Friday, September 22, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት ውስጡን ይፈትሽ!

ለአዲስ አበባና ለኦሮሚያ ልዩ ዞን በተዘጋጀው የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን ምክንያት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ሥፍራዎች የታዩት አመፆች፣ መንግሥት ውስጡን አብጠርጥሮ እንዲፈትሽ ያስገድዳሉ፡፡ መንግሥት ውስጡን በሚገባ እንዲፈትሽ የሚገደደው በክልሉ ውስጥ በተከሰተው ሁከት ምክንያት የሚሰሙት ቁጣዎች፣ በአብዛኛው በመንግሥት ሹማምንት ላይ ያነጣጠሩ በመሆናቸው ነው፡፡ መንግሥት በቃል አቀባዩ አማካይነት እንደገለጸው፣ ሁከት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች በየደረጃው ያሉ ሹማምንትና የፀጥታ ሠራተኞች የጥቃት ዒላማ ሆነዋል፡፡ በችግሩ ዙሪያ ከሚነገሩ ዋነኛ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የፍትሕ መጓደልና ሙስና ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እነዚህ መንግሥት ውስጡን እንዲፈትሽ ያስገድዳሉ፡፡

በግንቦት 2007 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከአጋሮቹ ጋር መቶ በመቶ የፓርላማ መቀመጫዎችን በመቆጣጠር፣ በምርጫው በሕዝብ ድምፅ ይሁንታ ማግኘቱን አረጋግጧል፡፡ በዚህም መሠረት ቀጣዮቹን አምስት ዓመታት የሚመራ መንግሥት መሥርቷል፡፡ ይሁንና አፍታም ሳይቆይ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የፍትሕ ዕጦትና ሙስና ጊዜ የማይሰጡ ፈተናዎች እንደሆኑበት አስታውቋል፡፡ ወዲያው ደግሞ ለዓመታት ያህል ተንጠልጥሎ የቆየውና የሰው ሕይወት ያለፈበት የማስተር ፕላን ጉዳይ ሌላ አመፅ ቀስቅሶ፣ ሕይወት እያለፈና ንብረት እየወደመ ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ላይ ሆኖ ነው መንግሥት ራሱን መፈተሽ ያለበት፡፡ ከሕግ የበላይነት፣ ከሰብዓዊ መብት አጠባበቅና ከዴሞክራሲ ያፈነገጡ አሠራሮችን ያርም፡፡

የመንግሥት አካላት የሆኑት ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው እንዴት እየተናበቡ ነው ሥራቸውን እየሠሩ ያሉት? የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቱ ምን ይመስላል? አስፈጻሚው አካል ከላይ እስከ ታች ያለው መዋቅሩ እንዴት እየሠራ ነው? ሕግ ተርጓሚው በትክክል ሥራውን እየሠራ ነው ወይ? ሕግ አውጪው (ፓርላማው) ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ወይ? በሕዝብና በእነዚህ አካላት መካከል ያለው ቅርርብ ምን ይመስላል? የሚሉትና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ አስፈጻሚው አካል በተደጋጋሚ እንዳመነው የመልካም አስተዳደር ዕጦት ሕዝብን እያስመረረ ነው፡፡ በደላላ የሚመራው ሙስና አገር እያጠፋ ነው፡፡ የፍትሕ መስተጓጎል ሕዝቡን ደም እንባ እያስለቀሰ ነው፡፡ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት አበላሽቶታል፡፡ መቶ በመቶ የፓርላማ መቀመጫ የያዘ መንግሥት አሁን ወሳኝ የሆነ ምዕራፍ ላይ በመድረሱ ራሱን ይፈትሽ፡፡ ያለምንም ርህራሔ ራሱን ይገምግም፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ሁከት የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ ነው፡፡ የአካል ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ የንብረት ውድመትም እየታየበት ነው፡፡ ይህ አመፅ በማስተር ፕላኑ ጉዳይ ላይ ተመሥርቶ ቢቀሰቀስም፣ አሁን አቅጣጫውን ቀይሯል፡፡ አመፁን የሚመራ የተደራጀ ኃይል ወይም ፓርቲ በግልጽ አለመኖሩም ታይቷል፡፡ ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች ውጤትም ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት ጥያቄው የሕዝብ ነው ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን ሌላ ዓላማ የሰነቁ ኃይሎች በማኅበራዊ ሚዲያ መሪ ሆነው ለመታየት እየሞከሩ ቢሆንም፣ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገር ያለበት ከሕዝብ ጋር ብቻ ነው፡፡ ሕዝቡን እንወክላለን ከሚሉ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ነው፡፡ በመሆኑም ከፓርቲዎቹም ሆነ ከሕዝቡ ጋር ሲነጋገር ውስጡን ፈትሾ መሆን አለበት፡፡ ጠንካራ ግምገማ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

መንግሥት ከሕዝብ ጋር ሲነጋገር ራሱን ለትችትና ለወቀሳ ያዘጋጅ፡፡ የነበሩትን ድክመቶች በትክክል አምኖ ሕዝቡ በግልጽ ምን እንደሚፈልግ ይረዳ፡፡ በሕዝብ ድምፅ ተመርጫለሁ ያለ መንግሥት ከምንም ነገር በላይ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ነው፡፡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ መጓደልና በሙስና የተመረረ ሕዝብ ጥቅሜንና ፍላጎቴን ይፃረራል በሚል ጉዳይ ላይ ተቃውሞ ሲያቀርብ፣ በሚገባ አዳምጦ ለመፍትሔ የሚረዳ አቋም ላይ መድረስ አለበት፡፡ ሕዝብን ሲያስመርሩ የነበሩ ሹማምንት ራሳቸውን ከተጠያቂነት ነፃ ለማውጣት በሚያደርጉት ጥረት፣ ሕዝብና መንግሥት የበለጠ እንዳይቃቃሩና አላስፈላጊ መስዕዋትነት እንዳይከፈል ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ በመብት ጥያቄ ስም የኃይል ተግባር ውስጥ የገቡ ወገኖችንም ሕዝቡ እንዲያስቆማቸው ማድረግ የሚቻለው፣ ሕዝብና መንግሥት ሲቀራረቡ ነው፡፡

አሁን የመንግሥት ዋነኛው ተግባር መሆን ያለበት ራሱን ፈትሾ ችግሮቹን ማወቅ ነው፡፡ ችግሮቹ ደግሞ በተደጋጋሚ የሚገለጹት ሕዝብን የሚያማርሩ አጉል ተግባራት ናቸው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለተነሳው ሁከት መነሻው ማስተር ፕላኑ ቢሆንም፣ ሕዝቡ በየደረጃው ባሉ ሹማምንት የደረሱበት የመብት ረገጣዎች የራሳቸው አሉታዊ ሚና አላቸው፡፡ መንግሥት ይህንን የሹማምንት ጉዳይ ያለምንም ይሉኝታ ይገምግም፡፡ አጥፊዎችን ለፍትሕ ያቅርብ፡፡ በምትካቸው ለሕዝብ አገልጋይ የሆኑትን ይመድብ፡፡ አሁን የቃላት ጋጋታ ሳይሆን የሚያስፈልገው ተግባራዊ ዕርምጃ ብቻ ነው፡፡ በሕዝብ የሚቀልዱ ተገምግመው ይወገዱ፡፡

መንግሥት ሁከቱ ከተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች ጋር በሰላማዊ መንገድ በመምከር መረጋጋት ይፍጠር፡፡ ሕዝቡ ወደ እርሻው፣ ንግዱና ወደ መሳሰሉት ተግባሮቹ በፍጥነት ይመለስ፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ይመለሱ፡፡ መደበኛው ሰላማዊ ሕይወት ይቀጥል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የሕግ የበላይነት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ይሰጠው፡፡ ዜጎች ከሰላማዊ የመብት ጥያቄ ይልቅ ወደ አመፅና ሁከት የሚያመሩት የሕግ የበላይነት ሳይከበር ሲቀር ነው፡፡ በሙስና የሚከብሩ ሹማምንትና አጋፋሪዎቸው ሕግ ሲጥሱ፣ ሌላው ዜጋም ያንኑ መንገድ ይከተላል፡፡ በመሆኑም ዜጎች በሕግ የበላይነት ተማምነው የመብቶቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጉ፡፡ በዚህ ረገድም መንግሥት ራሱን ያለ ይሉኝታ ይፈትሽ፡፡

ሕዝብ በማናቸውም ባልተመቹት ጉዳዮች ላይ የመብት ጥያቄ የማቅረብ ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ መንግሥትም ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ በመንግሥት ውስጥ ሌላ መንግሥት የመሠረቱ የሚመስሉ ኃይሎች መንግሥትን ሕዝባዊነት ሲያሳጡ፣ ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ይለያያል፡፡ በዚህ ቀዳዳም ሌላ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች በመግባት አጋጣሚውን ለግጭት ይጠቀሙበታል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰላማዊው ድባብ ወደ ብጥብጥ ይቀየራል፡፡ ይህ ደግሞ ታይቷል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ራሱን ለወቀሳ ያዘጋጅ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የመገናኛ ብዙኃንን፣ የሕዝቡንና የሌሎችን ትችቶች ይቀበል፡፡ ችግሮቹን ያርም፡፡ በተፈጠረው ችግር ላይ ግልጽ መረጃ ይስጥ፡፡ ችግሮችን ማድበስበስ ይቁም፡፡ አመፁ ተባብሶ ሰላምና መረጋጋትን እንዳያሳጣና ለሌሎች ጣልቃ ገብነት እንዳይገለጥ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ይሠለፍ፡፡ ሕዝብን ያዳምጥ፡፡ ከኃይል ዕርምጃ ይቆጠብ፡፡ የሕዝብን የልብ ትርታ ይስማ፡፡  ውስጣዊውን ችግር ፀረ ሰላም ኃይሎች ያራግቡታል ቢባል እንኳ፣ መንግሥት በድፍረት ራሱን ፈትሾ ለመፍትሔ ይትጋ፡፡ ከሕዝብ የሚፈለግበትን ይወጣ፡፡ ለዚህም ውስጡን ደጋግሞ ይፈትሽ!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...