ሰላም! ሰላም! “እነሆ ትዳሬም ንፋስ ገባው አገሬም ታራግብ ጀመር” አለ አሉ መላ ያጣው። እሱስ ከልብ አልጨነቅ ብለን እንጂ መላ አይጠፋም ነበር። ግን መላን ምላስ ከቀደመው ምን ይደረጋል? ምነው ጆሮን እንደ ሞባይል ስልካችን ስንፈልግ ‘ሳይለንት’፣ ስንፈልግ ‘ላውድ’ የሚያስደርግ ቴክኖሎጂ በተፈለሰፈልንና ባረፍን። እኔ ልሙት! ተፈጥሯዊ አሟሟት ነው ታዲያ። “ድሮስ በምን ልንሞት ኖሯል የምንምለው?” ብለው ባሻዬ በቀደም ከአንድ ሰው ጋር ሙግት ይዘው ሳገኛቸው ነው ይኼ አሁን የነካካሁት ነገር ሁሉ የመጣው። ‘እንዴት?’ እንዴት ማለት በደጉ ጊዜ ደግ ነበር። አሁንማ ይኼው ጊዜ ቀድሞን ሠልጥኖ እንዴት? ሳንል ‘እግዚኦ’ ሆነ ሥራችን። ለጊዜው ይኼን እንተወውና ወደ ዋናው ጉዳይ እንገባለን። አይዟችሁ በእኛ የጨዋታ መሥሪያ ቤት ወደ ዋናው ጉዳይ ለመግባት ሥራ አስኪያጁ ቀብር ሄደዋል፣ ስብሰባ ላይ ናቸው፣ ግምገማ አለባቸው አትባሉም። ስለዚህ ልባችሁን ጠብቃችሁ ወገባችሁን አጥብቃችሁ ባሻዬን ምን አሟገታቸው የሚለውን ላጫውታችሁ። እንዲያ ነው እንጂ ሲጫወቱ ውሎ ሲለያዩ ማማት!
እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ነኝ፡፡ ምን ሆነ መሰላችሁ? እኔ አንድ ‘ካሚዮን’ አሻሽጬ ከሰዓት የድለላ ኮሚሽኔን ሊሰጡኝ ቀጠሮ ይዤ ምሳዬን ለመብላት ወደ ቤት ስመጣ ሠፈርተኛው ተሰብስቧል። ደጋግሜ እንዳጫወቱኳችሁ የመንደራችን ነዋሪ የመሰብሰብም የመበተንም ችግር የለበትም። ባሰባሰበው ተሰብስቦ ተበተን ሲለው ይበታናል። እናም ውሉ ሁሉ እንዲሁ ሰበሰብነው ከማለታችን ሲበተን መኖሩ የዚሁ ቋሚ አመል ውጤት ነው። “ምንድነው እሱ?” ብዬ ጠጋ ከማለቴ፣ “ስማልኝ ይኼን ሰውዬ! የሞት መሀላዎችን ተቃውማችሁ ሠልፍ በመውጣት አውግዙ ይለኛል፤” ብለው ባሻዬ አንዴ ሰውዬውን አንዴ እኔን ቃኙን። “አልገባኝም!” ሰውዬውም እንዳልገባኝ አውቆ፣ “ይኼውልህ ወንድሜ አንተ ከእሳቸው በተሻለ ሁኔታ ሐሳቤ ይገባሃል። ስለዚህ አዳምጠኝና ታስረዳልኛለህ፤” ብሎ ሳንባ እንዳየች ድመት በዓይኑ ልምምጥ ያዘ። ድመቶች ግን ካልጠፋ ነገር መርጠው ሳንባ መብላት የሚወዱት ለምን ይሆን? እያልኩ በውስጤ የማይገናኝ ሳስብ ሰውዬው ቀጠለ። የማይገናኝ ነገር ማሰብና ማውራት በእኔ ተጀመረ እንዴ? ኧረ እንዲያውም አሉላችሁ ቴሌቪዢንና ሬዲዮ ላይ! ታዲያስ!
“ጊዜው ከፍቷል (በራሱ?) ሰላማችን ህልውናችን ነው። በአገራችን ደግሞ በተለምዶ የሞት መሀላዎች አሉ። ‘ሙቺ፣ ሙት፣ ስሞትልህ፣ ስቀበር፣ እኔ ልሙት’ የመሳሰሉት በጥቂቱ ተጠቃሽ ናቸው። እናም ሽብርና ሽብርተኝነት እንዲህ ሥጋት በሆነበት ጊዜ እነዚህ መሀላዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ ከቀጠሉ ‘ሳይኮሎጂካሊ’ አደጋ አላቸው…፤” እያለ ብዙ አወራ። እያስራቡ መስበክ የሚቀናቸው ብዙ ናቸው። ‘የሰው ሆዱ የወፍ ወንዱ አይታወቅም’ ብሎ ይሆን? አቋረጥኩት። “በአጭሩ?” ስለው፣ “በአጭሩ ሌላውንም ሆነ ራስን በመሀላ መግደል አጥፍቶ ከመጥፋት ወይም ከመሰል የሽብር ወንጀል ተለይቶ አይታይም። ይህን ጎጂ የመሀላ ብሂል ለማቆም ደግሞ ነዋሪው ሠልፍ ወጥቶ አቋም መውሰዱን እንዲገልጽ ነው የታሰበው፤” አለኝ። ቀስ በቀስ ተሰብሳቢው ጨመረ። እኔም ሊገባልኝ ብሎ ሳተኝ። ጉርምርምታው አየለ። ባሻዬ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር የእድሩ ሰብሳቢ እንደመሆናቸው አስቸኳይ ስብሰባ ለከሰዓት በኋላ መጥራታቸውን ወዲያው አወጁ። በአዋጅ አልቀናል እኮ ዘንድሮ!
ከስብሰባው በፊት ሌላ ስብሰባ ገጠመኝ። የት? ቤት! “እኔና አንተ…” አለች ከመግባቴ ውዷ ማንጠግቦሽ። ‘እኔና አንተ’ ካለች ነገር አለ ማለት ነው። “መነጋገር አለብን፤” ብላ ፊት ለፊቴ ቦታ ያዘች። ምሳ ከበላን በኋላ አይደርስም? ብልስ እኔ። አላልኩማ። ቀላል ጉዳይ መስሎኝ ነበር። ግን የነገር ቀላል አለው እንዴ? አቅለን አቅለን የት እንደደረስን ይኼው እየታዘባችሁት መሰለኝ። ማንጠግቦሽ ቀጠለች። “እስከ ዛሬ ድረስ ተቻችለንና ተከባብረን ኖረናል። ማን ከሚችለው በላይ እንደቻለ እሱ ያውቀዋል። አሁን ግን በቃኝ፤” አትል መሰላችሁ? እስኪ እናንተ ፍረዱ። ማን ነው ባልበላ ሆዱ የመገንጠል፣ የመገነጣጠል፣ የመለያየት ጥያቄን መስማት የሚያስችለው? “እና?” ብዬ አፌን ከፍቼ ቀረሁ። ደነገጠች። “በቃኝ ምን?” ብዬ ስጮህ፣ “ከዚህ በኋላ ዝም አልልህም ነው የምልህ። ጥያቄዬን በሰላማዊ መንገድ የማቅረብ አንተም ‘እህ?’ ብለህ መስማት አለብህ፤” ካለች በኋላ ለእኔ ጥቃቅን የሚመስሉ እሷን ግን እንቅልፍ ሲያሳጧት የሚያድሩ የቤት ለቤት እንከኖቼን ዘከዘከች። እኔ ደግሞ ልሄድ ነው የምትል መስሎኝ ክው ብያለሁ እኮ። ኋላ ለባሻዬ ልጅ ሳጫውተው፣ “እንዴ ይኼን ያህል አብራችሁ ኖራችሁ እንዲህ እንደ ዋዛ ልሂድ ትላለች ብለህ እንዴት አንተስ ታስባለህ?” አለኝ። ጉድ እኮ ነው እናንተ። ሕገ መንግሥቱ የሚፈቅድላትን፣ የሴቶች ጉዳይ የሚያግዛትን ባለጊዜ በጉልበት ላኖራት ያስባል እንዴ? “ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ሥር እናውላለን፤” ብለው ራሳቸው በቁጥጥር ሥር ዋሉ ስንል፣ ይኼው እኛስ ራሳችንን መቆጣጠር የተሳነን ጊዜ ላይ መስሎኝ ያለነው። ወይ ሰውና ተፈጥሮ!
ማንጠግቦሽ የምትለኝን ሁሉ እሺ ብዬ ምሳዬን ጥርግ አድርጌ በልቼ የይቅርታና የምሥጋና አፀፋ ለግሻት ስወጣ ስልኬ ‘ጢን’ ብላ ዝም አለች። “ያሸንፉ ይሸለሙ” የሚል የጽፁፍ መልዕክት ነው። እኔ ዕድሌን መቼ አጣሁት? ደጋግሜ እንዳጫወትኳችሁ እኔና አዳም ዕጣችንን የጣልነው፣ የወጣልንም እኩል ነው። “ተሸልመህ ብላ” ብሎ ነገር አይገባኝም። ስለዚህ የመልዕክት መስጫ ሳጥኔ እንዳይሞላ ‘ዴሊት’ ልጫን ስል ከአውሎ ንፋስ በላይ የተዋከበ ‘ሚስድ ኮል’ ደረሰኝ። ‘ኮሚሽኔን’ የሚሰጠኝ ሰው ነው። ‘እንዴት ቢሳሳ ነው መደወል የከበደው?’ እያልኩ መልሼ ስደውል፣ “ይቅርታ ያለዎት ቀሪ ሒሳብ አነስተኛ ነው…” አለች፡፡ ትንሽ ትልቁን አንቱ ማለት የማይሰለቻት ሴትዮ። አንዳንዴ ታዲያ ይገርመኛል። ምኑ መሰላችሁ? አሥር ሳንቲም ሳይኖረው ስልካችን ‘አነስተኛ ሒሳብ አለዎ’ መባላችን ማለቴ ነው። “ቴሌ እግዜር አሁንም ያሰበውን ያሳካለትና የዋለልን ትልቅ ውለታ ስናጣና ስናገኝ እኩል ማየቱ ብቻ ነው፤” የሚለኝ ወዳጄ አለ። ‘ብቻው’ የራሱ ስለሆነ ስታገኙት ብቻውን ጠይቁት። አያገባኝም። ይልቅ የማውቀውና የገባኝ ነገር ቤት ከመግባቴ በፊት (ባሻዬ የከሰዓቱን አስቸኳይ ስብሰባ ሲያውጁ ከሰማሁ በኋላ) የሃምሳ ብር ካርድ ፍቄ መሙላቴን ነው። እናም ያለኝን ቀሪ ሒሳብ ማን አነስተኛ አደረገው? ደወልኩ። “እህ?” ስል “እህ?” አለኝ መስመር ላይ። “ካርዴን ምን እንደጨረሰው እንዲጣራልኝ እፈልጋለሁ፤” አልኩኝ ዘና ቆፍጠን ብዬ። ሰው እኮ አገሬ ነው ብሎ ዝም የሚለውና ዝም የማይለው አለ። ‘ሁሉን ነገር ካልዘረገፍነው’ . . . ‘ምንም ነገር አትተንፍሱ’ . . . ግብግብ ሆነ እኮ የእኛ ኑሮ እናንተ! እና ሰውዬው “ፌስቡክ ተጠቅመው ይሆናል፤” አይለኝ መሰላችሁ? “መቼ? ደግሞስ ብጠቀም ሃምሳ ብር በ20 ደቂቃ ያልቃል?” ብዬ ቱግ ስል “ስልኩዎ 3G ነው?” ብሎ ልቤን አደረቀው። “ለአገር ጥቅም ብዬ ግድየለም ትቼዋለሁ፤” ብዬ ዘጋሁት። እዚያ ሞላን ስንል እዚህ እንጎላለን። እዚህ በላን ስንል እዚያ እንበላለን። እንደኔ ማስተዛዘኛውን ከአገር ጥቅም አይበልጥብኝም ያላለ ሰው መቼም ዘንድሮ በአጥንቱ መሄዱ ነው። እግዚኦ!
ባሻዬ ወደሚመሩት ስብሰባ ከመጓዜ በፊት አንድ የማሳየው ቪላ ነበርና ወደዚያው ገሰገስኩ። ተከራይ ናቸው ሰዎቹ። “ቤቱ ተስማምቶናል ነገ መጥተን የስድስት ወር እንከፍላለን፤” አሉ። “እንዳላችሁ…” ብዬ ሸኘኋቸው። “ዘንድሮ በቃሉ የሚገኘው እብድ ብቻ ነው፤” ይላሉ ባሻዬ በእንደወረደ አማርኛቸው። “እንዴት?” ስላቸው ሁሌም የሚመልሱልኝ መልስ ተመሳሳይ ነው። እርሱም፣ “ያው አንዴ አብዷልና የሚያወራውን አያውቀውም ቢያውቀውም አይገደውም። አንተም የሚናገረውን እንጂ ፍፃሜውን አትጠብቅም። ስለዚህ ቃሉን በከንቱ በመዝራት እንደ ቃሉ በየሥፍራው በከንቱ የሚገኘው እርሱ ብቻ ነው፤” ይሉኛል። እሱ ቃሉ ከሚያልፍ ሰማይና ምድርን ማሳለፍ የሚቀለው አምላክ ይሁነን እንጂ ሌላ ምንም ማለት አይቻልም። አይቻልምና የስብሰባው ሰዓት መድረሱን ተመልክቼ ወደ ቀዬዬ ገሰገስኩ። ነዋሪው ግጥም ብሏል። ባሻዬ የስብሰባውን አጀንዳ በአጭሩ አስተዋወቁ። “እንግዲህ የሞት መሀላ መማል ከሽብርና ከሽብርተኝነት ጋር ተደምሯል ነው የሚሉን። እዚህ ላይ አቋም ከመውሰዳችን በፊት የምትሉትን በሉ። የምትምሉትም ካለ ማሉ፤” አሉ። አንዱ እጁን አወጣ። “ተናገር” ተባለ። “እኔ . . .” አለ ዘለግ አድርጎ እሱነቱን “. . . እኔ . . . ይኼው ባሻዬ ይሙቱ ወዳጄ በቁሜ የሞትኩ ሰው ነኝ። እንደምታውቁት . . . ” ብሎ ሲያበቃ ሠፈርተኛው ሁሉ የሚያውቀውን የውስልትና ታሪኩንና መገለሉን ጨርሶ ወደ ማኅበሩ ለመቀላቀል ያሳለፋቸውን ክፉ ቀናት አተተ። ከዚያም፣ “በመጀመሪያ ራሱ መሀላ በመላ አገሪቱ መታገድ አለበት!” ብሎ አረፈው። የአንዳንዱ ሰው ሐሳብ ትዕዛዝ ይሁን አስተያየት አልገባ አላላችሁም ግን?
“እንዴት?” አሉት ባሻዬ፡፡ “እንዴት ጥሩ ነው ባሻዬ። ይኼው እርስዎ ይሙቱ…” ሲል ‘አንተ ሰውዬ አንዴ በቁሜ ሞቻለሁ ብለህ ነው ሰውዬውን አሥር ጊዜ የምትገላቸው?’ ብሎ ተሰብሳቢው አጉረመረመበት። “አስጨርሱኝ! በሞቴ አስጨርሱኝማ! አዎ መሀላ ራሱ ነው የሽብር ምንጩ። አዎ ‘የኤርትራን ጉዳይ እስከ ዘለዓለም ፈተነዋል ሐሳብ አይግባችሁ’ የሚል ግዳይ ቀረሽ ማስተማመኛ ቃል ሰምተን የሆነውን ዓየን፡፡ እሱን ተውትና ከሃያ ዓመት በፊት ‘ከሃያ ዓመት በኋላ በቀን ሦስቴ እንበላለን’ ተብለን ይኼው ዛሬ የኑሮ ውድነት የጠቀለልነውን ጉርሻ እያፈረሰብን ፍዳችንን እናያለን። አሁን ደግሞ . . . ” ሲል ባሻዬ አቋረጡት። “ከአጀንዳው እየወጣህ ነው ሐሳብህን አጠቃል፤” ተባለ። “ብዙ የምለው ነገር ነበረኝ ግን ሳሳጥረው ከመሀላ በፊት የምንምልበት አቅምና ማንነት ማበጀቱ ላይ ነው መነጋገር ያለብን። እንዲያ ካልሆነ ሁሉም ዓይነት መሀላ ፉከራ ወይም ፕሮፓጋንዳ የሽብር መንስዔ ይሆናል። ዲሞክራት ነን ካልን ሕዝብ ማዳመጥ! እኩልነት አስፍነናል ስንል እኩል ተጠቃሚ ማድረግ አለብን። በተግባር! እንጂ ባሻዬ ይኼው እርስዎ ይሙቱ ውዳጁ፣ ማንም በማንም መሀላ የሞተ የተጎዳ የለም። የማስፈጸም፣ የዕውቀትና የትጋት አቅሙን ሳይፈትሽ በገዛ ቃሉና በሰጠው ተስፋ ልክ ታንቆ የሞተ ብቻ ነው የማውቅ፤” ብሎ ጨረሰ። እሱ በጀመረው ሁሉም እየተነሳ ከአጀንዳ ውጪ ሲቀባጥር ጀንበር አዘቀዘቀች። የማንሰማው የለም እኮ እንስማ ካልን!
እንሰነባበት? ስብሰባው ተበትኖ ከባሻዬ ጋር ወደ ቤት ስንጓዝ “በነጌቲቭ አለቅን እኮ፤” አሉኝ። ሳዳምጣቸው ነገረ ሥራችን ሁሉ የአመድ አፋሽ ሥራ አልሆነብህም? እዚያ መገንባት እዚህ ማፍረስ? . . . እ? ዘመን እያሰሉ ሞት አልሆነብህም? ኑሮው ፖለቲካው ምኑ ቅጡ። ቢያንስ የያዝነውን ይዘን፣ ባለን ረክተን፣ በአጭሩ ዜሮን አስጠብቆ መኖር አልቻልንም እኮ። ‘ፖዘቲቭን’ ተውና ዜሮን መታደል አልቻልንም ስልህ፤” ሲሉኝ ገቡኝ። ቤታቸው አስገብቻቸው እኔም ወደ ቤቴ ገባሁ። አረፍ ብዬ ነገር ዓለሙን ሳሰላስል አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ከልብ ስንጨነቅ መላ አይጠፋም ነበር ለካ? አዎ እስቲ ከልብ እንጨነቅ፡፡ መልካም ሰንበት!