Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመድረክ የሟቾች ቁጥር ከ30 በላይ ነው አለ

መድረክ የሟቾች ቁጥር ከ30 በላይ ነው አለ

ቀን:

– ሰማያዊ ፓርቲና ኤፌኮ ለፖለቲካ ትግል የጋራ ግብረ ኃይል ሊያቋቁሙ ነው

ለአዲስ አበባና ለኦሮሚያ ልዩ ዞን የተዘጋጀውን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን በመቃወም በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የሟቾች ቁጥር ከ30 በላይ መድረሱን፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አስታወቀ፡፡

የመድረክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የውጭ ግንኙነት ኃላፊው ዶ/ር መረራ ጉዲናና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጥላሁን እንደሻው ይህን ያስታወቁት፣ ማክሰኞ ታኅሳስ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በፓርቲው ጽሕፈት ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

‹‹ባለፉት ሁለት ሳምንታት የአዲስ አበባ ከተማን ከሕግ አግባብ ውጪ ማስፋፋት ጋር በተያያዘ በሕዝቡ ዘንድ ካደረው ሥጋት በመነሳት፣ የተቀሰቀሰውን ሰላማዊ ሕዝባዊ ተቃውሞን በኃይል ለማስቆም የኢሕአዴግ መንግሥት በወሰደው ዕርምጃ በርካታ ተማሪዎችና ሌሎች ዜጎች መገደላቸውን መድረክ በእጅጉ ይኮንነዋል፤›› በማለት መድረክ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

‹‹መንግሥት መሠረታዊውን የጥናት ሐሳብ ለሕዝቡ አቅርቦ የሕዝቡ ስሜት ምንድነው የሚለውን ፈትሾ እንጂ ወደ ዝርዝር ጥናት የሚገባው፣ ዝም ብሎ የጉልበተኛ ሥራ መሥራት ተገቢ አይደለም፤›› ሲሉ የመድረክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች በተፈጠረው ረብሻ ሕይወታቸውን አጥተዋል በማለት መድረክ በመግለጫው የዘረዘራቸው 30 ግለሰቦች ሲሆኑ፣ የሟቾችን ዝርዝር ስምና የሞቱባቸውን ከተሞች አስታውቋል፡፡

በዚህ መሠረት በምዕራብ ወለጋ ጉልሶ ወረዳ፣ በምዕራብ ሐረርጌ በደኖ ወረዳ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ቶሌ ወረዳ፣ አዳበርጋ ወረዳ ሙገር፣ ምዕራብ ሸዋ ጨሊያ ወረዳ ባብቻ ከተማ፣ ምዕራብ ሸዋ ጨሊያ ወረዳ ጌዶ ከተማ፣ ምዕራብ ወለጋ ኢናንጎ ወረዳ፣ ሆሮ ጉድሮ ፊንጫ፣ ወሊሶ ከተማ፣ አመያ ከተማ፣ ወንጪ ከተማ፣ ግንደበረት ወረዳና ግንጪ ወረዳ ግለሰቦች የሞቱባቸው ሥፍራዎች እንደሆኑ መድረክ አስታውቋል፡፡

የሚካሄዱት እንቅስቃሴዎች ሰላማዊ ከሆኑ ይህን ያህል ሰዎች እንዴት ይሞታሉ? በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች እየታዩና ከቁጥጥር ውጪ በመሆናቸው ይህ ከምን የመነጨ ነው? ለሚሉ ጥያዎች፣ ‹‹ይህንን ንብረት እናወድማለን ጥፋት እናደርሳለን ብሎ የተነሳ እንቅስቃሴ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ተጣሰ በሚል መነሻ እንደሆነ ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ አንድ የተናደደ ወጣት ጠጠር ሊወረውር ይችላል፡፡ ይህ ተስፋ ከመቁረጥ የሚመነጭ ነው፡፡ ሥርዓቱ ሕዝቡን ወደ ተስፋ መቁረጥ እያሻገረው በመሆኑ የተከሰተ ነው፤›› በማለት ፕሮፌስር በየነ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በቅርቡ የተከሰተውን ችግር ያፈነዳው የማስተር ፕላኑ ጉዳይ ነው በማለት አስተያየት የሰጡት ዶ/ር መረራ፣ ‹‹ነገር ግን በተጨማሪም ሕዝቡ በአመራሩ የመሰልቸት፣ በተለይ የወጣቶች ተስፋ ማጣትና የመሳሰሉት ነገሮች ናቸው ይህን የፈጠሩት፤›› በማለት አክለው ገልጸዋል፡፡

የችግሮቹን ሁኔታ አጥንቶ መፍትሔ ማዘጋጀት አስቸኳይ ሥራ መሆን አለበት ያሉት ዶ/ር መረራ፣ ሁለት መፍትሔዎችን በአማራጭነት አቅርበዋል፡፡ እነዚህም ጊዜያዊና ዘለቄታዊ የሚሉ ናቸው፡፡

ጊዜያዊ መፍትሔው ‹‹ወጣ የተባለውን አዋጅ መሻር ነው፡፡ አዋጅ ደግሞ የሚሻረው በአዋጅ ነው፤›› በማለት በቅርቡ በጨፌ ኦሮሚያ የወጣውን የከተሞች ማሻሻያ አዋጅ እንዲሻር የጠየቁ ሲሆን፣ ዘላቂ መፍትሔው ብለው ያቀረቡት ደግሞ፣ ‹‹ኢሕአዴግ በቃኝ የኢትዮጵያን ሕዝብ መምራት አልቻልኩም ብሎ ከሥልጣን መውረድና ምርጫ ማካሄድ ነው፡፡ ይህን ማድረግ  አልፈልግም የሚል ከሆነ ደግሞ ቢያንስ ጥምር መንግሥት አቋቁሞ ከዚያ በኋላ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ ነው፤›› ሲሉ ዶ/ር መረራ ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመድረክ አባል የሆነው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የተለያዩ መግለጫዎችን በማውጣት በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም ሲገልጹ ከመቆየታቸው አንፃር፣ መድረክ መግለጫ ለማውጣት አልዘገየም ወይ ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበ ጥያቄ፣ ‹‹መድረክ ዘገየ አልዘገየ የሚለው ጉዳይ ይህን ያህል ብዙ ቦታ ልንሰጠው የሚገባ አይመስለኝም፡፡ ይህም ቢሆን ግን መድረክ ምንም አላለም ማለት አይደለም፡፡ በሕዝብ ግንኙነት በኩል መረጃዎች ሲሰጥ ነበር፤›› በማለት ፕሮፌሰር በየነ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ሰማያዊ ፓርቲና ኤፌኮ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች ስምምነት ላይ የደረሱት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግለጫ ለመስጠት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሁለቱ ፓርቲዎች አመራሮች ባደረጉት ስምምነት፣ በጋራ መግለጫ ከመስጠትም በላይ የጋራ ግብረ ኃይል በማቋቋም የፖለቲካ ትግል እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...