Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያ ግጭት ሕይወት እየጠፋና ንብረት እየወደመ ነው

በኦሮሚያ ግጭት ሕይወት እየጠፋና ንብረት እየወደመ ነው

ቀን:

– ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል በፀጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት ደርሷል አለ

– የክልሉ መንግሥት ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስጠነቀቀ

ኅዳር 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን ምክንያት የተነሳው ግጭት፣ ለሕይወትና ለንብረት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፡፡ ግጭቱንና አለመግባባቱን ለማብረድ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሕዝቡን በማወያየት ሥራ ቢጠመዱም፣ ግጭቱ ግን ተባብሶ በመቀጠል ሕይወት እየቀጠፈ ነው፡፡

በተለይ በምዕራብ ወለጋ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ በሚገኙ ከተሞች ለአብነትም ወሊሶ፣ ቶሌ፣ አመያ፣ ጨሊያ፣ ግንደ በረት፣ ጪቱ፣ ጉሊሶ፣ እናንጎና ጌዶ በተባሉ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ሕይወት እየጠፋና ንብረትም እየወደመ ይገኛል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ማረጋገጫ ባይሰጥም እስካሁን ከ30 በላይ ሕይወት መጥፋቱና ከ100 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው ይነገራል፡፡ መንግሥት ግን የተጠቀሰውን አኃዝ አይቀበልም፡፡ ይልቁንም በተቃውሞው የተሳተፉ አምስት ሰዎች መሞታቸውን ገልጾ፣ በየአካባቢው የሚገኙ የመንግሥት ተሿሚዎችና የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን እየገለጸ ነው፡፡ በንብረት በኩል በተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ መንግሥታዊ ተቋማት፣ የተሿሚዎች መኖርያ ቤቶች፣ የግል ኩባንያዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

ይህ ግጭት ተባብሶ የቀጠለው በማስተር ፕላኑ መነሻ ይሁን እንጂ ሲንከባለል በቆየ ብሶትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ባለሥልጣናት በአደባባይ በሚሰጡት ያልተገባ መግለጫ ሕዝብ በመበሳጨቱ መሆኑን፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አባል አቶ በቀለ ገርባ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የኦሮሚያ ክልል ምንጮች እንደሚሉት፣ ኅብረተሰቡ ለጥቃቅን አገልግሎቶች የሚጠየቀው ሕገወጥ ጉቦና በክልሉ የተንሰራፋው አድሎአዊ አሠራር የክልሉን ሕዝብ ሲያበሳጭ ቆይቷል፡፡

በርካታ አመራሮችም በተለይ በልዩ ዞኑ በሕገወጥ መንገድ ቦታ ይዘዋል የሚለው ሌላው ጉዳይ ሲሆን፣ ማስተር ፕላኑ በእርግጥ ተግባራዊ ከሆነ በሕገወጥ ያፈሩትን ሀብት ማጣት፣ ከዚህም ከባሰ መጋለጥ የሚያመጣባቸው በመሆኑ ሕዝቡንም ውስጥ ለውስጥ ሲያነሳሱ ቆይተዋል የሚል ሐሳብ እየተሰነዘረ ይገኛል፡፡

ክልሉን የሚመራው የኦሕዴድ አባላት ለዚህ ችግር ተገቢውን ትኩረት ካለመስጠታቸውም ባሻገር፣ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ተገቢነት ያላቸው ጥያቄ ለመመለስ ተነሳሽነትም እያሳዩ አይደሉም በማለት የሚወቅሱ አሉ፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች የኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የኦሕዴዱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በተደጋጋሚ አስተያየት እንዲሰጡ ቢጠየቁም፣ እንደማይመቻቸው በመግለጽ አስተያየት ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ሥጦታው ግን ማስተር ፕላኑ ለዚህ ግጭት ምክንያት እንደማይሆን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አቶ አባተ ግጭቱን ድብቅ ዓላማ ያላቸው አካላት በማስተር ፕላኑ ስም ቀስቅሰውታል ብለው ያምናሉ፡፡

ማክሰኞ ታኅሳስ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ምሽት የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ፣ ከፊት ለፊት ማስተር ፕላኑን በመቃወም ከጀርባ ደግሞ ከሽብርተኛ ኃይሎች ጋር በማበር የተሠለፉ መኖራቸውን ገልጿል፡፡  

ግብረ ኃይሉ እንዳለው፣ ውጭ ካለው የሽብር ኃይል ጋር ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ግንኙነት በመፍጠር የነውጡና የረብሻው አድማስ ወደ ከተሞችና ወደተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት እንዲሰፋፋ ተደርጓል፡፡ በዚህም በርካታ የመንግሥት፣ የግል ባለሀብቶችና የደሃ አርሶ አደሮች ንብረትና ሀብት ወድሟል ያለው ግብረ ኃይሉ፣ የኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ በተሰማሩ የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አባላት፣ እንዲሁም በመከላከያ ኃይል አባላት ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ደርሷል ብሏል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና የሕዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ በሽብርና በአመፅ ኃይሉ ላይ ሕጋዊና ተመጣጣኝ ዕርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

በገጠርም ሆነ በከተማ የሚኖሩ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት በትምህርት ተቋማትም ሆነ ከትምህርት ተቋማት ውጪ የሚገኙ ልጆቻቸውንና መላ ቤተሰባቸውን፣ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋና ንብረት እንዳይወድም፣ ዘረፋ እንዳይስፋፋ፣ የሽብር አመፅ አቀጣጣዮች ሰለባ እንዳይሆኑ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስቧል፡፡

በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው የመንግሥት አቋም፣ በክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ማረሚያ ቤቶችን በመስበር፣ የሕግ ታራሚዎችን በመልቀቅ፣ የፖሊስ ጽሕፈት ቤቶችን፣ የልማት ድርጅቶችን፣ የአርሶ አደር ምርቶችን፣ የግል መኖሪያ ቤቶችን በማቃጠልና በማውደም በጦር መሣሪያ የታገዘ ጥፋት፣ የጥፋት ኃይሎች ያላቸው ወገኖች በመፈጸም ላይ ናቸው ብሏል፡፡ እነዚህ ኃይሎችም ከድርጊታቸው ይቆጠቡ በማለት አስጠንቅቋል፡፡

‹‹እነዚህ የጥፋት ኃይሎች አብሮ የመኖር፣ የመቻቻልና የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ተምሳሌት የሆነውን የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ወንድሞቹ ጋር የጎሪጥ እንዲተያይ፣ እንዲሁም በእምነቶች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ ከድርጊታቸው ጎን የቆመን ኃይሉ ሁሉ አሠልፈው ወደ ሕገወጥ ተግባር ተሸጋግረዋል፤›› በማለት የክልሉ መንግሥት ገልጿል፡፡

በመሆኑም መንግሥት የእነዚህን የጥፋት ኃይሎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን የመናድ ተግባር ለማስቆምና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ግዴታ መሠረት በማድረግ በድርጊቱ ዋና ዋና ተዋናዮች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እየታየ ያለው ሁከት ከማስተር ፕላን በዘለለ ሌላ አቅጣጫ እየያዘ መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ ሀብቱ አድማሱን ሊያሰፋ እንደሚችልም ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...