Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኢትዮጵያና በቱርክ መካከል የተደረሰው ለዲፕሎማቶች መኖሪያ የመሬት ልውውጥ ስምምነት ፓርላማውን አነጋገረ

በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል የተደረሰው ለዲፕሎማቶች መኖሪያ የመሬት ልውውጥ ስምምነት ፓርላማውን አነጋገረ

ቀን:

በኢትዮጵያና በቱርክ መንግሥታት መካከል የተፈረመውን ለኤምባሲ፣ ለሚሲዮን መሪዎችና ለዲፕሎማቶች መኖሪያ ግንባታ የመሬት ልውውጥ ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበው አዋጅ ፓርላማውን አነጋገረ፡፡

የስምምነቱ ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ አባሪ እንደሚገልጸው ስምምነቱ የተፈረመው እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 2010 ነው፡፡ የስምምነቱ ዓላማም በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል እያደገ የመጣውን የንግድ፣ የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የተለያዩ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ትብብሮች የበለጠ ለማጠናከር ነው፡፡

የስምምነቱ መሠረት የቱርክ መንግሥት 3,000 ካሬ ሜትር ከክፍያ ነፃ የሆነ መሬት በቱርክ አንካራ ለሚገኘው ለኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ የተከለለ ቦታና ለሚሲዮን፣ ለአምባሳደር መኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል መሬት የመስጠት ግዴታን ያስቀምጣል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአፀፋው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት 7,192.8 ካሬ ሜትር በአዲስ አበባ የሚገኝ ለሚሲዮን፣ አምባሳደርና ዲፕሎማቶች መኖሪያ ግንባታ የሚውል መሬት ለመስጠት ግዴታ መግባቱን በስምምነቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚያቀርበው 7,192.8 ካሬ ሜትር ውስጥ፣ 4,192.8 ካሬ ሜትር የሚሆነው መሬት 3,200,000 ዶላር ሊዝ የሚከፈልበት መሆኑ ስምምነት ተደርጓል፡፡

የግንባታ ቦታው የሚሰጠው በሰጥቶ መቀበል መርህ ሆኖ፣ ሁለቱም ወገኖች መሬቱን የሚጠቁሙበት የዲፕሎማቲክ ተልዕኳቸውን ለማሳካት ብቻ መሆኑን ስምምነቱ ይገልጻል፡፡

እያንዳንዱ ወገን ፕሮጀክቱንና ግንባታውን መቼ እንደሚጀምር በግሉ መወሰን እንደሚችል በስምምነቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ተፈጻሚ በሚሆንበት ወቅት እያንዳንዱ ወገን መሬቱን የሰጠውን አገር ሕግ ደንብና ቴክኒካዊ መሥፈርቶች የማክበር ግዴታ እንዳለበት በስምምነቱ ሰፍሯል፡፡

በሁለቱ ወገኖች መካከል አለመግባባት ቢፈጠር በግልግል ዳኝነት የሚፈታ መሆኑን ስምምነቱ ይገልጻል፡፡ ስምምነት የገቡት አገሮች ዋና መዲናቸውን ቢቀይሩ ስምምነት ለገባው አገር ካሳና ምትክ ቦታ የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡

ኢትዮጵያ በቱርክ የምትፈልገው ቦታ 3,000 ካሬ ሜትር ከሆነና መርሁም ሰጥቶ መቀበል ከሆነ፣ ኢትዮጵያም መስጠት የሚገባት 3,000 ካሬ ሜትር ብቻ መሆን እንዳለበት፣ አለበለዚያ እንደዚህ ዓይነት ስምምነት በኖረ ቁጥር ገንዘብ ላለው መሬት ሲሸጥ ሊቀጥል ነው ወይ? በማለት አንድ የምክር ቤቱ አባል ጥያቄያቸው በቋሚ ኮሚቴ እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡

ሌሎች አባላት ደግሞ የሊዝ አዋጁ መሬት በጨረታ በሊዝ እንደሚያዝ፣ እንዲሁም በምደባ መንግሥት ሊዝ የሚከፈልበት መሬት ሊያቀርብ እንደሚችል ደንግጐ ሳለ፣ ፓርላማው የሊዝ ዋጋ ያለበትን ስምምነት ሊያፀድቅ እንደማይገባና ይህ ምክር ቤት የሊዝ ዋጋ ሊወስን እንደማይችል ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን በዝርዝር እንዲመለከተው ጠይቀዋል፡፡ የቀረበው የስምምነት ማፅደቂያ አዋጅም በአንድ ድምፀ ተአቅቦ ለውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ ተመርቷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...