Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበጭልጋና በመተማ ወረዳዎች የተነሳው ግጭት ሞትን ጨምሮ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ

በጭልጋና በመተማ ወረዳዎች የተነሳው ግጭት ሞትን ጨምሮ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ

ቀን:

– የክልሉ መንግሥት መነሻው የ‹‹ፀረ-ሰላም›› ኃይሎች ሴራ ነው ብሏል

– ነዋሪዎች የአማራና የቅማንት ማኅበረሰቦች ግጭት ነው ብለውታል

ከኅዳር 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙት በጭልጋና በመተማ ወረዳዎች በተቀሰቀሰው ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን የአማራ ክልል ገለጸ፡፡ ግጭቱ በፈጠረው ሥጋት ዜጎች ከአካባቢያቸው እየተፈናቀሉ እንደሆነ ምንጮች ለሪፖርተር የገለጹ ቢሆንም፣ የክልሉ መንግሥት ለጉዳዩ የተሰጠው መፍትሔ አንፃራዊ ሰላም አምጥቷል ብሏል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው አካላት በፈጠሩት ብጥብጥ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥት ኃላፊዎች ከወረዳዎቹ አመራሮች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከኅብረተሰቡ ጋር በመመካከር በአንፃራዊነት ሰላም ለመመለስ ተችሏል፡፡

ታኅሳስ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፣ በወረዳዎቹ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጸው፣ በሕዝቡ መካከል ያለውን ሰላምና መረጋጋት በማናጋት ግጭቱ እንዲባባስ በሚያደርጉ ‹‹ፀረ ሰላም›› ኃይሎች ላይ መንግሥት አስፈላጊውን ዕርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡

ነዋሪነታቸውን በጭልጋና በመተማ ያደረጉ የሪፖርተር ምንጮች ግን በአካባቢው ውጥረቱ አሁንም እንዳለ ገልጸው፣ የበርካታ ሰዎች ሕይወት እንደጠፋ፣ በአካልና በንብረት ላይም ጉዳት እየደረሰ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ሴቶችና ሕፃናትን ወደ ሌሎች አካባቢዎች በተለይ ወደ ደምቢያ ወረዳ እየሸሹ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በአማራና በቅማንት ሕዝቦች መካከል ያለው ግጭት እንደቀጠለ አክለዋል፡፡ አቶ ንጉሡ በግጭቱ የሰው ሕይወት መጥፋቱን የገለጹ ቢሆንም፣ ምን ያህል ሰው ሕይወቱን እንዳጣ ግን መረጃ እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ግጭቱ የሕዝብ ጥያቄ እንዳልሆነ ተከራክረዋል፡፡ ‹‹እንደሚወራው ማንነት ላይ በተሰጠው ምላሽ የተነሳ ግጭት አይደለም፡፡ የቅማንት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ሕገ መንግሥቱም ቢሆን የሚደግፈው በመሆኑ፣ ክልሉም አምኖበት ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድርም ተወስኖ የአስተዳደር እርከን ደረጃውን ለመወሰን ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ይህን ሰበብ አድርገው ግጭት ያስነሱት ሌላ አጀንዳ ያላቸው አካላት ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

የግጭቱ መነሻ የቅማንት ብሔረሰብ የማንነት ጥያቄ እንደሆነ የሚገልጹ አካላት ደግሞ፣ ጉዳዩ ሲንከባለል ለበርካታ ዓመታት መቆየቱን ያመለክታሉ፡፡ አቶ ውብሸት ሙላት ‹‹አንቀጽ 39›› መጽሐፋቸው ላይ ቅማንት የራሱ የሆነ የጋራ የትውልድ አመጣጥ አፈ ታሪክ ያለው፣ እንደ አንዳንድ ሰዎች ምስክርነት ከጭልጋ፣ ከላይ አርማጭሆና ከጎንደር ከተማ ተያያዥነት ባለው አካባቢና በሌሎች የሰሜን ጎንደር ወረዳዎች የሚኖር፣ የራሱ የሆነ ባህልና ልማዳዊ ሥርዓቶችም ያለው ማኅበረሰብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አቶ ውብሸት በተጨማሪም በተራዘመው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸው እየከሰመና እየተዋጠ ቢሄድም፣ የራሳቸው እምነትና ባህልም እንደነበራቸው አመልክተዋል፡፡

ቅማንት ጥያቄውን ለአማራ ክልል መጀመሪያ ሲያቀርብ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39(5) ላይ የተቀመጠውን የተለየ ማንነት መሥፈርት እንደማያሟላ ገልጾ ክልሉ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎት ነበር፡፡ የማኅበረሰቡ ተወካዮች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይግባኝ አቅርበው፣ ምክር ቤቱም ባቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት ጥናት ለማድረግ የማኅበረሰቡ አባላት በሚኖሩባቸው ቦታዎች በመንቀሳቀስ ላይ እያለ የክልሉ መንግሥት በራሱ ተነሳሽነት ችግሩን ለመፍታት ኮሚቴ አቋቁሞ ኅብረተሰቡን በማነጋገር ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ሥራ መጀመሩን በመግለጹ፣ ጥናቱ መቋረጡን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ከዚህ በኋላ ክልሉ ጉዳዩን መርምሮ የክልሉ ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ጉባዔውን መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲያከናውን፣ ማኅበረሰቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ወስኗል፡፡ ይሁንና የማኅበረሰቡ አካላት ውሳኔው ከፊል መፍትሔ ነው ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ምክር ቤቱ የቅማንት ማኅበረሰብ ራሱን ችሎ በሚኖርባቸው የጭልጋና የላይ አርማጭሆ ወረዳዎች በሚገኙ 42 ቀበሌዎች ማዕከል አድርጎ ራሱን በራሱ እንደሚያስተዳድር መወሰኑ ይታወሳል፡፡ የቅማንት ማኅበረሰብ በአይከል፣ በመተማ፣ በቋራ፣ በወገራ፣ በደምቢያና በጐንደር ዙሪያ በተበታተነ ሁኔታ ይገኛል የሚሉት የማኅበረሰቡ አባላት ግን፣ ውሳኔው የተሟላ አይደለም በማለት የቅማንት ሕዝብ የሚገኝባቸውን ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ በቅማንት አስተዳደር ሥር እንዲሆኑ ለማድረግ፣ የአስተዳደር ደረጃውን በዞን ደረጃ ለማድረግ እንደሚታገሉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በዚሁ መሠረት ጉዳዩን በይግባኝ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡ ሲሆን፣ ጉዳዩን የመረመረው ምክር ቤትም ውሳኔውን ሰኔ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰጥቷል፡፡ ምክር ቤቱ የማኅበረሰቡ ተወካዮች የክልሉ መንግሥት የሰጠው ውሳኔ ሁሉንም ቀበሌዎች ያላከተተና የተሸራረፈ በመሆኑ ቅሬታ ማቅረባቸውን ያስታወሰው ውሳኔ፣ ክልሉ ቅማንት ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር የሰጠውን ውሳኔ እንዳፀደቀው ገልጿል፡፡ ‹‹የክልሉ መንግሥት በጀመረው አግባብ እንዲፈታ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል፤›› ይላል፡፡

እንደ ሪፖርተር ምንጮች ገለጻ፣ በጭልጋና በመተማ የተነሳው ግጭት ቅማንቶች በውሳኔው ደስተኛ ባለመሆናቸው፣ አማራዎች ደግሞ ቅማንቶች የተለየ ማንነት አላቸው ብለው የሚያምኑ ባለመሆናቸው ምክንያት ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት ግን እነዚህን ጉዳዮች ሰበብ በማድረግ ግጭት እንዲፈጠር የፈለጉ አካላት የፈጠሩት ችግር እንጂ፣ ሕዝቡ እንዲህ ዓይነት አለመግባባት የለውም ሲል አስተባብሏል፡፡ ‹‹ፀረ ሰላም ኃይሎችም በአማራና በቅማንት ሕዝቦች ዘንድ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ለዘመናት በመፈቃቀርና በመረዳዳት ሲኖር የነበረውን ሕዝብ ለማጋጨት የሚያደርጉትን ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ያቁሙ፤›› ሲሉ አቶ ገዱ አስጠንቅቀዋል፡፡

       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...