Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዲዛይንና የጥገና ሥራን በአንድ ያጠቃለለ አዲስ የግንባታ አሠራር ተግባራዊ ሊሆን ነው

የዲዛይንና የጥገና ሥራን በአንድ ያጠቃለለ አዲስ የግንባታ አሠራር ተግባራዊ ሊሆን ነው

ቀን:

– አዲሱ አሠራር ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ በሚፈጀው የነቀምት-ቡሬ መንገድ ላይ ይጀመራል

በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ ነው የተባለው የዲዛይንና የጥገና ሥራውን አጠቃልሎ ለአንድ ኮንትራክተር የሚያሰጥ አዲስ የግንባታ አሠራር፣ 256 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው የነቀምት-ቡሬ መንገድ ላይ ተግባራዊ ሊደረግ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው የዲዛይን፣ የግንባታና የጥገና ሥራን አጠቃልሎ ለአንድ ኮንትራክተር ለመስጠት የሚያስችለው የነቀምት-ቡሬ መንገድ ፕሮጀክት ዓለም አቀፍ ጨረታ ሒደትም በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ የባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለዚህ መንገድ ግንባታ ተወዳዳሪ ኮንትራክተሮች ያቀረቡት ዋጋና ሌሎች መወዳደሪያ መሥፈርቶች እየተገመገሙ ናቸው፡፡ በቅርቡም ውጤቱ ይፋ ሆኖ ጨረታውን ከሚያሸንፉ ኮንትራክተሮች ጋር ስምምነት ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአዲሱ አሠራር የነቀምት-ቡሬ መንገድን ለመገንባት በወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ከስምንት በላይ የሚሆኑ የቻይና፣ የህንድ፣ የቱርክና የስፔን ኮንትራክተሮች ተፎካካሪ ሆነው ቀርበዋል፡፡

256 ኪሎ ሜትሩ የመንገድ ፕሮጀክት ለሦስት ተከፍሎ ለሦስት ኮንትራክተሮች የሚሰጥ መሆኑንም፣ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ የነቀምት-ቡሬ መንገድ ግንባታ በዚህ ዓመት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑም ይኼው ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአገሪቱ የመንገድ ግንባታ ልምድ አንድ ኮንትራክተር ግንባታውን ብቻ እንዲያከናውን፣ ዲዛይኑ ደግሞ በሌላ አማካሪ ድርጅት እንዲከናወን ይደረግ የነበረው ኮንትራት ለረጅም ጊዜ ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ ቆየት ብሎም በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ ደግሞ ዲዛይንና ግንባታውን በማጣመር እንዲሠራ እየተደረገ እንደነበርም ይታወሳል፡፡

አዲሱ አሠራር ግን ከዚህ በተለየ ዲዛይኑን፣ ግንባታውንና ከመንገዱ ግንባታ መጠናቀቅ በኋላም የጥገና ሥራን የሚያካትት ነው፡፡ ይህ አሠራር ሦስቱንም ሥራዎች አጣምሮ ለመሥራት አሸናፊ የሚሆነው ኮንትራክተር ኃላፊነት የሚወስድበት ይሆናል፡፡ የነቀምት-ቡሬ መንገድ ፕሮጀክት አጠቃላይ ግንባታን ለማከናወን አሸናፊ የሚሆኑ ኮንትራክተሮች፣ መንገዱን ካስረከቡ በኋላ ለአምስት ዓመታት የጥገና ሥራ ያከናውናሉ፡፡

ዲዛይን፣ ግንባታና የጥገና ሥራን አጣምሮ ለአንድ ኮንትራክተር እንዲሰጥ የሚያስችለው አሠራር ለአገሪቱ እንግዳ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሳምሶን፣ ወደዚህ አሠራር መገባቱ የአገሪቱን የመንገድ ግንባታ ክንውን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ መሸጋገሩን ያሳያል ብለዋል፡፡ ቀልጣፋ አሠራርን ይፈጥራል ሲሉም አክለዋል፡፡ የነቀምት-ቡሬ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ከተጀመረ በኋላም ይህ አሠራር በሌሎች በተመረጡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...