Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላሳዩ ነጋዴዎች ቦታ የሚያዘጋጅ ኮሚቴ ተቋቋመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከንግድ ይልቅ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲያዘነብሉ ግፊት ሲደረግባቸው የቆዩ ባለሀብቶች፣ በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ ባሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ቦታ የሚያገኙበትን መንገድ የሚያመቻች ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡

ኮሚቴው በኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው የሚመራ ሲሆን፣ ንግድ ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በአባልነት ተካተዋል፡፡

ታኅሳስ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ከኤምኤች አማካሪ ድርጅት ዶ/ር መሰለ ኃይሌ ጋር መግለጫ የሰጡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ገመቹ፣ ኮሚቴው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ዞኖች ውስጥ ቦታ እንዲያገኙ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች ገልጸዋል፡፡

‹‹የአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንደፍላጎታቸው የፋብሪካ ሕንፃዎችን ተከራይተው፣ በለማ መሬት ላይ የራሳቸውን ግንባታ እንዲያከናውኑ ለማድረግ የፓርኮቹ ዲዛይን ተዘጋጅቷል፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አሥር ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመገንባት አቅዷል፡፡ ከሚገነቡት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ ቁጥር ሁለት 186 ሄክታር፣ ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ 275 ሄክታር ይለማል፡፡

ለእነዚህ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገው 250 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም ባንክ በብድር የተገኘ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ጥናቱ በኮንትራክተሩ አማካይነት እየተካሄደ መሆኑ ታውቋል፡፡ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለጨርቃ ጨርቅ፣ ጋርመንትና ጫማ አምራቾች የሚሰጥ ነው፡፡ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ ለምግብ፣ መድኃኒትና ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠይቁ ምርቶች ይመረቱበታል፡፡ ይህንን ሥራ በማካሄድ ላይ የሚገኘው የኮርያ ኩባንያ የሆነው ዶሀ ነው፡፡

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዲዛይንና ግንባታ በጥምር እየተካሄደ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ሐምሌ 2007 ዓ.ም. የቻይና ኩባንያ ከሆነው ሲሲኢቢሲ ጋር ውል ተገብቶ ሥራው እየተካሄደ ነው፡፡

ይህ ፕሮጀክት በመቶ ሄክታር ላይ እየተካሄደ ሲሆን፣ ስፋታቸው የተለያዩ 35 ፋብሪካዎችን የሚይዝ ሕንፃዎች፣ ለአንድ ሺሕ ሠራተኞች የመኖርያ ቤቶችና የጋራ መጠቀሚያ ግንባታዎችን አጣምሮ የያዘ ፕሮጀክት ነው፡፡

የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመጀመርያው ምዕራፍ 150 ሄክታር ላይ ይገነባል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት አጠቃላይ ጥናት እየተካሄደ ሲሆን፣ ግንባታውን የአገር ውስጥና የውጭ አገር ኩባንያዎች በጋራ ያካሂዱታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪ በቅርቡ በአዳማ፣ መቐለ፣ ኮምቦልቻ፣ ጂማና ባህርዳር ከተሞች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡

አቶ ሲሳይ እንደገለጹት፣ በእነዚህ አምስት ፓርኮች ግንባታ ላይ ሰባት የአገር ውስጥና አምስት የውጭ አገር ተቋራጮች እንዲሳተፉ ተወስኗል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለመግባት በርካታ የውጭ ኩባንያዎች ጥያቄ እያቀረቡ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችም ቦታ እንደተዘጋጀ ተገልጿል፡፡

አቶ ሲሳይ እንደገለጹት፣ የኮርፖሬሽኑ ዋነኛ ዕቅድ በአገሪቱ የኤክስፖርት ምርቶችን ማስፋትና የሥራ ዕድል ፈጠራና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲካሄድ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መሠረት አገሪቱ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ኤክስፖርት፣ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገቢ ማግኘት የሚያስችላት ሲሆን፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በአሥር ዓመት ውስጥ ሁለት ሚሊዮን ሠራተኛ የመቅጠር አቅም ይኖራቸዋል፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግርንም ተግባራዊ ለማድረግ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጥምረት እንደሚኖር አቶ ሲሳይ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በተለይ በንግድና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገቡ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በዘርፉ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች፣ በአቶ አህመድ በሚመራው ኮሚቴ አማካይነት ቦታቸውን ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች