Monday, November 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበዕቅድ ለተያዙ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ማጋጠሙ ለፓርላማው ተገለጸ

  በዕቅድ ለተያዙ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ማጋጠሙ ለፓርላማው ተገለጸ

  ቀን:

  – የአገር ውስጥ ባንኮችና የውጭ ኢንቨስተሮች በአማራጭነት ታይተዋል

  በግንባታ ላይ ከሚገኙት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ውጪ፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ለተያዙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ማጋጠሙን የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች ለፓርላማው አሳወቁ፡፡

  የፓርላማው የአካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴርና የተጠሪ መሥሪያ ቤቶችን የ2008 ዓ.ም. የሥራ ዕቅድና የመጀመርያው ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸምን ሰኞ ታኅሳስ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በገመገመበት ወቅት ነው ይህ የተገለጸው፡፡

  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበጀት ዓመቱ በዕቅድ የያዛቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና ፕሮጀክቶቹ ሊገጥሟቸው ለሚችሉ ችግሮች ወይም ሥጋቶች ምን ያህል ዝግጅት እንደተደረገ ማብራሪያ የጠየቀው ቋሚ ኮሚቴው፣ በዕቅድ የተያዙት ፕሮጀክቶች በፋይናንስ እጥረት ምክንያት እስካሁን ወደ ተግባር አለመግባታቸው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና በሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ ተደርጓል፡፡

  ለዚህ በጀት ዓመት ወደ ተግባር እንዲገቡ በዕቅድ የተያዙት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ጨሞጋ ይዳ 278 ሜጋ ዋት፣ ገባ 214 ሜጋ ዋት፣ ሐለሌ ወራቤሳ 422 ሜጋ ዋት፣ አይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ 300 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

  እነዚህ ፕሮጀክቶች እንዴት ወደ ትግበራ ሊገቡ እንደሚችሉ ለቀረበው ጥያቄ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ በሰጡት ምላሽ ከላይ ለተገለጹት ፕሮጀክቶች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ከውኃ፣ ከፀሐይ፣ ከጂኦተርማልና ከንፋስ መገኘት የሚችሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን ከነቦታቸው መለየታቸውን ገልጸው፣ ‹‹እንዴት እንገነባቸዋለን የሚለው ጥያቄ አለ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የፋይናንስ እጥረት ነው፤›› ብለዋል፡፡

  በዚህ የተነሳም በዚህ ዓመት ተግባራዊ መደረግ የሚገባቸውን ፕሮጀክቶች በመለየት፣ አብዛኞቹ በውጭ ኢንቨስትመንት እንዲገነቡ መወሰናቸውን ገልጸዋል፡፡

  ‹‹ይኼም ማለት የውጭ አልሚዎች ለብቻቸው ኃይል አመንጭተው ለመንግሥት እንዲሸጡ፣ ወይም ከመንግሥት ጋር በጋራ እንዲያለሙ አቅጣጫ ተቀምጧል፤›› ብለዋል፡፡

   ሦስተኛው አማራጭ ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በራሱ ግንባታውን እንዲያካሂድ ማድረግ ሲሆን፣ ከፋይናንስ አኳያ ያለውን ችግር ለመቅረፍም የአገር ውስጥ ባንኮች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

  የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድሙ ተክሌ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የራሱን ቦንድ በመሸጥ ብድር የሚያገኝበት መንገድ እየተጠና መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን ዕውን ለማድረግ ግን ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ወሳኝ መሆኑንና በዚህ ረገድም ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጥናቱ የታሪፍ ማሻሻያን የተመለከተ ስለመሆኑ የገለጹት ነገር የለም፡፡

  የፋይናንስ እጥረቱ የመነጨው ከዕቅድ ስፋት፣ አገሪቱ ካላት የገንዘብ አቅም አንፃርና ከብድር መጠን አኳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የብድር መጠናችን እንደ አገር የሚታይ ነው፡፡ ብድር ስለተገኘ ብቻ የሚወሰድበት መንገድ የለም፡፡ ፓርላማውም በዚህ ላይ ትኩረት የሰጠ ይመስለኛል፤›› ብለዋል፡፡

  በመሆኑም አዋጭ የሆነው አማራጭ የውጭ ኩባንያዎች ለብቻቸው ኃይል አመንጭተው ለመንግሥት እንዲሸጡ፣ ወይም ከመንግሥት ጋር በጋራ እንዲያለሙ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የአዋጆች ማሻሻያ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የውጭ ኩባንያዎች ሊመጡ የሚችሉት የራሳቸውን ትርፍ ስለሚያዩ ነው ብለዋል፡፡

  በጂኦተርማል የኃይል ማመንጨት ተግባር ላይ የሚሳተፉ የውጭ ባለሀብቶችን ማስተናገድ እንዲቻል የሚያስፈልገው የአዋጅ ማሻሻያ ከሳምንት በፊት ተጠናቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

  የሕግ ማሻሻያው በሌሎቹም የኃይል ማመንጫዎች ዘርፎች ላይ እንደሚያስፈልግ ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...