Thursday, June 8, 2023

‹‹የመንግሥት ሥልጣን ላይ ሕግን መሠረት ያደረገ ልጓም የሚያደርጉ ተቋማት መፍጠር ለኢትዮጵያ አሁንም ፈተና ነው››

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዶ/ር ደረጀ ዘለቀ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር

ዶ/ር ደረጀ ዘለቀ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ በቅርቡ በመረጃ ነፃነት ሕጉ አፈጻጸም ላይ በሒልተን ሆቴል የተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ዶ/ር ደረጀ የመነሻ ጥናት አቅርበው ነበር፡፡ በውይይቱ ላይ በቀረበው ጥናትና በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ሰለሞን ጎሹ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የመረጃ ነፃነት ሕጉ ኅዳር 15 ቀን 2001 ዓ.ም. ከወጣ በኋላ ባሉት ዓመታት ምን ዓይነት ለውጦች ታይተዋል?

ዶ/ር ደረጀ፡- ሕጉ በ2001 ዓ.ም. የወጣ ቢሆንም የሕጉን አፈጻጸም የሚወስኑ ቅድመ ዝግጅቶች መደረግ ነበረባቸው፡፡ ሕጉ ራሱ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ የዝግጅት ጊዜን ይፈቅዳል፡፡ ከሕጉ ጋር ተያይዘው የመጡ መርሆዎች በርካታ ረጅም ዘመን የወሰዱ አሠራሮችንና አስተሳሰቦችን መለወጥ ግድ የሚሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከ2004 ዓ.ም. በኋላ በነበሩት ጥቂት ዓመታት ይኼ ነው የሚባል ትርጉም ያለው ለውጥ መጠበቅ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ መጠነኛ የሆነ የለውጥ አዝማሚያ አሳይቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ሥር የሰደደው የሕዝቡና የመንግሥት አሠራር ባህል ሚስጥራዊነትን ያበረታታል፡፡ ይህን ለመቀየር ሕጉ ምን ሚና ይኖረዋል?

ዶ/ር ደረጀ፡- አዋጁ ከመውጣቱም በፊት የመረጃ ነፃነት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠ መብት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ በሆነባቸው ሃያ ዓመታት አንዳች ነገር መኖር አለበት፡፡ ከዜሮ የሚጀመር አይደለም፡፡ ጥናቱ የሚያሳየው ይህንን መሠረታዊ የሆነ የእሴት ለውጥ የሚጠይቅ ሕግ ተፈጻሚ ለማድረግ እጅግ በጣም ብዙ ርቀት እንደሚቀር ነው፡፡ የመረጃን ዋጋ ከመረዳት አንፃር ያለው ባህል ሕጉ ከሚያልመው እውነታ በብዙ ርቀት የሚገኝ ነው፡፡ የተለየ ንቃት ያላቸው ጥቂት ተቋማት አሉ፡፡ የሕጉ መሠረታዊ መነሻ በመንግሥታዊ ተቋማት ይዞታ የሚገኝ መረጃ የሕዝብ ነው፣ ተቋማቱ ባለአደራዎች ናቸው የሚል ነው፡፡ በተጨባጭ በተቋማቱና ጉዳዩ በሚመለከታቸው ኃላፊዎች ዘንድ ያለው አመለካከት ግን የዚህ ቀጥተኛ ተቃራኒ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በውይይቱ ተሳታፊዎች መንግሥት ሕጉ እንዲወጣ ከማድረግ ባሻገር፣ ተፈጻሚነቱን የመከታተል ቁርጠኝነት የለውም የሚል ወቀሳ ተሰንዝሯል፡፡ ከሌሎች አገሮች አንፃር ሕጉን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰደው የዝግጅት ጊዜ በዝቷል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ደረጀ፡- የመረጃ ነፃነት ሕግን ነጥሎ ማውጣት የቅርብ ጊዜ ጅምር ነው፡፡ መሠረታዊው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ዳብሮ ሥር የሰደደባቸው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶች ውስጥ ለብዙ ዘመናት ይህንን ሕግ ማውጣት አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ሕጉ ባለመውጣቱ መብቱ በመሠረታዊ ደረጃ የተገደበ አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያም ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትንና ለዚህም አስፈላጊ የሆኑ ተዛማጅ መብቶችን እውን ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ፣ የዝግጅት ጊዜው ማጠርና መርዘም አያከራክረንም ነበር፡፡ ምናልባትም ሕጉ መውጣቱ መንግሥታዊ ተቋማት የመረጃ አደረጃጀት ሥርዓታቸውንና ግንዛቤያቸውን በመለወጥ ረገድ አስገዳጅ ኃይል ያለው በመሆኑ ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሕጉ በመንግሥት ወይም በገዥው ፓርቲ ፍላጎት ሳይሆን ሻል ባሉ ጥቂት ተራማጅ ግለሰቦች ግፊት ብቻ እንደወጣ አስተያየት ቀርቦ ነበር፡፡ በዚህ ይስማማሉ?

ዶ/ር ደረጀ፡- አስተያየቱ ወሳኝ የሆነ የአገራችንን ማኅበረ ፖለቲካዊ ጉዳይ የሚያነሳ ነው፡፡ መርሁ በሕገ መንግሥቱ ያለ ነው፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት ይህ ተፈጻሚ ሳይሆን ለምን እንደቀረ እንደ አንድ መላ ምት ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሕጉ ተግባራዊ የማይሆነው በእምነት ወይም በቁርጠኝነት እጦት ከሆነ በጣም አደገኛ ነው፡፡ የማን እምነትና የማን መለኪያ የሚለውን ካነሳን ችግር ነው፡፡ ዝም ብሎ እመኑኝ እኔ ቁርጠኛ ነኝ ማለት አይቻልም፡፡ በሠለጠነ ሥርዓት ውስጥ እመኑኝ ዋስትና ሊሆን አይችልም፡፡ ሁሉም ሊተማመኑበትና ሊገዙበት የሚችለው የሕግ ቃል ኪዳን አለ፡፡ ሕጉ ከየትም ቢቀዳ ተፈጻሚነቱ ተግባራዊ የሚደረገው ሁሉም ላይ ነው፡፡ ሕግ ማውጣት በራሱ ተፈጻሚነቱን ግን አያረጋግጥም፡፡ የሕጉ ተፈጻሚነት የሚወሰነው ሕጉ ሊተገበር ባለበት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መድረክ ላይ ባለው ከባቢ ሁኔታ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የገዥው ፓርቲ ልሂቃን ያላቸው እምነትና ፍልስፍና ቁልፍ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሰፈረውም ሆነ በመረጃ ነፃነት ሕጉ የተካተቱት መሠረታዊ መርሆዎች ያለምንም ጥያቄ የሊበራል እሴቶች ናቸው፡፡ የኮሙዩኒስት እሴቶች አይደሉም፣ የአምባገነን እሴቶች አይደሉም፡፡ ስለዚህ የገዥው ፓርቲ ልሂቃን እነዚህን እሴቶች የማያምኑባቸው ከሆነ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለአንድ ርዕዮተ ዓለም ድጋፍ መስጠት ወይም ማጣጣል መብት ነው፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ከገባ ብትወድም ባትወድም ለዚያ መገዛት አለብህ፡፡ ባትገዛ ደግሞ ተጠያቂ የምትሆንበትን ሥርዓት መዘርጋት ግድ ነው፡፡ ይህ በሌለበት ሁኔታ በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ልባቸው የማይወደው ሕግ ተፈጻሚ ይሆናል ብሎ ማሰብ እጅግ የዋህነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29(6) እና (7) ላይ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ ገደብ የሚጣልበትን አካሄድ ደንግጓል፡፡ በመረጃ ነፃነት ሕጉ ላይ የተዘረዘሩት ገደቦች ብዛትና ገደቦቹን ለመግለጽ የሚያሻሙና የሚያምታቱ፣ ግልጽነት የሚጎላቸው ቋንቋዎችን መጠቀሙ ክፍተት መፍጠሩም ይነገራል፡፡ በዚህ ግምገማ ይስማማሉ?

ዶ/ር ደረጀ፡- መረጃ የማግኘት መብት ገደብ የማይጣልበት ፍፁም መብት አይደለም፡፡ በሁሉም አገሮች ተሞክሮ የሚንፀባረቅ ነው፡፡ መረጃ በሙሉ ለሕዝብ ተደራሽ መሆን አለበት የሚለው ገዥ መርህ ነው፡፡ ስለዚህ መረጃ መከልከል ልዩ ሁኔታ ነው፡፡ የክልከላ ምክንያቶቹን መሟላት የማረጋገጥ ኃላፊነት የመንግሥት ተቋማት ነው፡፡ በዚህ መሠረት የሚሰጡ የክልከላ ውሳኔዎች አግባብነት የሚፈተሽበት የሕግ ማዕቀፍ መኖር አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ የተቀመጡ እንደ የግል ነፃነት ያለመደፈር መብት፣ የቢዝነስ ሚስጥሮች፣ ብሔራዊ ደኅንነት፣ የአገር መከላከያ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና የመሳሰሉት የክልከላ ምክንያቶች በሁሉም አገር ያሉ ናቸው፡፡ ችግሩ ያለው እነዚህ የክልከላ ምክንያቶች የሚተከሉበት ከባቢ ሁኔታ ላይ ነው፡፡ መብቱን በፍፁም የሚጠላ በሚስጥራዊ አሠራር ውስጥ የኖረ ማኅበረሰብና ቢሮክራሲ ውስጥ ስትወስደው የክልከላ ምክንያት የሚፈልጉ ባለሥልጣናት ባሉበት ከባቢ ሁኔታ ካስገባኸው፣ የክልከላ ምክንያቷ አንዲትም ብትሆን ከመከልከል አይመለስም፡፡ መሠረታዊው ነገር የክልከላ ምክንያቶቹ መብዛትና ማነስ አይደለም፡፡ መለመን መረጃ የማግኘት ወሳኝ የአሠራር መንገድ በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ፣ የክልከላ ምክንያቶች ባይኖሩም እንኳን ተጠያቂነት በሌለበት ዓውድ እንቢ መባሉ አይቀርም፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ የሚሆነው ሕጉ የክልከላ ምክንያቶችን በጽሑፍ መስጠት ቢያስገድድም በጥናቱ ከተሳተፉት ውስጥ 99 በመቶ የሚሆኑት በቃል ነው አይቻልም የተባሉት፡፡ ሳይብራሩ የተቀመጡ በጣም ጥቅል የሆኑ የክልከላ ምክንያቶችን በሌሎች ደንቦች፣ በአሠራር ማኑዋሎችና በመመርያዎች ማፍታታትና መዘርዘር ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የመረጃ ነፃነት ሕጉ እንደ የሚስጥር ሕግ፣ የመረጃ ምደባና ሚስጥራዊነት ማብቂያ ሕግ፣ የመረጃ ዋጋ ተመን ሕግ፣ የመረጃ አፈትላኪዎች ጥበቃ ሕግ መውጣት ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ እንደሚያደርገው ታሳቢ ተደርጎ የወጣ ነው፡፡ የእነዚህ ሕግ አለመውጣት በእናንተ ጥናትና በስብሰባው ተሳታፊዎች እንደ ተግዳሮት ተጠቅሷል፡፡ የፈጠረው ክፍተት ምን ይመስላል?

ዶ/ር ደረጀ፡- የእነዚህ ሕጎች አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ አይነሳም፡፡ ነገር ግን በመብቱ አፈጻጸም ላይ የሚኖራቸው ሚና ከፍና ዝቅ ሊል የሚችለው በአጠቃላይ በአገር ውስጥ ባለው የሕግ የበላይነትና የሰብዓዊ መብቶች አከባበር ደረጃ ነው፡፡ እርግጥ የሕጎቹ አለመውጣት ለመብቱ ተፈጻሚነት የራሱ የሆነ አደናቃፊነት ሚና አለው፡፡ ነገር ግን ይኼን ጉዳይ የትኩረት አቅጣጫ ማድረግ ከእነዚህ ሕጎች አለመውጣት ውጪ የመብቱ ጥበቃ ይዞታ ደህና ነው የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ያደርሳል፡፡

ሪፖርተር፡- የመረጃ ነፃነት ሕጉ ከመገናኛ ብዙኃን ሕግ ጋር መቀላቀሉን እንደ ችግር ያዩት ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ የሚዲያ ተቋማትና ማንኛውም ግለሰብ መረጃ የሚያገኙበት አሠራር ተመሳሳይ መሆኑ በሌሎች አገሮች የተለመደ ነው?

ዶ/ር ደረጀ፡- ሕጉ ለሁሉም መረጃ ፈላጊዎች ነው የሚለው፡፡ ነገር ግን በመርህ ደረጃ መረጃ ፈላጊዎችን ለሁለት ከፍለን ማየት አለብን፡፡ በአንደ በኩል ለዕለት ተዕለት ኑሮውና ለግል ሕይወቱ እንደ ሜድካል ሪከርድ፣ የግብር መረጃ የሚፈልግ አለ፡፡ በሌላ በኩል ለአጠቃላይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ለተጠያቂነት፣ ለሰብዓዊ መብት መከበርና ብልሹ አሠራሮችን ለመዋጋት ቁልፍ የሆነ ሚና የሚጫወተው ሚዲያ አለ፡፡ ሁለቱ መረጃ የሚፈልጉበት ምክንያት የተለያየ ነው፡፡ በግለሰብ በኩል መሻሻሎች አሉ፡፡ ሚዲያውን በተመለከተ ግን የምርመራ ሥራ የሚሠሩና ተጠያቂነትንና የሕግ የበላይነትን የተመለከቱ ጥያቄዎች ይዞ የሚሠራው ሚዲያ ያለበት ሁኔታ እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በአጠቃላይ እንደ ማኅበረሰብና አገር ከፍተኛ አደጋ ይደቅናል፡፡ ነፃና ውጤታማ ሚዲያ በሌለበት ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብን መገንባት አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንዶች እንዲያውም ሕጉ ለጋዜጠኞች የዕለት ተዕለት ሥራ ተግባራዊ የሚሆን አይደለም ብለው ተከራክረዋል፡፡

ዶ/ር ደረጀ፡- የመረጃ ነፃነት ሕጉ ከመገናኛ ብዙኃን ሕግ ጋር መቀላቀሉ አይደለም ይህን ችግር ያመጣው፡፡ አንድ ላይም ሆነ ተነጣጥለው ቢወጡ ካልተፈጸመ ትርጉም የለውም፡፡ መረጃ የማግኘት መብት የሁሉም ዜጎች ነው፡፡ እርግጥ መረጃ የማግኘትን መብት ከሚዲያ አንፃር ብቻ መመልከት የሕጉን አንድ ምዕላድ ገንጥሎ እንደመጣል ነው፡፡ ሆኖም ከግለሰብ ይልቅ ሚዲያ መረጃ የታጠቀ ዜጋ ለመፍጠር ፍቱን ነው፡፡ ይህ ዓይነት ዜጋ ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎችን በማክበር ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ቁልፍ ሚና አለው፡፡ ከዚህ አንፃር ከሚዲያ ይልቅ በተናጠል ለግል ሕይወታቸው መረጃ እንዲያገኙ ማድረግን መደፍጠጥ ይሻላል፡፡ የአዋጁን ዋና ዓላማ ካየን ሚዲያው ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የሕዝብ ግንኙነት ቢሮዎች በሕጉ ሲቋቋሙ ዋናው ዓላማ የመረጃ ፍሰቱን ማሳለጥ ቢሆንም፣ በተግባር መረጃ እንዳይሰጥ ዘብ እየቆመ ነው የሚል ቅሬታ ቀርቧል፡፡ የቢሮውን ሚናና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችን ሥራ እንዴት አዩት?

ዶ/ር ደረጀ፡- ይኼ ቅሬታ በአብዛኛው የሚቀርበው በሚዲያ ባለሙያዎች ነው፡፡ የዕለት ተዕለት ሥራቸው ያገናኛቸዋል፡፡ ነገር ግን በእኛ ጥናት የሕዝብ ግንኙነት  ባለሙያዎች ስለመረጃ ነፃነት ሕጉ ያላቸው ግንዛቤ እጅግ ውስን መሆኑ ተመልክቷል፡፡ መረጃ ከመስጠታቸው በፊት የኃላፊዎችን ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ መረጃ የመስጠትና ያለመስጠት ውሳኔ በተግባር የሚሰጠው በሥራ ኃላፊዎች እንጂ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች አይደለም፡፡ ኃላፊዎቻቸው የማይደሰቱበትን ሥራ ቢሠሩ የሥራ ዋስትና እንዳላቸው እርግጠኛ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ለችግሩ እነሱን ብቻ መውቀስ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ የሥራ ኃላፊዎች እንደ ነገሥታት ሁሉን አዛዥ በሆኑበት ሁኔታ በአንድ ጥግ የተቀመጠ ምስኪን ሠራተኛ ሕጉ ላስቀመጠው መርህ ተገዥ እንዲሆን መጠበቅ ተገቢ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የመረጃ ነፃነት ሕጉን የማስፈጸም ኃላፊነት የተሰጠው ለእንባ ጠባቂ ተቋም ነው፡፡ ይህ ውሳኔ ተቋሙ አስቀድሞ ከነበረው አቅምና ልምድ አንፃር ቅሬታ ቀርቦበት ነበር፡፡ ባለፉት ዓመታት ተቋሙ የሄደበት አቅጣጫ ይህን ያፋለሰ ነው ይላሉ?

ዶ/ር ደረጀ፡- ጥያቄው በተወሰነ ደረጃ እኔ ልመልሰው የምችል አይደለም፡፡ የተወሰነ ሥራ እንደሠራ አምናለሁ፡፡ ለተቋሙ ኃላፊነቱን የመስጠት ውሳኔው ፖለቲካው ውሳኔ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ጥቅምና ጉዳቱ ምናልባትም የወደፊት የጥናት ነጥብ ሊሆን ይችላል፡፡ በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ሌሎች እንደ ፍርድ ቤት ያሉ አማራጭ ተቋማት ከእንባ ጠባቂ ተቋም የተሻሉ ስለመሆናቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ የመንግሥት በተለይ የአስፈጻሚው አካል ሥልጣን ላይ ሕግን መሠረት ያደረገ ልጓም የሚያደርጉ ተቋማት መፍጠር ለኢትዮጵያ አሁንም ፈተና ነው፡፡ ይኼንን በአዋጅ ሳይሆን በሒደት ነው ማምጣት የሚቻለው፡፡

ሪፖርተር፡- መረጃን ያለ ሕግ አግባብ የከለከለ ተቋም ላይ በተለያዩ እርከኖች ይግባኝ በማለት ሌላ ውሳኔ ማግኘት እንደሚቻል የሕግ ማዕቀፉ ያስቀምጣል፡፡ በመድረኩ እንደተገለጸው ይህን አሠራር ተከትሎ የመሟገት ባህል ግን ሥር አልሰደደም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ምንድነው?

ዶ/ር ደረጀ፡- ሚዲያን በተመለከተ የተቀመጠው ጊዜና ሒደት የተወሳሰበ በመሆኑ አያበረታታም፡፡ ሕጉ ግን ታሳቢ ያደረገው መረጃ ወዲያው እንዲገኝ ነው፡፡ የይግባኝ ሒደቱ በተለየ ሁኔታ የሚፈጸም ነው፡፡ እንኳን ሌላ የተወሳሰበ መረጃ ይቅርና የሥራ ልምድ ለማግኘት እንኳን እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ለመከራከር የምትገደድበት ሁኔታ አለ፡፡ ሕጉ ለሠለጠነ ማኅበረሰብ የሚሆን ነው፡፡ የማላምንበትም ቢሆን በሕጉ መሠረት መጫወት አለብኝ፡፡ አለበለዚያ የሚመጣውን ኃላፊነት ለመሸከም ነው መዘጋጀት ያለብኝ፡፡ በተግባር ያለው ሁኔታ ግን ከሕግ ማዕቀፉ ያለው ርቀት በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ይህን ሰፊና ጥልቅ ችግር መቅረፍ ስንችል ነው የመረጃ ነፃነት ሕጉን ትርጉም በሚሰጥ መንገድ መተርጎም የምንችለው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -