህ ወዲህ ግን ነጋዴዎቹ በሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ብቻ ሽያጭ ማከናወን እንደሚገባና፣ ይህንንም በየወሩ ለግብር አስገቢው መሥሪያ ቤት ማሳወቅና መካፈል እንደሚጠበቅባቸው ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ የመንግሥትና የግል ገቢያቸውም ሳይቀላቀል ለየብቻ እንዲይዙ፣ ዓመታዊውንም ግብር ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ጥቅምት 30 ቀን ድረስ በማሳወቅ እንዲከፍሉ አመልክተዋል፡፡ በዓመቱ መጨረሻ ተጠራቅሞ ግብር ሲከፈል ጫና የሚፈጥር ከሆነ፣ በየወሩ ወይም በየሦስት ወሩ በታሳቢ የዓመቱን ግብር እንዲከፍሉ ብለዋል፡፡

ቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው ቶሚ እንተርናሽናል ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሴክተር መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በሌላ በኩል የጥሬ ቆዳ ሳይበሰብስ ወይም ሳይበላሽ እስከ 20 ቀናት ማቆየት የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ጣሊያን አገር ከሚገኘው አንድ ኩባንያ ጋር የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በመነጋገር ላይ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የሚያካሂደው ንግግር እንዳበቃ በቅርቡ ውል እንደሚፈርም የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አቶ ገብረሕይወት ገብረእግዚአብሔር ይህንን ያስታወቁት፣ በቢሾፍቱ ከተማ በግብር ምክንያት ተዘግተው የነበሩት ልኳንዳ ቤቶች መከፈታቸውንና ነጋዴውም የግብር ምህረት የተደረገለት መሆኑን ምክንያት በማድረግ የቢሾፍቱ ከተማ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ታኅሳስ 3 ቀን 2005 ዓ.ም. ባካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ በተለይ ከሪፖርተር ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ነው፡፡

እንደ አቶ ገብረሕይወት ማብራሪያ፣ በዓለም ላይ አዲስ የሆነው የዚህ ዓይነቱ ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ መግባት ሁለት ዓብይ ጥቅሞች አሉት፡፡ አንደኛው ነጋዴዎቹ ጥራቱን የጠበቀ ቆዳ ወደ ውጭ በመላክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አገሪቱ ከዘርፉ ጠቀም ያለ የውጭ ምንዛሪ የማግኘት አጋጣሚው የተመቻቸ እንዲሆን ማድረጉ ነው፡፡

ጥሬ ቆዳ ወደ ፕሮሰስ እስከሚገባ ድረስ ከላይ ከፍ ብሎ ለተጠቀሰው ቀናት ያህል ሳይበላሽ ማቆየት የሚያስችለው ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ፣ በኬሚካል ደረጃ የተደረሰበት ግኝት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዚህም ቴክኖሎጂ ፈጣሪ የሆነው ኩባንያ ኃላፊ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከሥጋ ነጋዴዎች ማኅበራት ጋር እንደተገናኙና ሐሳብ ለሐሳብ እንደተለዋወጡም አስረድተዋል፡፡

ስለኩባንያው ማንነት እንዲገልጹ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ገብረሕይወት፣ ‹‹በውል ከመፈራረማችን በፊት የቴክኖሎጂው ባለቤት የሆነውን ኩባንያ ስም ከወዲሁ መግለጽ ትክክል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አመሃ በርሄ አገር አቀፍ የሥጋ አምራቾችና አቀናባሪዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አገር አቀፍ ማኅበሩ ዘመናዊና ኤክስፖርት ቄራ የማቋቋም፣ የቆዳ፣ የሌጦና ሌሎች የሥጋ ተረፈ ምርቶችን አዘገጃጀትና አያያዝ የማዘመን ዕቅድ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች