Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የእናት ባንክ ካፒታል እንዲያድግ ተወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ከዓመታዊ ትርፍ አምስት በመቶውን ለሴቶች የብድር ማስያዣ ለማዋል ስምምነት ተደረሰ

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሌሎች ባንኮች በተለየ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት የተመሠረተው እናት ባንክ፣ ባለአክሲዮኖች የባንካቸውን ካፒታል ለማሳደግና ከዓመታዊ ትርፋቸው አምስት በመቶ የሚሆነውን ሴት ተበዳሪዎች ለሚያስፈልጋቸው ብድር ማስያዥያ እንዲውል ወሰኑ፡፡ ባንኩ ባለፈው ቅዳሜ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ የወሰነው በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንኮች ካፒታል ሁለት ቢሊዮን ብር መድረስ ይኖርበታል የሚለውን መመርያ ተግባራዊ ለማድረግ ነው፡፡

እናት ባንክ እስካሁን የተመዘገበ ካፒታሉ 500 ማሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህንን ካፒታል ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ደግሞ ተጨማሪ አክሲዮኖች እንዲሸጡ ተወስኗል፡፡

ካፒታሉን ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ለማድረስ የተደረሰውን ስምምነት ወደ ተግባር ለመለወጥና ምን ያህል አክሲዮኖች ለገበያ ይቅረቡ የሚለውን ሥራ፣ ቦርዱ እንዲያስፈጽም ጠቅላላ ጉባዔው ውክልና ሰጥቷል፡፡

የባንኩን ካፒታል ማሳደግ ላይ ከተላለፈው ውሳኔ ቀደም ብሎ የባንኩ 2007 በጀት ዓመት አፈጻጸም ይፋ ተደርጓል፡፡ የ2007 በጀት ዓመቱ የሥራ ክንውን ውጤትን የሚያሳዩት አኃዛዊ መረጃዎችም ባንኩ ከቀደመው በጀት ዓመት በተለያዩ አገልግሎት ዘርፎቹ ዕድገት ማሳየቱን ነው፡፡

ባንኩ ከፍተኛ እመርታ አስመዝግቦባቸዋል ከተባሉት ክንውኖቹ መካከል አንዱ ዓመታዊ የትርፍ መጠኑ ከቀደመው በጀት ዓመት ከ80 በመቶ በላይ ማደጉ ነው፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ተሾመ እንደገለጹት፣ በ2006 በጀት ዓመት ከታክስና ከመጠባበቂያ በፊት አግኝቶ የነበረው ትርፍ 38.5 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2007 በጀት ዓመት ግን ይህ የትርፍ መጠን ወደ 71.2 ሚሊዮን ብር አድጓል፡፡ ባንኮች ከፍተኛ የሚባል ውድድር የሚያደርጉበትና ለህልውናቸው መሠረት ነው ተብሎ በሚታመነው የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ረገድም፣ የእናት ባንክ ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል ሲሉ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

በቀደመው የበጀት ዓመት 1.09 ቢሊዮን ብር የነበረውን ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑንም ወደ 1.7 ቢሊዮን ብር አድርሻለሁ ብሏል፡፡ ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢውም በ2006 በጀት ዓመት ከነበረበት ከ98 ሚሊዮን ብር ከእጥፍ በላይ በማሳደግ 198 ሚሊዮን ብር ሊደርስ መቻሉንም አስታውቋል፡፡

በተለይ ባንኩ የሰጠው ብድር ከፍተኛ የሚባል ዕድገት የታየበት ሲሆን፣ በ2006 መጨረሻ ላይ 1.08 ቢሊዮን ብር የነበረው የብድር መጠን በ2007 መጨረሻ ላይ 1.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተሰጠው አጠቃላይ የብድር መጠን ስብጥር ሲታይም ለኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰጠው ብድር ብልጫውን ይዟል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከተሰጠው 1.13 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር ውስጥ 299 ሚሊዮን ብር ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ተሰጥቷል፡፡ ከኮንስትራክሽን ዘርፍ ቀጥሎ ከፍተኛ ብድር የተሰጣቸው ዘርፎች የወጪና የገቢ ንግዶች ናቸው፡፡ እንደ ባንኩ መረጃ ለገቢ ንግድ 289.7 ሚሊዮን ብር፣ ለወጪ ንግድ ደግሞ 225.3 ሚሊዮን ብር ተሰጥቷል፡፡

የባንኩ አስቀማጮች ቁጥር ከ17,314 በላይ ሊደርስ ችሏል፡፡ እንደ ባንኩ መረጃ የባንኩ አስቀማጮች ቁጥር በ136 በመቶ አድጓል፡፡ የሴት አስቀማጮችም ቁጥር ከቀደመው ዓመት 138 በመቶ አድጓል፡፡

ባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ እንዳመለከቱት ደግሞ፣ ከባንኩ አስቀማጮች ውስጥ 10,317 ወይም 60 በመቶው ሴቶች ናቸው፡፡ ከተመሠረተበት ዓላማ አንፃር ሴት አስቀማጮችን ማበራከት መቻሉም ተገልጿል፡፡

ባንኩ በ2007 በጀት ዓመት መልካም አፈጻጸም አሳይቷል የተባለው ሌላው ክንውን፣ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ከ1.4 ቢሊዮን ብር ወደ 2.2 ቢሊዮን ብር ማድረሱ ነው፡፡ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማጎልበትን ቀዳሚ ዓላማው አድርጎ የተነሳው እናት ባንክ ዕድገት እያሳየና የተመሠረተበትን ዓላማ ከማሳካቱ ረገድ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑ ቢገለጽም፣ አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱ ይጠቀሳል፡፡

በተለይ በባንኩ የሴት ተበዳሪዎችን ቁጥር ለማሳደግ የተለያዩ አሠራሮችን የቀየሰ ቢሆንም፣ አሁንም አብላጫውን ብድር እየሰጠ ያለው ለወንዶች ወይም ወንዶች ለሚመሩዋቸው ኩባንያዎች ነው፡፡

ባንኩ በበጀት ዓመቱ ለ111 ሴት ተበዳሪዎች ብድር ሰጥቷል፡፡ 111 ተበዳሪዎች የወሰዱት ብድር መጠን 293.01 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህም በበጀት ዓመቱ ከተሰጠው ብድር ውስጥ 25.6 በመቶ ነው፡፡ በቀደመው ዓመት ሴቶች ወስደው የነበረው ብድር 162.08 ሚሊዮን ብር እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህ ረገድ አሁንም ክፍተት እንዳለ የገለጹት የባንኩ ኃላፊዎች፣ ባንኩ የሴት ተበዳሪዎችን የማሳደግ ሥራውን ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ሴት ተበዳሪዎችን ለማብዛት በተለይ ማስያዣ በማጣት ብድር ማግኘት የማይችሉ ሴቶችን ለማገዝ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተገበረ ነው፡፡ ሌሎች የሚያስቀምጡትን ገንዘብ ሴት ተበዳሪዎች ዋስትና እንዲያገኙ በማድረግ የሚሰጠውን የብድር አገልግሎት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ባንኩ አስታውሷል፡፡

በቀዳማይ እመቤት ሮማን ተስፋዬ ባስቀመጡት 100 ሺሕ ብር ሴት ተበዳሪዎች ዋስትና አግኝተው ብድር በመስጠት የተጀመረው አገልግሎት 250 የሚደርሱ ሴቶች ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡

ሦስት ሺሕ የሚሆኑ ሴቶች በተመሳሳይ መንገድ ሌሎች በሚያስቀምጡት ገንዘብ በመያዣነት ተጠቅመው ብድር ለማግኘት እንዲችሉ የሚያስችል ሥልጠና ይሰጣል ተብሏል፡፡ ባንኩ ይህንን አሠራር ለማስፋትም ለሴቶች ለሚበደሩት ብድር ማስያዣ እንዲሆን ከ2007 በጀት ዓመት ትርፍ ላይ አምስት በመቶ ወይም ሁለት ሚሊዮን ብር እንዲሰጥ ወስኗል፡፡

ባንኩ በ2006 በጀት ዓመትም በተመሳሳይ መንገድ 1.05 ሚሊዮን ብር መመደቡ ይታወሳል፡፡ እናት ባንክ በአሁኑ ጊዜ ከ12 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት ሲሆን፣ ከጠቅላላ ባለአክሲዮኖቹ ውስጥ 66 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች